ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ሲከሰት ማህበራዊ ቀረቤታን ለመግታት ታስቦ የተወሰደው የገጽ ለገጽ ትምህርትን የማቆም ርምጃ የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት አንጻር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ቢታመንም ዛሬም ድረስ በትምህርት መርሃ ግብሩ ላይ መዛባት እንዲፈጠር አድርጓል። ለወራት የተቋረጠው የክፍል ውስጥ መማር ማስተማር ሂደት ወደ ነበረበት ቢመለስም ኮቪድ-19 ያስከተለው ችግር እዚህ ድረስ መጥቷል። ለአብነት የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና መስጫ ጊዜን፣ የዩኒቨርሲቲ መግቢያና መውጫን፣ የተማሪዎች የመመረቂ ጊዜ መራዘምን መጥቀስ ይቻላል።
ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም የተሰጠውን የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈው ለፈተናው ቀን መድረሳቸውን ይናገራሉ። የ2013 ዓ.ም ተፈታኞች ኮቪድ-19 ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ የትምህርት መርሃ ግብሩን እንዳዛባባቸው ይገልጻሉ። ከመምራን ጋር የነበራቸው የመማር ማስተማር ተራክቦ ውስን እንደነበር ያስታውሳሉ። የተሰጠው የማካካሻ ጊዜ አጭር በመሆኑ በርካታ ይዘቶች በውስን ሰዓት ውስጥ ታጭቀው ይቀርቡ እንደነበር ይገልጻሉ። ይህም ተማሪው በራሱ ጥረት ያልተማረውን እንዲሸፍን አስገዳጅ ሁኔታ ፈጥሯል።
ይህን ሁሉ አልፈው ፈተና ላይ ከተቀመጡ በኋላ ፈተና ተሰርቋል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የተመለከቱት ጉዳይ የስነ ልቦና ጫና እንደፈጠረባቸውና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በውጤታችን ላይ ችግር ይፈጥርብናል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ይናገራሉ።
ተማሪዎቹ በኮቪድ-19 ምክንያት የተስተጓጎለውን ትምህርት ለመሸፈን ያደረጉትን ጥረት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለመዳሰስ ሞክሯል። በተጨማሪም አሁን ካነሷቸው ቅሬታዎችና አስተያየቶች ጋር በተያያዘ የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ከፈተናው መጠናቀቅ በኋላ የሰጡትን መግለጫ ከተፈታኞቹ ጥያቄ ጋር በማጣጣም ለማቅረብ ተሞክሯል።
ብሩክ ኃይሉ በምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ሲሆን ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 2014 ዓ.ም የተሰጠውን የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች አንዱ ነው።
ብሩክ ኮቪድ-19 በትምህርቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳደረገበት እና አስተዋጽኦም እንዳደረገለት ይናገራል። የኮቪድ-19 መከሰት አሉታዊ ጎን የመማር ማስተማሩን ሂደት እንዳደናቀፈው፤ በይበልጥም ተማሪዎች ከመምህራን ጋር በክፍል ውስጥ የሚያደርጉትን መስተጋብር /interaction/ እንደጎዳው ይናገራል። ተማሪዎች ያልገባቸውን ጉዳይ ጠይቀው የመረዳት እድል እንዳያገኙ ማድረጉን፤ መምህሩም የተማሪዎቹን ክፍተት እያየ እገዛ የሚያደርግበትን እድል እንዳላገኘ ይገልጻል። እንደ እርሱ አባባል ኮቪድ-19 ተማሪዎች ከመማር ማስተማር አውድ እንዲወጡና ተከታታይነት ያላቸው የትምህርት ይዘቶችን በተመደበላቸው ሰዓት ተምረው ለፈተና እንዳይዘጋጁ አድርጓል። ከትምህርት ቤት መራቅ መዘናጋትን እንደሚፈጥርና ከተማሪዎች ጋር የነበረው የእርስ በእርስ ቅርርብ መቋረጡም፤ አንዱ ከሌላው የሚያገኘውን መረጃና እውቀት እንዲያጣ ያርጋል ይላል ብሩክ።
በሌላ በኩል ብሩክ በኮቪድ-19 ምክንያት ፈተናው መራዘሙ ሰፊ የጥናት ጊዜ እንዳገኝ እረድቶኛል ይላል። በክፍል ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቶች ያልተሸፈኑ የትምህርት ይዘቶችን በራሱ ጥረት የመሸፈን እድል እንደሰጠው ይገልጻል። ብሩክ መማሪያ መጽሀፉን ጨርሶ ቀደም ሲል የተሰጡ የሶስት ዓመት ፈተናዎችን የመመልከት እድል ማግኘቱን ገልጿል። በተመለከታቸው ጥያቄዎች መሰረት እራሱን እያዘጋጀ መቀመጡን የተናገረው ብሩክ፤ የዘንድሮው ፈተና ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩት ፈተናዎች ከበድ ያለ ነው ይላል። የተፈታኙ ቁጥር ከአምናው በእጥፍ መጨመሩን ተከትሎ ውስን ተማሪዎችን ለመውሰድ ታስቦ ፈተናው እንዲከብድ የተደረገ ይመስለኛል ይላል።
ብሩክ በተለይም የመጨረሻዎቹን ፈተናዎች ሲፈተን ፈተና ወጥቷል ተብሎ የተናፈሰው ወሬ የስነ ልቦና አለመረጋጋት ፈጥሮበት እንደነበር ይገልጻል። ከተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት አንጻር ችግሮችን ለማባባስ የሚፈልጉ አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ የተናገረው ብሩክ፤ ፈተና ወጥቷል የሚለው ውዥንበርም ሁከት ለመፍጠር ታስቦ የሚናፈስ ተራ ወሬ ሊሆን እንደሚችል ይገምታል። ያም ሆኖ መንግሥት በየዓመቱ የሚከሰቱትን እንዲህ አይነት ችግሮች ለማስወገድ ሌላው ዓለም የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ ሊጠቀም ይገባል ይላል።
እንደተባለው ፈተና አስቀድሞ የሚወጣ ከሆነ ለፍተው ጥረው ውጤት ለማምጣት የሚተጉ ተማሪዎችን ሞራል የሚጎዳ፤ መጪው ተማሪም ለጥናት ዝግጁ እንዳይሆን የሚያደርግ ትውልድ ገዳይ ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል።
ፈተና ይሰረቅም አይሰረቅም የሚናፈሰው ወሬ የተማሪዎችን የ12 ዓመት ድካም መና ለማስቀረት ምክንያት ስለሚሆን መንግሥት ካለፉ ልምዶች እየተማረ ፈተናውን አስተማማኝ ሊያደርግ ይገባል። በስርቆት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚጥሩ ተማሪዎች የጎበዝ ተማሪዎችን እድል ከመዝጋት ውጪ የሚያተርፉት አንዳችም ነገር አይኖርም። ምናልባት ፈተና ወጥቷል የሚባለው እውነት ከሆነም መንግሥት ሁኔታውን ተከታትሎ በአጥፊዎች ላይ ርምጃ መውሰድ እንደሚገባውና ጎበዝ ተማሪዎች የሥራቸውን ውጤት የሚያገኙበትን አማራጭ መፈለግ እንደሚገባው ተናግሯል።
ሌላው አስተያየቱን የሰጠን የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተፈታኝ ተማሪ አቤነዘር አበበ ነው። አቤነዘርም ልክ እንደ ብሩክ ሁሉ ለፈተናው የረዥም ጊዜ ዝግጅት ማድረጉን ይናገራል። ከቅርብ ዓመታት በፊት በ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተደረገው ስርቆት በተፈታኞች ላይ የስነ ልቦና ችግር እየፈጠረ መሆኑን ይናገራል። ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ እንዲህ አይነቱን ስጋት ለማስቀረት ከዓምና ጀምሮ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እጠቀማለሁ ማለቱን አስታውሶ፤ እስከ አሁን ድረስ አሠራሩ አለመቀየሩ በየዓመቱ ተማሪዎች እንዲሸበሩ አድርጓል ይላል።
ተማሪዎች አስቸጋሪውን የኮቪድ-19 ችግር ተቋቁመው ለፈተና ከበቁ በኋላ ድካማቸውን መና ለማስቀረት የሚደረገውን ስርቆት መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራል። ፈተና ከመፈተኑ በፊት በርካታ ዝግጅቶችን ሲያደርግ እንደነበር የሚገልጸው አቤኔዘር ፈተና ተሰርቆ ከሆነ ግን ድካሙ ከንቱ እንደሚሆን እና የትምህርት ስርዓቱም በየዓመቱ በሚደረጉ ስርቆቶች ችግር ውስጥ መውደቁን ይናገራል። ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን አጣርቶ አጥፊዎችን በመቅጣት ስርዓት ጠብቀው የተፈተኑ ተማሪዎችን ውጤት በተገቢው መንገድ ማሳወቅ እንዳለበት ተናግሯል።
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በርካታ ተማሪዎችን አሳልፈናል የሚል ስም ለማግኘት ሲሉ ፈተና ሊያሰሩ ይችላሉ የሚለው አቤኔዘር፤ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ አስተማሪ የሆነ ርምጃ ሊወስድ ይገባል ይላል። እንዲህ አይነቱ ተግባር የትምህርት ስርዓቱን የሚጎዳ፣ የሀገርን ገጽታ የሚያበላሽና ትውልድን የሚገድል በመሆኑ መንግሥት በእንዲህ አይነት ተግባር ላይ የተሰማሩ ተቋማትንም ሆነ ግለሰቦችን መንጥሮ በማውጣት ሊቀጣቸው ይገባል። በአንዳንድ ግድ የለሽ ግለሰብ የሚሠራ መጥፎ ተግባር የብዙ ተማሪዎችን ህይወት የሚያበላሽ፤ ከዚህ በኋላ የሚመጡ ተማሪዎችን ተግቶ የመማር ተስፋ የሚያስቆርጥ እንደሆነ አቤኔዘር ተናግሯል። የትምህርት ስርዓቱ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ የሚመለከተው አካል ስምን የሚያድስ ጠንካራ ሥራ መሥራት አለበት ይላል። የፈተና ስርቆት አጥንተው ለሚፈተኑ ተማሪዎች ሀዘን ለማይዘጋጁት ደስታ የሚፈጥር በመሆኑ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ፈተናው መሰረቁን ካረጋገጠ ውጤቱን እስከ መሰረዝ የሚያደርስ ውሳኔ ሊያስተላልፍ ይገባል ብሏል።
ከስላሴ ካቴድራል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያነጋገርነው ተማሪ አሴር ዳዊት በበኩሉ፤ ጥሩ ውጤት አምጥቶ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ጥሩ ዝግጅት ሲያደርግ እንደከረመ ተናግሯል። የአስራ አንደኛ ክፍል ትምህርትን በወቅቱ አለመሸፈናቸውን የተናገረው አሴር፤ የፈተናው ጊዜ መራዘም በስፋትና በጥልቀት ያልተማሩትን ትምህርት ለማካካስ እንደረዳው ይገልጻል። ይህ ወቅት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ገብተው የመጀመሪያውን መንፈቅ ትምህርት የሚያጋምሱበት ነው ያለው አሴር፤ የፈተናው መርሃ ግብር ከዚህ በላይ ቢራዘም ጥሩ አለመሆኑን ይገልጻል።
ፈተናው ወጥቷል የሚል ወሬ ከሰማ በኋላ ለማረጋገጥ ሲሞክር በቴሌግራም ላይ የተለቀቁ መልሶችን ማየቱን ተናግሯል። ይህም የነበረውን ተስፋ እንዳደበዘዘበት ገልጿል።
የፈተና መሰረቅ ጊዜ ያጠፋበትና የደከመበት የትምህርት ውጤት እንዲሰረዝ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረበት ተናግሯል። ከዚህ በፊት ፈተና ተሰርቆ ከሰባት መቶ መታረም የሚገባው አጠቃላይ ውጤት ከሶስት መቶ መታረሙን ያስታወሰው አሴር፤ አሁንም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይደገም ሰግቷል። እንዲህ አይነቱ አሠራር ተማሪዎች በተለያዩ ትምህርቶች የተለያየ ችሎታ ስለሚኖሯቸው በአንዱ ያጡትን ውጤት በሌላው የማካካስ እድል እንዳያገኙ ያደርጋል ብሏል።
ከፈተናው በፊት በተሰጡ መግለጫዎች የፈተናው ደህንነት ከምንግዜውም በላይ አስተማማኝ መሆኑን ሰምቶ እንደነበር የጠቀሰው አሴር፤ ሁኔታው እንደተባለው አለመሆኑ በቀጣይ የሚፈተኑ ተማሪዎችም አመኔታ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል። የ12ኛ ክፍል ፈተና የተማሪዎችን የወደፊት ህይወት የሚወስን ትልቅ ጉዳይ ነው ያለው አሴር በዚያው ልክ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላል።
የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አቶ ተፈራ ፈይሳ የፈተናውን ሂደት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ሁሉ በሰላም መጠናቀቁን ገልጸዋል። 617 ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ ተማሪዎች በ2ሺ ሰላሳ ስድስት ጣቢያዎች ላይ ፈተና ለመውሰድ መመዝገባቸውን አስታውሰዋል። ከዚህ ውስጥ ፈተና ይወስዳሉ ተብሎ የታሰበው 565 ሺ ሁለት መቶ ሃምሳ አምስት ወይም ከተመዘገበው 91 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ፈተና ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ መለየቱን ገልጸዋል። ፈተና ላይ ይቀመጣሉ ተብለው ከተለዩት ውስጥ 545 ሺ ሶስት መቶ ሰማኒያ አንድ ተማሪዎች ፈተና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ይህም ፈተና ይወስዳሉ ተብሎ ከታሰቡ ተማሪዎች 96 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት መውሰዳቸውን ያረጋግጣል ብለዋል። ሀገራችን በውስጥም በውጭም ኃይሎች እየፈተነች ባለችበት ወቅት በዚህ ደረጃ እቅድን ማሳካት መቻልና ትልቅ የሰው ኃይልና ቁሳቁስ አንቀሳቅሶ ፈተና መስጠት ስኬት ተደርጎ ይታያል ብለዋል። ይህም አመራሩ ለስራው የሰጠው ትኩረትና በየደረጃው ከፌደራል እስከ ፈተና ጣቢያ በኮማንድ ፖስት ተደራጅቶ የተሠራ በመሆኑ የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት ችግሮች ያጋጠሙ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የፈተናውን አጠቃላይ ሂደት ሊያዛቡ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሁለት ከፍለው ለማየት ሞክረዋል። የመጀመሪያው በመፈተኛ ክፍል ውስጥ የሚስተዋል ኩረጃ ነው። ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየት ርምጃ መወሰዱንና ስጋትን ማስወገድ እንደተቻለ ተናግረዋል።
ሁለተኛው ቴክኒካል ምልከታዎችና ክትትሎችን የሚጠይቅ ነው። በሶሻል ሚዲያ ተሰራጨ የተባለው የፈተና ቴክኒካል ጉዳይን የሚመለከት በመሆኑ በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲና በትምህርት ሚኒስቴር በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከሱፕር ቫይዘር፣ ከጣቢያ ኃላፊዎች፣ ከፈታኞች የሚመጡ ሪፖርተሮችን መሰረት በማድረግና ከፈተናው እርማት ክፍል የሚገኙትን ትክክለኛ መረጃዎች መሰረት አድርጎ ከተጠና በኋላ የውጤት ትንተናውና ሪፖርቱ የሚያመላክቱት ነገር እንደሚባለው ሆኖ ከተገኘ በተማሪ፣ በትምህርት ቤትና በትምህርቱ አይነት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አሠራር ነው።
በራሳቸው ጥረት የሠሩ ንጹህ ተማሪዎችን ማዕከል በማድረግ ተፈጠረ የተባለውን ችግር በኤጀንሲው በኩል ተቆጣጥሮ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል እድል መኖሩን ገልጸዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/2014