በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ሀገራችን አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ መመሳሰል ወደ ነበረው 1970 ዎቹ የጋዜጣው እትሞች ጎራ ብለናል። በዚህም በወቅቱ ሶሞሊያ ኢትዮጵያን የወረረችበትና ኢትዮጵያውያንንም ይህን ወረራ ለመቀልበስ ሰራዊቱና ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር የተነቃነቁበትና ይህን ተከትሎም በየአካባቢው በደሎች ይመዘገቡ የነበረበት ወቅት ነው። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በዚህ ላይ ተመስርቶ ሰፊ ዘገባ ያቀርብ የነበረበት ወቅት ነበር። ከእነዚያ የጋዜጣው ዘገባዎች ቀንጨብ አርገን ለዛሬ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።
በወበራ 675 የሶማሊያ ወታሮች ተደመሰሱ
ድሬዳዋ (ኢ-ዜ-አ-) አባት ጦረኞችና አገር ወዳድ ግለሰቦች ከመደበኛው መለዮ ለባሹና ከሚሊሻው ጦር ጎን በመሰለፍ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በወበራ አውራጃ በተለያዩ ቀበሌዎች በቅርቡ ባደረጉት አሰሳ ፮፻፸፭ የሶማሊያ መደበኛ ወታደሮችን ገድለው ከ፩ሺ፷፮ በላይ የሚሆኑትን በማቁሰል ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎችና በርከት ያሉ ምሽጎችን ደምስሰዋል።
ከዚሁ በቀር በፕሮፓጋንዳ ውስጥ ለፀረ አብዮት አንድነት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን በአረብኛ ቋንቋ የተጻፉ ልዩ ልዩ ጽሁፎች ከመማረካቸውም በላይ ዘርፈዋቸው የነበሩትን ፪ሺህየቀንድ ከብቶችና የሚሸጥ እህል ለባለንብረቶች እንዲመለሱ ያደርጉ መሆናቸውን የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ ትናንት አስታውቀዋል። በሜታ ወበራ በተባለው ቀበሌ ከተደመሰሱት ፶ የሶማሌ ወታደሮች መካከል የጦር መሪ የነበረው ሻምበል አብዱላሂ የሱፍ የተባለው እንደሚገኝበት የፖሊስ አዛዡ ጨምረው ገልጠዋል።
በጠቅላላው አውራጃው ውስጥ የተሰማራው ሠራዊት ወራሪውን የሶማሊያ ጦር በመደምሰስ በመልካ በሎ ወረዳ በጃጃ በሐረርና በሸዋ በር ቀበሌዎች በደደር ወረዳ በሐረዋጫ አካባቢ በሜታ ወረዳ ዋይቤር ታዌ ቂዌና ዳዶ እንዲሁም ራሚስ በተባለው ወንዝ አካባቢ በጎሮጎርቱ ወረዳ መካኒሳ አካባቢ በካራሚሌና በቆቦ ከተሞች ለ፲፬ ጊዜ በተደረገው አሰሳ ፮፻፸፭ የጠላት ወታደሮች በመደምሰስ ከ ፩፻፷፮ በላይ የሚሆኑትን አቁሱሎ ከባድና ቀላል መሣሪዎችን ከመሰል ጥይቶች ጋር ማርኳል።
ሠራዊቱ በአሁኑ ጊዜ በየደረሰበት የእብሪተኛውን ወራሪ ጦር ድል በመምታት ይጠቀምባቸው የነበሩትን በርካታ የጠላት ምሽጎች በመደምሰስ ላይ ነው።
በሌላ በኩል በሲዳሞ ክፍለ ሀገር በአዶላ ወረዳ ባለፈው ረቡዕ በተደረገው አሰሳ ፬ የሶማሊያ መደበኛ ወታደሮች ሲገደሉ ከ፴ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው መሆኑን የጀምደም አውራጃ የሕዝብ ድርጀት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ትናንት አስታወቀ።
በአውራጃው ረዳት አስተዳዳሪ አዝማችነት በተካሄደው በዚሁ አሰሳ የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ መለዮ ለባሾች አባት ጦረኞች የክብረ መንግሥት ከተማ የአብዮት ጥበቃ አባሎች የኰባ ቦሣና የደራሪቱ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር አባሎች የመንግሥት ሠራተኞች ወዛደሮች ተካፋይ በመሆን ከፍተኛ ጀብዱ መፈጸማቸው ታውቋል።
በተለይም የክብረ መንግሥት ከተማ የአብዮት ጥበቃ አባል የሆነች አንዲት ጓድ የአሳሹን ቡድን ቀድማ በመምራት በሞቃዲሾ መንግሥት ወታደሮች ላይ የፈጸመችው የማጥቃት ርምጃ በጓዶች ዘንድ ከፍ ያለ ምስጋናና አድናቆት አትርፋለች።
ይህ አሣሽ ቡድን ይህንን ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ የቻለው የክብረ መንግሥት ከተማ ቀበሌ ፳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቂልጡመራ በተባለው ቀበሌ የሶማሊያ መደበኛ ወታደሮች ከብትና ንብረት ዘርፈው ለማምለጥ ሲሞክሩ ባደረገው የመከላከል ውጊያ መሆኑ ተገልጧል።
ታህሳስ 15 ቀን 1970 ዓ.ም
የሰተዋ ገበሬዎች ታፍነው የተወሰዱ ጓደኞቻቸውን አስለቀቁ
ድሬዳዋ፤ (ኢ-ዜ-አ-) በሐረርጌ ክፍለሀገር በድሬዳዋ ኢሣና ጎረጎራ የሰተዋ ቀበሌ አካባቢ አርሶ አደሮች በእብሪተኛው የዚያድ ባሬ መደበኛ ወታደሮች ታፍነው ተወስደው የነበሩትን የስምንት አርሶ አደሮች አስተባባሪዎችን አስለቅቀው በደህና ወደ ሠፈራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል።
ስምንቱ ሰዎች ታፍነው የተወሰዱት የሶማሊያ መደበኛ ወታደሮች የሰተዋ ቀበሌ በወረሩበት ጊዜ ሁኔታውን ለበላይ ለማሳወቅ በሚጓዙበት ወቅት ከመንገድ ተጠልፈው ነው። በዚሁ አፈጻጸም በኩራ ወደ ተባለው የጦር ሠፈር ተወስደው ለአንድ ወር ተኩል ያህል በረኃብ በጥማትና በምርመራ ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ አርሶ አደሮቹ ወደ ሥፍራው በመሔድ ባላቸው መሣሪያ በመጠቀም የጠላት ወታደሮቹን አባርረው ያላንዳች ጉዳት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸውን አንድ የአውራጃው አስተዳደር ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ገልጧል።
ስምንቱም ሰዎች ባለፈው ማክሰኞ በአውራጃው አስተዳደር ጽህፈት ቤት በመቅረብ የደረሰባቸውን በደል በዝርዝር ከገለጡ በኋላ ስለኢትዮጵያ አብዮት ሂደትና ይዘት ገለጣ የተደረገላቸው መሆኑን ቃል አቀባዩ ጨምሮ ገልጧል።
(ታኅሳስ 27 ቀን 1970 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ታፍነው ወደ ሶማሌ ተወስደው የነበሩ አራት ወጣቶች ተመለሱ
ጐባ (ኢ/ዜ/አ/) አድኃሪው የሞቃዲሾ መንግሥት ወታደሮች በመደበኛና በሚሊሺያውና በአባት ጦረኞች እየተመቱ በመፍረክረካቸው በባሌ ክፍለሀገር ከሃንሰቦ ወረዳ ታፍነው ተወስደው የነበሩት አራት ወጣቶች ከጠላቶቻቸው ከሶማሌያ ወታደሮች እጅ አምልጠው ባለፈው አርብ ገናሌ ከተማ ገብተዋል።
የስምንተኛና የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች የነበሩት እነዚሁ ወጣቶች ታፍነው ሊወሰዱ የቻሉት በክረምቱ ወራት ት/ቤታቸው ለእረፍት ሲዘጋ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ከከተማ ወደ ገጠር ሄደው በነበሩበት ጊዜ ነው።
ወጣቶቹ ታፍነው በቆዩበት አካባቢ ስላለው ሁኔታ ሲያብራሩ የዕለት ስንቅ እንኳ የሌላቸው እነዚህ የሶማሊያ ወታደሮች በመደበኛ በሚሊሺያና በአባት ጡረተኞች ጦር እየተመቱ በመፍረክረካቸው በየጫካው በመሹለክለክ የሕዝብን ንብረት እየዘረፉ ከመብለታቸውም በላይ በጐሳና በሓይማኖት ሕዝብን ለማከፋፈል የሚነዙትን ፕሮፓጋንዳ የሚያከሽፍባቸውን ኢትዮጵያውያንን በየዕለቱ እንደሚገድሉ ገናሌ በገቡበት ጊዜ ለአውራጃው አስተዳዳሪ ጽህፈት ቤት በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል።
ወጣቶች ከዚህም አያይዘው የሶማሊያ ወታሮች በአሁኑ ጊዜ መውጫና መግቢያ ቀዳዳ በማጣት በረሃብ የተዳከሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እንደነሱ ታፍነው የተወሰዱት ኢትዮጵያውያን በዚያ የሚገኙት ጠላቶቻቸውን ተቋቁመውና ተከላክለው ወደ ቤት ንብረታቸው በቅርቡ እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
(ታኅሳስ 16 ቀን 1970 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2014