ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ እኔና ባልደረባዬ ከሥራ እንደወጣን የእግር እንቅስቃሴ እያደረግን ወደ ቤታችን ለመሄድ በማሰብ ከአራት ኪሎ ፒያሳ፤ ከፒያሳ የቸርችል ጎዳናን ይዘን ቁልቁል ወደ ለገሀር እያዘገምን ነው፡፡
ቸርቸል ጎዳና አዲስ አበባን በማስዋብ ፕሮጀክት ከለሙ ቦታዎች አንዱ ስለነበር ማራኪ የአይን ማረፊያ ሆኗል፡፡ የስጋጃ ምንጣፍ መስሎ በተሠራው የእግረኞች መንገድ ላይ ሰዎች ደስታቸውን እያጣጣሙ ላይ ታች ይላሉ፡፡ አንዳንዶችም ለማረፊያ በተዘጋጁት ቄንጠኛ መቀመጫዎች ላይ ሆነው ያወጋሉ፡፡ እኛም የመንገዱን አዲስ ገጽታ እያደነቅን ጉዟችንን ቀጥለናል፡፡
ከአራት ኪሎ በፒያሳ አድርገን ቴዎድሮስ አደባባይ እስክንደርስ ድረስ በተለይም የትራፊክ መብራት ባለባቸው ቦታዎች ህጻናት ልጆችን ታቅፈው የሚለምኑ በርካታ ልጅ እግር እናቶችን አይተናል። በየጎዳናው ልጅ እየያዙ የሚለምኑ ሰዎች ቁጥር እየበዛ መምጣቱ የሁላችንም ትዝብት እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡
አማራጭ ከመፈለግ ይልቅ ልመናን እንደሥራ ቆጥረው ነጋ ጠባ አላፊ አግዳሚውን እየተማጸኑ የሚኖሩ እንዳሉ ሁሉ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ከችግራቸው ለመውጣት የሚታትሩም አሉ፡፡ ካለንብት ቦታ ብዙም ሳንርቅ ያየነውን ሌላ የህይወት መልክ ላስቃኛችሁ፡፡
ከቴዎድሮስ አደባባይ ወረድ ብሎ በስተግራ በኩል በቆሎ እየጠበሱ የሚሸጡ ሴቶች ተቀምጠዋል። እኛም መንገድ አንዲያካሂደን ብለን በቆሎ እሸት ልንገዛ ጎራ አልን፡፡ የእኔም የጓደኛዬም ትኩረት ህጻን ልጇን በእቅፏ ይዛ ምድጃውን እያራገበች በቆሎ የምትጠብሰው ልጅ ላይ ሆነ፡፡ እድሜዋ በሃያዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ይገመታል። ወጣቷ የልጅ እናት በእቅፏ የያዘችው ህጻን ልጅ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶት ፊቱን ንፋስ ይወለውለዋል፡፡ የአብራኳን ክፋይ በጉያዋ ሸጉጣ የተቀመጠችው እናት እጆቿ በሥራ ተጠምደዋል፡፡ ምድጃውን ያራግባሉ፤ በቆለውን ያዟዙራሉ፡፡ ለመኖር፤ ልጅን ለማሳደግ ሲባል እንዲህ አይነት ዋጋ ይከፈላል፡፡
ራሳቸውን ችለው ለመኖር ምንም አይነት ጥረት ሳያደርጉ በየጎዳናው ልጅ ታቅፈው የሚለምኑ ሰዎች ባሉባት አዲስ አበባ ከተማ እንዲህ አይነት እናትን ማየት ያጽናናል፡፡ ደግሞም መንግስት ልመናንና ሌብነትን ለማስወገድ ቆርጦ በተነሳበት በዚህ ወቅት የሰው እጅ ሳያዩ ለመኖር የሚጥሩትን ማበረታታት ካልተቻለ ከችግር መውጣት አይቻልምና ትኩረታችን አድርገነዋል፡፡
ወጣቷ የልጅ እናት ማረፊያ ቤት እንኳ የላትም። ለጊዜው ለልማት ተብሎ በፈረሰ ቤት ውስጥ ከእህቷ ጋር ትኖራለች፡፡ የራሷንና የልጇን የእለት ጉርስ ለመሸፈን እጇ ላይ ባለቻት ትንሽ ገንዘብ ከሰል ማንደጃ ገዝታ በቆሎ እየጠበሰች ለመኖር ትጥራለች። ከወጣቷ የህይወት ተሞክሮ፤ ከጥንካሬዋም ከድክመቷም እንማርበታለን በሚል የዚህ አምድ አንግዳ ልናደርጋት ወደናል፡፡
ብርቱካን ዋካልቶ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ልዩ ስሙ ዳናቶራ በሚባል የገጠር መንደር ነው፡፡ ብርቱካን ለቤተሰቦቿ ሶስተኛ ልጅ ስትሆን ሁለት ወንድሞችና አራት እህቶች አሏት። ቤተሰቦቿ ስለትምህርት ያላቸው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ በልጅነቷ ቶሎ ብላ ትምህርት ቤት የመግባት እድል አላገኘችም ነበር፡፡
እስከ አስራ ሁለት ዓመቷ ድረስ ታናናሽ እህቶቿንና ወንድሞቿን በመንከባከብ እና ለቤተሰቦቿ በመታዘዝ እንዳደገች ትናገራለች፡፡ በተለይም የማገዶ እንጨት መስበርና ውሃ መቅዳት የዘወትር ተግባሯ ነበሩ፡፡ ለትምህርት ካላት ፍላጎት የተነሳ ቤተሰቦቿን ጎትጉታ ዘግይታም ቢሆን ትምህርት ቤት ትገባለች፡፡ ቤተሰቦቿ ካለባቸው የአቅም ውሱንነት አንጻር ብርቱካን እስከ ሶስተኛ ክፍል ከተማረች በኋላ ለማቋረጥ ትገደዳለች። ቤተሰቦቿ በግብርና የሚተዳደሩና በቂ የእርሻ መሬት የሌላቸው በመሆኑ የሰባት ልጆቻቸውን ወጪ ችለው ሊያስተምሯቸው እንዳልቻሉ ብርቱካን ትናገራለች፡፡ በዚህ የተነሳ ከፊሎቹ በተለይም ሴቶቹ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሰው ቤት በሰራተኝነት ተቀጥረው እራሳቸውንም ቤተሰቦቻቸውንም እንዲደጉም ይፈረድባቸዋል፡፡
ብርቱካን ትምህርቷን አቋርጣ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቷ በፊት ለቤተሰቦቿ እየተላላከች ለአራትና አምስት ዓመታት እቤቷ አሳልፋለች፡፡ በእነዚህ ዓመታት ወላጆቿ ዳግም ወደ ትምህርት ቤት እንዲመልሷት ያላደረገችው ሙከራ አልነበረም፡፡ ግን አንዳሰበችው አልሆነላትም፡፡ ጓደኞቿ ትምህርት ቤት ውለው ሲመጡ እርሷ ቤት ተቀምጣ በመዋሏ ምክንያት ወንጀል እንደሰራ ሰው ትሸማቀቅ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ ለዚህም ቤት መቀመጡ የአዕምሮ ረፍት አልሰጣትም፡፡ ምናልባትም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እየሠራች የምትማርበት ሁኔታ ካለ እድሏን ለመሞከር ትወስናለች፡፡
ብርቱካን ልክ የአስራ ስድስት ዓመት ታዳጊ ስትሆን የትውልድ መንደሯን ትታ ወደ አዲስ አበባ ትሰደዳለች፡፡ አዲስ አበባ የመጣችው ከታላቅ እህቷ ጋር ነበር፡፡ ሁለቱም በሠራተኝነት ሰው ቤት ተቀጥረው እራሳቸውንም ቤተሰብንም ለመርዳት አስበው ነበር ከሀገራቸው የወጡት፡፡
ብርቱካን አዲስ አበባ እንደመጣች በአንድ ምግብ ቤት በእቃ አጣቢነት ተቀጥራ መስራት ትጀምራለች። በሠራችባቸው ጥቂት ዓመታትም ከሚከፈላት ገንዘብ አብላጫውን ለቤተሰቦቿ እየላከች በተለይም ወንድሞቿ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ድጋፍ ታደርግላቸው ነበር፡፡
ብርቱካን እየሠራች ለመማር ብታስብም ሁኔታዎች አላመች ይሏታል፡፡ ከጠዋት እስከማታ ያለ እረፍት የምግብ ቤቱን እቃ ታጥባለች፡፡ በሌላ በኩል ትምህርቷን ሳትቀጥል እድሜዋ እየገፋ መሄዱ አሳስቧታል፡፡ ከእርሷ ጋር ትምህርት የጀመሩ ጓደኞቿ አንዳንዶቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆነዋል፡፡ እርሷ ገና ከሶስተኛ ክፍል መጀመሯ ተስፋ አስቆርጧት የትምህርቱን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ከውስጧ አውጥታ በአንድ ልቧ ስራዋን እየሠራች መኖሯን ትያያዛለች፡፡ እንደውም የቀረበላትን የትዳር ጥያቄ ተቀብላ አግብታ ለመኖር ትወስናለች፡፡
በዚሁ መሰረት በስራ አጋጣሚ ከተዋወቀችው ጓደኛዋ ጋር አብሮ የመኖር ዓላማ ይዛ ትቀራረባለች። ጓደኛዋ በዘበኝነት እርሷም በእቃ አጣቢነት እየሰሩ ቤት ተከራይተው የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይጀምራሉ።
‹‹ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንባው ቁጢጥ›› እንዲሉ በዚህ እቅድ ላይ እያሉ ብርቱካን ታረግዛለች። ጓደኛዋ ከነገ ዛሬ ቤት ተከራይተን እንቀመጣለን እያለ ሲያዘናጋት ከርሞ መጨረሻ ላይ አቅሙ እንደማይፈቅድ ይገልጽላታል፡፡ ያም ሳያንስ አብሯት ለመኖር ቃል ገብቶ የቀረባት ጓደኛዋ ጸባዩ ይቀያየርባት ጀመር፡፡ የተለያዩ ሰበቦችን እየደረደረ ከፊቷ ይጠፋል፤ ጉዳዩን ሁሉ ለእርሷ ብቻ ይተውላታል፡፡ ይባስ ብሎ ሆዷ እየገፋ ሲመጣና የመውለጃዋ ጊዜ ሲቃረብ አካባቢውን ጥሎ ይጠፋል፡፡
ብርቱካን ሰማይ ምድሩ ይደፋባታል፡፡ በተለይም የመውለጃዋ ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ እራሷን ከሥራ አግልላ ስለነበር ቤት መከራየትም ሆነ የእለት ጉርስ ማግኘት አልቻለችም ነበር፡፡ ለትንሽ ቀናት ትሠራበት በነበረው ቤት ያሉ ጓደኞቿና አንዳንድ ሰዎች እየረዷት ተቀምጣለች፡፡
ኋላ ግን አንዲት በቅርበት የምታውቃት ቅን ሰው ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር ታገናኛታለች። በዚሁ መሠረት ስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው ማዘር ትሬዛ በጎ አድራጎት ድርጅት ነፍሰ ጡሯን ወጣት እስከተወሰነ ወር ለመርዳት ወደ ማቆያው ይወስዳታል፡፡ ብርቱካን ልጇን ወልዳ እስከ ሶስት ወር ድረስ በድርጅቱ እየተረዳች ከቆየች በኋላ ለጊዜው ስሙን የዘነጋችው ሌላ ድርጅት ወስዷት ለስምንት ወር ያህል ተንከባክቦ መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍ ካደረገላት በኋላ ይሸኛታል፡፡ ብርቱካን ከዚህ በኋላ እራሷንና ልጇን ለማኖር የሚያስችላትን ሥራ እየሠራች ለመኖር መጣር ት ጀምራለች፡፡
እዚያው ማቆያ ከተዋወቋቸው እና እንደርሷው አይነት ተመሳሳይ ታሪክ ካላቸው ሁለት የልጅ እናቶች ጋር አንዲት ትንሽ ክፍል በአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ተከራይተው መኖር ይጀምራሉ፡፡ ብርቱካን የንግድ ሥራ ሞክራ አታውቅም፡፡ ጓደኞቿ እንደካልሲ፣ ማስክ፣ የጆሮ ጌጣጌጥ የመሳሰሉ ነገሮችን እያመጡላት በመሸጥ በምታገኛት ገቢ የልጇንና የራሷን የእለት ጉርስ ችላ መኖር ትጀምራለች፡፡ ተሯሩጣ መሥራት ስለማትችል በቀን የምታገኛት ትርፍ ከእለት ወጪ የሚተርፍ አልነበረችም፡፡ በዚህ የተነሳ ከጓደኞቿ ጋር እያዋጣች የምትከፍለውን የቤት ኪራይ መክፈል ያቅታታል፡፡ ያም ሆኖ ጓደኞቿ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የቤት ኪራይ ሳትከፍል እንድትኖር በማድረግ ይደግፏት ነበር፡፡ ኋላ ግን የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሲመጣና የቤት ኪራይ ክፍያውም ሲጨምር ብርቱካንና ጓደኞቿ ፈተና ውስጥ ይገባሉ፡፡
የቤት ኪራይ መክፈል ያልቻሉት ጓደኛሞች ፒያሳ ከቴዎድሮስ አደባባይ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ጆን ኤፍ ትምህርት ቤት አካባቢ ለልማት ተብለው በፈረሱ ቤቶች ውስጥ ዘው ብለው ይገባሉ፡፡ ቤቶቹ ፈራርሰው በጅምር የቀሩ በመሆኑ እንደነገሩ በላስቲክ ጠጋግነው ይኖሩባቸዋል፡፡ ግን ፈቃድ የሰጣቸው አካል ባለመኖሩ ሁሌም በስጋት ውስጥ ናቸው። አንድ ቀን የሚመለከተው አካል ተነሱ ካላቸው መውደቂያ የላቸውም፡፡
አሁን ብርቱካን የቤት ኪራይ ባይኖርባትም እንደምንም ብላ የእለት ጉርሷን ለመሸፈን እየጣረች ነው፡፡ ማለዳ ተነስታ ልጇን በጀርባዋ አዝላ ወደ መርካቶ በመሄድ እሸት በቆሎ አንዱን በአምስት ብር ሂሳብ ገዝታ ወደ ማረፊያዋ ትመለሳለች፡፡ በቆሎ አንድ ቀን ካደረ ጣእም ስለማይኖረው ቢያንስ በቀን ከሃያ ፍሬ በላይ አትገዛም፡፡ ከመርካቶ መልስ እስከ ተወሰነ ሰዓት ድረስ ለልጇ ምግብ አዘጋጅታ ከሰጠች በኋላ ልክ ዘጠኝ ሰዓት ሲል አሁንም ልጇን አዝላ የከሰል ማንደጃዋንና በቆሎዋን በዘንቢል አንጠልጥላ ወደ ቸርችል ጎዳና ትሄዳለች፡፡
ብርቱካን በቆሎ እየጠበሱ በመሸጥ አራት ወራትን አሳልፋለች፡፡ በክረምቱ ወቅት ልጇን ዝናብ እያስመታች መጥፎ ጊዜን እንዳሳለፈች ትናገራለች፡፡ በቀን ከሃያ ራስ የማይበልጥ እሸት በቆሎ እየገዛች እስከ ሁለት ሰዓት ቆይታ ሸጣ ትገባለች፡፡ ከአንድ በቆሎ ላይ አምስት ብር ትርፍ ታገኛለች፡፡ በአጠቃላይ የከሰልና የትራንስፖርት ወጪዋን ችላ በቀን እስከ ሰባ ብር ይዛ ወደ ቤቷ ትገባለች፡፡
ብርቱኳን ከአንድ እህቷ በስተቀር ልጅ እንደወለደች ቤተሰቦቿ አለማወቃቸውን ትናገራለች። በሆነ አጋጣሚ ወደ ሀገር ቤት ሄዳ በነበረበት ሰዓት ልጇን ሰው ጋር አስቀምጣ ለመሄድ ተገድዳለች። ለዚህም እንደምክንያት የምታቀርበው ሰርታ ለመለወጥ ፈልጋ ከሀገሯ ወጥታ ሳለ እራሷን ሳትችል ልጅ በመውለዷ ቤተሰቦቿ እንዳያዝኑባት በመፍራት ነው፡፡ በዚህም ላይ የልጇ አባት አብሯት አለመኖሩ ትልቅ የሞራል ወድቀትም፤ ሀፍረትም ፈጥሮባታል፡፡
ብርቱካን በቆሎ እሸት ሲጠፋ ምን ሰርታ መኖር እንዳለባት ከአሁኑ ሀሳብ ገብቷታል፡፡ በመስተንግዶም ይሁን በቤት ሠራተኝነት ሰው ቤት ተቀጥራ መሥራት ብታስብም ከልጅ ጋር የሚመቻት አይደለም፡፡ አሠሪዎችም ልጅ ያላትን ሠራተኛ አይፈልጉም፡፡
ለእንደዚህ አይነት ህይወት የዳረጋት የቤተሰቦቿ መጥኖ አለመውለድ መሆኑን ባሰበች ጊዜ ይሰማታል። በትውልድ አካባቢዋ ለተለያዩ ችግሮች የተዳረጉ በርካታ ልጆች እንዳሉ የምትናገረው ብርቱካን ወላጆች የማሳደግ አቅም ሳይኖራቸው ልጅ ባይወልዱ እንደሚሻል ትናገራለች፡፡ ከእንዲህ አይነት ቤተሰብ የወጡ ልጆችም ከመለመንና የሰው እጅ ከማየት ሠርተው ለመኖር እንዲጥሩ ትመክራለች፡፡ ብርቱካን ዛሬም ድረስ የልጇ አባት ጠይቋት እንደማያውቅና የት እንዳለም እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡
በደንብ ማንነቱን ሳታውቅ የቀረበችው ጓደኛ በችግር ላይ ሌላ ችግር ስላመጣባት አዝናለች፤ በራሷም ስህተት ተጸጽታለች፡፡ ለዛሬ ከብርቱካን ጠንካራና ደካማ ጎን ያገኘነውን ትምህርት ይዘን እንሰናበት፡፡ ሳምንት በሌላ ባለታሪክ እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014