አንዳንድ ጊዜ በሕይወት ውስጥ መሰናክሎች ያጋጥማሉ። መሰናክሎቹ ከምጣኔ ሀብት፣ ከፖለቲካ አልያም ከማኅበራዊ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ስናጣ ያልተለመደ አካሄድ መከተል ይመጣል፡፡ በተለይ ጤና ነክ ችግሮች ሲያጋጥሙና መፍትሔ ሲጠፋ ጫናው ይበረታል። ይሄኔ ጅብ ከሚበላኝ በልቸው ልቀደስ የሚለው ይመጣል፡፡
ከመሞት መሰንበትም ሊባል ይችላል፡፡ ከሰሞኑ በአውሮፓ ሁለት መንትያ እህትማማቾች ላልተለመደ ነገር እንደ ህመም ማስታገሻ ተጠቅመዋል ። እህታማማቾቹ ያላቸው ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋግር ይነሳሳሉ፤ አንደኛዋ ላጋጠማት ህመም የሌላኛዋን የጡት ወተት እንደ መድኃኒት ትሞክረዋለች ።
ተመራ ሞውሪ ሀውስሌይ እና ቲኣ ሞውሪ ሀርድሪክት የሚባሉት እነዚህ መንትያዎች ከአሥርዓመት በፊት በታዋቂነት ረድፍ ነበሩ የሚለው የስካይ ኒውስ ዘገባ ያልተለመደ ድርጊታቸው የማህበራዊ ሚድያዎች መነጋገሪያ መሆኑን ይጠቁማል። ክስተቱ ከአባወራዋ አዳም ሀውስሊ ሁለት ልጆች የወለደችው ተመራ ሞውሪ ትታመማለች። ከህመሟም ለመፈወስ መድኃኒት ፍለጋ ብዙ ትማስናለች።
ይህን ያስተዋለችው እህቷ የጡት ወተት ለጎልማሶች ጠቀሜታ እንዳለው የሚያትት ዘገባ በአጋጣሚ አግኝታ ታነባለች፡፡ ወዲያውኑም እህቷን ታስባለች፡፡ ጊዜም ሳታጠፋ የራሱዋን የጡት ወተት ለእህቷ ለመስጠት ትወስናለች፡፡ ታደርገዋለችም፡፡ የጡት ወተቱም ለእህቷ መድኃኒት ይሆናታል።
ታማሚዋ ፈጣሪዋን በማመስገን እህቷ ባደረገችው ጭምር በእጅጉ ትደሰታለች፡፡ ቲኣ! የጡት ወተትሽ በሕይወቴ ከሞከርኳቸው ወተቶች ሁሉ እጅግ በጣም ምርጡ ነው ፤ ›› በማለት በሆነው ሁሉ በእጅጉ መደሰቷ ምለጸን ስካይ ኒውስ ዘግቧል። ተመራ በቡና ሲኒ የተሞላ ወተቷን ይዛ ‹‹ደህና ነኝ፤ ጤነኛነት እና የተሻለ ስሜት ይሰማኛል›› የሚል በመጻፍ “ጤናማና የተሻለ ስሜት ይሰማኛል” በሚል ከፎቶዋ ግርጌ ጽፋ በማኅበራዊ ገፆች ትለቃዋለች፡፡
ድርጊቱ ግን ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማኅበራዊ ገፆች እሰጥ አገባ ውስጥ የከተተ ነበር ። ወተቷን የሰጠችው መንትያ እህት ‹‹እህቴ ማስታገሻ ለማግኘት ተስፋ በሚያስቆርጥ ስሜት ውስጥ ነበረች። የጡት ወተት የአካል ባህሪዎችን ለማዳን ስላለው ፋይዳ የሚያትተውን ዘገባ ላኩላት›› ትላለች፡፡
ኮሪ ሀርድሪክት ከተባለ ተዋናይ ሁለት ልጆችን የወለደችው ቲኣ እህቴ የጡት ወተት ለኮረዶች ያለውን ፋይዳ ተገንዝባ የጡት ወተቱን ለመጠቀም መስማማቷን ታደንቃለች ። የእናት ጡት ወተት ለጨቅላ ህፃናት ጠቀሜታው የላቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለኮረዶች ወይም ለጎልማሶች ስላለው አስተዋፅዖ የሚገልፅ መረጃ ጥቂት ነው። ባለሙያዎችም በጉዳዩ ላይ በሳይንሳዊ ምርምር የተደገፈ ማስረጃ እንደሌለም ይናገራሉ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ