አስራ አምስተኛው የዓለም ውሃ ዋና ቻምፒዮና ዛሬ በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አስተናጋጅነት ይጀመራል። ለስድስት ቀናት በሚካሄደው የዓለም ውሃ ዋና ቻምፒዮና ሁለት ወንድና ሁለት ሴት ኢትዮጵያውያን የውሃ ዋና ስፖርተኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል።
በዓለም አቀፉ የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን (ፊና) አዘጋጅነት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አቡዳቢ ከተማ በሚካሄደው ቻምፒዮና በሴቶች ራሄል ፍስሃ እና ብርሃን ደመቀ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በወንዶች ኦቻላ እኛኮቤ እንዲሁም ጥላሁን አያል ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ይጠበቃል።
በዚህ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን ከሚወክሉት ስፖርተኞች መካከል ራሄልና ኦቻላ ባለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ አገራቸውን ለመወከል በፌዴሬሽኑ በኩል ቢመረጡም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ይሁንታ ባለማግኘታቸው ከውድድሩ እንደቀሩ ይታወሳል።
በውሃ ዋና ስፖርት ራሄል ፍስሀ ተስፋ የተጣለባት የ25 ዓመት አትሌት ስትሆን፣ በሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ በ50 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ተሳትፋ በመጀመሪያው ዙር 4ኛ ሆና በማጠናቀቅ ትልቅ ተስፋ የተጣለባት እንደሆነች ይታወቃል።
ራሄል እድሜና ልምድ ያበሰላት ጎበዝ ዋናተኛ መሆኗ ከሪዮ ኦሊምፒክ ጀምሮ ሲነገር የቆየ ሲሆን ከአምስት ዓመት በኋላም በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ለመወከል ዝግጅት ስታደርግ የቆየችና ዓለም አቀፉ የውሀ ስፖርቶች ፌዴሬሽንም ለተሳትፎ እውቅና ሰጥቷት ወደ ቶኪዮ ማቅናት እንዳልቻለች ይታወሳል። በዘንድሮው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠበቁ ታላላቅ ቦጋለ አበበ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የዓለም ውሃ ዋና ቻምፒዮና ከተለያዩ አገራት ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስምንት አትሌቶች በአጭር ርቀት ወይም ሃያ አምስት ሜትር ፉክክር የሚሳተፉ ሲሆን በአርባ አራት አይነት ውድድሮችም በሁለቱም ፆታዎች ይከናወናሉ።
አራት ስፖርተኞችን ጨምሮ ሰባት አባላትን የያዘው የኢትዮጵያ የውሃ ዋና ልኡካን ቡድን ከትናንት በስቲያ ወደ አቡዳቢ ያቀና ሲሆን፣ በውድድሩ የውሃ ዋና ስፖርት ተወዳዳሪዎች ከሚያደርጉት ተሳትፎና ተፎካካሪነት በተጨማሪ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩት የተዛባ ዘገባ ትክክል አለመሆኑን ለማሳወቅ የሚያስችል ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከውሃ ዋና ልኡካን ቡድኑ በተጨማሪ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰረት ደምሰው ከውድድሩ ጎንለጎን አቡዳቢ በሚካሄደው የዓለም አቀፉ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን (ፊና) ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከሚሳተፉ የተለያዩ አገራት የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች ጋር የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታና ያለችበትን እውነተኛ ገፅታ በመግለፅ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጨውን አፍራሽ አመለካከት ለመቀየር ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ውሃ ፌዴሬሽን ባለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ትልቅ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑ በ2021 የውሃ ዋና ብሄራዊ ቡድኑን ይዞ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋና አክራ በተዘጋጀው የአፍሪካ ውሃ ዋና ቻምፒዮና ላይ መሳተፉ ይታወቃል።
ዛሬ በይፋ የሚጀመረው የዓለም ውሃ ዋና ቻምፒዮና በ2020 ሊካሄድ ታስቦ የነበረ ሲሆን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ለአንድ ዓመት ለመራዘም ተገዷል። በዚህም መሰረት ዛሬ የሚጀምረው ቻምፒዮና ‹‹25 ሜትር›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ይህም በቻምፒዮናው የሚደረጉ ፉክክሮች አጭር ርቀት ወይም ሃያ አምስት ሜትር ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ለማመላከት የተሰጠ ስያሜ መሆኑ ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7/2014