ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ገበያ በስፋት ከሚያቀርቡ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም፤ በነበረው ብልሹ አሠራርና ቢሮክራሲ ሳቢያ ሀገሪቱ በዘርፉ ለማግኝት ያቀደችውን ያህል ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች። ነገር ግን በሀገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ባደረገው የኢኮኖሚ እና የተቋማት ሪፎርም በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ በዘርፉ አስደናቂ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል።
ለውጡ ከመጣ ወዲህ በዘርፉ የተገኝውን አበረታች ውጤት አጠናክሮ በማስቀጠል አገሪቱ በዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን መስሪያ ቤት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሠራ እንደሚገኝ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ኡመር ይናገራሉ።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ ባለስልጣኑ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የምርት ጥራቱ ተጠብቆ የአገሪቱ ምርት የውጭ ገበያው ላይ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ምርቱም ለውጭ ገበያ ቀርቦ ገበያውን እንዲቆጣጠር ሁለት ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል። የመጀመሪያው የኢትዮጵያን ቡና በስፋት የሚጠቀሙ ወይም የሚገዙ ነባር ደንበኞች ከተጠቃሚነታቸው እንዳይወጡና የምርት ፍላጎታቸውን እያሰፉ እንዲሄዱ ገበያውን የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል። ለአብነት ጀርመን፣ ሳውዲ ዐረቢያ፣ አሜሪካ፣ ቤልጄየም፣ ጣሊያንና ደቡብ ኮሪያ የታወቁ የኢትዮጵያ ቡና ገዥ አገሮች ናቸው። እነዚህ አገሮች በደንበኝነታቸው ጸንተው እንዲዘልቁ ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመት ከገዙት በላይ እንዲገዙ እየተሠራ ይገኛል።
ሁለተኛው ደግሞ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በማፈላለግ የአገሪቱን የቡና ምርት በስፋት በማስተዋወቅ አዳዲስ ደንበኛ የማፍራት ሥራ ይሠራል። አዳዲስ ገበያ ሲባል ቡናን በስፋት የሚጠቀሙ እንደኤዥያ የመሳሰሉ አገሮች የኢትዮጵያን ቡና በማስለመድ ምርቱን በተሻለ ዋጋ እንዲገዙ በማድረግ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ እየተሠራ ነው።
በዚህም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ ባለስልጣኑ እነዚህን ሁለት ስትራቴጂዎች ነድፎ በተሠራው ሥራ፤ ለአብነት ከኤዥያ አገሮች ቻይናን ብንወስድ ከፍተኛ የቡና ምርት ተጠቃሚ አገር ናት። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ቻይና የኢትዮጵያን ቡና በስፋት ከሚገዙ 10 የኢትዮጵያ ቡና ከሚጠቀሙ ወይም ከሚገበዩ አገሮች ተርታ ውስጥ አልነበረችም። የአገሪቱን የቡና ምርት በስፋት በማስተዋወቅ አዳዲስ ደንበኛ የማፍራት ሥራ በስፋት በመሠራቱ አሁን ላይ ቻይና የኢትዮጵያን ቡና በስፋት ከሚጠቀሙና ከሚገዙ 10 አገሮች ውስጥ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በተመሳሳይ አውስትራሊያ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን ቡና በስፋት ከሚገዙና ከሚጠቀሙ 10 አገሮች መካከል አልነበረችም። ነገር ግን የአገሪቱ ምርት አዳዲስ ገበያዎችን ሰብሮ እንዲገባ በተሠራው ሰፊ የማስታወቂያ ሥራ አሁን ላይ አውስትራሊያ የኢትዮጵያን ቡና በስፋት ከሚጠቀሙና ከሚገዙ 10 አገሮች ውስጥ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ከዚህ አኳያ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት የተያዘው እቅድ በጥሩ ሁኔታ ሊሳካ የቻለው፤ ዓለም አቀፍ የቡና ዓውደ ርእዮች ላይ በመሳተፍ የተለያዩ ቡና ተቀባይ ኩባንያዎች ጋር በመገናኝት ምርቱን እንዲገዙ የማግባባት ሥራ በመሥራቱ፣ የጋራ ውይይቶችን በማካሄድ፣ ነባር ደንበኞች ከገበያው እንዳይወጡ በነርሱም ሆነ በእኛ በኩል የተስተዋሉ ክፍተቶች ካሉ ተነጋግሮ መግባባት ላይ በመድረስ እንዲሁም በበይነመረብ ምርቱን በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ በመሠራቱ ነው።
በዚህም በተለይ ለውጡ ከመጣ በኋላ በተሠራው የሪፎርምና ሰፊ የማስታወቂያ ሥራዎች አገሪቱ በታሪኳ ከዘርፉ ከፍተኛውን ገበያ ማግኝት ችላለች፡፡ በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመት በዘርፉ ለማግኘት ከተያዘው እቅድ አኳያ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሲታይ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኝት ተችሏል። በሩብ ዓመቱም 70 ሺ 880 ነጥብ ዘጠኝ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 297 ነጥብ 84 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኝት ታቅዶ 86 ሺ 288 ነጥብ አንድ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 327 ነጥብ 87 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ከተያዘው እቅድ አኳያ የዕቅዱን 122 በመቶ ማሳካት መቻሉን አቶ ሻፊ ይናገራሉ።
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ባለፈው ዓመት 53 ሺ 443 ነጥብ 05 ቶን ቡና ተልኮ 180 ነጥብ 79 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ከዚህ አኳያ ዘንድሮ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በሁለት ሺ 845 ነጥብ 09 ቶን ቡና እና በ143 ነጥብ 08 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር ብልጫ አለው። ይህም በአገሪቱ ታሪክ እስከአሁን ካሳለፍናቸው ሩብ ዓመቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ በሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የተገኘበት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት እንደሆነ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከዘርፉ ለማግኝት የታቀደውን ገቢ ለማሳካት ዓለም አቀፍ የቡና ዓውደ ርእዮች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያ ቡና ፈላጊ አገራት ቁጥርንና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ በስፋት እንደሚሠራ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የፊታችን ታኅሣሥ 2014 ላይ በቻይናዋ ሻንጋይ ግዛት በሚካሄደው አራተኛው የቻይና የውጭ ንግድ ትርዒት ላይ ለመሳተፍ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በንግድ ትርዒቱ ላይ አብዛኞቹ ቡና ላኪ፣ ቡና ቆይ፣ ቡና አልሚ ማህበሮች እንዲሁም ስድስቱ የኦሮሚያ፣ የሲዳማና የደቡብ ክልሎች ቡና አቅራቢ ማህበራት ይሳተፋሉ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱና ቡና ላኪዎች ማህበር ንግድ ትርዒቱን ከሚመሩ አካላት ጋር በመነጋገር ማህበራቱ እንዲሳተፉና መሳተፍ የሚያስችላቸውን የግብዣ ወረቀት እንዲደርሳቸው ያደርጋሉ። ስለዚህ በንግድ ትርዒቱ መሳተፍ የሚፈልጉ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ቀድሞ መረጃው እንዲደርሳቸው ተደርጓል። ቡና ላኪና አቅራቢ ማህበራት በንግድ ትርዒቱ ላይ በተሳካ ሁኔታ ተሳታፊ ሆነው ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
በንግድ ትርዒቱ ቡናን ጨምሮ በልዩ ልዩ መስክ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በንግድ ትርዒቱ እያንዳንዱን የኢትዮጵያ ቡና ዓይነት በማቅረብ የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል። በዚህም እያንዳንዱ የአገሪቱ ባለ ልዩ ጣዕምና ጥራት ያለው ቡና እየተቀመሰ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ይተዋወቃል።
ከዚህም ባሻገር በንግድ ትርዒቱ “ቢዝነስ ቱ ቢዝነስ” የሚል የውይይት መድረክ ስላለ በመድረኩ ገዢው የሚፈልገው ቡና “ምን ዓይነት እንደሆነ? በምን መልኩ እንዲዘጋጅለት እንደሚፈልግ? ምን ያህል መጠን ቡና እንደሚያስፈልገው?” ያነሳል። በአንጻሩ ደግሞ ቡና ላኪ ማህበራት “ይህን ዓይነት ቡና አለኝ። ይሄን እሴት ጨምሬ አቀርባለሁ” ብሎ ከቡና ተረካቢ ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር እዛው ኮንትራት ተፈራርመው የሚመጡበት ዕድል አለ። ኮንትራቱ ከተፈረመ በኋላ ምርቱ ወይም ቡናው በቀጥታ የሚላክ ይሆናል።
እንዲሁም የንግድ ትርዒቱ አዳዲስ የገበያ ዕድል ከመክፈቱ ባለፈ ነባር ቡና ተረካቢ አገሮችን ገበያው ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርግ ነው። ነባር ደንበኞች “ምርቱ አለ ወይስ የለም? ምርቱን ልታቀርብ ትችላለች ወይስ አትችልም?” የሚለውን የሚያውቁበትና ገዢው ራሱ “ይሄንን ምርት አገኛለሁ” ብሎ በኛ ላይ እምነት የሚጥልበት ሁኔታን ይፈጥራል። ስለዚህ በኤግዚቢሽኑ ላይ መሳተፍ ምርትን በብዛት ለመሸጥና ለማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ምርቱ ያለና ማግኘት የሚችሉ መሆኑን ከገዢው ጋር የመተማመን ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የአገሪቱን የቡና ምርት በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ በመሠራቱ በቻይና ገበያ ሰብሮ በመግባት አሁን ላይ የኢትዮጵያን ቡና ከሚገበዩ አስር ከፍተኛ ገዢዎች ተርታ ቻይና የተሰለፈች ቢሆንም ቅሉ፤ ከዚህ በላይ የአገሪቱን ምርት በስፋት ተጠቃሚ እንድትሆን አራተኛው የንግድ ትርዒት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
በጥቅሉ በአራተኛው ዙር የቻይና የውጭ ንግድ ትርዒት በመሳተፍ የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕም እና ጥራት ያለው ቡና ለዓለም ገበያ የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል። የንግድ ትርዒቱም እያደገ የመጣውን የኢትዮ ቻይና የቡና ግብይት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እንዲሁም ከፍተኛ ግብይት ከሚፈጽሙ አካላት ጋር ለመገናኘትና ለቻይናውያን የዘርፉ ባለሀብቶች የኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች አገራት ጋር ያለውን ልዩነት ለማስተዋወቅ የንግድ ትርዒቱ የላቀ ሚና ይጫወታል። ስለዚህ አራተኛው የቻይና የንግድ ትርዒት ለኢትዮጵያ ቡና ገበያ ሰፊ ዕድል ይዞ የመጣ ስለመሆኑ ዳይሬክተሩ ያብራራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ በዓመት 10 የተለያዩ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ላይ ትሳተፋለች። በቻይናም ሆነ በሌሎች አገሮች የንግድ ትርዒቶች ላይ መሳተፏ አገሪቱ የቡና ምርቷን በስፋት እንድትሸጥ ዕድል ይፈጥራል። ቡና በስፋት በሚሸጥበት ጊዜ ደግሞ በቡናው ዘርፍ ተዋናይ የሆኑ አካላት በሙሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
አገሪቷም ከዘርፉ ማግኝት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ያደርጋል። ሌላው ደግሞ በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ቡናችንን በምናስተዋውቅበት ጊዜ “የኢትዮጵያ ቡና ከሌላው አምራች አገሮች የሚለይበት ምንድነው?” የሚለውን ነገር ተጠቃሚው ለይቶ እንዲያውቅ ይረዳል። ተጠቃሚው ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕምና ጥራት ያለው ቡና ለይቶ ካወቀ የኢትዮጵያ ቡና ገበያው ላይ ተመራጭ ይሆናል። ይህም ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ነው።
ኤግዚቢሽኖች ገዥና ሻጭ ፊት ለፊት የሚገናኙበት መድረክ በመሆኑ፤ ፊት ለፊት ተገናኝተው ችግሮች ካሉ ችግሮችን የሚፈቱበት፤ አዳዲስ ኮንትራት የሚፈራረሙበት መድረክ ነው።
በሌላ በኩል በመድረኩ “ገቨርመንት ቱ ቢዝነስ“ የሚል ስብሰባ ስለሚኖር መንግሥት ምርቱን ከሚረከቡ ባለሀብቶች ወይም የኩባንያ ኃላፊዎች ጋር በዘርፉ ስላሉ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎች የሚመክርበትን ዕድል ይፈጥራል። በዚህም መንግሥት “በኢንፖርትና ኤክስፖርት መካከል ያለው ክፍተት ምንድነው? ምን መስተካከል አለበት? በነርሱ በኩል ያለው ችግር ምንድነው?” የሚለውን ሁለቱም አካላት የበኩላቸውን የቤት ሥራ ወስደው ችግሮችን በጋራ በመፍታት ገበያውን ዘመናዊ በማድረግ ምንም ችግር ሳይፈጠር የተሳለጠ እንዲሆን ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል። በመሆኑም አራተኛው የቻይና የውጭ ንግድ ትርዒት የፊታችን ታኅሣሥ ወር ላይ በቻይናዋ ሻንጋይ ግዛት የሚካሄድ ሲሆን፤ ቡናን ጨምሮ በልዩ ልዩ መስክ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2014