በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ አሻራቸውን ካኖሩ የትንፋሽ መሳሪያ (ዋሽንት) ተጫዋቾች ቀዳሚው ነው። ከቀድሞው ማዘጋጃ ቤት እስከ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ምስረታ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ የባህል የሙዚቃ ቡድን ምልክት ከሆኑት አንዱ ነበር። ለሀገራችን የባህል አምባሳደር ሆነው ታላላቅ ስራዎችን ሰርተው ካለፉ የሙዚቃ ፈርጦች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ወጋየሁ ንጋቱ «ፍቅር እስከ መቃብር»ን ሲተርክ የምንሰማትን ልብ አስኮብላይ ዋሽንትና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ኢትዮጵያዊነታችንን በድምፅ ምናብ አግዝፎ እየሳለ እንካችሁ ያለን፤ ስለሙዚቃ የኖረ ለሙዚቃ ዋጋ የከፈለ በሀገሩ የማይደራደር ባለሙያ፤ ዮሐንስ አፈወርቅ። እኛም ዛሬ ይህንን ታላቅ የጥበብ ሰው በ ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› አምዳችን ልንዘክረው እና የሕይወት ጉዞውን ልናወሳ ወደናል፤ መልካም ንባብ!
ልጅነት – ከጎጃም አዊ ዞን እስከ አዲስ አበባ
ከጎጃም ምድር በአዊ ዞን በፋግታ ሊኮማ ወረዳ ልዩ ስሙ በክታ ከምትባል ቦታ ነው የዋሽንቱ ንጉሥ አቶ ዮሐንስ አፈወርቅ የፈለቀው። ከወላጅ እናቱ እማሆይ ወለላ ተገኘ እና ከቄስ አባቱ አፈወርቅ ጀንበሬ በ1939 ዓ.ም ተወለደ። ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በአርቲስቱ ህይወት ዙሪያ ባዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ላይ ስለ ልጅነት ገጠመኙ ሲናገር፤ ወላጅ አባቱ ቄስ ስለነበሩ ምኞታቸው እና ፍላጎታቸው ልጃቸው የቤተክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆን እንጂ ሸንበቆ (ዋሽንት) እንዲጫወት ስላልነበር ብዙ ጊዜ ሽንበቆውን ሰብረው እሳት ውስጥ ይጥሉበት እንደነበር ተናግሯል። ባለዋሽንቱ አፈወርቅ ልጅ ሳለ እነ ዝግኒን ፣ሻንቲን ፣በስኒን ፣ጉደርን ዋኝቶ ቢሻገር ዋኝቶ ይመለሳል። በድልድዩ ቢያልፍ በድልድዩ ይመለሳል እንጂ ከዚያ ከወንዞቹ ማዶ ያለውን ዓለም ፤ ከአቦ ደብር ወዲያ ያለው ዓለም እምብዛም አያሳስበውም ነበር።
ከጓደኞቹ ጋር ከፋግታ ተነስቶ በሩጫ ቲሊሊን አቋርጦ የቡሬን ጠበል ጠጥቶ እያገሳ በመጣበት አኳኋዋን ወደ ደብሩ ይመለሳል እንጂ ወደ ፊት ልቀጥል አይልም ነበር። አንድ ቀን ታዲያ የፋግታ ከተማ ሻይ እንዲቀምስ አድርጋ ከተማን እንዲናፍቅ አደረገችው፡፡ ዮሐንስም የቀመሳትን ሻይ ለመደጋገም ቢፈልግም ገንዘብ ማግኘት አልቻለም። እናም ገንዘብ የሚያገኝበት መላ ፈለገ፡፡ በሲምዛ እንጨት ላይ እሾህ በማድረግ እንደ ቀስት በመጠቀም ገበያ ሊሸምት እና ሊሸጥ ከወጣው ገበያተኛ ሽንኩርት እና ዝንጅብል እየወጋ በመውሰድ ሽንኩርት እና ዝንጅብል ለሻይ ነጋዴው በመስጠት በምላሹ ሻይ ይጠጣ ነበር።
በሻይ የገባው የከተማ ፍቅር ልቡን ይይዘው አእምሮውን ይቆጣጠረው ገባ፡ ፡ እንዲያው በሰማይ በርሬ በምድር ተሽከርክሬ ያሰኘው ጀመር። ታዲያ ይህ ሂድ ሂድ የሚያሰኘውን ስሜት አስተናግዶ ይሄይስ የሚለውን የልጅነት ስያሜውን በራሱ ፍቃድ ቀይሮ ዮሐንስ በሉኝ ማለት ጀመረ። አንድ ጠዋት ከፋግታ ገስግሶ አዲስ ቅዳም ገባ፡፡ ጀንበር ስትዞር መሸብኝ ልመለስ አላለም፡፡ ከአዲስ ቅዳም ባህር ዳር በሚወስደው አውቶቡስ ለመሳፈር ባለቤቱን አቶ ንዋይ ወልደ ማሪያምን በያዝኩት ሰላሳ ሳንቲም ዳንግላ ድረስ ውሰዱኝ ብሎ በመለመን እርሳቸውም ፈቅደውለት ጉዞ ጀመረ፡፡
ከዛም ተሳፋሪው ዳንግላ አካባቢ ምሳ ለመብላት ሲወርድ ዮሐንስ መኪና ውስጥ ቀረ፡፡ ታዲያ ረዳቱ እንደ ዮሐንስ አጠራር አውታንቲው ውረድ እንጂ ሲለው አልወርድም ይህ አውቶቡስ ወደሚሄድበት ከተማ ነው የሚሄደው ፤እኔ እናትም አባትም የለኝም የአገሬው ሰው እረኛ አድርጎኝ ከብት ካስጠበቀኝ በኋላ ምንም ገንዘብ አይሰጠኝም፤ ስለዚህም አልወርድም በማለት በዚሁ አውቶብስ አዲስ አበባ ሊመጣ ችሏል፡ ፡ የመኪናው ባለቤት አቶ ንዋይም ዮሐንስን ወደ ቤታቸው ወስደው ማኖር ጀመሩ፡፡ ታዲያ በአዲስ አበባ አቶ ንዋይ ቤት እየኖረ ሳለ የሰፈሩ ልጆች እየተነኮሱ ማስቸገር ጀመሩ፡፡ «ባላገሩ!» እያሉ ሲያሾፉበት ትእግስቱ ከቀናት በላይ አላለፈም እያነሳ ያፈርጣቸው ጀመረ፡፡ ፋግታ መስክ ላይ ከብት ሲጠብቅ ትግልና ዋሽንት አይደል ውሎው! ስሞታ በዛ፤ ጎረቤቱ ተንጫጫ፤ አቶ ንዋይ ልብስ አልብሰው በዚያው አውቶቡሳቸው አዲስ ቅዳም መለሱት፡ ፡
ዮሐንስ በአዲስ ልብሱ ሆኖ አዲስ አበባ ደርሶ መመለሱን እየተናገረ ፋግታዎችን ሲያስደምም ከሰነበተ በኋላ ዳግመኛ ወደ አዲስ አበባ በእግሩ ጎዞ ጀመረ፡፡ ቲሊሊ ፣ቡሬ ፣ፍኖተ ሰላም ፣አማኒላ ጠላ ቤት እየገባ እየዘፈነ ሳንቲም እያገኘ ስንቅ እያደረገ ከመሸበት እያደረ ደብረ ማርቆስ ገባ፡፡ ከማርቆስ ደግሞ እንዲሁ ጠላ ቤት ሲዘፍን ያገኙት ወታደሮች በመኪና አዲስ አበባ አደረሱት፡፡ ታዲያ አዲስ አበባ እንደ መጀመሪያው አይደለም ዮሐንስ የተቀበለችው፡፡ ዩሐንስም ቢሆን እንደ ቀድሞ ባዶ እጁን ሳይሆን ሽንበቆውን (ዋሽንቱን) በመያዝ ስለነበር ከዚህ ቀደም ይጣሉት የነበሩ ልጆች ዋሽንቱን ሲጫወት ከበውት ማድመጥ ጀመሩ። ልጆቹ በዋሽንቱ ከመማረካቸው የተነሳ ዮሐንስን ማክበር ማጫወት እንዲያውም ሳንቲም እያመጡ ብስኩት፤ ሳንቡሳ ሻይ መጋበዝ ጀመሩ፡፡ ታዲያ ከልጆቹ ጋር አብሮ መጫወት የዮሐንስ የዘውትር ተግባሩ ሆነ። እናም አንድ ቀን እንደተለመደው ከሰፈር ልጆች ጋር ሊጫወት በወጣበት አንድ ሰው ወደ ትልቅ ጠጅ ቤት ይዞት ሄደ፡፡ እማሆይ ጠጅ ቤት ዋሽንት በሚጫወትበት ጊዜ ሽልማቱ በዝቶ ሳንቲም በሳህን እየሰበሰቡ ይሰጡት ጀመረ፡፡
የእማሆይ ጠጅ ቤት
በሳምንቱ መጀመሪያ የተለመደው ተግባሩን ሊከውን የወጣው ዮሐንስ አንዱ ወዳጁ መርካቶ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት ይዞት ሄደ፡ ፡ ታዲያ እዚያ አንድ ሰው ከበሮ እየመታ አልፎ ሂያጁን እያዝናና ለስራም ለግብይትም የወጣ ሰው ቆም እያለ እያየ እያደነቀ ሳንቲም እየሰጠው ይሄዳል። ዮሐንስም ዋሽንቱን ይዞ ከአጠገቡ በመሆን መጫወት ጀመረ። የዮሐንስ ከከበሮው መቺው ጋር አብሮ መሆን ሰው ሁሉ እንደ ብርቅ እንዲያያቸው እና ሽልማቱ እንዲጨምር ሆነ፡፡
ታዲያ ይህንን ሽልማት እና አድናቆት ያየው ዮሐንስ አፈወርቅ ባለ ከበሮውን ጅግሶ በዶሶን ወዳጁ አድርጎ፣ ጂግሶ ከበሮውን ዮሐንስም ዋሽንቱን ይዘው ሙያቸውን እያሳደጉ ሳንቲምም እያገኙ የልጅነት ጊዜያቸውን መግፋት ጀመሩ፡፡ ዮሐንስን ጠጅ ቤት ውስጥ ሲጫወት ያገኙት አንድ የፖሊስ መኮንን ኮልፌ የፖሊስ ማሰልጠኛ አስገብተውት ነበር፡፡ የወታደር ቤት ለዮሐንስ ብዙም አልተስማማውም፤ ትቶት ወጣ፡፡ ዋሽንቱ ስለሌለች በረንዳ ወደቀ፤ ተሸካሚነት ጀመረ፡፡ እንደገና ዋሽንት አገኘና ወደ ሙዚቃው ተመለሰ፡፡ ዳግም ከጂግሶ በዳሶ ጋር ገጠመና ደቡብ ኢትዮጵያን ዞራት፡ ፡ አፖስቶ፣ ይርጋለም፣ ዲላ፣ አለታ ወንዶ፣ አገረ ሰላም፣ ሻሸመኔ፣ ከቡና ቤት እስከ ሰርግ ቤት ፣ከጠጅ ቤት እስከ መኖሪያ ቤት እየዞሩ አደመቁት፡፡
በወቅቱ በሽልማት ብቻ ከአንድ ሺህ ብር በላይ ሰበሰቡ፡፡ ከዚያ መልስ ነው በ1959 ዓ.ም ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን የተቀላቀሉት፡ ፡ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን ከተቀላቀለ ሶስት አመት በኋላ ትዳር መሰረተ፡፡በ1961ዓ.ም ደግሞ ደራሲ ተስፋዬ ለማ የደረሰውን “እኛም አለን ሙዚቃ ስሜት የሚያነቃ” የሚለው ሙዚቃ እየተሰራ የሙዚቃ መሳሪያ የሚተዋወቅበት ነበር፡፡ ታዲያ የተስፋዬ ድርሰት የባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያ ከፍ ያደረገ እና ያስተዋወቀ በመሆኑ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጣ፡፡
ጉዞ ወደ አሜሪካና ከጉዞው መልስ
ጌታመሳይ አበበ ማሲንቆ ያስተማረው ቻርልስ የተባለ አሜሪካዊ አገሩ ከሚገኙ የተለያዩ ሰዎች ጋር በመጻጻፍ ለኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የውጭ ጉዞ አመቻቸ፡፡ ታዲያ በዓመቱ ሶስተኛ ወር የአሜሪካ አርማ ያለው የአገሩ አውሮፕላን መጥቶ ከአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ አሳፈራቸው፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲጓዙ ቆይተው በ12 ሰዓት አሜሪካ ኒውዮርክ ገቡ፡፡ ባህሩን እያቋረጡ እያሉ በሃሳብ ወደ ኋላ ተመልሶ አጨዳ ላይም ሆኖ አረም ላይ እያለ አውሮፕላን በሰፈሩ ሲያልፍ በዚህ ሄጄ ብሞት ብሎ ያሰብ ነበር፡፡
ከአሜሪካ መልስ ዮሐንስ በ40 ብር ደመወዝ ከኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ወደ አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ገባ፡፡ አገር ፍቅር የሙዚቃ ሙያን የበለጠ እንዲያዳብር ዕድል የፈጠረለት መሆኑን በተለያየ ጊዜ ተናግሯል። ይሁንና በደመወዝ ጭማሪ ቅሬታ አድሮበት ወደ ኦርኬስተራ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያም የአብዮቱን መምጣት ተከትሎ በ1968ዓ.ም በመንግሥት ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ጋር ተቀላቀለ፡፡
ከአብዮቱ በፊት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ከኦርኬስትራዎችም ሆነ ከቴአትር ቤቶች ሙዚቃዎችን ይገዛ ነበር፡፡ ከመቶ በላይ የዋሽንቱ ንጉሥ ዮሐንስ አፈወርቅ የሚሆኑ የዮሐንስ የዋሽንት ስራዎችም የተቀረጹት እንዲህ ባለ ሁኔታ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን ሬድዮንም ሆነ ቴሌቪዥን የሚሰማም ሆነ የሚመለከት ሁሉ ባለዋሽንቱን ባያውቅም እንኳ ለዜማዎቹ አዲስ አይደለም፡፡ የዮሐንስ ስራዎች በተለይ በ1966 ዓ.ም በወሎ ክፍለ ሀገር የተወሰኑ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ የሀዘን ዜና ሲሰራ ማጀቢያ ሆኖ ያገለገለ እና ጉዳዩ በሰው ልብ እና አእምሮ ገዝፎ እንዲሰማ ያደረገውን ዜማ ሰርቷል፡ ፡ የፍቅር እስከ መቃብር ልብ ወለድ ድርሰት በሬድዮ ሲተረክ ከተራኪው ወጋየው ንጋቱ ባልተናነሰ ድርሰቱ ላይ ነፍስ የዘራበት በዋሽንት የተቀነባበረው የዮሐንስ አፈወርቅ ስራ ነው ፡፡
ህዝብ ለህዝብ- ከህዝብ መተዋወቂያ መድረክ
በአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ አቀናባሪነት የተለያዩ የሙዚቃ ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን ተቋቋመ፡፡ በዚህም መሰረት ጌታመሳይ አበበ መስንቆ፣ አሌያስ አረጋ በክራር፣ ኮት ሁጁሉ በቤዝ ጊታር፣ በከበሮ ተካ ጉልማ፣ በዋሽንት ዮሐንስ አፈወርቅ በመሆን ነበር። ሙዚቃውን በመስራት በተለያዩ ቦታዎች ጉዞ ሲያደርጉ የነበረው፡፡ ሁሉም ሙዚቀኛ ሁለት ሁለት ሆኖ አንዱ ሲደክመው ሌላኛው እንዲያግዝ ሲደረግ አርቲስት ዮሐንስ አፈወርቅ ግን ብቻውን ከአንድ ሰዓት በላይ ለማይቋረጠው ሙዚቃ በብቃት ቅኝት እየሰጠ ያገለገለ የዋሽንት ንጉሥ ነው፡፡
ስለዚህ የዋሽንት ንጉሥ ጸሐፊ ተውኔት እና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ ሲናገሩ «ዮሐንስ ዝም ብሎ ዋሽንት ብቻ የሚጫወት ሙዚቀኛ አይደለም ፤በሚጫወት ወቅት ዐይንም ቀልብም የሚስብ እንስቃሴ ስለሚያደርግ የተመልካች ትኩረት በሙሉ እሱ ላይ ስለሚሆን ሌሎች ሙዚቀኞችንና ተወዛዋዦችን እስከ መሸፈን ይደርስ የነበረ ሙዚቀኛ ነበር፡፡ የሚገርመው ዋሽንት መጫወት ከባድ ትንፋሽ ይፈልጋል፤ ያንን ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጨመሩ የተለየ ተሰጥኦ እንዳለው ያስታውቃል፡፡ ማንም ይህንን በቀላሉ ሊያደርገው አይችልም ፤ዮሐንስ ግን ይህንን የታደለ ሙዚቀኛ ነበር» ብለዋል፡፡ ጸሐፊ ተውኔት እና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ አክለው ሲናገሩ ታዳሚ ከነበሩ ሰዎች መካከል የተወሰኑ ፈረንጆች መጥተው ዮሐንስ አፈወርቅ ከኋላ የሚረዳው ነገር አለ እንጂ ብቻውን ይህንን ሊያደርግ አይችልም ሲሉኝ የሙዚቃው ባለሙያው የተለየ ተሰጥኦ ያለውና ያለ አንዳች የሰውም ሆነ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚጫወት ነግሬያቸው በመድረክ ላይም እየተጫወተ ከጀርባው ወስጄ አሳይቻቸዋለው ብለዋል። ዮሐንስ አፈወርቅ በባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ ሙዚቀኞች አንዱ ናቸው። የሙዚቃና ቴአትር ሙያተኛው ተስፋዬ አበበ “ዋሽንት ከኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከባዱ ነው” ይላሉ። “ዋሽንት ትንፋሽ ይጠይቃል። አለስልሶ ለመጫወትም ብቃትም ያስፈልጋል።
ዮሐንስ በዚህ በኩል አንቱ የተባለ ነው፤ ምትክ የለውም። “ዮሐንስ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በነበሩ ጊዜ ‘ሶሎ’ ሲጫወቱ የተስተዋለውን ጥበብ ተስፋዬ ያስታውሳል። ትዝታ፣ አምባሰል፣ ባቲ የኢትዮጵያ ቅኝቶችን በረቀቀ ሁኔታ ያስደምጡ ነበር። ተስፋዬ አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ሳይሆን ሳያልፉ በፊት ላበረከቱት አስተዋጽኦ መመስገን አለባቸው ይላል። የአምስት ልጆች አባት የነበረው ባለዋሽንቱ ዮሐንስ አፈወርቅ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ከአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ በጡረታ ተሰናብቷል፡፡ ህይወቱ እስካለፋችበት ጊዜ ድረስ በወር ሰባት መቶ ብር ይከፈለው ነበር፡፡
የዋሽንቱ ንጉሥ በጡረታ ቢገለልም ከዋሽንቱ አልተያየም፤ ከወጣት ሙዚቀኞች ጋርም በጥምረት ይሠራ ነበር።’ኢትዮ ከለር’ በተወዛዋዡ መላኩ በላይ የተመሰረተ የባህል ሙዚቃ ቡድን ሲሆን፤ ወጣትና አንጋፋ ሙዚቀኞችን በጋራ መድረክ ላይ በማቅረብ ይታወቃል። ከዮሐንስ ጋር በአንድ መድረክ የተጫወተው መላኩ በላይ፤ ዮሐንስን የሚያስታውሳቸው ዋሽንትን የላቀ ደረጃ በማድረሳቸው ነው።”የሸምበቆ መሳሪያው ዋሽንት ተንቆ በግለሰብ ደረጃ ብቻ የሚጫወቱት ተብሎ ነበር። እሱ ግን ዋሽንት ከባንድ ጋር ተቃኝቶ እንዲቀርብ አድርጓል።” ዮሐንስ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃን ከማሳደግ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቃቸውን ይናገራል።
ለዓመታት ከዮሐንስ አፈወርቅ ጋር መሥራት ከማያልቅ እውቀታቸው መቅሰም መሆኑን ያወሳል። “ሰዓት ላይ ጥንቁቅ ነበረ፤ ቀድሞን ይደርሳል። በሥራው አመስጋኝ ነበር። ከክፍያው በላይ ሥራው ላይ ያተኩራል፤ ሥራውን ይወዳል።” መላኩ እንደሚለው አዝማሪዎች እንዲሁም ዋሽንት ተጫዋቾች ሙያው ትልቅ መሆኑን በዮሐንስ ስኬት ውስጥ አይተዋል።”እረኞችን ዋሽንት ለካ እንደዚህ እውቅና ያሰጣል አስብሏል። አልበም ማውጣትም ይቻላል የሚል ተስፋ የሰጠ፣ ብዙዎችን ያነቃቃም ሙዚቀኛ ነበረ።
”በዕድሜው ጸጋ ይበልጥ ዳብሮና በክህሎትም በልጽጎ የጣፈጠ ክህሎቱን እንካችሁ ሲል ነበር፡፡ ስለአርቲስቱ የሙያው ባልደረቦቹ ሲናገሩ ዮሐንስ ዝናው ከፍ ያለ ባለሙያ ቢሆንም በገንዘብ ደረጃ ምንም የሌለው ሰው ነው፡፡ የቀድሞ አርቲስትና እና ሯጭ አንድ ናቸው ያሉት አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ ሲሆኑ ሁለቱም በተሰለፉበት መስክ አገር ያስጠሩ ሲሆን ለግላቸው ግን ምንም ጥሪት ያላስቀመጡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው ብለዋል፡፡ ሌላኛው የአርቲስቱ ወዳጅ የደራሲን ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ደራሲ አበረ አዳሙ እንዳሉት ዮሐንስ አፈወርቅ በሙያው አንቱ የተባለ ለአገርም የዋለው ውለታ ብዙ ቢሆንም ከገንዘብ አንጻር አንዳች የሌለው ሰው ነበር፡፡ አርቲስቱ ከዚህ ቀደም ዐይኑን እንኳን ታሞ የሚታከምበት አጥቶ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እንዳሳከመው አስታውሰዋል፡፡ በጊዜው አርቲስቱ ሲናገር «ለፍቻለው፣ ደክሚያለው፤ ይህ አይገባኝም ነበር። ነገር ግን ምንም ማድረግ ስለማልችል ትቼዋለው፡፡
ለእኔ የጡረታ ገንዘቤ ይበቃኛል፤ ልጆቼ እንደሆነ እድሜ ለኢትዮጵያ ህዝብ አድገው ተምረው እራሳቸውን ችለዋል» ብሏል። ይህንን የዋሽንት ንጉሥ ባሳለፍነው ሳምንት በሞት አጥተነዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብሩ የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ 9:00 ሰዓት ተፈጽሟል። ዮሐንስ አፈወርቅ በአደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ72 ዓመቱ የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው። ለቤተሰቦቹ ፣ ለመላው አድናቂዎቹ እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች መጽናናትን እንመኛለን፡፡ ሰላም!