አሁን ከመቼውም በላይ ፈተና ውስጥ ነን። እንደ አገርም ሆነ፤ ወይም እንደ ሕዝብ ከባድ ፈተና ውስጥ ነን። ፈተናው ደግሞ ከየትም ሳይሆን በውጭና ባእዳን እጅ የተደገፉ፤ የራሳችን ወገኖች የፈጠሩት ሲሆን አገርና ህዝብ እየተፈተኑ ያሉትም በእነዚሁ የራሳችን ክፋይ በሆኑ ወገኖች ነው።
እንደ አለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ችግር አጥቷት አያውቅም፤ ከችግሮቹ ሁሉ እጅጉን የከፋው ጦርነት ሲሆን እሱም ዙር እየጠበቀና ዙሩንም እያከረረ ሲደጋግማት መታየቱ ነው። ከጦርነቶች ሁሉ ደግሞ በቁጥርም ሆነ በቦታ ሽፋን የሚበልጠው ያካሄድነው የእርስ በርስ ጦርነት መሆኑ ደግሞ እራሱን ችሎ ሌላ ተረክና ታሪክ ነውና የእስከዛሬውን በዚሁ ጠቅልለነው፤ “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሃ ይጠጣል” በሚለው “ደምድመነው” ወደ ዛሬው፣ ወቅታዊ ጉዳያችን እንምጣ።
ይህ አሁን የምንጽፈው የወደፊት የአገራችን ታሪክ ገና አሁኑኑ እጅግ ውስብስብ ሲሆን ለመወሳሰቡም የባለድርሻ አካላቱ መብዛትና የተዋኒያን ህልቆ መሳፍርትነት ነው። የአገር ውስጦቹን እንኳን ትተን የውጭዎቹን ብንቆጥር ከሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድና ኬንያ በስተቀር ከኢትዮጵያ ጎን ማንም የለም። ሁሉም “ባይጠቅምም ዓላማችንን ለማሳካት ይረዳናል” መርህ (በተለይ አሜሪካ) ከማእከላዊ መንግሥትነቱና ገዥ ፓርቲነቱ ተገንጥሎ መቀሌ በመመሸግ መልሶ ወደ ኋላ ተኩስ ከከፈተው ሕወሓት ጋር ወግኗል። ውጉዝ ከመ አሪዎስ እንዳላሉት ሁሉ ዛሬ “ባይጠቅምም ዓላማችንን ለማሳካት ይረዳናል” በሚል መርሃቸው ወደ መደገፍና የገዛ አገሩን እንዲያፈርስ መደላድል መፍጠራቸው (ከአላማቸው አኳያ) ምንም የሚያስገርም አይደለም። የቻይና ወደ አፍሪካ ማዘንበል፣ የሩሲያ ከአፍሪካ ጋር በግልፅ ስምምነት መፍጠርና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማንሰራራት መጀመር ወዘተ ለአሜሪካ ራስ ምታት ቢሆኑ የሚደንቅ አይደለም።
በተለይም ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልኩ በአፍሪካ የመሪነት ሚናን ከመጫወትም ባለፈ በቀንዱ ጂኦፖለቲክስ (በተለይም ከቀይ ባህር ስትራቴጂያዊነት አኳያ) ወሳኝ ከመሆኗ፤ ነባሩ የእነ አሜሪካ ትክል ነቅሎ አዲሱና የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ከመትከል አኳያ ያለውን ትንቅንቅ ስንመለከተው ይህ ኢትዮጵያን የማፍረስ ብርቱ ርብርብ መከሰቱ ምንም አያስገርምም፤ የሚያስገርመው ተባባሪዎቹ ብቻ ሳንሆን ግንባር ቀደም አፍራሾቹ እኛው መሆናችን ነው። ወጣቶቻችን ላይ የወደቀው ኃላፊነት ክብደትም ምንጩ ይሄው ከእኛው የወጡ አፍራሾችን መቃፍረስ መሆኑ ነው።
ከጥንቃቄ ጉድለት፤ ከአመራር ማጣት፤ አርቆ ማስተዋል ካለመቻል ወዘተ ምክንያት ይህ የ”ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ” ቡድን እቅዱ እንዳይሳካ ማድረግ ይጠበቃል። የሚያስገርመው ለእነሱ አድሮ፣ ለእነሱ ተገዝቶ፣ ጀርባውንም ለእነሱ አከራይቶ ተጋላቢ ጌኛ የሆነው የራሳችን ጉድ እንጂ ሌላ አይደለም።
ይህ እየተነጋገርንበት ያለው የወቅቱ የአገራችን ጉዳይ ከእስከዛሬዎቹ የእርስ በርስ ጦርነቶቻችን ሁሉ የከፋ መሆኑ እየተነገረ ነው። በተለይ በግፍ አገዳደልና ንፁሀንን በማሰቃየቱ በኩል ተወዳዳሪ የለውም ተብሎ ሪኮርድ ስለመያዙ እየተፃፉ ያሉት ገፆች ብዙ ናቸው። በመሆኑም ይህንን እጅግ አሰቃቂ ተግባር፣ አገርን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳን ወገን አላማውን በአጭር የማስቀረት አገራዊ ኃላፊነት ከማንም በላይ በወጣቱ ትከሻ ላይ ወድቆ መገኘቱ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ በመላው አገሪቱ ከዳር እስከ ዳር በመደራጀትና በመንቀሳቀስ ምን እያደረገ እንደ ሆነ ይታወቃል። በተለይ በአማራ ክልል ከ”ፋኖ” ጀምሮ ሁሉም አካላት ከፍተኛ የሕይወት መስዋእትነትን እየከፈሉ ይገኛሉ።
“በድጋሚ የበደልን ቀንበር ልንሸከም የምንችልበት ምክንያት የለም”፣ “ትህነግን ሳይደመሰስ እንቅልፋ አንተኛም”፣ “ደሴን የሚረግጣት የአሸባሪው ምርኮኛ ብቻ ነው፤ ከተማችንን አሳልፈን አንሰጥም”፣ “የአሸባሪውን ቀብር በወሎ ምድር እናደርገዋለን” ወዘተ በሚሉ መሪ መልእክቶች የታጀበው የደሴ ወጣቶች የተቃውሞ ሰልፍ፤ የአሸባሪውን ሕወሓት ወረራ ለመቀልበስና ቡድኑን እስከወዲያኛው ለመደምሰስ ወደ ግንባር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የከተማው ወጣቶችም ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም። በሌሎች ክልሎችም እንዲሁ።
ጁንታው በዚህ አገር የማፍረስ ፅኑ ፍላጎትና አቋሙ ከፀና ቆይቷል። ለዚህ ደግሞ ማስረጃው በመንግሥት የተወሰደውን ተኩስ የማቆም ውሳኔ ተከትሎ የእሱ አሻፈረኝ ባይነትና ጭራሽም ወደ አጎራባች ክልሎች በመሄድ መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ማድረስ፤ ይህን ጥፋቱንም እስካሁንም ድረስ አለማቆሙና በባእዳን እየተደገፈ በጥፋት ሀይቅ ውስጥ እየዋኘ መገኘቱ ነው።
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው፣ ተመራማሪና አሰልጣኝ ሳምሶን ይስሀቅ እንደሚሉት ከሆነ ይህ የጁንታው እርምጃ ፍፁም ስህተትና የጥፋት ጎዳናን የመከተል አካሄድ ነው። በመሆኑም፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣ በተለይም ወጣቱ በዚህ እኩይ ተግባር ሊታለልና ከማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ወደ ኋላ ሊል አይገባም።
እንደ አቶ ሳምሶን ገለፃ የሀሰት ፕሮፓጋንዳንና ተጨባጭ ያልሆነን መረጃ ስርጭት በተመለከተም ህብረተሰቡ በእንደዚህ አይነት ውዥንብሮች ፈፅሞ ሊረበሽ አይገባም። “እንዲህ አደረኩ፣ እንዲህ ላደርግ ነው” ወዘተ በሚለው ሊረበሽ አይገባም። ይህ ህዝቡን በስነ ልቦና ጦርነት የማዳከም ስትራቴጂ መሆኑን ማወቅ ይገባዋል። እርግጥ ነው ከጦርነት ጋር ተዳምሮ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር እንደሚረብሽ የታወቀ ነው። ቢሆንም ህዝቡ ተግባሩ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሏቸው ወገኖች ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ ተስፋ ከመቁረጥ ሊቆጠብ፤ ሊረጋጋ ይገባል። ከመረጋጋትና ማረጋጋት አኳያ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም በተለይ አረጋውያን፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎችም በሀሰት መረጃው ማእበል የተረበሸውንና የተደናገረውን ክፍል በማረጋጋት በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ይህንኑ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል። ወጣቶችም ይህንን በአገር ላይ የመጣን አደጋ ከማክሸፍ አኳያ ሚናቸው ከፍተኛ እንዲሆን ይጠበቃል።
በተለይ የመገናኛ ብዙኃንም ይሁኑ የማህበራዊ ሚዲያው ተሳታፊዎች ከእንደዚህ አይነቱ፣ ከጦርነቱ በባሰ ሁኔታ ህዝብና አገርን ከሚጎዳ ተግባር በፍጥነት ሊቆጠቡና እውነታውን ለህዝብ በማሳወቅ ህዝቡን የማረጋጋትና ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ሳምሶን ማንኛውም ሚዲያ፣ እዚህም ያለ ውጭ፣ በከፍተኛ ኃላፊነት፣ ሙያዊ ግዴታና ህጋዊ አግባብ ሊንቀሳቀስ ይገባል፤ አገርና ህዝብ በሌለበት ሁኔታም የእነዚህ ወገኖች ህልውና ሊቀጥል አይችልምና ከዚሁ አኳያ መስራት እንዳለባቸውም የሚያሳስቡት አቶ ሳምሶን፣ በጦርነቱም ሆነ እሱን ተከትለው የመጡት የሀሰት መረጃዎች መጥለቅለቅ በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ አገሪቱ፤ ከዛም ባለፈ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ስነአእምሮ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በዚህ የዲጂታል ዘመን ይህ ሊከሰት እንደሚችል አውቆ ህዝቡ በፍፁም ሊረበሽ አይገባም። ከሁሉም በላይ ግን ሚዲያው፣ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያው በከፍተኛ ኃላፊነት ሊንቀሳቀስና ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል በማለት የሚያሳስቡት አቶ ሳምሶን በተለይ ይህን ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ ወጣቱ የመሪነት ሚናውን መወጣት እንዳለበት ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውቀዋል።
ይህንን ሁሉ ግፍ፤ በተለይም የአሁኑን የሽብርተኛውን መጠነ ሰፊ ጥቃትና የሽብር ተግባር ከመመከት አኳያ የወጣቱ ተሳትፎ ምን እንደሚመስልና ምንስ መሆን እንዳለበት የተለያዩ ሰዎች አስተያየታቸውን የሰጡን ሲሆን ቀዳሚውና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊ አንዱ ናቸው።
“የውስጥ ባንዳውም ሆነ የውጭ ኃይሎች እየወጉን ያሉት ድንገት ተነስተው አይደለም። ለዓመታት መሳሪያ ሲገዙ፤ ታንክ ሲያስመጡ፤ ምሽግ ሲቆፍሩ ኖረው ነው ዛሬ እየተኮሱብን ያሉት።” የሚሉት ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት በሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አድነው አበራ ናቸው። “በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ የወጣቱ ምላሽ ዘርፈ ብዙ ነው። አንድ ሁለት ተብሎ የሚያልቅ አይደለም። እስከ ሕይወት መስዋእትነት ድረስ ዋጋ እየተከፈለ ይገኛል።” ሲሉም የወጣቱን ወቅታዊና የአገርና ህዝብ ህልውናን የመታደግ እንቅስቃሴ ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ባልደረባ የሆነው ወጣት ጥላሁን ውቤም በተመሳሳይ በወጣቱ በኩል ያለውን አገራዊ ጥሪ ተቀብሎ የመንቀሳቀስ ሁኔታ በአድናቆት ከገለፀ በኋላ “የቤተሰቦቼ ሁኔታ መስመር የሚይዝልኝ ቢሆን እኔም አሁኑኑ ወደ ግንባር በመሄድ ከመከላከያ ጎን መቆም እፈልጋለሁ። አገር ቀልድ አይደለም፤ መጠቃት እጅግ ከባድ ነው፤ ይህንን ሁሉ ግፍ ተቀብሎ መኖር የሚፈልግ ወጣት ስለሌለና እኔም የዛው አባል ስለሆንኩ” በማለት ነበር አስተያየቱን የሰጠን።
እንደ አቶ አድነው አገላለፅ ወጣቱ በበርካታ መስኮች በመሰማራት ውጤታማ በመሆን ላይ ነው። ካከናወናቸውና እያከናወናቸው ከሚገኙት ተግባራት መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል።
በቀጥታ በአውደ ውጊያው ከኢትዮጵያ ውስጥና ውጭ ኃይሎች፤ አሸባሪዎች፤ ባንዳዎች፤ ከሃዲዎች እየተፋለመ ይገኛል። መከላከያን፣ ልዩ ኃይልን፣ ሚኒሻን በመቀላቀል እንዲሁም በፋኖ ተደራጅቶ በሺዎች የሚቆጠሩት ለወገን ጦር ደጀን በመሆን፤ ስንቅ በማቀበል፤ የአካባቢውን ደህንነት ተደራጅቶ ከጁንታው ተላላኪና ሰርጎ ገቦች በመጠበቅ ላይ ይገኛል።
ይህ ብቻም አይደለም፤ ወጣቱ የዘማች ቤተሰብ የደረሰ የእርሻ ሰብል ይሰበስባል፤ አሸባሪ ኃይሎች በከፈቱት ጦርነት የተፈናቀሉና በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ህጻናት፤ እናቶች፤ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን ይንከባከባል፤ የየአካባቢውን ማህበረሰብ፣ ተቋማት፣ በማስተባበር እንዲደግፉ እያደረገ ይገኛል።
ወጣቱ ትክክለኛ መረጃን በመስጠት ቀድሞ በሀሰት ፕሮፓጋንዳና ሆድ አደር ሎቢስቶች የተወሰደብን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ከማክሸፍና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወደ መሃል እንዲሳብ በማድረግ ረገድ ጀብድ እየሰራ ነው።
ለህሊናና ለሀገር የሚቆረቆሩ ወጣት ዲያስፖራ አባላት በዲጂታል ሚዲያው አማካኝነት ሌት ተቀን የተዛባ የሀሰት ፕሮፓጋንዳን በመመከት የጠላቶቻችን ዓላማና አጀንዳ በዓለም መድረክ ተቀባይነት እንዳይኖረው ከማድረግና ማምከን አኳያ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፤ እየተጫወቱም ነው።
የጁንታውን የሀሰት መረጃ ሳያላምጡ በቀጥታ በመቀበል የሚያራግቡና ለውሳኔ መጠቀም ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች በሀገርና ከሀገር ውጭ በመደራጀት ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ጫና ፈጥረዋል። ምሳሌ “ድምጻችን ይሰማ”፤ “ነጩ ፖስታ ወደ ነጩ ቤተመንግሥት” … ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።
ዳይሬክተር አድነው እንደሚሉት የወጣቱ ተሳትፎ በዚህ የሚያበቃ አይደለም። በቀጣይም የሀገራችን አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት እስከሚረጋገጥ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ወጣቱ በመዝመት፤ ቀፎው እንደ ተነካ ንብ በነቂስ በመውጣት ክንዱን ለጠላት ማሳየት አለበት። በአሁኑ ወቅት አገራችንን የገጠማት ፈተና እንደ አገር የሁላችንም እንጂ የእከሌ የእከሌ … የሚል ነገር የለውም። ጠላቶቻችን እንደ ስትራቴጂ በሚከተሉት ከፋፍለህ ግዛ መሰሪ አመለካከት በፍጹም ችግሩን የተወሰነ አካባቢ ችግር አድርጎ መውሰድ እንደሌለበት በውል በመገንዘብ ሀገራዊና ህዝባዊ አንድነትን ባጠናከረ መልኩ በጋራ ምላሽ በመስጠት የጠላትን አከርካሪ መስበር ይገባል።
በመጨረሻም፣ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት በመዝመት መከላከያን በመቀላቀል፤ በመደገፍ፤ አካባቢን በንቃት በመጠበቅ፤ የአካባቢውን ጸጥታ ኃይል በመደገፍና በመተባበር፤ የሚነዙትን የጠላት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ትርክቶች ራስንና ነዋሪውን በመጠበቅና በመመከት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
እኛም “ወጣት የነብር ጣት” የሚለውን ዘመን ተሻጋሪ ጥቅስ በመጥቀስ በዚሁ ተሰናበትን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2014