የስፖርቱ ዓለም ሁሌም በተአምራት የተሞላ ነው። አይሆንም የተባለ የሚሆንበት፣ ይሆናል የተባለው የማይሆንበት ዓለም ስፖርት ነው። ለማመን የሚከብዱ ክብረወሰኖች፣ ታሪክ የማይዘነጋቸው ጀግኖችና ከህሊና የማይጠፉ ድልና ሽንፈቶች የስፖርቱን ዓለም የሚያጣፍጡ ቅመሞች ናቸው። ከዚህ ባሻገር ግን ስፖርት እጅግ አስገራሚና ፈገግ የሚያደርጉ ክስተቶችን ማስተናገዱ የተለመደ ነው።
የዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም ዛሬ ላይ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የማራቶን ውድድር ለማጠናቀቅ ሁለት ሰዓት በሚፈጅበት ዘመን ይህን ርቀት ሮጦ ለማጠናቀቅ ሃምሳ አራት ዓመት ስለፈጀበት አትሌት ወይም አንድ ግለሰብ የሚነግረን ይሆናል።
አትሌቱ የማራቶን ውድድሩን የጨረሰው ጋብቻ ፈጽሞ፤ ስድስት ልጆችና አስር የልጅ ልጆችን ካፈራ በኋላ ነው። አትሌት ሺዞ ካናኩሪ እ.አ.አ በ1912 በስዊድን ስቶኮልም የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ነው ጃፓንን በመወከል የተሳተፈው። ይህ እንዲታወስ ያረገውን አስገራሚ ታሪክ የጻፈበት መቼትም የስቶክሆልሙ ኦሊምፒክ ነው።
የማራቶን ክብረ ወሰን ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያዊው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ እጅ የነበረ ሲሆን፤ አትሌቱም 42 ኪሎ ሜትር ከ 195 ሜትር ርቀቱን በሁለት ሰዓት ከሶስት ደቂቃ ከ 59 ማይክሮ ሰከንድ መግባቱ ይታወሳል። ይህ የዓለም ክብረወሰን በተለይም በኬንያውያንና ኢትዮጵያውያን የርቀቱ ፈርጦች ተደጋግሞ በመሰበር አሁን ላይ በኬንያዊው የረጅም ርቀት ቁንጮ አትሌት ኢልዩድ ኪፕቾጌ እጅ ላይ ይገኛል። ኪፕቾጌ ክብረወሰኑን ለመጨበጥም ርቀቱን ያጠናቀቀው ሁለት ሰዓት ከአንድ ሰከንድ ከ39 ማክሮ ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቦ ይገኛል።
በኪፕቾጌ በሁለት ሰከንድ ብቻ በመበለጥ የዓለም ቁጥር ሁለቱ የማራቶን ሯጭ ደግሞ ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተከታይ ነው። በጥቅሉ ማራቶንን ለማጠናቀቅ ሁለትና ከሁለት ሰዓት በላይ ቢፈጅም አንድ ጃፓናዊ አትሌት ግን ማራቶንን ለመጨረስ 54 ዓመታት በላይ መፍጀቱ ከስፖርቱ ዓለም ድንቃ ድንቅ ታሪኮች የአንዱ ባለቤት እንዲሆን አድርጎታል።
እ.አ.አ በ1912 በስዊድን መዲና ስቶኮልም ተካሂዶ በነበረው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ጃፓንን በመወከል ለመሳተፍ ሺዞ ካናኩሪ የተባለው አትሌት ምርጥ ሰዓት አስመዝግቦ ወደ ስፍራው ተጉዞ ነበር። አትሌት ሺዞ ካናኩሪ በዛን ዘመን በተካሄደው የማራቶን ውድድር የገባው በከፍተኛ የድካም ስሜት ከመሆኑም በላይ ምግብ ሳይስማማው ቀርቶ እንደነበር ታሪክ ይገልጻል።
ውድድሩ በተደረገበት ዕለት በስቶክሆልም ከፍተኛ ሙቀት በመኖሩ በርካታ አትሌቶች ውድድሩን እንዳቋረጡ ይነገራል። ውድድሩን ካቋረጡት አትሌቶች መካከልም ጃፓናዊው አትሌት ሺዞ ካናኩሪ አንዱ ነበር። ካናኩሪ ውድድሩን አቋርጦ የጃፓን የስፖርት ባለስልጣናትን ሳያናግር ወደ አገሩ መመለሱን የአትሌቱ ታሪክ ይገልጻል። ከስቶክሆልም ኦሊምፒክ በኋላ ግን የስዊድን ባለስጣናት አትሌቱ ጃፓን መኖሩን ሳያውቁ ጠፍቷል የሚል ግንዛቤ ነበራቸው። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ እ.አ.አ በ1967 ከስዊድን ቴሌቪዥን ጋር በመነጋገር በ1912 የጀመረውን ውድድር እንዲያጠናቅቅ አደረገ።
ሺዞ ካናኩሪ ውድድሩን ለመጨረስ 54 ዓመታት፤ ስምንት ወራት፤ ስድስት ቀናት፤ አምስት ሰዓታት፤ 32 ሰከንድ እና 20 ነጥብ ሶስት ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶበታል። ውድድሩን የጨረሰውም ጋብቻ ፈጽሞ፤ ስድስት ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን ካፈራ በኋላ መሆኑ ደግሞ አነጋጋሪ ነበር። ምንም እንኳን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት የኦሊምፒክ ውድድር ቢቋረጥም፤ ሺዞ ካናኩሪ በ1916 የክረምት ኦሊምፒክ ላይ ጃፓንን እንዲወክል ተመርጦ ነበር። ካናኩሪ በቤልጅየም 1920 ላይ ማራቶንን ሁለት ሰዓት ከ 48 ደቂቃ ከ45 ነጥብ 4 ሰከንድ በማጠናቀቅ 16ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቆ ነበር።
በ1924 ደግሞ በድጋሚ ውድድር ላይ የተሳተፈው ካናኩሪ ማራቶንን ሳይጨርስ ቀርቶ ነበር። ያም ሆነ ይህ 1912 በስቶክሆልም ከተማ የጀመረውን የማራቶን ውድድር ከ54 ዓመታት በኋላ በእርጅና ዘመኑ በመጨረሱ ሁሌም ኦሊምፒክ በተቃረበ ቁጥር እንዲታወስ አድርጎታል። አትሌት ሺዞ ካናኩሪ እ.አ.አ በ1983 በተወለደ በ92 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም ስሙን በስፖርቱ ዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ በማኖሩ ሁሌም ስሙ ይነሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 2014 ዓ.ም