አዲስ አበባ፡- ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች በአጭር ጊዜ በጥምር የጸጥታ ሃይሎች ነጻ መውጣታቸው የአሸባሪው ሕወሓት ወታደራዊ አቅሙ መዳከሙንና አከርካሪው መሰበሩን እንደሚያሳይ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሕግና ታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ ገለጹ፡፡
ዶክተር አልማው ክፍሌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሕወሓት የሽብር ቡድን ያለ የሌለ ኃይሉን፤ ገንዘቡንና አቅሙን ተጠቅሞ ደሴንና ኮምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ ከወረራቸው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ተገዶና ተገርፎ እንዲወጣ መደረጉ አከርካሪው መሰበሩን ያሳያል።እነዚህ አካባቢዎች በአገር መከላከያና በሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ትግል ነጻ መውጣታቸው ትልቅ ድል ነው ብለዋል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከአሸባሪው ሸኔና ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጋር በማበር አዲስ አበባን ለመያዝ ቋምጦ እንደነበረ አውስተው፤ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና በሌሎች ጥምር የጸጥታ ሃይሎች የሚደነቅ ተጋድሎ እንኳን አዲስ አበባ ሊረግጥ ቀርቶ በወራራ በያዛቸው ከተሞችና አካባቢዎችም ቅስሙ ተሰብሮና ተሸንፎ መውጣቱን ተናግረዋል።ይህም ሁለቱን አሸባሪ ቡድኖችና ምዕራባውያንን አንገት ያስደፋ አኩሪ ድል እንደሆነ ገልጸዋል። በጠለምት ግንባር ብዙ ጊዜ ሞክሮ ያልተሳካለት የሽብር ቡድኑ የብዙ ብሔር ብሔረሰብ ስብጥር ባለበት በወሎ በኩል ለቁጥር የሚያዳግት ታጣቂ ሃይል አሰማርቶ ሽንፈት መቅመሱ ለኢትዮጵያ ወዳጆች ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር አልማው ገለጻ፤ የደሴና ኮምቦልቻ በጀግኖቹ ተጋድሎ ከሽብር ቡድኑ ነጻ መሆን የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ረገድ የራሣቸው ድርሻ አላቸው። ምክንያቱም በተለይ ኮምቦልቻ ከተማ የኢትዮ ጁቡቲ የንግድ መተላለፊያ መስመር አንዱ አካል ነው፡፡ “የወሎ አካባቢ ወያኔ ደርግን ለመጣል የተጠቀመበት አካባቢ ነው።ከታሪክ አንፃር ቢታይ እንኳን በዚህ አካባቢ በኩል ብዙ ጊዜ ድል ቀንቶታል።በአጠቃላይ ወሎ ለወያኔ የማርያም መንገዱ ናት” ያሉት ዶክተር አልማው፤ በለመደው፣ በሚያውቀውና እጅግ በሚያስቸግረው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ላይ ድል መደረጉ ትልቅ ኪሳራ እንደረሰበት ያሳያል ብለዋል፡፡
በሽብር ቡድኑ ነጻ ያልሆኑ ቀሪ አካባቢዎችን ከማስለቀቅ አንጻር ትልቅ የቤት ሥራ አሁንም ይጠብቀናል፤ ነጻ በወጡ አካባቢዎችም ሁሉም ሕብረተሰብ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ ይኖርበታል። ለጸጥታ ሃይሎች አስተማማኝ የኋላ ደጀንም መሆን ያስፈልጋል ሲሉ ዶክተር አልማው አመልክተዋል።
አላዛር መኮንን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014