የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግና በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ውጤታማ ለማድረግ በተለያዩ ክልሎች የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ከዓመታት በፊት ተጀምሮ ሲሰራበት ቆይቷል። ይሁን እንጂ ይህ ፕሮጀክት መክሸፉ ወይም የታቀደለትን አላማና ግብ አለመምታቱ ተረጋግጧል። ይህንንም ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከሸፈው የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ላይ ችግሮችን ለይቶ ትኩረት አድርጎ ለመሥራትና ወደ ውጤት ለመመለስ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። በዘርፉ የተለያዩ የሪፎርም ጥናቶችን በማድረግም የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ማሻሻያዎች ተደርገውበት እንደ አዲስ ለመጀመር ታስቧል።
በዚህም መሠረት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ልማት ፕሮግራምን በተመለከተ የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ትናንትና ከትናንት በስቲያ በቢሾፍቱ ከተማ ተሠጥቷል። የላቀ ችሎታ ያላቸውን አትሌቶች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በብዛትና በጥራት ማፍራት እንዲቻል የተሰጠው ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና፣ በታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ፕሮግራም ላይ ይታዩ የነበሩ ውስንነቶች ተቀርፈው በአካል ፣ በአዕምሮ እና በሥነ ልቦና መልካም ባህርይ እና የአሸናፊነትን ሥነ ልቦና የተላበሱ አትሌቶችን ለማፍራት ያስችል ዘንድ የአደረጃጀት፣የአሠራር እና የአትሌቶች ቅብብሎሽን በተመለከተ የተዘጋጁ የተለያዩ ጥናቶችና ሠነዶች በስፖርት ሳይንስ ምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ታዳጊና ወጣት ስፖርተኞችን እንዴትና በምን አይነት የስፖርት አይነቶች ለይቶ በማሠልጠን የላቁ ስፖርተኞች ማፍራት እንደሚቻል የሚጠቁሙ አምስት ሞዴሎች በመድረኩ ቀርበው አስተያየት ተሠጥቶባቸዋል።
በዋናነት ከዚህ ቀደም የነበሩ የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶች በተለያዩ አካባቢዎች ሲከፈቱ ስፖርቱን ከማሳደግ ይልቅ ለፖለቲካ አላማ እንዲውሉ መደረጉ ለመክሸፋቸው ምክንያት ተደርጎ አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን፣ ይህ በቀጣይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ተጠቁሟል። በተለይም በተለያዩ አካባቢዎች እምቅ አቅምንና ተሰጥኦን በመለየት ረገድ በአግባቡ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተነስቷል።
ከዚህ ቀደም ታዳጊ ወጣቶችን ለማሠልጠን የሚመደቡ አሠልጣኞች ብቃት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እንደነበርም በመድረኩ ተገልጿል፡፡ አቅሙና ብቃቱ የሌላቸው አሠልጣኞች ወረቀት እየተሰጣቸው ብቻ ወደ ሥልጠና የሚገቡበት አጋጣሚ ነበር። ይህም ለታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ውድቀትና ለአገሪቱም ስፖርት እድገት እንቅፋት መሆኑ ተመልክቶ፣ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በአሠልጣኞች ጉዳይ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
እንደ አዲስ የሚጀመረው የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ወደ ተግባር ሲገባ ከፌዴሬሽኖች መርሐግብር ጋር መጣጣም እንደሚኖርበት ተገልጿል፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችም ቢካተቱና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሊጣጣሙ እንደሚገባ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።
እንደ አዲስ በሚጀመረው የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት እንደየ ስፖርቶቹ አይነትና ባህሪ ታዳጊዎችን ከዘጠኝ ዓመት ጀምሮ በመመልመል ሥልጠና ለመስጠት በቀረቡት ሞዴሎች ተገልጿል። ይሁን እንጂ ይህ ከኢትዮጵያውያን የኑሮ ዘይቤ ጋር ላይጣጣም እንደማይችል ተጠቁሞ፣ ይህ ጉዳይ በአግባቡ መጤን እንዳለበት በመድረኩ ተነስቷል። ለዚህም ወላጆች ልጆቻቸውን ከዘጠኝ ዓመት ጀምሮ ለመልቀቅ ፍቃደኛ ላይሆኑ እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
የማዘውተሪያ ስፍራዎችና ሌሎች በርካታ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ስለ ስፖርቱ ሳይንስ ማውራት የሚለውጠው ነገር እንደሌለም አስተያየት ተሰንዝሯል፤ ስፖርቱን ከትምህርት ፖሊሲ ጋር አቆራኝቶ የሚሰራበትን መንገድ መፈለግ ቅድሚያ ሊሠራበት እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።
በሥልጠናው መድረክ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር እና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የጤና ሚኒስቴር እና የጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚና እና የክልል ታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ሥልጠና ማዕከላት አመራሮች፣ የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት ፕሬዚዳንቶች፣ የጽ/ቤት ኃላፊዎችና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014