አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ኢትዮጵያን እንደሚያፈራርስ በገሀድ አውጆ ጦርነት ከከፈተ ጊዜ ጀምሮ ምዕራባውያኑ ሃይ ከማለት ይልቅ አይዞህ እያሉት እዚህ አድርሰውቷል። ሀገር የማፈራረስ ተልዕኮ ይዞ የተነሳን የጥፋት ቡድን የልብ ልብ መስጠታቸው ሳያንስ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉለት በትረ ስልጣን ሊያስጨብጡት ሲሟሟቱለት ይታያል። የምዕራባውያኑ ጣልቃ ገብነትና ለአሸባሪ ቡድኑ የሚያደርጉት ፍጥጥ ያለ አድልዎ ቁጭት ያልፈጠረበት ኢትዮጵያዊ ወጣት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።
የውጭ ኃይሎች ለምን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ማሳደር ፈለጉ? የሚለውን ለመርዳት እያንዳንዱ ወጣት የፖለቲካ ተንታኝ ባይሆንም የሚያውቀው ነው። ግብራቸው ፍላጎታቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነውና።
በዓለም ላይ ሌላ ምንም ጉዳይ ያለ እስከማይመስል ድረስ ሙሉ ጊዜያቸውን ኢትዮጵያ ላይ አድርገው አንዴ የኢኮኖሚ ሌላ ጊዜ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ጫና የሚያደርጉት የሚጋልቧቸውን ፈረሶች ወደ ስልጣን በማምጣት ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ መሆኑ ያልገባው ወጣት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። የምዕራባውያኑ ሚዲያዎች በበሬ ወለደ ዘገባቸው የአሸባሪውን ቡድን ድል አድራጊነት፤ የመንግሥትን ተሸናፊነት እየዘገቡ በሥነ ልቦና ሊያዳክሙን ሲሞክሩ ታዝበናል።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ያላሉት የለም። ‹‹አዲስ አበባ በሕወሓት ታጣቂዎች ተከባለች፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕወሓት ታጣቂዎች የጥቃት ክልል ውስጥ ነው፤ አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ስለሆነች አንዳንድ ሀገራት ዜጎቻቸውን እያስወጡ ነው›› የሚሉና የተለያዩ ማስበርገጊያዎችን እየተናገሩ አዲስ አበባን የጦርነት ቀጣና አድርገው በመሳል ዘገባዎችን ሲያሰራጩ ሰንብተዋል።
መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ የጸጥታ ስጋት እንዳይኖር ሲሠራና የወጠኑት ትርምስ የሚጨናገፍ መስሎ ሲሰማቸው ደግሞ ‹‹ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት እየደረሰባቸው ነው›› በሚል የሚዲያ ጦርነት ሲያካሂዱ እንደነበር የሚታወስ ነው።
መንግሥት የአዲስ አበባን ሰላምና ጸጥታ ለማስተማመን ከመደበኛ የጸጥታ ሃይሉ ባሻገር ከሰላሳ ሁለት ሺ በላይ ነዋሪዎችን በተለይም ወጣቶችን በማሰልጠን አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ አድርጓል። የሽብር ተልዕኮ አንግበው ያደፈጡ የአሸባሪው ቡድን አባላት ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያቀዱትን ጥፋት መፈጸም እንዳይችሉ ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ተደራጅተው የሰላም ስጋት ናቸው የሚሏቸውን እንቅስቃሴዎች በአይነ ቁራኛ እየተከታተሉ በመዲናዋ ሊፈጸም የታቀደውን ትርምስ አምክነዋል። ከዚያም ባሻገር በግንባር ተሰልፈው ከአሸባሪው ቡድን ጋር እየተፋለሙ ናቸው። አሁንም የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያነት ተከትለው ወደ ግንባር ለመሄድ የተዘጋጁም በርካቶች ናቸው።
በዛሬው የወጣቶች አምዳችንም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ሀገርን ከተቃጣባት አደጋ ለመታደግ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ የሚያስቃኝ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ወደ ግንባር መዝመት ተከትሎ ወጣቱ ምን ተሰማው የሚሉና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችንም የሚዳስስ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ፕሬዘዳንትና አንዳንድ ወጣቶች የሰጡትን አስተያየት በማከል እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት ገዛኸኝ ገብረማርያም አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያ ላይ ጦር ከሰበቀ ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ሀገራቸውን ላለማስደፈር ከደጀን እስከ ግንባር ተሰልፈው ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ስለመሆናቸው ይናገራል። ሰላም የአንድ ወቅት ጉዳይ ሳይሆን የዘወትር እስትንፋሳችን ነው ያለው ፕሬዚዳንቱ፤ ከሃዲዎችና ግብረ አበሮቻቸው ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ካነሱ ጊዜ ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ድርጊታቸውን በማውገዝ፣ ደጀን በመሆንና ግንባር ሄደው በመሰለፍ ጭምር ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውን ይገልጻል።
ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት በመንደርና በቀጣና እየተደራጁ የአካባቢያቸውን ሰላም ሲጠብቁ እንደነበር የጠቀሰው ፕሬዘዳንቱ፤ አሁን ግን የአሸባሪው ሃይሎችና ግብረ አበሮቻቸው አዲስ አበባ ላይ ትኩረት ያደረገ ትርምስ ለመፍጠር ያቀዱ መሆናቸውን ተከትሎ ከሰላሳ ሁለት ሺ በላይ ወጣቶች ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሰላምና ጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሙያዊ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ መደረጉን ገልጿል።
ስልጠናውን የወሰዱት ወጣቶች ቁጥር ሰላሳ ሁለት ሺ የሚገመት ቢሆኑም በተለያየ ምክንያት ያልሰለጠኑ ወጣቶችም ቢሆኑ የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በንቃት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግሯል። ብዙኋኑ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችም ደም በመለገስ፣ ሀብት በማሰባሰብና የተፈናቀሉ ወጎኖችን በመርዳት ደጀንነታቸውን እያሳዩ መሆናቸውን ተናግሯል።
ኢትዮጵያን ለማዳን አካባቢያቸውን ከመጠበቅ ባለፈ መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የህይወት መስዋዕትነት ለመከፍል ወደ ግንባር የዘመቱ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በርካቶች መሆናቸውን ወጣት ገዛኸኝ ገልጿል። አሁንም በራሳቸው ተነሳሽነት መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል ሀገራቸውን ከጠላት ለመመከት የተዘጋጁ እንዳሉ ጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ወጣቶች ከበፊቱ የበለጠ መነቃቃትና ቁርጠኝነት የሚፈጥርባቸው መሆኑንም ፕሬዘዳንቱ ተናግሯል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግንባር መገኘት በተለይም ለወጣቱ የሚስተላልፈው መልዕክት አለ ያለው ወጣት ገዛኸኝ፤ ባለአደራው ትውልድ ከአባቶቹ የተረከባትን ሀገር አስከብሮ ለመጪው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያሳስብ መልዕክትም ጭምር መሆኑን ጠቅሷል።
ማንኛውም ወጣት ከመንደር እስከ ግንባር ድረስ ባለው አደረጃጀት ንቁ ተሳታፊ በመሆን አገሩን ለማዳን የሚያደርገውን ርብርብ የሚያጠናክርም ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጊዜ በግንባር እየተገኙ ጦሩን ሲያበረታቱ እንደነበር የጠቀሰው ገዛኸኝ፤ አሁን ሙሉ ጊዜያቸውን ወደ ጦርነቱ ማድረጋቸው ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያ ላይ አደጋ የፈጠሩ አሸባሪዎችን በቁርጠኝነት እንዲታገል መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብሏል።
ወጣቱ ከፌስቡክና ከአልባሌ ንግግሮች እራሱን ቆጥቦ ከመሪው ጎን በግንባር በመሰለፍ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ይኖርበታል። የተከፈተብንን ጦርነት አሸንፈን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ እንድታደርግ የወጣቱ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። አሁን ያለው ትውልድ ይህንን የገጠመውን ችግር በድል ተወጥቶ እንደ አድዋ ጀግኖች እየተዘከረ የሚኖር መሆን አለበት። ይህን ጸረ ሰላም፣ ጸረ ልማትና ፀረ-እድገት የሆነ አሸባሪ ቡድን በማጥፋት ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ሰላሟ የመመለስ ኃላፊነት አለበት። የአዲስ አበባ ወጣቶች ከአሁን ቀደም እያደረጉት እንዳለው ሁሉ ለጠላት ቀዳዳ ባለመክፈት የገጠመንን ችግር ወደ መልካም ታሪክ የመቀየር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያ እንዲከተሉ ጥሪ አስተላልፏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በሚሰሩት ሥራ ወጣቱ እጅግ ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው ገዛኸኝ፤ ሁልጊዜም አርአያነታቸውን የመከተልና የማበልጸግ ፍላጎቱ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሷል። ወጣቱ የመንግሥትን አቅጣጫዎች ያለምንም ተቃርኖ በራሱ ፍላጎት ሲተገብር እንደነበርም አስታውሷል። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር መገኘታቸውም በወጣቱ ላይ የፈጠረው ስሜት ቀላል አለመሆኑን ተናግሯል።
በተለይም ህግ የማስከበር ርምጃው ከተጀመረ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ከመከላከያው ጎን በመቆም በተለያየ መንገድ አጋርነታቸውን ሲያሳዩ እንደነበር ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በጦር ግንባር ተገኝተው ውጊያውን መምራታቸው ደግሞ በወጣቱ ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊ ተጽእኖ ከፍ ያለ እንደሆነ ጠቅሷል።
መንግሥት አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ በከፍተኛ ግለት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ በከተማ የሚገኙትን የአሸባሪ ቡድኑን አባላት በንቃት በመከታተልም ይሁን በግንባር ያሉትን በመፋለም ወጣቱ የመጣበትን ሞራል የበለጠ በማሳደግ ለሀገራዊ ጥሪው አስፈላጊውን ምላሽ እንዲሰጥ ወጣት ገዛኸኝ ጥሪ አቅርቧል።
ሀሰተኛ መረጃዎችን ላይክና ሼር ማድረግ የአሸባሪውን ቡድን ሀሳብ ማፋፋትና ማሳደግ ነው ያለው ፕሬዚዳንቱ፤ ወጣቱ ሥነ ልቦናን ለመስረቅ ታስበው የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን ከመስማት እንዲቆጠብ ሁልጊዜም ሀገሩን ከጠላት ለመከላከል በልበ ሙሉነት እንዲዘጋጅ መልዕክት አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ተመልምለው ስልጠና የወሰዱ ወጣቶችንም አነጋግሯል። ወጣት ይቆዩ ጆሃር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ነዋሪ ሲሆን በራሱ ተነሳሽነት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ስልጠና እንደወሰደ ይናገራል። ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ እንዳለች የገለጸው ወጣት ይቆዩ ጆሃር ሀገሩን ከተደቀነባት አደጋ ለማውጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ስልጠና መውሰዱን ይናገራል። ሰልጥኖ ወደ ሥራ ከተሰማራ በኋላም በአካባቢው የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራትን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠቱን ተናግሮ የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ አንጻር የበኩልን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጿል።
አንዳንድ ጊዜ ህግ ወጥ ድርጊትን ሲመለከትና ጸጉረ ልውጥ ሰዎችን አይቶ መታወቂያ ሲጠይቅ፣ ምን አገባህ የሚል ምላሽ እንደሚሰጠው የተናገረው ይቆዩ ጆሃር ቀበሌው ካሰለጠነ በኋላ የፖሊስ አጋር እንደሆኑ የሚገልጽ መታወቂያ አለመስጠቱ አንዲህ አይነት ክፍተትን ፈጥሯል ይላል። የተሰጠውን የደንብ ልብስ መልበስም ወንጀለኞቹን እንዲሸሸጉ ከማደረግ ውጪ ጥፋተኞችን አድብቶ ለመከታተል የሚረዳ አለመሆኑን ተናግሯል።
‹‹ያለችኝ አንድ ሀገር ነች›› የሚለው ይቆዩ ጆሃር ለግሉ የሚያደርገውን ጥንቃቄና እንክብካቤ ለሚኖርበት ከተማም የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ይገልጻል። ከዚህም ባለፈ የሀገሪቱ የሰላም ጉዳይ በፍጥነት የማይስተካከል ከሆነና የአሸባሪው ቡድን ጥፋት የማያቆም ከሆነ መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን ተናግሯል። የሌሎች ጓደኞቹም ሀሳብ ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጿል። በተለይም ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ውጊያውን ለመምራት ወደ ግንባር መሄዳቸውን ተከትሎ ወጣቱ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሮበታል ብሏል።
መንግሥት እየተዋጋ ያለው የምዕራባውያንን አጀንዳ ለማስፈጸም ከተገዙ ባንዳዎች ጋር እንደመሆኑ የውስጡንም የውጭውንም ጫና ማሸነፍ የሚቻለው አንድነትን በማጠናከር ስለሆነ ወጣቱ አንድ ሆኖ በመቆም ጠላቱን መመከት እንዳለበት ገልጿል። የውጭ ኃይሎች አዲስ አበባ ስጋት ውስጥ እንዳለች የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙትም ህዝብን ተስፋ በማስቆረጥ አሸባሪው ቡድን በወሬ አዲስ አበባን እንዲቆጣጠራት ካላቸው ምኞት ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ከተማዋን በአሸባሪዎች ላለማስደፈር በንቃት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግሯል።
ሌላው አስተያየቱን የሰጠን ወጣት ገብሬ ከበደ ሲሆን እርሱም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የአካባቢ ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅ ስልጠና ከወሰዱ ወጣቶች አንዱ ነው። የውጭ ሚዲያዎች አዲስ አበባ በአሸባሪዎች ተከባለች የሚል ዘገባ ማስተላለፍ ሲጀምሩ ገብሬ አዲስ አበባን ከጥቃት የመታደግ ንቃቱ እንደጨመረና ሀገሩን ከጠላት የመከላከል እልህ እንደያዘው ይናገራል። ስልጠና ከመውሰዱ በፊትም ከአካባቢው ሰዎች ጋር በመሆን የሰፈሩን ሰላምና ጸጥታ የማስጠበቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መሰንበቱን ይገልጻል። አሁን የውጭ ሀይሎች ትኩረታቸውን አዲስ አበባ ላይ አድርገው የሽብር ነጋሪት መጎሰማቸው ወጣቱ የበለጠ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚያነቃቃ እንጂ የሚያስበረግግ አይደለም ይላል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ከሰፈር እስከ ግንባር ባለው ሀገርን ከጠላት የመታደግ እንቅስቃሴ ውስጥ ታሪክ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱን ለመምራት ወደ ግንባር የመሄዳቸው ውሳኔም በወጣቱ ላይ ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረ ገልጿል። የሀገር መሪ ግንባር እየተዋጋ ቁጭ ብሎ የሚመለከት ወጣት አይኖርም ያለው ወጣት ገብሬ፤ ከደጀንነት ወደ ግንባር በመሄድ እንደአባቶቹ ታሪክ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ በውጭም በውስጥም የሚሠሩ ጠላቶች የሚያደርጉትን ርብርብ አንድ ሆኖ መመከት ስለሚያስፈልግ ወጣቱ አንድነቱን በማጠናከር ሀገሩን ለማዳን የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት ብሏል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2014