አንዳንዶች ‹‹የኢትዮጵያ ቅኔ ዩኒቨርሲቲ ነው›› ይሉታል። ምክንያቱም ተማሪው ከመምህሩ ጋር ሰምና ወርቁን እያስማማ ሲዘርፍ ማስተዋል በቦታው የዕለት ተዕለት ተግባር ስለሆነ። ሌሎች ደግሞ የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ እትብት የተቀበረበት ስፍራ ነው ይሉታል። ምክንያቱም የሚያውቁት የሐዲስ አለማየሁ የፍቅር እስከመቃብር ድርሰት ታሪክ ዋነኛ መቼት በመሆኑ ነው። ዲማ ከአዲስ አበባ በደጀን ታጥፎ ወደ ሞጣ በሚጓዘው መንገድ ከብቸና ከተማ በስተ ምስራቅ ይገኛል። ምቹውን የደጀን እና ቢቸና አስፓልት መንገድ እንዳጠናቀቁ ምእራባውያን ‹‹አፍሪካን ማሳጅ›› እያሉ የሚሳለቁበት ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገድ ይቀበሎታል።
የውጭ ጎብኚዎች ይህን ስም ያወጡለት በጉዞው ላይ ምቾት እየነሳ እና እያንገራገጨ ከተሽከርካሪው ወንበር ጋር ስለሚያፋትጋቸው ነው። ውብ የባህል፣ የሃይማኖት እንዲሁም የተፈጥሮ ቦታ አጣምሮ ወደያዘችው ዲማ መጓዝ ለሚሻ ሰው ይህ ትንሽ ችግር እንቅፋት እክል እንዳይሆንበት ማሰቡ መልካም ነው። መንገዱ ለቱሪስት በተለይም ለህጻናትና አረጋውያን የማይመች መሆኑን ልብ ይሏል። ‹‹ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም›› በምስራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ወረዳ ከሚገኙት ስመ ጥር የቱሪስተ መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው፡ ፡
እነማይ ወረዳ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በምስራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙ 21 ወረዳዎች ውስጥ አንዱ ነው። እነማይ ከአዲስ አበባ በ265 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ከባህርዳር ደግሞ በ222 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው። ዲማ ጊዮርጊስ ገዳም በአካባቢው ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኑ ታምኖበት የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች መጠነኛ የማስተዋወቅ ስራ እያከናወኑበት ይገኛል። ይሁንና ታሪካዊውን በይበልጥ ታዋቂ ያደረገው የሐዲስ አለማየሁ ድርሰት መሆኑ የማይካድ ነው።
የገዳሙ ትርጓሜ
የገዳሙ መጠሪያ ስም በቀድሞ ዘመን ‹‹ደብረ ድማህ›› ይባል የነበረ ሲሆን ከጊዜ ቆይታ በኋላ ስያሜው ወደ ‹‹ዲማ›› ተለወጧል። ታሪክ አዋቂ አባቶች እንደሚሉት ከሆነ ደብረ ድማህ ማለት ከግዕዝ የተወረሰ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም (ራስ፣ የሁሉ የበላይ ወይም ጭንቅላት) እንደማለት ነው። ከዚህ ትርጓሜ መረዳት እንደሚቻለው ቦታው በጊዜው የጎጃም ማዕከል እንደነበረ ነው። የገዳሙ መጠሪያ ስም ‹‹ደብረ ዲማ›› ሲሆን በትርጓሜው መሰረት ገዳሙ የሁሉ የበላይ መሆኗን ለማመላከት የወጣ መሆኑን መገንዘብ ያስችላል። በሌላ በኩል ዲማ ማለት ቀይ ማለት እንደሆነ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ። በጊዜው አንድ ትልቅ ቀይ ዛፍ በቦታው ስለነበረና ስሙም ከዚህ የተወሰደ መሆኑን ለማመላከት እንደሆነም ይነገራል፡፡
ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም የተመሰረተው በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግስት በ1297 ዓ.ም ነው። ከአፄ ይስሃቅ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ደግሞ በገዳምነት ተሰይሞ፤ በሚሰጠው ትምህርት አማካኝነት ዝናው የናኘ ሊሆን በቅቷል። ዲማን የመሰረቱት አባት አባ በኪሞስ የተባሉ ሰው ናቸው። በጎጃም እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክ እየጠመቁ ሳለ አንድ ቀን ከአማንያን ብዛት የተነሳ የማጥመቅን ስራ ሳይጨርሱ ጀንበር ትጠልቅባቸዋለች። ይህ ሲሆን አምላክን ይለምኑታል። ብርሃንም ወርዶላቸው ስርዓተ ጥምቀቱን ይፈፅማሉ። ይሄ ተእምር እንዲፈፀም ያስቻሉት አባት ከዚያ ጊዜ በኋላ ስማቸው ተከስተ ብርሃን እንደተባለ እና በገዳሙ ታሪክ ትልቅ ቦታ እንደተሰጣቸው በድርሳናት ላይ ተፅፎ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሀዲስ ኪዳን ሥርዓተ ህግ መሠረት አራት የአስተዳደር ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነርሱም ደብር፣ ገዳም፣ ገዳም ወደብር እና ገጠር በመባል ይታወቃሉ። የዲማ ጊዮርጊስ አስተዳደር ሥርዓት ደግሞ ገዳም ወደብር የሚባለው ዓይነት ነው። ባህሪውም ስጋዊና መንፈሳዊ ገጽታ ያለው ሲሆን የገዳምነትንና የደብርነትን ስራ አጣምሮ ይዟል። እንደገዳምነቱም በመነኩሴ ብቻ ነው የቅዳሴ ሥነሥርዓት የሚካሄደው። አስተዳደሩንም በበላይነት ይመሩታል።
እንደ ደብርነቱ ደግሞ ስጋዊ ህይወት የሚመራበት በመሆኑ ስጋዊ የአስተዳደር ሥርዓትም ጐን ለጐን ይካሄድበታል፡፡ የዲማ ገዳም ወደ ብር የሰበካ ጉባኤ በበላይነት የሚተዳደረው በመነኩሴ ሲሆን መጠሪያ ማዕረጉም ‹‹ርዕሰ መምህር›› ይባላል። መምህሩ የሚመረጡት በህዝብ ነው፡፡ የሃይማኖት ህፀፅና ነውር ካልተገኘባቸው በስተቀር እስኪሞቱ ድረስ ወንበራቸው የፀና ነው። አሁን ገዳሙን የሚመሩትና የሚያስተዳድሩት መምህር አባ ወልደ እየሱስ የሚባሉ ዕድሜያቸው በ60ዎቹ የሚገመት መነኩሴ ናቸው።
የገዳሙ ቅኝት
ዲማ ጊዮርጊስ ከትንሿ የገጠር ከተማ በስተደቡብ ከደልዳላ ስፍራ ላይ በአረንጓዴ እጽዋት መሀል ይገኛል። በደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ የተጠቀሱትን መንደሮች አቀማመጥና የቤቶች አሰራር ሲመለከቱ ድንገት የዋና ገፀ ባህሪዎቹ የበዛብህና ሰብለ ወንጌል ታሪክ ትውስ ይላል። በቦታው የካህናት ዜማ እና የከበሮው ድምፅ ሲያስተጋባ በምናብ ይደመጣል። የዲማ ጊዮርጊስ ደብር ዙሪያውን የታጠረ ሲሆን ከድንጋይና ከጭቃ የተገነባ ነው። ከፍታው ሁለት ሜትር ተኩል ይደርሳል። ውፍረቱ ደግሞ ከሁለት ሜትር በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ይህ አጥር በክረምት ወቅት አረምና የሙጃ ሳር ስለሚበቅልበት ከርቀት ሲታይ ቁጥርነቱን ለመለየት እንደሚያስቸግር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። መሀል ላይከነ ግርማ ሞገሱ ጉብ ብሎ የሚታየው የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጣሪያ ከረጃጅም የጥድ፣ የወይራና የዋንዛ ዛፎች በላይ ከፍ ያለ ነው።
ጣሪያው የቆርቆሮ ክዳን ሲሆን ከጣሪያው አናት ላይ ባለው ጉልላት የተንጠለጠሉት መርገፎች (በጉልላቱ እና ክፈፉ ላይ የሚሰቀሉ የቤተክርስቲያን ጌጦች) ወትሮም ቢሆን ነፋስ ሲያነቃንቃቸው ጥዑመ ዜናም ይለግሳሉ። ጉሉላቱ ላይ ደግሞ ባለ 15 ጫፍ የሆነ ከነሐስ የተሰራ መስቀል ከነግርማ ሞገሱ ይታያል። ወደ ጥንታዊው ገዳም ውስጥ ብዙም ዘልቀን ሳንገባ በስተሰሜን አቅጣጫ በግምት 50 ሜትር ሲቀረን የመነኮሳቱን የመኖሪያ ገዳም እናገኛለን። የመነኮሳቱ መኖሪያ ገዳም እንደ ግብር ማብያ አዳራሽ የተንጣለለ ነው። መነኮሳቱ የሚተዳደሩት በግብርና ነው። ንብ ማነብ፣ የፍየል ርባታ እንዲሁም ከመኖሪያቸው ጀርባ በሚገኝ ቦታ ላይ የጓሮ አትክልትና የአገዳ እህል ያመርታሉ። ራሳቸውን ከማስተዳደር ባሻገር ቤተክርስቲያኑን ይንከባከባሉ።
ዲማን አሁን አሁን የተለያዩ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መዳረሻቸው አድርገውታል። በተለይ ሴት የቅኔ መምህሯን ለማየት እና ቅርሶቹን ለመጎብኘት በርካታ ሰዎች ወደ ስፍራው ማምራት ጀምረዋል። የዝግጅት ክፍላችን ዘጋቢ በቦታው ተገኝቶ ይሄን መታዘብ ችሏል። የአገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች ስፍራውን እንዲመለከቱ አስጎብኚዎች ከዚህ በተሻለ መንገድ ጥረት ማድረግ እና የማስተዋወቅ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል። ወደ ገዳሙ ከመገባቱ በፊት በስተምዕራብ አቅጣጫ ከአጥር ውጭ ራቅ ብሎ በትናንሽ ጐጃዎቹ የተከበበ አንድ አሮጊ የቆርቆሮ ቤት ይገኛል። የዲማ ጊዮርጊስ መንፈሳዊ ትምህር ቤት ነው።
ጎጆዎቹ ዙሪያቸውን በሰንሰል ታጥረዋል። ፍቅር እስከ መቃብርን ካነበቡ ወይም ትረካውን ከሰሙ ይህን ጊዜ አንድ ነገር በአይነ ህሊናዎ ይመጣበዎታል። ይህም የፍቅር እስከ መቃብሩ የበዛብህ ቦጋለና የቅኔ መምህሩ የአለቃ ክንፈ የቅኔ ማዕበል መሆኑን ወዲያው ይረዳሉ። ከጎጆዎቹ አለፍ ብለን ወደ ቤተክርስቲያኑ ስንገባ አጥሩ በደቡብና በምእራብ አቅጣጫ ሁለት በሮች እንዳሉት እናያለን፡፡ ዋናው የምዕራቡ በር ነው። ይህ በር ደጀ ሰላም ይሰኛል። ሶስት ሜትር በሶስት ሜትር ስፋት አለው። አገልግሎቱ ለመውጫና መግቢያ ነው።ከላይ ባለ አንድ ደረጃ ህንፃ ይዟል። የፎቁ ርብራብ ከተጠረበ ጽድ ጣሪያው ደግሞ ከቆርቆሮ የተሰራ ነው።
በደጀ ሰላሙ የተገናኘ ሰው የእግዜር ሰላምታ ተለዋውጦ ማለፍ ባህሉ ነው። በቅጥሩ ውስጥ ዕድሜ ጠገብ የጽድ ዛፎችና ጥቂት መቃብር ቤቶች ይታያሉ፡፡ መቃብር ቤቶችን የደብሩ አገልጋይ የሆኑ ሴት መነኮሳትና አቅመ ደካሞች ይኖሩባቸዋል። በክብ ቅርፅ የታነፀው የዲማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ግድግዳው ከድንጋይና ከሲሚንቶ የተዋቀረ ነው። በሶስት አቅጣጫዎች በሮች አሉት። በሮቹ ባለሰፋፊ የጽድ ሳንቃዎች ናቸው። ከመስታወትና ከብረት በመስቀል ቅርጽ የተሰሩ 30 የሚደርሱ መስኮቶች አሉት። የገዳሙ ውስጣዊ ገጽታ በተዋቡ ጥንታዊ ስዕሎች የተነቆጠቆጠ ነው። በጨርቅ ላይ የተሳሉ የቅዱሳን ስዕሎች በተጠረበ እንጨት ላይ ተወጥረው ለዕይታ ቀርበዋል።
ድንቅ ቅርሶች
ታሪካዊው ገዳም በውስጡ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶችን እንዲሁም የነገስታትን አሻራ ይዟል። ከብዙ በጥቂቱም የአፄ ዮሀንስ አራተኛ የወርቅ ዘውድ፣ የወርቅ መስቀሎችን፣ የአፄ ይሳቅ የወርቅ ጫማ፣ የበትረ ሙሴ ተምሳሌት የሆነ የወርቅ ዘንግ በገዳሙ ይገኛሉ። የንጉስ ተክለሐይማኖት ጦር፣ በስዕል የተዋቡ በርካታ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍት፣ አርባአቱ ወንጌልና ገድለ ጊዮርጊስ የተባሉ ጥንታዊ ጽሁፎች አሁንም በገዳሙ ይገኛሉ።
አፄ ሚኒሊክ ለዲማ የሰጡት ውስጡ በህብረ ቀለማት ያማረ እና እስከ 70 ሰዎችን መያዝ የሚችል ክብ ቅርጽ ያለው ድንኳን አለ። ድንኳኑ ለክብረ በዓላት እና አስፈላጊ ለሆኑ ጊዜዎች ብቻ ይወጣል። የራስ መኮንን ካባና ሌሎች የጽሁፍ መረጃዎችን እንዲሁም የወርቅ እና የብር መገልገያዎቸ አያሌ ናቸው። ይሁንና እስካሁንም የጎብኚ ያለህ እያሉ የሚጣሩ ይመስላል። ለቅርሶቹ የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም እየተገነባ ሲሆን፤ አጠቃላይ ወጪው እስከ አራት ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ካህናቱ ይገልጻሉ። አብዛኛው ስራው ተጠናቋል። በብል እና በተባይ እየተጎዱ የሚገኙ ጥንታዊ ብራና መጽሐፍትን ከጉዳት ለመከላከል አይነተኛ መፍትሔ ነው። እስካሁን ቅርሶቹ የሚገኙት በእቃ ቤት ውስጥ ነው። በዚህ ስፍራ መቀመጣቸው ለጉስቁልና የዳረጋቸው ቢሆንም በቀጣይ ጊዜያት ወደ ዘመናዊው ሙዚየም እንዲገቡ ተደርጎ ምቹ አየር እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
የአብነት ትምህርት
በአስተዳደሩ በኩል የገዳሙን ማህበረሰብ በአራት ተከፍሎ ተመድቧል፡፡ ክፍፍሉም የሹም ሽር ቤት፣ የቄስ ቤት፣ የመሪ ቤት እና የጨዋ ቤት በመባል ተሰይሟል። የሹም ሽር ቤት የሚባለው ለደብርነት ማዕረግ ወይም በቅኔ ማህሌት እያገለገሉ ስለ ሀገር ጉዳይ ለሚቆረቆሩ የሚሰጥ ሹመት ነው፡፡ የሹም ሽር ቤት ውስጥ በወቅቱ የተሾሙትንና የተሻሩትንም ያጠቃልላል፡፡ የቄስ ቤት የሚባሉት ትምርታቸውን እየተከታተሉ ከቤተ መቅደስ በድቁና፣ በቅኔ ማህሌት፣ ሰአታት በመቆም፣ ከበሮ በመምታት መቋሚያና ጸናጽል በማቀበል ሲያገለግሉ አድገው አካለ መጠን ሲደርሱ መንኩሰው ከቤተ መቅደስ በቅዳሴ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ የመሪ ቤት የሚባሉት ደግሞ ከዚህ በላይ በተመለከተው መሰረት አድገው ንጉስ ነን አንፈልግም ብለው ሚስት አግብተው ቤት ሰርተው በቅኔ ማህሌት እያገለገሉ ለአገር ጉዳይ ሲወጡ ሲወርዱ የሚኖሩ መምህራን ናቸው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የጨዋ ቤት የሚባለው ነው። ዲማ ውስጥ የተወለደ ልጅ ሁሉ በአራት ዓመቱ እንደ ደንብ ሆኖ ከቤተክርስቲያን ተማሪ ቤት ሳይገባ አይቀርም፡፡
የጨዋ ቤት የሚባለው ግን ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርት እድሉ ሳይሆን ይቀርና አቋርጦ በእርሻና በንግድ የሚተዳደረውን ሰው ለመግለጽ ነው፡፡ ይህ ማህበረሰብ የጨዋ ልጅ ተብሎ እርስቱን ይዞ ቤተክርስቲያን እየደገፈ ይኖራል፡፡ ማናቸውንም የአገር ሆነ የመንደር ጉዳይ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች መክረውበት ነበር የሚፈጸመው። ህዝቡ የሚተዳደረው በመረጣቸው ልጆች ስለሆነ በየ3 ዓመቱ ምርጫ እያደረገ የሚገባው በየደረጃው እየሻሩና እየሾሙ ይኖሩ ነበር፡፡
በዚህም የዲማ አስተዳደር አሳታፊ ነበር ማለት ይቻላል። ዲማ ለመንፈሳዊ ትምህርት ሃይማኖትን፣ ህግንና መንፈሳዊ ሥርዓቶችን ያስተምራል። በስጋዊ በኩልም መልካም አስተዳደርን፣ ሀገር ጥበቃንና እንዲሁም የወገን ፍቅርን ለህዝብ ሲያስተምር የኖረ ደብር ነው፡፡ በአብነት ትምህርት አሰጣጡ ዘመናዊ ትምህርት ባልተስፋፋበት ወቅት ጭምር እንደ አንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከሀገሪቱ አንደኛ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ለሚመጡ ተማሪዎች እውቀትን ሲለግስ ኖሯል። አንጋፋው ደራሲ ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ እና ሌሎችም ምሁራን በዚሁ የአብነት ትምህርት ቤት ተምረዋል። በዲማ የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ ስድስት የትምህርት ክፍሎች ይገኛሉ። እነርሱም የንባብ ቤት፣ የዜማ ቤት፣ የቅኔ ቤት፣ የቅዳሴ ቤት፣ የአቋቋም ቤትና እና የትርጓሜ ቤት በመባል ይታወቃሉ። በየትምህርት ክፍሎቹ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ ሊቃውንት ሲገኙ ብቸኛዋ ሴት የቅኔ መምህርም ትገኛለች። የአብነት ተማሪዎች የእራሳቸው የመቃብር ቤት ውስጥ ሶስት እና አራት ሆነው ይኖራሉ።
በርካቶችም አነስተኛ ማረፊያ የምትሆን ጎጆ ቤት አሰናድተው ይኖራሉ። አሁን አሁን ከቤተሰብ ገንዘብ መደጎም ጀመሩ እንጂ የቆሎ ተማሪዎች ቀለባቸውን ለምነው ነበር የሚያገኙት። በቦታው የቅኔ ትምህርቱን የሚከታተለው ዳንኤል ይታይ ከባህርዳር ዙሪያ ለቅኔ ትምህርቱ ነው ዲማ የተገኘው። ዳንኤል እንደሚናገረው፤ በትረ ውዳሴ ማርያም፣ቅዳሴ እና መዝሙረ ዳዊትን እንዲሁም በግዕዝ ቋንቋ በሚገባ አጥንቷል። አሁን በቅኔ ቤት አንድ ዓመት ያስቆጠረ በመሆኑ እራሱን በዕውቀት ሲገመግም አጋማሽ ላይ ይገኛል። የቅኔ ቤት የጨረሰ ተማሪ ወደ አቋቋም ቤት ነው የሚሸጋገረው። በአቋቋም ቤት ደግሞ ሙሉውን ያወቀ ተማሪ ቀጣዩ ክፍል የዜማ ቤት ነው የሚሆንለት። ጠንካራ ተማሪም ከሆነ የቅኔ ቤትን ለመጨረስ እስከ ሁለት አመት ሊፈጅበት ይችላል። ነገር ግን እንደ ዘመናዊ ትምህርት ግማሹን ወይም አብዛኛውን ስላወቀ ብቻ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው አይሸጋገርም። ይልቁንም ሙሉ በሙሉ ከመምህሩ የሚሰጠውን ዕውቀት ተቀብሎ ብቁ እስካልሆነ ድረስ በእድሜ ቆይታ ብቻ አያልፍም።
ያለዕውቀት ያለፈ ተማሪ በኋላ ላይ ማነው ያስተማረህ ተብሎ ስለሚጠየቅ እና የመምህሩ ጥንካሬ ስለሚፈተሽ ሁሉም ተማሪ በቃሉ ሸምድዶ ዕውቀቱን ሲይዝ ወደ ሌላ ትምህርት ክፍል ይሸጋገራል። ግስ እና ታሪክ የመሳሰሉ መጻህፍትን ከባህር ዳር እና ከተለያዩ ከተሞች ገዝተው የሚማሩት የቆሎ ተማሪዎች በዲማ ቆይታቸው አምስትም ሆነ ስምንት ዓመት ቢቆዩ ምንም አይነት የትምህርት ክፍያ አይጠየቁም። ነገር ግን የቆይታ ጊዜ የምግብ እና የተለያዩ ወጪዎቻቸውን እራሳቸው እንዲሸፍኑ ይደረጋል። ተማሪ ዳንኤል እንደሚለው ቆሎ ተማሪ ለምኖ ካልበላ ትምህርቱ አይገባውም ተብሎ ስለሚታሰብ አንዳንድ ጊዜ በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች ምግብ ይወስዳል። ይሁንና አብዛኛው ተማሪ ከቤተዘመድ የሚቸረውን ጥቂት ገንዘብ አብቃቅቶ በመኖር እየተማረ ይገኛል።
በመሆኑም ቦታው የዕውቀት ማዕድ በበቁ መምህራን የሚሰጥበት በመሆኑ ዝናው ከጎጃም አልፎ በሌሎች አካባቢዎችም የናኘ ነው። ዲማ ታሪካዊነቱ በዕውቀት አበርክቶቱ ብቻ አይደለም። በጣሊያን ወረራ ወቅት የአርበኞች ማዕከል ሆኖ አገልግሏል። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር የተቆቋመበት ታሪካዊ ቦታ መሆኑንም አባ ወልደስላሴ የተባሉ የአካባቢው ታሪክ አዋቂ ይናገራሉ። በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ዘመንም በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱሉሽ የሚል ማህተም ተቀርፆ የጀግኖች ማህበር ተቋቁሞ አርበኞችን በተለያየ መልኩ ይረዱ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።
የዲማ ልዩ ክስተት
በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ብዙዎች ሊመለከቷቸው የሚጓጉላቸው መነኩሴዎች አሉ። እማሆይ ብርሐን የተባሉት መነኩሴ በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለረጅም ዘመናት ማለትም ለ30 ዓመታት ኖረዋል። በነዚህ ሁሉ ዘመናት ግን ባዶ ሜዳ ላይ ተቀምጠው ነው ጸሎት ሲያደርሱ የሚውሉት። ነገር ግን ዝናብ ሲዘንብ እንኳን እርሳቸው የነበሩበት ቦታ ላይ ደረቅ ሆኖ ይታያል። ከብዙዎች አንደበት እንደተመሰከረላቸው መነኩሴዋ በአካባቢው ሲኖሩ የሚመገቡት ‹‹ቱልት›› የተባለው ቅጠል ነው። በጸሎት እና በምህላ አብዛኛውን ጊዜም ያሳልፋሉ። እርሳቸው ካልፈለጉ ማንም ሰው ቢመጣ ሊያናግሩ አይችሉም። አሁን ላይ ግን አነስተኛ የጭቃ ቤት በቤተክርስቲያኑ ደጀ ሰላም በስተቀኝ ተሰርቶላቸው እዛው አረፍ ይላሉ። መሬት ላይ በተቀመጡበት ፊታቸውን ወደ መሬት አድርገው በማጎንበስ ነው የሚተኙት። ለረጅም ሰዓት በዝምታ እና በጸሎት የሚያሳልፉት እናት የአካባቢው ክስተት ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አስደናቂው የአኗኗር ዘይቤያቸው ለሩቅ አገር ሰዎችም ጭምር እንግዳ በመሆኑ አነስተኛ ማረፊያቸው ላይ መጥቶ የሚጎበኛቸው ሰው በርካታ ነው።
ተነግሮ ከማያልቀው የዲማ ጊዮርጊስ ገዳም ጥቂትም ቢሆን ጨለፍ አድርገን ወደ ናንተ ለማድረስ ሞከርን። ገዳሙ በአጠቃላይ በእጅ ያለ ወርቅ ሆነብን እንጂ በየዓመቱ በሚሊዮኖች ቱሪስቶች ሊጎበኙት የሚችሉት ድንቅ። ከአዲስ አበባ እንብዛም የማይርቀውን ይህን ታሪካዊ ቦታ መጎብኘት የሚሰጠው የመንፈስ እርካታን በሌላ በምንም መተካት አይቻልም። በተለይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በዚህ ስፍራ ቢገኙ ብዙ እንደሚያተርፉ መገመቱ ብዙም ከባድ አይሆንም። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011
በጌትነት ተስፋማርያም