
በእንግሊዝ አዳዲስ መኖሪያ ቤቶችና ሕንጻዎች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪ ኃይል ለመሙላት (ቻርጅ ለማድረግ) የሚያስችል የቻርጀር ቦታ እንዲዘረጉ በሕግ እንደሚገደዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ።
መንግሥት እንዳለው ውሳኔው በአገሪቷ በየዓመቱ እስከ 145 ሺህ የሚደርሱ የኃይል መሙያ (ቻርጅ ማድረጊያ) ቦታዎችን ለመዘርጋት ያለመ ነው። በአዲሱ ሕግ መሠረትም አዲስ የተገነቡ የገበያ ማዕከላት፣ የሥራ ቦታዎችና እድሳት ላይ ያሉ ሕንጻዎች ሕጉን ተግባራዊ ያደርጋሉ።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ ውሳኔው የተላለፈው ዩናይትድ ኪንግደም በኤሌክትሪክ ኃይል ወደሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ለመሸጋገርና ዓላማ በያዘችበት ወቅት ነው፡፡ ከ2030 ጀምሮም በነዳጅና ናፍጣ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ ታግዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን “ዩኬ መኪናዎቿን፣ ከባድ ተሽከርካሪዎቿን፣ አውቶብሶቿን እና ሌሎች የትራንስፖርት መንገዶችን ‘በሚያስደንቅ ሁኔታ’ ልትቀይር ነው” ብለዋል።
“ይህንን ለውጥ የሚያንቀሳቅሰው ኃይል መንግሥት አይሆንም። ንግድም አይሆንም። ይህንን የሚያንቀሳቅሰው ተገልጋዮቹና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን መዘዝ አይተው ከእኛ የተሻለ የሚፈልጉት የዛሬ ወጣቶች ናቸው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ።
ይሁን እንጂ ሌበር ፓርቲ የተዋወቀው አዲሱ ሕግ በኃይል መሙያ ( ቻርጅ ማድረጊያ) ላይ ያለውን የጂኦግራፊ ክፍፍል ታሳቢ ያደረገ እንዳልሆነ ተናግሯል።
“ለንደንና ደቡብ ምስራቅ ከተቀሩት እንግሊዝና ዌልስ የተሻለ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ የሚያደርጉበት ቦታ አላቸው። ግን እስካሁን ይህንን ችግር ለመፍታት የሚረዳ ምንም መፍትሔ አልተቀመጠም” ብሏል ፓርቲው።
ከዚህም ባሻገር ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወይም እኛ የምንፈልጋቸውን ግዙፍ ፋብሪካዎች ለመገንባት የሚያስፈልገውን ኢንቨስትመንት መግዛት የሚችሉበት እገዛም የለም ብሏል-ሌበር።
መንግሥት በበኩሉ አዲሱ ሕግ በአሁኑ ጊዜ የነዳጅ ወይም የናፍጣ መኪናን ነዳጅ የመሙላት ያህል ቀላል እንደሚያደርገው ገልጿል።
ያለምንም ንክኪ ክፍያ ለመፈፀምም ቀላል መንገድ መሆኑን ጠቅሶ ” ይህም በሁሉም አዳዲስ ፈጣን የኃይል መሙያ (ቻርጅ ማድረጊያ) ቦታዎች እንደሚጀመር አስታውቋል።
እንግሊዝ በአሁኑ ጊዜ ወደ 25 ሺህ የሚጠጉ የኃይል መሙያ( ቻርጅ ማድረጊያ) ቦታዎች ያሏት ሲሆን የውድድር እና የገበያ ባለሥልጣን ከ2030 በፊት አስር እጥፍ የሚሆን የኃይል መሙያ ቦታዎች ሊያስፈልጋት እንደሚችል ገልጿል።
ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የምታደርገው ሽግግር ዩናይትድ ኪንግደም የአየር ንብረት ግቦችን ለመምታት የያዘችው ስትራቴጂ አካል ሲሆን በ2019 ከዩኬ 16 በመቶ የልቀት መጠን መኪኖችና ታክሲዎች ይሸፍናሉ።
እንደ ጃጓርና ቮልስ ያሉ በርካታ የመኪና አምራቾች ከ2025 እስከ 2030 ባሉት ጊዜያት ኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት አቅደዋል። ፎርድም በ2030 በአውሮፓ የሚሸጡ መኪኖቹ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ እንደሚሆኑ ገልጿል።
ይሁን እንጂ አራት የዓለማችን መኪና አምራቾች፣ ቮልስዋገን፣ ቶዮታ፣ ሬኖልት ኒሳን እና ሃዩንዳይ ኪያ በ2025 ዜሮ ልቀት ያላቸውን መኪኖች ለመሸጥ በኮፕ 26 ስብሰባ ላይ ፊርማቸውን አላኖሩም።
በዩኬ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መኪኖች ሽያጭ እያደገ ሲሆን በ2020 ከተሸጡ መኪኖች 10 በመቶ የሚሆኑት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ናቸው። ይህም በ2018 ከነበረው በሁለት ነጥብ አምስት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ኅዳር 15/2014