ፋሽን እና ፎቶ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ፎቶዎች በሞዴሉ ወይም የሞዴሏ ውበት ተደግፈው ፋሽንን ፍንትው አድርገው ያሳያሉ። ሞዴሎችም አካላዊ ውበታቸውን ተንተርሰው ፋሽንን ያስተዋውቃሉ። የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት፤ ከፎቶ አንጻር ሞዴሎች አራት አይነት የፋሽን ፎቶዎችን ይነሳሉ።
የመጀመሪያው ካታሎግ ፎቶግራፊ ይባላል። ከአራቱ ፎቶ አይነቶች ቀላሉ ነው ሊባል ይችላል። አላማው በተለይ ልብስን ማስተዋወቅ እና ማሻሻጥ ሲሆን የፎቶግራፈሩ ትኩረትም ከሞዴሉ ወይም ሞዴሏ ይልቅ ልብሱ ላይ ነው።
የሞዴሎቹ ፎቶ አነሳስም ሳይሆን ልብሱን ማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ነው። ሁለተኛው የፎቶግራፍ አይነት ሀይ ፋሽን ፎቶግራፊ ይባላል። ይሄ ደግሞ ታዋቂ ሞዴሎች የተጋነነ ልብስ ለብሰው እና ጸጉራቸውን አስውበው የሚነሱት ፎቶ ነው። ብዙ ጊዜ በመጽሄት የፊት ገጽ ላይ የሚታተም ነው።
ሶስተኛው ስትሪት ፋሽን ፎቶግራፊ ይባላል። የሁለተኛው ተቃራኒ ነው ማለት ይቻላል። ሰዎች የአዘቦት ልብስ ለብሰው የሚነሱት እና ብዙም የተጋነነ ነገር የሌለው የፎቶግራፍ አይነት ነው። አራተኛው ኤዲቶሪያል ፋሽን ፎቶግራፊ የሚባል ነው። ይህ ደግሞ ለመጽሄቶች ጥቅም ላይ የሚውል እና አንድ ታሪክን ለመተረክ የሚነሳ ነው። አብሮትም ጽሁፍ ይኖራል።
የፋሽን ፎቶግራፍ አይነቶቹ በዚህ መልኩ በአራት ዋነኛ ክፍሎች ሲከፈሉ ፋሽኑን የሚያስተዋውቁት ሞዴሎች ደግሞ ከ10 በላይ በሚቆጠሩ ዘርፎች ይከፋፈላሉ። ከነዚህ መካከል ኮመርሻል ሜዴሊንግ ፤ ፊትነስ ሞዴሊንግ ተጠቃሽ ናቸው።
የኛን ሀገር በተመለከተ ከላይ ከጠቀስናቸው የፋሽን ፎቶግራፍ አይነቶች በብዛት የተለመደው ካታሎግ ፎቶግራፊ ይመስላል። የሌጋሲ ሞዴሊንግ አካዳሚ ኤጀንሲ ባለቤት እና ዋና ዳይሬክተር የሆነው ሞዴል ልደቱ ብርሀኑም ተመሳሳይ አስተያየት ይሰጣል።
“ብዙውን ጊዜ እኛ ሀገር የፋሽን ፎቶግራፊ የሚካሄደው አልባሳትን ለማስተዋወቅ ነው” ይላል። ይህ ደግሞ ሌሎች የፋሽን ፎቶግራፊ ዘርፎች ትኩረት እንዳያገኙ አድርጓል። ይሁንና ካታሎግ ፎቶግራፊ እና ኮመርሻል ሞዴሊንግ በብዛት ጥቅም ላይ ይዋሉ እንጂ በሌላ በኩል ሌሎቹም የፋሽን ፎቶግራፊ አይነቶች ጤነኛ ባልሆነ መልኩ እየተስፋፉ ይመስላል።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚታዩ የአንዳንድ የሴት ኢትዮጵያውያን የፋሽን እና ሞዴሊንግ ፎቶግራፎች ጤነኛ አይመስሉም። ያለ ምንም አላማ እንዲሁ በጣም በተራቆተ ሁኔታ ፎቶ ተነስተው የሚለጥፉ ወጣት ሴቶች ተበራክተዋል። ብዙዎቹም ሞዴል እንደሆኑ ይናገራሉ።
ነገሩ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የተደበላለቀ ስሜት የፈጠረ ሆኗል። ይህ ሁኔታ በእርግጥ ከፋሽን ፎቶግራፊም ሆነ ከሞዴሊንግ ጋር የሚገናኝ እና ሙያው የሚጠይቀው ነው ወይ የሚለውን ሞዴል ልደቱን ጠየቅነው። “በሌሎች ሀገራት ምርቶችን ለማስተዋወቅ ተመሳሳይ ፎቶዎች ይነሳሉ። ለምሳሌ ፓንት ለማስተዋወቅ ፓንት አድርገው ፎቶ ሊነሱ ይችላሉ። ጡት ማስያዣ ለማስተዋወቅ ጡት ማስያዣ አድርገው ሊነሱ ይችላሉ። የእኛ ከዚያ ጋ ይያያዝ አይያያዝ አላውቅም። ነገር ግን አንዳንዶች በአቋራጭ ዝናን ለማግኘት መሰል የተራቆቱ ፎቶዎችን እንደሚነሱ እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንደሚለቁ እገምታለሁ” ይላል።
በእርግጥም አንዳንዶቹ የተራቆቱ ፎቶዎች ሲታዩ ከፋሽን እና ሞዴሊንግ ጋር ምን እንደሚያገናኛቸው ለማወቅ ያዳግታል። ተነሺዎቹ ምን አይነት ምርት ማስተዋወቅ እንደፈለጉ ወይም ምን አይነት መልእክት ማስተላለፍ እንደፈለጉም አይታወቅም። ምናልባትም ሞዴል ልደቱ እንደሚለው አንዳንዶች ራሳቸውን የማህበራዊ ሚዲያው መወያያ ነጥብ ለማድረግ የተነሷቸው ይመስላሉ።
በሌላ መልኩ ሁሉም የፋሽን ፎቶግራፊ ምርትን ለማስተዋወቅ ብቻ እንደማይውል እና አንዳንዴም ሞዴሎች ተሰጥኦቸውን ለማሳየት እንደሚነሱ ሞዴል ልደቱ ይናገራል። ”በሌላው አለም ሞዴሎች አዳዲስ የፎቶ አነሳስ ስልት (ፖዝ)እንዳላቸው ለማሳየት ወይም የራሳቸውን የሞዴሊንግ አቅም ለማሳየት ፎቶዎችን ይነሳሉ” ሲል ያብራራል።
ይህ ምናልባት አሁን እኛ እያነሳን ካለነው ጉዳይ ጋር ሊቀራረብ ይችላል። ምናልባት ሞዴሎቹ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ የዘየዱት መላ ሊሆን ይችላል። እንዲያም ሆኖ ግን ይህ አይነቱ አካሄድ ሙያዊ አካሄድ አይመስልም። ዘርፉን ኢንደስትሪ ለማድረግ ለሚያቅድ አካል ይህ አይነት ግላዊ አካሄድ በጎ የሚባል አይደለም።
በሌሎች ሀገራት ሞዴሎችን የሚያዘጋጁ እና ፕሮፋይላቸውን የሚመዘግቡ እንዲሁም ስራውን የሚያገናኙ ኤጀንሲዎች የሉም ያሉት ደላሎች ናቸው። እነዚህ ደላሎች ደግሞ ሙያው በስርአት መመራት ከጀመረ ከገበያ ስለሚወጡ መሰል ቅጥ ያጡ አካሄዶችን ያበረታታሉ።
በኢትዮጵያ የመጀመሪው የሞዴሊንግ ኤጀንሲ ከፍቻለሁ የሚለው ሞዴል ልደቱ፣ መሰል አቋራጭ መንገዶች አደገኛ መሆናቸውን ይጠቅሳል። መሰል እንቅስቃሴዎች ሞዴሎችን፤ ፎቶግራፈሮችን ፤ ሜካፕ አርቲስቶችን ፤ ዲዛይነሮችን እና መሰል ባለሙያዎችን አስተባብሮ በሚይዝ ኤጀንሲ በኩል ካልተመሩ ዘርፉ ለማደግ ይቸግረዋል ሲል ያብራራል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁሉም የፋሽን ፎቶግራፎች በምእራባውያን አለባበስ ብቻ መነሳታቸው ሌላኛው ግራ አጋቢ ነገር ነው። ስለዚህ የጠየቅነው ሞዴል ልደቱ ይህም ስህተት እንደሆነ ይናገራል። በሀገር ውስጥ አልባሳት መነሳት እንደሚቻልም ተናግሯል። በእሱ የሞዴሊንግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከሚማሯቸው ትምህርቶች መሀከል አንዱ ቱሪዝም እንዲሆን ማድረጉን የሚናገረው ሞዴል ልደቱ፣ በቅርቡም ተማሪዎች አንድ ብሄር ወስደው ስለዚያ ብሄር አለባበስ ጥናት አድርገው እንዲመጡ እና በዚያ ብሄር ልብስ ፎቶ እንዲነሱ ማድረጉን ይገልጻል።
የኢትዮጵያ አልባሳት ለፋሽን ፎቶ የሚመጥኑ ናቸው። ሞዴል ለመባልም መራቆት አያስፈልግም። አሁን የሚታየው ነገር የሚያመለክተው ዘርፉ መሪ እና ባለቤት ስለሌለው ያለ ቀያሽ እንዲሁ ከሙያው ስነ ምግባር ውጭ በሆነ መንገድ እየነጎደ እንደሆነ ነው። ይህ አይነት አካሄድ ደግሞ ዘርፉ ወደ ኢንዱስትሪ ለማደግ እንደሚቸገር አመላካች ነው።
በፋሽን ፎቶግራፊው ውስጥ የምናየው የአደረጃጀት ስብራትን ነው። ይህን ስብራት ባለሙያዎች ሊወያዩብት እና ስር ሳይሰድ ሊያርሙት ይገባል። አልያም ሰንብቶም ቢሆን የፋሽን እና ሞዴሊንግ ዘርፉን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ማህበራዊ ስርአቶችንም ሊገዳደር ይችላል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/2014