ኢትዮጵያ የመጣችባቸው መንገዶች ወጣ ገባ ናቸው፡፡ ለዓለም ማህበረሰብ ጭምር ሚስጥር ሆነው እስከዛሬ የዘለቁት ታላላቅ የኪነጥበብና የኪነህንጻ ቅርሶች፣ ዓለም ስለዴሞክራሲ ግንዛቤ ባልያዘበት ዘመን ዴሞክራሲያዊ በሆነው የገዳ ሥርዓት የሚተዳደሩ ህዝቦች የሚገኙባ አገር፣ ለጥቁር ህዝቦች ጭምር የኩራት ምንጭ የሆነ የአድዋ ድልን ለመላው ጥቁር ህዝብ ያበረከተች አገር፣ ወዘተ ታሪኮች የአገራችን የከፍታ ዘመናት ነበሩ፡፡
በአንጻሩ በመካከል በተፈጠረ ክፍተት ህዝቦችዋ ለድህነትና ለረሃብ የተጋለጡበትና የኢትዮጵያ መገለጫ እስከመሆን የደረሰበት አስከፊ ጊዜንም አሳልፋለች፡፡ ሁሉም ግን የኛው ታሪኮች ናቸው፡፡ ትናንት ያሳለፍናቸውም ሆነ ዛሬ እየኖርናቸው ያሉ የህይወት ዘይቤዎች ለነገ ታሪክ በመዝገብ ሰፍረው ይኖራሉ፡፡
ከትናንት በስቲያ በአገራችን ተከብሮ የዋለው 123ኛው የአድዋ ድልም የኋለኛው ታሪካችን አንዱ አካል ነው፡፡ ይህ ታሪክ አውሮፓውያን በከፍተኛ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ደርሰው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በታጠቁበትና በዚያም ተነሳስተው አፍሪካውያንን ለመቀራመት በተንቀሳቀሱበት አስከፊ ዘመን የተገኘ ድል በመሆኑ ከፍ ብሎ የሚዘከር ታሪክ ነው፡፡ በዘመኑ ኢትዮጵያ የዚሁ ትንኮሳ እጣ ቢደርሳትም አባቶቻችን ግን ይህንን መቀበል አልሆነላቸውም፡፡ ግን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አልነበራቸውም፡፡
የነበራቸው ከሁሉም የላቀ አንድ መሳሪያ የአገራዊ አንድነትና የአልሸነፍ ባይነት ጠንካራ ወኔ ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱም ይህንን ወኔ ታጥቀው እና ከምንም በላይ አገራቸውን አስቀድመው የሽንፈት ታሪክ ለትውልድ ትተው ላለማለፍ ሲሉ በጀግንነት ከጠላት ፊት ቆሙ፡፡ ምንም እንኳን የጠላት ጦር የያዘው መሳሪያ ዘመናዊ ቢሆንም ከኢትዮጵያውያኑ ወኔ የላቀ አልነበረምና ከሽንፈት አላዳነውም፡፡ እናም ኢትዮጵያውያኑ አገራቸውን አስከበሩ፤ ለሌሎች ጥቁር ህዝቦችም የሞራል ስንቅ ሆኑ፣ የቅኝ ግዛት ግፍ እንዲበቃም የራሳቸውን የታሪክ አሻራ አኑረው አለፉ፡፡
ይህ የቀደመ ታሪካችን ታዲያ የኛው የኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን አባቶቻችንን ስናስብ መቼም የማይረሳና ትልቅ ጀብድ መፈፀማቸውን እንገዘነባለን፡፡ እናም የነሱን አደራ ተቀብለንና የራሳችንን እሴት ጨምረን ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ የሞራል ስንቅ ይሆኑናል፡፡
ዛሬ ላይ የአገር መከላከያ ሰራዊታችን እያደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የመከላከያ ሰራዊታችን አገራዊ አንድነቱን ለማስጠበቅ ከሚደርገው ጥረት ጎን ለጎን በተለያዩ ምክንያች እዚህም እዚያም እየተከሰቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮችንም ሃላፊነት ወስዶ በማረጋጋትና ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በማሳየት እንዲሁም በልማቱም ላይ ከአርሶ አደሩና ከሌሎች የአገሪቱ አምራች ህዝቦች ጎን በመቆም እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ የቀደመውን የጀግኖች አባቶቻችን ገድል የሚያንፀባርቅ ትልቅ ተግባር ነው፡፡ ዛሬ ላይ መከላከያ ሰራዊታችን ከአገርም አልፎ በአፍሪካ በሰላም ማስከበር ተግባራት በመሰማራት እስከህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቹ ጭምር እየከፈለ ያለ የኩራት ምንጭ ነው፡፡
በዚህ ዘመን እንደከዚህ ቀደሙ ቅኝ የመገዛት እጣ ይገጥመኛል ወይም ወረራ ያጋጥመኛል የሚል የጎላ ስጋት የለም፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል ዓለም ከዚህ አስተሳሰብ ወጥቶ የአገራት ሉአላዊነት ላይ የጋራ መግባባት የፈጠረበት ዘመን ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአገር ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ በቂ ቁመናና ብቃትን የተላበሰ የአገር መከላከያ ሰራዊት አለን፡፡
በመሆኑም አሁን ያለው ትልቁ ፈተና የኢኮኖሚ ትግል ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት መሪና ተመሪ በሁሉም ጉዳዮች ባይግባቡ እንኳን የሀገርን ነፃነት፣ አንድነት፣ እኩልነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲን በተመለከተ ጉዳዮች ተግባብተውና አንድ ሆነው ከራሳቸው አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ድል ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በደምና አጥንት የተጠበቀን አንድነት ከስነ ልቦናና ከክብር ትሩፋትነት አልፎ ለኢኮኖሚ ፀጋነት እንዲተርፍ በደም ሳይሆን በላብ፣ በአጥንት ሳይሆን በጉልበት የምንከፍለው የመጪው ትውልድ እዳ እንዳለብን አውቀን ልንሰራ ይገባል፡፡
አሁን ከፊታችን የተደቀነው ትልቁ ጠላታችን ድህነት ነው፡፡ ይህ ጠላት ደግሞ ልክ በአድዋ ጦርነት ወቅት ጀግኖች አባቶቻችን እንደከፈሉት መስዋዕትነት የህይወት ዋጋ ባያስከፍልም ትልቅ ልፋትና ጥረትን ይጠይቃል፡፡ አባቶቻችን በደምና በአጥንት ያቆዩትን አገራዊ ሉዓላዊነት እኛ ደግሞ በጉልበታችንና በጥረታችን ታግዘን ለቀጣዩ ትውልድ የበለፀገች አገር ለማውረስ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ አለብን፡፡
ለዚህ ደግሞ በለውጥ ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ ቀደም ሲል ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ችግሮችን ከሞላ ጎደል እየመለሰ ያለ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በተለይ በአገራችን እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚስችል ሥርዓት ለመፍጠር መሪዎቻችን እየተጉ ይገኛሉ፡፡ አሳታፊ የፖለቲካ አውድን ከመፍጠር፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶችን ከማስከበር፣ አገራዊ አንድነትን ከማጠናከርና መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለአገራዊ አንድነትና እድገት በማሰለፍ ለጋራ ዓላማ ከመነሳት አንጻር እየተፈጠረ ያለው ለውጥ ከፍተኛ እመርታ የታየበት ነው፡፡
በመሆኑም ለዚህ እውን መሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት እንደ ትናንቶቹ ኢትዮጵያውያን በህይወት መስዋዕትነት ብቻ ሳይሆን እየኖርን በመስራት፣ በደም የተቀበልናትን ሀገር ነፃነቷን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ጠንክረን መታገል ይገባናል። በልዩነት ተቆራቁሰን እርስ በእርስ የምንጫረስና የምንጠፋፋ ሳይሆን የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ እንድንችል በህብረትና በአንድነት፣ በፍቅርና በይቅርታ ወደፊት መራመድ ይገባናል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011