አዲስ አበባ፡- አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች በትምህርት ቤቶች ላይ ባደረሰው ውድመት ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምሕርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ተገለጸ።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች ካደረሰው ሰብዓዊ ጥፋት በተጨማሪ የትምሕርት እና ሌሎች ሕዝብ የሚገለገልባቸውን ማኅበራዊ ተቋማት አውድሟል።
በአማራ ክልል ብቻ በወረራቸው አካባቢዎች ከአራት ሺህ በላይ ትምሕርት ቤቶች እንደወደሙ ተገልጿል። በዚህም ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምሕርት ገበታ ውጭ ሆነዋል። የትምሕርት ተቋማቱን መልሶ ለመገንባት እና ትምሕርት ለማስጀመርም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግም የክልሉ ትምሕርት ቢሮ ጥናት አመልክቷል።
በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደሙ የትምሕርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ የትምሕርት ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።
የትምሕርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የወደሙ ትምሕርት ቤቶች መልሰው ሲገነቡ በነበሩበት ደረጃ ሳይሆን በተሻለ ጥራት እንደሚሆን ተናግረዋል። በዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአሸባሪ ቡድኑ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት በሚቻልበት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በባሕርዳር ከተማ ምክክር ተካሂዷል። በምክክሩ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014