አዲስ አበባ፡– አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭ ጠላቶች አብሮ መሰለፉ የባንዳነት ተግባሩን አረጋግጧል ሲሉ የቀድሞው የሕወሓት ታጋይ አቶ ሊላይ ኃይለማርያም አስታወቁ፡፡
አቶ ሊላይ ኃይለማርያም በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሽብር ቡድኑ አባላት ከሰሞኑ ጦርነቱ የአሜሪካ አስተዳደር እንደሚመራውና ተማክረው እንደጀመሩት በሚዲያቸው ወጥተው አረጋግጠዋል።የአሜሪካ አስተዳደርም ኢትዮጵያን እየወጋት እንደሆነ በግልጽ ነግረውናል ብለዋል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት የባንዳ አባቶቹን ሥራ በማስቀጠል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከጠላት አገራት ጋር መሰለፋቸው ከሰሞኑ የሽብር ቡድኑ አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ ይፋ አድርጓል።በተለያዩ ጊዜያት ከግብጽ፣ ከጣሊያንና ከሌሎች አገራት ጋር ተሰልፈው ኢትዮጵያን ሲወጉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ ሴራዎችን ሲሸርቡ ኖረዋል፤ ኢትዮጵያን ሆነ ብለው ያለ ባህር በር አስቀርተዋታል።እንዲሁም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ከአሜሪካ አስተዳደሮች ጋር ሁነው በዘርና በቋንቋ ከፋፍለው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲጥሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በ1967 ዓ.ም ታላቋን ትግራይ እንመሰርታለን ያሉትን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ቢጥሩም እቅዳቸው አልተሳካላቸውም የሚሉት አቶ ሊላይ፤ የአሸባሪው ሕወሓት ታሪክ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያን ለማፍረስ መንቀሳቀሳቸው አዲስ ነገር ሳይሆን አባቶቻቸው ከባእዳን ጋር ሁነው ኢትዮጵያን ሲወጉ ነበር፤ አሁንም የሽብር ቡድኑ ይህን ተግባር እያስቀጠለ ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ ቁንጮ ጌታቸው ረዳ ስለ ትግራይ ሕዝብ ሥነ ልቦና የሚያውቅ ሰው አይደለም፤ የትግራይ ሕዝብን ወክሎ ሊናገርም አይችልም፤ ብቃቱም የለውም የሚሉት አቶ ሊላይ፤ አዲስ አበባ እንደሚገቡና የያዟቸውን ቦታዎች በራሳቸው ፈቃድ ለቀው መውጣታቸውን ሲገልጹ ነበር። ነገር ግን የሽብር ቡድኑ አባል ጌታቸው ረዳ ስለጦርነቱ በሚናገርበት ጊዜ የራዕይ ፓርቲ አባላት እንዳረጋገጡት ከከሚሴ እስከ ደሴ ባለው መንገድ በግራም በቀኝም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች ረግፈዋል።ሬሳቸውም እንዳልተነሳ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
አሸባሪው ሕወሓት ያረጀ የፖለቲካ ድርጅት ነው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችል አቅሙም ብቃቱም የለውም ያሉት አቶ ሊላይ፤ ለዚህም ነው አገር የማፍረስ ዓላማ ያለው ጦርነት ይዞ የመጣው ብለዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014