በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሁለት በአቅም የማይመጣጠኑ ልጆች ነበሩ። አንደኛው ወፍራም ሲሆን፤ ሌላኛው ኮስማና የሰውነት አቋም ያለው ነው። የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ደግሞ እነርሱን እያጋጩ ዘና ማለትን የሚፈልጉ ናቸው። እናም ዘወትር ያደባድቧቸዋል። በዚህም ኮስማናው ልጅ ሁልጊዜ ተደብድቦ ወደ ቤቱ ይገባል።
በዚህም የተናደዱ እናቱም «እያለቃቀስክ አትምጣ፣ የአንተ እጅ ምን ይዟል!» ብለው ይገርፉታል። አንድ ቀን ይህንን ሁሉ የሚቀይር ነገር ተፈጠረ። የሳይንስ አስተማሪያቸው ስለ ኃይል ሰጭ ምግቦች ሲያስተምሩ ድንችን እንደ አንድ ኃይል ሰጭ ምግብነት አነሱ። ለዚህ ኮስማና ልጅ ከሰማይ መና ወረደለት ። ዓይኖቹም በሩ። ምክንያቱም እናቱ ድንች ነጋዴ በመሆናቸው ይህን የመደብደብ አባዜ ድራሹን ለማጥፋት ያስችለዋል።
ስለዚህም በድንች ኃይሉን ገንብቶ የሳቀበትንም፤ የደበደበውንም ለመቀጥቀጥ ቤቱ እንደገባ ድስት ሙሉ የድንች ቅቅል በሚጥሚጣ አስቀርቦ ራቱን በላ። ጠዋትም ቁርሱ እርሱኑ ደገመ። ይባስ ብሎ በቦርሳው ድንቹን ይዞ ትምህርት ቤት ሄደ። በዕረፍት ሰዓት እጅጌውን እየሰበሰበ «ዛሬ እስከዛሬ ከሚደበድበኝ ጋር መጋጠም እፈልጋለሁ» አለ።
ተማሪዎቹም የልጁን ኮስማና ሰውነት እያዩ ደነገጡ። «ምን ተፈጠረ?» ሲሉ ጠየቁትም። እርሱም «ትናንት የተማርነውን ታስታውሳላችሁ ድንች ኃይል ይሰጣል» እያለ በቦርሳው ያመጣውን ቅቅል ድንች ፈረካክሶ እያከፋፈለ መጎረሩን ቀጠለ። ቤት ውስጥ ያደረገውንም ሁሉ ነገራቸው።
ይህን ጊዜ በበሉት ድንች መለወጣቸውን ለማየት አንዳንዱ መላ ሰውነቱን ሲቃኝ፤ አንዳንዱ ደግሞ ኃይለኛነቱን አምኖ እርሱን መፍራት ጀመረ። ሲደበድበው የነበረው ልጅም ወዲያው መጣ። ግን ስለሚደበድበው ልጅ ቀድሞ ሰምቶ ነበርና ጉልበቱ ተብረከረከ። ማጣላትና መዝናናት የሚወዱት ተማሪዎችም መምጣቱን ሲያዩ «ግጠመው፣ ግጠመው» አሉ። ልጁ ግን ስለፈራ በእንቢታ ትከሻውን ሰበቀ። «ፈሪ! ፈሪ! ፈሪ!» እያሉ ሲሳለቁበት እንደምንም ደፍሮ ገጠመው።
ይሁንና በፍራቻ ውስጥ ስለነበር ተሸነፈ፤ ቀጫጫው ልጅ ተሸክሞ በማንሳት መሬት ላይ ዘረረው። ከዚያ በኋላ ደብዳቢም፤ አስለቃሽም ቀረለትና እፎይ አለ። ቀጭኑ ልጁ ኃይል ያገኘው ከበላው ድንች ሳይሆን ከተማረው ትምህርት ነው። ወፍራሙና የማይፈራውም የፈራው ከተማረውና ድንች ኃይል እንደሚሰጥ በማመኑ ነው።
ሁለቱም በሰውነት አቋም አልቀየሩም። የቀየራቸው ትምህርቱና ተግባሩ ነው። ዘወትር ለማሸነፍ እንጂ ለማልቀስ ካላቀድን አሸናፊዎች መሆናችን እንደማይቀር ከላይ ያነበብነው ታሪክ አስረግጦ ይነግረናል። ምስጢሩ ያለው ኃይል የሚሰጠው ትምህርት የቱ ነው የሚለውን መለየት ላይ ነው።
ልክ እንደቀጭኑ ልጅ ድንቹ ላይ እምነት መጣል ይገባል። ምክንያቱም በእዬዬ የሚሸነፍም ሆነ የሚያሸንፍ የለም። ለቅሶ ሁልጊዜ ያስደበድባል፤ ታላቅነትን፣ ክብርና ገናናነትን ማግኘት አያስችልም። በመከራ ውስጥ ጽናትና ቆራጥነትን የሚያነግቡ ሰዎች ሥነ ልቦናቸው በአሸናፊነት እንጂ በአልቃሻነት ላይ አይመሰረትም፡፡
ወፍራሙ ሰው ያንደባልለናል አይሉም፤ ድንች ኃይል ይሰጣል ብለው ያምናሉ እንጂ። እንደ ቀጭኑ ልጅ በመጠን ቢያንሱም በትምህርቱ ግን እንደ ወፍራም ይገዝፋሉ። ይህ ሥነ ልቡና በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ሊመጣ ያስፈልጋል። የአሸንፋለሁ ስሜት። የአሸናፊነትን ባህል ከእነ አጼ ምኒልክ ተምረን ነበር ።
ግን እዬዬን ስለመረጥን ብቻ ይህንን መፍትሄ አድርገን መውሰድ አንፈልግም። ሁሌ በየትምህርቱ «ተመትተህ መጥተህ አታለቃቅስ› ይባላል። መፍትሄው አንድነት መሆኑም ይመከራል። ለአፍሪካ ኩራት የሆንን እኛ ነን ስለዚህም ሁሌ አሸናፊዎች እንደሆንን ይገለጽልናል። ይሁንና በታሪክ ኩራት ብቻ ራሳችንን ኮፍሰን እንቀመጣለን። ታሪክ ተናጋሪ ብቻ እንሆናለን። መሆን ያለበት ግን ከታሪኩ ተምረን አሸናፊነትን በተግባር ማሳየት ነው። ዛሬ አገር የምትፈልገው በርትቶ የሚጋፈጥ፤ ቁስላቸውን አሥረው የሚዋጉ እንጂ ቁስላቸውን እያዩና እያሳዩ የሚያለቅሱትን አይደለም። ለዚህም ማሳያው ዓድዋ ነው።
የለቅሶ ሥነ ልቡና ችግርን ግዙፍ አድርጎ ወደማየት ይመራል። ችግር ከላይ መፍትሄው ከታች ከሆነ ውጤቱ ተሸናፊነት ነው። ስለዚህም አዘውትሮ የደረሰን ጭቆና፣ ያጋጠመን መገፋት፣ የሆነን ግፍ ከማሰብ ተላቆ ስለ መፍትሄው ማሰብና መፍትሄውን በአንድነት ለመተግበር መሞከር ይገባል።
ከተማረው ትምህርት በኋላ ቀጭኑ ልጅ ወፍራሙ ልጅ ስላለው አቅም፣ ኃይል፣ ችሎታ አልተጨነቀም። ይልቁንም ትኩረቱን ያደረገው በኃይል ሰጪነቱ ላይ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ጀግንነትን፣ ጽናትንና ቆራጥነትን አላብሶ ማንም እንዳያስለቅሰውና እንዳይደበድበው አስችሎታል። እናም ትናንትም ሆነ ዛሬ ችግሮች ነበሩ፤ ይኖራሉ።
ወሳኙ ነገር መሆን ያለበት ምን ገጠመን ሳይሆን እንዴት እንወጣው ነውና በዚህ ላይ ሊሰራ ይገባል። መቱኝ፣ ተመታሁ፣ መታቱኝ፣ አስመቱኝ፣ እያሉ ማለቃቀስ ወኔን ይሰልባልና መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ጀግንነትን ካለፉት አባቶች ተምሮ ከመወቃቀስ ወጥቶ በአንድነት ለኃይል ምንጭ የሆነውን ትልቅ እምነት መላበስ ያስፈልጋል። ቁስልን ማከም እንጂ ማከክ እንደማያድነው አምኖ ለመፍትሄው መትጋት ላይ እናተኩር።
የጀግና ሕዝብ ሥነ ልቡና ከዚህ በፊት መቶኛልና አልችለውም የሚል ሳይሆን የአሸናፊነት ስነልቦናን መላበስ ኃይል ይሰጣል የሚለው ነውና በትምህርቱ ለተግባሩ ይሰራ እንላለን! ድሮ ከልጆች ጋር ስንጫወት ተመትተን ከመጣን ወላጆቻችን ይቆጣሉ፡፡ ‹ለምን ታለቃቅሳለህ› የሚለው የመጀመሪያ ቁጣቸው ነው፡፡ ወይ እዚያው ታግለህ አሸንፈህ መምጣት ነው፤ አለያም ደግሞ መሸነፍህን አምነህ በቀጣይ እንዴት እንደምታሸንፍ ማሰብ ነው፡፡ ማለቃቀስ መፍትሔ አይሆንም ይባላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2011