በአሁኑ ሰዓት ሁሉ ነገራችን ፈተና ውስጥ ነው። በመሆኑም ነው “የህልውና ዘመቻ” ጥሪ አስፈልጎ ዜጎች ምላሽ እየሰጡ የሚገኙት።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ አሁን በገጠመን ችግር ምክንያት ብቻም ሳይሆን፣ ኮቪድ-19ኝን ጨምሮ፣ በበርካታ ምክንያቶች የመማር-ማስተማር ሂደቱ ሲደነቃቀፍ ቆይቷል። ችግሩ እስከ ብሔራዊ ፈተና መሰረቅ ድረስ ዘልቆ መስተጓጎልን አስከትሎ እንደነበርም የሚታወስ ነው። ይህ ሁሉ መንገራገጭ የተማሪዎችን ጊዜ (እድሜ) ከመብላቱም በላይ ለስነ ልቦና ችግር ሁሉ ዳርጓቸው ተመልክተናል።
ድምፃዊው “ያሁኑ ይባስ . . .” እንዳለው፣ የአሁኑ ግን ከሁሉም የከፋ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይማሩ ከማድረግ አልፎ በሠላም እንዳይኖሩ ሁሉ በማድረግ የመኖር ህልውናቸውን ለአደጋ ዳርጎታል፤ አንዳንድ የሽብርተኛው የሽብር ተግባራት የበረታባቸው አካባቢዎች ሕይወታቸውን እስከ ማጣት ድረስ ነው የችግሩ ስፋትና የህልውና ስጋቱ የተራመደው። ይህ ደግሞ እድሜው ከድህረ 1983 ዓ.ም ጀምሮ ሲቆጠር በሠላም ገብቶ በሠላም የወጣበትን የትምህርት ዘመን ለማግኘት ያስቸግራል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአሁኑ የነፃነት ታጋይ (ተመልሶ) በይፋ ወደ ሽብር ተግባሩ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርት ስርዓቱ መስተጓጎል የገጠመው ሲሆን ከአሁኑ ጋር ያለው ልዩነት የአሁኑ ድንበሩን እያሰፋና ትምህርት የማይሰጥባቸው አካባቢዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዳቸው ነው።
ይህ ሁኔታ በበርካታ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለ ቢሆንም በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች የችግሩ ስፋትና የተፅዕኖው ደረጃ ከፍ ያለ ሲሆን፤ አማራ ክልልን የመሳሰሉት ችግሩ ጎልቶ የሚታይባቸው አካባቢዎች ናቸው።
በቅርቡ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት “በአማራ ክልል የሚገኙ አንድ ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች፤ በ2014 የትምህርት ዘመን ትምህርታቸውን መከታተል እንደማይችሉ” ታውቋል።
እንደ ትምህርት ቢሮው ሃላፊ መግለጫ “ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን የተገደዱት፤ በአማራ ክልል ባለው ውጊያ በርካታ ትምህርት ቤቶች በመውደማቸው ምክንያት” ሲሆን፤ ለዚህም ‘ወራሪዎች’ ሲሉ የጠሯቸውን የትህነግ አማጽያንን ተጠያቂ አድርገዋል።
እንደ ዶ/ር ይልቃል ማብራሪያ የሽብር ቡድኑ “የትምህርት ተቋማትን እየዘረፈ እና እያወደመ ነው”፤ ለዚህም በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር ቆይተው በተለቀቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳትም በማስረጃነት አስደግፈው ጠቅሰዋል።
እስከ ሴፕቴምበር 16/2021 ድረስ ብቻ ከተጠናቀረው መረጃ መረዳት እንደሚቻለው “በአማጽያኑ ቁጥጥር ስር በነበሩ አካባቢዎች የሚገኙ 268 ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት” ደርሶባቸዋል። “ከአንድ ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በከፊል” ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የጉዳቱ መጠን መረጃው እስከ ተጠናቀረበት ወቅት ብቻ ያለውን እንኳን ብንመለከት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ ደግሞ ጉዳቱ አሁን ብቻ ሳይሆን እስከ ተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል ይገመታል።
ምንም እንኳን “የትምህርት ሚኒስቴር በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን [በመደበኛነት ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ] የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ” ቢታወቅም “ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን ግን ከወጪ ጋር በተያያዘ “ብዙ ፈተና ያጋጥመናል ብለን እናስባለን” የሚለው የትምህርት ቢሮ ሃላፊው ስጋት ይህንኑ የችግሩን ስፋትና የመማር-ማስተማሩ ሂደት ያጋጠመውን ፈተናና የገባበትን ቅርቃር በግልፅ የሚያሳይ ነው።
እዚህ ላይ ምንም እንኳን በአማራ ክልል የመማር-ማስተማሩ ሂደት ከፍተኛ አደጋ እንዳጋጠመው እንግለፅ እንጂ ትሕነግ እራሱ በፈጠረው ችግር የራሱን ክልል የመማር-ማስተማር ሂደትም ፈተና ውስጥ እንደከተተው መረዳት አያቅትም።
በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ትምህርት ቆሟል። በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ወደ ሌሎች አንፃራዊ ሰላም አላቸው ወደሚባሉና ሌሎች ክልሎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሄደው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው። እነዚህም እድለኛ ሆነው የጥናት መስካቸው የተገጣጠመላቸው ሲሆኑ፤ ሌሎች ወደየቤታቸው ተመልሰው ተቀምጠዋል።
ይህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የተደረገ ሲሆን፤ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በጦርነቱ ምክንያት ስለ ተዘጉ ከዛ የመጡት ተማሪዎች በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተደልድለው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። የአሸባሪው የሽብር ተግባር ችግሩ ያልነካው የትምህርት እርከን የለም እያልን ነው።
ለማሳያ ያህል እነዚህ ሁለቱን አነሳን እንጂ በአሁኑ ሰዓት የመማር-ማስተማሩ ሂደት የትምህርት ስርዓቱን እስከ ማዛባት ድረስ ሊዘልቅ የሚችል የጥፋት አድማሱን እያሰፋ ሲሆን ይህም አገር አቀፋዊ ሊሆን እንደሚችል የብዙዎች ስጋት ሆኗል።
ችግሩን ለመቋቋም ይቻል ዘንድ እንደ መፍትሄ የተወሰዱ የተለያዩ አማራጮች ያሉ ሲሆን፤ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ተማሪዎች በሌሎች የተሻለ ሰላም ወዳላቸው አጎራባች ትምህርት ቤቶች ሄደው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረጉ አንዱና ቀዳሚው ነበር። በአማራ ክልልም የተደረገው ይኸው ነው።
ዶ/ር ይልቃል እንደሚሉት ይህ ቢደረግም “ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተማሪዎች ወላጆች ሃብት ንብረታቸውን አጥተዋል”፤ ይህ ደግሞ በራሱ ተማሪዎቹ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ሄደው ለመማር እንዳይችሉ አድርጓቸዋልና በሽብር ቡድኑ የተፈፀመው ተግባር መጠነ ሰፊ ከመሆኑም በላይ ትውልድን የማጥፋት ባህርይንም የተላበሰ ነው።
“ትምህርት ቤቶቹ ቢኖሩ እንኳን ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት የሚያስችል አቅም የላቸውም” የሚሉት የቢሮው ሃላፊ በጦርነቱ ምክንያት የምግብ እጥረት መከሰቱንም “የምግብ እጥረት ባለበት ሁኔታ ተማሪዎች ለመማር ይቸገራሉ” በማለት ያስረዳሉ።
“ጦርነቱ ራሱ በተማሪዎች ላይ የሚያስከትለው የስነ ልቦና ጫና፤ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመለሱ ሊያደርግ ይችላል” በማለት ስጋታቸውን የሚገልፁት ዶ/ር ይልቃል ይህን መሰሉ ችግር “ባለፈው ሰኞ መስከረም 3 በክልሉ በተጀመረው የአዲሱ የትምህርት ዘመን ምዝገባ ወቅት መስተዋሉን”ም አስረድተዋል። “በዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በሰሜን ጎንደር በርካታ ወረዳዎች እና ደቡብ ወሎ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በከፊል የተማሪዎች ምዝገባ እንቅስቃሴ” እንዳልነበረም ጭምር ተገልጿል።
ኃላፊው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እስከ ሰጡበት ሴፕቴምበር 16/2021 ድረስ ብቻ “በትግራይ አማጽያን ቁጥጥር ስር ባሉ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የሚያስተናግዱ፤ 2ሺህ 900 ገደማ ትምህርት ቤቶች “ እንደነበሩ የታወቀ ሲሆን ይህ ፅሁፍ እስከወጣበት የዛሬው እለት ድረስ (የግጭት ቀጣናው እየሰፋ ከመምጣቱ አኳያ) ይህ ቁጥር የት ድረስ ከፍ ብሎ እንደሆነ መገመት አያስቸግርምና የትምህርት ዘርፉ የገጠመውን ፈተናና የገባበትን ቅርቃር መገመት አያቅትም።
በክልሉ እንደ አፋጣኝ መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደ ርምጃ ያለ ሲሆን እሱም “በሽብርተኛው ቡድን ወረራ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ተማሪዎች በሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ፤ [….] ማንኛውም ትምህርት ቤት የተለያዩ ምክንያቶችን (የክፍል ጥበት አለብኝ፣ መምህር የለኝም ወዘተ) በመደርደር ተፈናቃይ ተማሪዎችን አለመቀበል ፈፅሞ ተቀባይነት” የሌለው መሆኑ፤ በመሆኑንም የዞን አመራር፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት አመራር እና የት/ቤት ርዕሰ መምህራን በጋራ ተመካክረው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ [….]”፤ እንዲሁም “ማንኛውም ት/ቤት ተፈናቅለው የመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ ሀገራዊም ሆነ የዜግነት ግዴታ” ያለበት መሆኑን በመግለፅ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቁሉ ተማሪዎች የመማር እድል እንዲያገኙ ማድረግ ነው።
ምንም እንኳን ጉዳዩ በአገር አቀፍ ደረጃ ምን ገፅታ እንዳለውና የሽብር ቡድኑ የጥፋት መጠን የት ድረስ እንደ ዘለቀ ለማወቅ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ በመመላለስ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም፣ ከአጠቃላይ ሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ችግሩ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱን ነው። የማትሪኩሌሽን ፈተናውን አስመልክቶ ያለው ሁኔታ እስካሁን በውል ባይታወቅም፤ አዝማሚያው እንደገና ወደ 2015 ዓ.ም እንዳይንከባለል እየተሰጋ ነው። (በቅርቡ ፈተናው ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2፣ 2014 ዓ.ም እንደሚሰጥ የፈተናዎች ድርጅት ማስታወቁ ይታወሳል። ልብ እንበል፣ ይህ ተማሪዎች በ2013 ዓ.ም ይወስዱት የነበረ፤ ነገር ግን በተለያዩና ቀደም ሲል በጠቀስናቸው ችግሮች ምክንያት ሲንከባለል የመጣ ፈተና ነው።)
እርግጥ ነው፤ በአገራችን ሰላም ከጠፋ ቆየ። የግጭት ቀጣናዎቻችን እየሰፉ፤ የሠላም ቀጠናዎቻችን እየጠበቡ በመምጣት ላይ ያሉ ይመስላሉ። የዚህ ሁሉ አድራጊ ፈጣሪዎቹ ደግሞ እኛው እንጂ ሌላ አይደለም። ለዚህም ነው ሁሉም ስለ ሠላም ቢሰራ፣ ስለ ሠላም ሲል ቢዘምር፤ የሠላም ቀጥተኛ ተቃራኒ የሆነውን ጦርነት ባይመኘው ጥሩ ነው እየተባለ በአጀንዳ ሳይቀር ተቀርፆ ለውይይት ሲቀርብ የተኖረው። ምናልባት ለዚህም ይሆናል “በ2014 ዓ.ም በተመረጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በሙከራ ደረጃ የሠላም ትምህርት መሰጠት ሊጀመር መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያስታወቀው። […] በ2014 ዓ.ም በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት (ሴሚስተር) ላይ ትምህርቱ መሰጠት ይጀመራል።” (ይህ ሚኒስቴር አሁን ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ተመልሷል።) የሚል ዜና ሲሰማ (ደብረ ዘይት በተደረገ የባለ ድርሻ አካላት ምክክር ላይ) ብዙዎች የተደሰቱት። ችግሩ የአንድ ሚኒስቴር ይህን ማድረግ ሳይሆን የሁሉም በተመሳሳይ መንገድ ስለ ሠላም አለመዘመር ነው።
በ”ከፍተኛ የትምህርት ዘይቤ” ድንቅ ስራቸው ‹‹ሠው ከሙሉ የሠውነት ደረጃ የሚደርሠው በትምህርት ነው!›› የሚሉት እጓለ ገ/ዮሐንስ በትምህርት ተኪ የለሽነት እጅጉን የሚያምኑ ሲሆን፤ ለዚህም “ትምህርት፣ ትምህርት፣ አሁንም ትምህርት” በማለት በከፍተኛ አፅንኦት የገለፁት ጉዳይ ነው። ይሁንና እኝህ ኢትዮጵያዊ ምሁር እንዲህ ይበሉ እንጂ የትምህርት ጉዳይ በኢትዮጵያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ፤ በሠላምና ጦርነት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ስለ መግባቱ እዚህ ከጠቀስናቸው በላይ ማሳያዎቹ እልፍ ናቸው።
ከላይ አጣብቂኝ ውስጥ ስለመግባቱ ተነጋግረናል። የቀረን “መውጫው መንገድስ ምንድን ነው?” የሚለውን መመለስ ሲሆን፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መፍትሄው የሽብር ቡድኑን በማስወገድ በመላ አገሪቱ ሠላምን ማስፈንና ሕይወት በሠላማዊ መንገድ እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ለዚህ እውን መሆን ደግሞ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞና ፀረ ሽብር ቡድኑ እንቅስቃሴና የህልውና ዘመቻው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2014