ያለፈው ዓመት ይህ ሳምንት ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ለኢትዮጵያ አሳዛኝ ቀን ነበር። በሩዋንዳ ተከሰተ ሲባል የምንሰማው የዘር ጭፍጨፋ እዚሁ አገራችን ላይ በተደራጀ ሁኔታ የተፈጸመበት ቀን።
ሳምሪ በተባለ የጭፍጨፋ ቡድንና በወቅቱ የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው አካል ታጣቂዎች ጭምር የተሳተፉበት ይህ ጭፍጨፋ፤ የአማራ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን ኢላማ ያደረገ ነው። በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ 48 ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሺ በላይ ንጹኃን ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል።
በጩቤ የተወጉ ፤ በካራ የተቀሉ ፤ በገጀራ የተጨፈጨፉ ፤ በጥይት የተደበደቡ በርካታ ዜጎች አስከሬናቸው ለቀናት በየመንገዱ ፤ በየጢሻው ፤ በየማሳው በየጉድባው ወድቆ የተገኘበት ወቅት ነበር። በርካታ የጅምላ መቃብሮችም ተገኝተዋል። የብዙሃኑን አስከሬን ለማግኘት ቀናትን የፈጀ አሰሳ ተደርጓል።
ታሪኩ እንዲህ ነው። ሕወሓት ጥቅምት 24 የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝን አጥቅቶ ታሪካዊ ነውር ፈጸመ፤ የሰሜን እዝን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ካደ። ይህን ተከትሎም መንግሥት ፈጣን ምላሽ ሰጠ።
የአገር መከላከያ ሠራዊትን እርምጃ መሸከም ያልቻሉት ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው ሲሉ የነበሩት የከሃዲው ሕወሓት ጀሌዎች ወደኋላ መፈርጠጥ ጀመሩ። ወደኋላ ሲሮጡ ግን እንዲሁ በባዶው ሊሸሹ አልፈለጉም። ይልቁንም ደግመው እንደማይመለሱባት ያረጋገጧትን የምእራብ ኢትዮጵያዋን የማይካድራ ምድር በደም አጥበው አጨማልቀዋት ለመሄድ ወሰኑ። ለዚህም ሲያደርጉ በሰነበቱት ዝግጅት መሰረት የሳሉትን ካራ እና ገጀራ ፤ የታጠቁትን ሽጉጥ እና ጠመንጃ ሊጠቀሙበት ቆረጡ።
በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የሕውሓት ጦር ሽንፈት ደርሶበት ከአካባቢው ሲወጣ በተለይ በንጹኃን የአማራ ተወላጆች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ መሆኑን የዐይን እማኞችን ጠቅሶ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በወቅቱ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ጥቃቱን አስመልክተው በወቅቱ እንዳወጧቸው መረጃዎች፤ ጅምላ ጭፍጨፋው ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ በማለዳ የአካባቢው ፖሊሶች በማይካድራ ከተማ በተወሰኑ መንደሮች ቤት ለቤት እየዞሩ በሥፍራው የሚኖሩትን መለየት ጀመሩ። በተለይም ከተለያዩ አካባቢዎች በጉልበት ሥራ በአካባቢው የተሰማሩትን ሠራተኞች መታወቂያ ካርዳቸውን በማየት ትግሬ ያልሆኑትን አጣርተዋል፤ ቢያንስ 60 ከሚደርሱ ሰዎች ላይም የሱዳን ሲም ካርዳቸውን ከኪስ ስልካቸው በዘመቻ መልክ ወሰዱ።
ሲምካርዱ የተወሰደው ነዋሪዎች ጥቃቱ ሲፈጸምባቸው ለእርዳታ ጥሪ እንዳይደውሉ ለመከላከልና ወይም ከሌሎች ጋር ግንኙነት እንዳያደርጉ ለመገደብ ታስቦ መሆኑን ሌሎች መረጃዎች ይጠቁማሉ። ቀድሞ መንግሥት የመረጃ መረቡንና የኪስ ስልክ አገልግሎቱን በክልሉ እንዲዘጋ አድርጎ ስለነበር የኢትዮጵያ ሲም ካርድ በክልሉ አገልግሎቱን አቁሞ ነበር።
የጭፍጨፋው ፈጻሚዎች የትግራይ ተወላጆች በዚያን እለት ከአካባቢው ዞር እንዲሉ አሳስበዋቸዋል። አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች (ሴቶችና ወጣቶች) ጭፍጨፋው ከመድረሱ በፊት፤ ጥቃቱ ለተደገሰላቸው ሰዎች ሹልክ ብለው አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ መምከራቸውንም አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማይካድራን ጅምላ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ያካሄደውን ጥናት ዋልታ ቴሌቪዥን ጠቅሶ ሰሞኑን እንደዘገበው፤ ጥቃቱ ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ የትግራይ ተወላጆች ከአካባቢው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። የአሸባሪው ቡድን ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እስከ ህዳር አንድ ድረስ አማሮችን ለይቶ በማይካድራ ጭፍጨፋ አካሂዷል።
የማይካድራውን ጭፍጨፋ የፈጸሙት ለዚህ ዓላማ የተመለመሉ እና የተዘጋጁ «ሳምሪ» እየተባሉ የሚጠሩ የወጣት ስብስቦች ለሕውሓት ታማኝ የሆኑ አካላት ናቸው። ንጹኃኑ ተጨፍጭፈው በየመንገዱ የተጣሉት ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት ሲሆን፣ በዕለቱ በተፈጸመው ጭፍጨፋም ከ አንድ ሺ 500 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመገደላቸው በተለያዩ ወገኖች በወቅቱ ተጠቁሟል።
የጎንደር የዩኒቨርሲቲ የማይካድራ የዘር ጭፍጨፋ አጥኚ ቡድን በበኩሉ ባካሄደው ጥናት እንዳመለከተው፤ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በፈጸመው ጅምላ የዘር ጭፍጨፋ አንድ ሺ 644 ሰዎች ሰለባ ሆነዋል። ከእነዚህ የአማራ ተወላጆች መካከልም አንድ ሺ 563 በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን አጥተዋል። 81 ሰዎች ደግሞ ለእድሜ ልክ አካል ጉዳት እና ለስነ ልቦና ቀውስ ተጋልጠዋል።
ጅምላ ጥቃቱ ሲጀመር በልዩ ሁኔታ የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት ልዩ ስሙ ‹‹ግንብ ሠፈር›› በሚባለው መንደር እስከ ወልቃይት ቦሌ ሠፈር ድረስ የሚገኙ ወገኖችን፣ ግፍና ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መጨፍጨፋቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያሳያል። ጅምላ ጭፍጨፋውን ዩኒቨርሲቲው የዘር ማጥፋት ሲል ገልጾታል። በማይካድራ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ወንጀል ፈጻሚዎች በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ክስ ሊመሰረትባቸው የሚችሉ ተጨባጭ የምርመራ ሰነዶችን ቡድኑ በሚገባ ማደራጀቱንም መረጃዎች ያሳያሉ።
የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አንዳንድ መገናኛ በዙሃን ደግሞ ይህን አሀዝ ከ600 በላይ እያሉ በወቅቱ ሲገልጹት ነበር። በቅርቡ የወጣው የተመድ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ ሪፖርት ደግሞ ይህን አሀዝ 200 ሲል ገልጾታል።
መረጃዎቹ እንዳመለከቱት፤ በጥቃቱ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ የጉልበት ሰራተኞች በጭፍጨፋው ሰለባ ተደርገዋል፤ ከአንድ ቤት ከሦስት እስከ ስድስት ሰዎች በግፍ የተጨፈጨፉበት ሁኔታ ታይቷል። በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ማጥቃትም መከላከልም የማይችሉ እናቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያንና አሮጊቶች ጭምር የዚህ ጭፍጨፋ ሰለባ ሆነዋል። ነፍሰጡሮች እና እመጫቶችም ተጨፍጭፈዋል ፤በጅምላ ጥቃቱ አስገድዶ መድፈርም ተፈጽሟል።
ሰለባዎቹ ንጹሃን የቀን ሠራተኞች እንጂ ካለው የጦር ግጭት ጋር በቀጥታ የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት ተሳትፎ ያሌላቸው ስለመሆናቸው በወቅቱ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር የወጣው መረጃ ያስረዳል። ከዐይን እማኞች የሰበሰበውን መረጃ ጠቅሶ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳስታወቀው፤ ንጹሃን ሰዎች በስለታማ ነገሮች ተወግተው ነው የተገደሉት። ይህንንም በወቅቱ ተቋሙ በገለልተኛ ምርመራ ማረጋገጡን ይፋ አድርጎ ነበር።
ጭፍጨፋውን ተከትሎ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ሱዳን ሸሽተው የገቡ ስለመሆናቸው በወቅቱ ዋሽንግተን ፖስት ያወጣው ዘገባና ሌሎች መረጃዎችም ያመለክታሉ። ወደ ሱዳን የተሰደዱት ጭፍጨፋውን ያመለጡት ብቻ አይደሉም። ከስደተኞቹ አብዛኞቹ ጭፍጨፋውን የፈጸመው የሳምሪ ቡድንና ሌሎች በጭፍጨፋው የተሳተፉ የአስተዳደር አካላትና ታጣቂዎች መሆናቸው ይገለጻል።
በአጠቃላይ የማካድራ ካድሬዎች ማለትም ሳምሪዎችና የአካባቢው አስተዳደር ካራና ጩቤ ጨብጠው ዕድሜን፣ ጾታን፣ ሀብትን እምነትን ሳይለዩ አማራ ናቸው ያሏቸውን የቻሉትን ያህል መጨፍጨፋቸው ነው የተጠቆመው።
የማይካድራው ጅምላ ጭፍጨፋ በመጥረቢያ እና ካራ ጩቤና ገጀራ በመሳሰሉት ስለታማ መሳሪያዎች እና ነዳጅ (ጋዝ) ጭምር ነው የተፈጸመው ። እንዲሁም ቦንብ እና ክላሽንኮቭ ነዳጅ (ጋዝ) ሌሎች መሣሪያዎች ገንዘብና አስካሪ መጠጥ ሳምሪ ለተባለው የጥፋት ቡድን ቀደም ብሎ እንዲደርሰው መደረጉን በወቅቱ በመገናኛ ብዙሃን የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ ሆን ተብሎ ሌሎች የሞት ድግስ የተደገሰላቸው ተጋባዦች እንዳይሰሙ እና እንዳይሸሹ ታስቦ የተደረገ ነው። ጥቃቱን ሰምተው በመሸሽ ለማምለጥ የሞከሩ ሰዎችም በጥይት እየተለቀሙ እንዲገደሉ መደረጉን መረጃዎቹ ያስረዳሉ።
ከጭፍጨፋው የተረፉ ተጎጂዎች እንደተናገሩት ደግሞ፤ በማይካድራ አማራዎች ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ባለሀብቶችም ድጋፍ ታክሎበታል። ለጭፍጨፋው የሚውሉ የጦር መሣሪያዎችም ሆነ ስለታማ መሣሪያዎች እንዲሁም ለገዳይ ወጣቶች የአልኮል መጠጥና ገንዘብ እንዲሁም የሬሳ ማመላለሻ ጭነት መኪናና ትራክተር ባለሀብቶች ማቅረባቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያስረዳል።
ጭፍጨፋውን አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትየጵያ ሰብአዊ መብት ጉባዔ በወቅቱ ባካሄዷቸው ምርመራዎች አረጋግጠዋል። በጅምላ ጭፍጨፋው የተፈጸመውን ጭፍጨፋ እና ጉዳት የሮይተርስ ዜና ወኪል ፣ ፋይናንሺያል ታይምስ፣ አሶሺየትድ፣ ፕሬስ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ማለትም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንዲሁም አፍሪካን ኒውስ እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው ሰፊ ሽፋን የሰጡትና በመላ ዓለም የተደመጠ ነው።
የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች የፈጸሙትን ወንጀል ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ፣ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን ጭምር ለማጋለጥ ዓለም አቀፍ መድረኮችን ለመጥራት ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማይካድራ የዘር ጭፍጨፋ አጥኚ ቡድን አስታውቋል።
ጭፍጨፋው በተፈጸመበት አካባቢ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን መረጃ የጅምላ ጭፍጨፋው በሲቪል ሰዎች ላይ በቀጥታ ታልሞ የተፈጸመ ስልታዊ ጥቃት ሲል ገልጾት ነበር። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባዔ የጭፍጨፋው አብዛኛው ተጠቂዎች አማሮች ነበሩ ሲሉ ያስረዳሉ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጭፍጨፋውን የዘር ማጥፋት ማለቱ ይታወቃል። በቅርቡ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጣምራ ያካሄዱት ጥናትና ምርመራ ውጤት ከዓለም አቀፍ ሕግ ማዕቀፍ አንፃር በታጣቂዎቹ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንጂ የዘር ማጥፋት እንዳልሆነም አስታውቋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኅዳር 1 ቀን ለወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት መረጃ ይህንኑ ነው ያረጋገጡት።
የትህነግ አመራሮች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጭፍጨፋውን ማን እንደፈጸመው መጣራት እንዳለበት ሲገልጹ ቢቆዩም፣ ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ሪፖርት በማይካድራው ጭፍጨፋ ትሕነግ ያሰማራው ሳምሪ የተሰኘው ገዳይ ቡድንና የሕወሓት ልዩ ኃይል ፣ፖሊስ፣ ሚሊሻ እንዲሁም የአስተዳደር አካላት መሳተፋቸውን አረጋግጧል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/2014