ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን እንደማይፈቅዱ ትራምፕ ዳግም አስታወቁ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን እንደማይፈቅዱ በድጋሚ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ ከ‹ፎክስ ኒውስ› (Fox News) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ልትሆን እንደማትችል ገልፀዋል። ‹‹እስራኤል ጥቃት ከመሰንዘሯ በፊት ኢራን የጦር መሳሪያ ለማምረት የቀራት ጥቂት ሳምንታት ብቻ ነበር›› ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ካላቆመች፣ አሜሪካ ያለምንም ማመንታትና ጥያቄ በድጋሚ ወታደራዊ ርምጃ እንደምትወስድ ፕሬዚዳንቱ አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ ከቀናት በፊት ሲናገሩም፣ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የመገንባት ጥረቷን ከቀጠለች ከባድ ወታደራዊ ርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀው ነበር። ትራምፕ የኢራኑ የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከእስራኤል-ኢራን ጦርነት መቆም በኋላ ላስተላለፉት መልዕክት ምላሽ በሰጡበት ንግግራቸው፣ ኢራን ዩራኒየሟን እንደገና እንደምታበለጽግ የሚያሳይ መረጃ ካገኙ ዳግም ያለማቅማማት ድብደባ ለመፈፀም እንደማያወላውሉ ተናግረዋል።

አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከተኩስ አቁሙ በኋላ በተሰማው የመጀመሪያ ንግግራቸው፣ ኢራን ጦርነቱን ማሸነፏንና በኳታር በሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት በመሰንዘር አሜሪካን በጥፊ እንዳለቻት ተናግረው ነበር። ትራምፕ ለኻሜኒ ንግግር በሰጡት ምላሽ፣ ኢራን በጦርነቱ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳስተናገደችና የኒውክሌር ጣቢያዎቿ እንደወደሙ ጠቅሰው፤ ‹‹ኻሜኒ በትክክል የት ተደብቆ እንደነበር አውቅ ነበር፤ ከእስራኤልና ከአሜሪካ ጦር ሕይወቱን ያተረፍኩለት እኔ ነኝ›› ብለዋል። የኻሜኒን ንግግርም ‹‹የጥላቻና የንዴት መልዕክት›› ሲሉ ገልፀውታል።

የእስራኤልና ኢራን ውጊያ በተጀመረ በዘጠነኛው ቀን አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟ ይታወሳል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦራቸው በፎርዶው፣ ናታንዝና ኢስፋሃን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የተሳኩ ጥቃቶችን መፈፀሙንና ጣቢያዎቹን ከጥቅም ውጪ ማድረጉን ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ትራምፕ ይህን ቢሉም ከአሜሪካ የስለላና ደህንነት ተቋማት ሾልኮ በወጣ ምስጢራዊ መረጃ፣ የአሜሪካ ጥቃቶች በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያደረሱት ጉዳት ትራምፕ አክብደው በገለጹት ልክ እንዳልሆነ ተገልፆ ነበር። መረጃው የአሜሪካ ጥቃቶች የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር በወራት ብቻ ወደ ኋላ እንዲመለሱ አድርጓል ብሏል።

ትራምፕና የአስተዳደራቸው ባለስልጣናት በበኩላቸው ይህን መረጃ አጣጥለውታል፤ መረጃውን ያሰራጩትን መገናኛ ብዙሃንንም አብጠልጥለዋቸዋል። ትራምፕ ‹‹የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል›› ሲሉ በቁጣ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹በታሪክ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች አንዱን ለማሳነስ ሙከራ አድርገዋል›› ሲሉ መገናኛ ብዙሃንን ወቅሰዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት ‹‹እናንተ መገናኛ ብዙኃን ትራምፕ ሲሳካላቸው አትወዱም። ለትራምፕ የምታሳዩት ምቀኝነት በደማችሁ ውስጥ የሰረፀ ነው። ትራምፕ እንዲሳካላቸው አትፈልጉም›› በማለት መገናኛ ብዙሃኑንና ዘገባዎቻቸውን በከባድ ኃይለ ቃላት ወርፈዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ደግሞ ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት የሚያስችል ዩራኒየምን እንደገና በወራት ጊዜ ውስጥ ማበልፀግ ለመጀመር የሚያስችል አቅም እንዳላት ይፋ አድርጓል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ፣ አሜሪካ በሦስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ያደረሰችው ድብደባ ከባድ ቢሆንም አጠቃላይ ውድመት አለመድረሱን ገልጸዋል። ‹‹እውነቱን ለመናገር አንድ ሰው ሁሉም ነገር እንደወደመ እና ምንም የቀረ ነገር የለም ብሎ መናገር አይችልም። በወራት ጊዜ ውስጥ ጥቂት ማብላያዎችን በማሽከርከር የበለፀገ ዩራኒየም ያመርታሉ። የኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ አቅሞችን ይዘዋል። ስለዚህ ከፈለጉ ይህንን እንደገና መጀመር ይችላሉ›› ሲሉ ግሮሲ ተናግረዋል። ይህ የዋና ዳይሬክተሩ ሃሳብ ዶናልድ ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ‹‹ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል›› ሲሉ ከተናገሩት መረጃ ጋር ይቃረናል።

ኢራን በበኩሏ የኒኩሌር ጣቢያዎቿ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰባቸው እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መረጃዎችን አስተላልፋለች። አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ‹‹ጥቃቱ ምንም ፋይዳ የለውም›› ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አባስ አራግቺ ግን ‹‹ከመጠን በላይ እና ከባድ›› ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማትና ወታደራዊ ጣቢዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ለ12 ቀናት የዘለቀ የአየር ውጊያ አካሂደዋል። እስራኤል በፈፀመቻቸው ጥቃቶች በርካታ የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸው እና ወታደራዊ ተቋማት መውደማቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ኢራንም በወሰደቻቸው የአፀፋ ርምጃዎች በእስራኤል ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። በጥቃቶቹ ሰላማዊ ዜጎችና የመኖሪያ አካባቢዎች ሰለባ እንደሆኑም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

አሜሪካም ከእስራኤል ጎን ተሰልፋ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ፈፅማለች። ኢራን አሜሪካ በኒውክሌር ጣቢያዎቿ ላይ ለፈፀመችባት ጥቃት ኳታር በሚገኘው አል-ኡዴይድ የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት በመፈፀም የአፀፋ ምላሽ ሰጥታለች። ከጦር ሰፈሩ ጥቃት ጥቂት ሰዓታት በኋላ ሁለቱ ሀገራት ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ተገልፆ የ12 ቀናቱ የአየር ላይ ውጊያ እንደቆመ ይታወሳል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You