አፍሪካዊቷን ግዙፍ አገር ሱዳን እ.ኤ.አ ከ1989 አንስቶ ለሶስት አሥርት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያስተዳደሩት ኦማር ሃሰን አልበሽር ከሁለት ዓመት በፊት ከስልጣን ከተወገዱ ማግስት አንስቶ አገሪቱ የሰላም አየር መተንፈስ አልሆነላትም::
በተለይ የሽግግር መንግሥቱን በጋራ በሚመሩት ወታደራዊ እና የሲቪል ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች ‹‹አደገኛ›› የተባለ ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትለዋል::በተለይ ባለፈው መስከረም ወር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግሥት መሞከር ነገሮችን ከድጡ ወደ ማጡ አስተላልፏቸዋል:: ክስተቱም የሽግግር አስተዳደሩን በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት አባላት መካከል ከፍተኛ ውጥረትን አንግሶ ቆይቷል::
ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ነው የሚሉ በርካታ አስተያየት ሰጪዎችም፣ በሽግግር ሂደት ላይ ያለው የሀገሪቱ መንግሥት በራሱ የመጣው በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ነውና ከሸፈ የተባለው መፈንቅለ መንግሥት በእርግጥም ስለ መክሸፉ ጥርጣሬ እንዳላቸው ሲገልጹ ተደምጠው ነበር::
የተፈራውም አልቀረ በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር በሁለት ወር ውስጥ ሁለተኛው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተካሂዷል:: ትላንት ንጋት ላይ ያልታወቁ ወታደሮች ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሃምዶክንና በርከት ያሉ የሲቪል አመራሮችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል::ሱዳን በየአቅጣጫው እየነደደች፣ ወደ ምድራዊ ገሃነም እየተቀየረች ነው:: አሁን ባለው ሁኔታ አገር ሆና የመቀጠሏ ነገር አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል::ወታደርና ህዝቡ የለየለት አመፅና ድብልቅልቅ ውስጥ ገብተዋል::
ወደ ዋና ከተማዋ የሚያስገቡ ዋና መንገዶች በወታደሮች ተዘግተዋል።በዋና ከተማዋ ካርቱም የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ታውጅል::ክስተቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ ተቋማት እና አገራት ውግዘት እያስተናገደ ይገኛል::
የፖለቲካ ተንታኞችም ሆኑ የሱዳንን ፖለቲካን በአይነ ቁራኛ የሚከታተሉ ምዕራባውያን አገሮች ብሎ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ሽግግሩ ከታሰበው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሳይደርስ እንዳይንገራገጭና ቀውሱም ለጎረቤት አገራት እንዳይተርፍ ስጋታቸውን እያስቀመጡ ናቸው::
ሱዳን ውስጥ በየትኛውም መልኩ የሚከሰት አለመረጋጋት ዳፋው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቀጣናው በተለይ ለጎረቤት ሀገራት ሰላምና መረጋጋት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም እያሉ ናቸው::ቀውሱ በቀጥታ ተጽዕኖ ከሚደርስባቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነች::
ኢትዮጵያና ሱዳን ለዘመናት የዘለቀ የጋራ ግንኙነትን የመሰረቱ፣ በተለያዩ የኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብርና ትስስሮሽ የተዋሃዱ ናቸው::የውስጥ ችግር ያልበገረው ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸውና 750 ኪሎ ሜትሮች ያህል የጋራ ድንበር የሚጋሩት ሁለቱ አገራት ጎረቤት ብቻ ሳይሆን ቤተሰብም ጭምር ናቸው::
ኢትዮጵያ ሱዳን ከአልበሽር መውረድ በኋላ ከገባችበት ቀውስ ወጥታ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገርና የህዝቡ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ በተለይ የሲቪልና ወታደራዊ ኃይሉን አለመግባባት ለመፍታት ኢትዮጵያ ትልቅ የማደራደር ሚና ተወጥታለች::
በተለይ የሽግግር መንግሥቱን በጋራ በሚመሩት ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እልባት እንዲያገኙ የምትችለውን መፍትሄ ከመጠቆም ባለፈ የሰላም ምኞትን በተደጋጋሚ ስትገልፅም ቆይታለች::
ይሁንና ነገሮች መልካቸውን ለውጠው ከብዙ ድርድርና ውይይት በኋላ የመሪነት ስልጣን የያዙት ግለሰቦች፣ የትላንት ውለታን በልተዋል::ከአዲስ አበባ ይልቅ ዋሽግተንን፣ ከክፉ ቀን ወዳጆቻቸው ኢትዮጵያ ይበልጥ ግብፅን ሲመርጡም ታይቷል:: የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በመጠቀም ድንበራችንን አልፈውም ገብተዋል::ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ከግብፅ ጋር አብራ ዓለምን ስታስተባብርና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፊት ስትሞግተን ቆይታለች::
ይህንን ታሪክ ዋቢ የሚያደርጉ አንዳንድ ፀሐፍትና ምሁራንም፣ የሱዳን ቀውስ ውስጥ መግባት ለኢትዮጵያ በተለይም ከድንበር ጋር በተያያዘ ያለውን ጉዳይ ለመጨረስ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላታል የሚል አስተያየታቸውን ሲያጋሩ ይደመጣል::
ለመሆኑ የሱዳን ቀውስ በኢትዮጵያና በቀጠናው ላይ ምን አይነት ተፅእኖ ይኖረዋል?ተፅእኖውን ለመቋቋምስ ምን መደረግ አለበት?የምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ቀውስ ውስጥ መግባትስ ለኢትዮጵያ መልካም እድልን የሚፈጥርና ሊያስፈነድቅ የሚችል ነውን? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የተለያዩ ምሁራንን አነጋግረናል::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣ ‹‹የሱዳን ቀውስ ውስጥ መግባት፣ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ውስጥ ያሉ አገራት ህዝቦች በደህንነትና በሰላም የመኖር ዋስትና አደጋ ውስጥ የሚከት ነው፣ በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ጫናው ከፍ የሚል ነው ይላሉ::
ቀውሱን ተከትሎ በተለይ የስደተኞች ጎርፍ ሊመጣ የሚችለው ወደ ኢትዮጵያ ስለመሆኑ የሚጠቁሙት ዶክተር ሳሙኤል፣ ይህን ተከትሎም የተለያዩ አጀንዳን ያነገቡ ኃይሎች ተቀላቅለው ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ እንደሚችሉም ያስገነዝባሉ::
‹‹የሱዳን ቀውስ ከዚህ ባሻገር በምእራብና ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች ምቹ ሁኔታና ጥሩ የመተላለፊያ ድልድይ እንዲያገኙ በር የሚከፍት ነው›› የሚሉት ምሁሩ፣የሱዳን ስትራቴጂካል ማእከላዊነትም በሽብር ሥራ ላይ የተሰማሩ ኃይሎች በጋራ አህጉሪቱን እንዲበጠብጡ እድል እንደሚፈጥርም ያመላክታሉ::
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ የሱዳን ቀውስ የአፍሪካ ህብረት 2063 አጀንዳ ተግባራዊነት በተፈለገው መጠንና ፍጥነት እንዳይሳካ ማነቆ የሚፈጥር ነው:: አብዛኛው በጀት ከልማት ይልቅ ጸጥታን የማስከበር በተለይ ሽብርና ሽብርተኞችን ለመከላከል እንዲውል ምክንያት ይሆናል::ከሰላም ይልቅ የጦርነት ወጪዎች እንዲጨምሩም ሊያስገድድ ይችላል::
የዚህ ድምር ውጤትም በአሁኑ ወቅት ያለውን ድህነትና ሰብአዊ ቀውስ ይበልጥ ያባብሰዋል:: የምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሁለንተናዊ ቀውስ ጫናም በተለይ አጎራባቾችና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ኢጋድ አባል አገራትን የሚነካ ነው::
አንዳንድ ፀሐፍትና ምሁራንም፣የሱዳን ቀውስ በቀጠናውና በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ጫና ቀላል እንዳልሆነ ይስማሙበታል::ይሁንና ‹‹የሱዳን ቀውስ ውስጥ መግባት በተለይ ለኢትዮጵያ መልካም እድል ይዞ የመጣ በተለይም ከድንበር ጋር በተያያዘ ያለውን ጉዳይ ለመጨረስ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ›› የሚል አስተያየትን ያጋራሉ::
ዶክተር ሳሙኤል በአንፃሩ፣ይህን ፈፅሞ አይቀበሉትም፣ መፍትሄ ብለው የሚያስቀምጡትም፣ኢትዮጵያ በቀድሞ አቋም መፅናት እንዳለባት ነው:: ‹‹ኢትዮጵያ በታሪኳ ስትከተለው የነበረውን የዲፕሎማሲ መርህና አቋም ከአገሮች ጋር ሰላማዊ የሆነ ቁርኝት እና ግንኙነት የሚያበረታታ ነው›› የሚሉት ዶክተሩ፣ጎረቤት ሱዳን በታሪኳ ባሳለፈችው አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በወታደራዊውና በሲቪሉ መካከል የሀሳብ መቀራረብን ለማምጣት ድልድይ በመሆን ታሪካዊ ኃላፊነቷን መወጣቷን በማስታወስ፣ እንደ ትላንቱ ነገም ይህን አኩሪ ምግባሯን እንደምትቀጥል አፅንኦት ይሰጡታል::
ኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ የለማች፣ በጋራ ተጠቃሚነት የምታምንና ጠንካራ የሆነች ሱዳን ስትኖር በሁሉ ረገድ ትርፋማ እንደምትሆን በማመን በጎረቤቷ ቀውስ መደሰትን ምርጫዋ ማድረግ እና ጮቤም መርገጥ እንደሌለባት የሚያምኑት ዶክተር ሳሙኤል፣ይልቁንም ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በሁሉ ረገድ ተባባሪ መሆን እንዳለባትም ያሰምሩበታል::
‹‹ጎረቤቷ በቀውስ ውስጥ በሆነችበት በአሁኑ ወቅት፣ቁስሏ ላይ እንጨት መሰካት ሳይሆን የሽግግር መንግሥቱ ወደ ቦታው እንዲመለስና ሌሎች ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት በሚያስተባብራቸው ሥራዎች ውስጥ የራሷን በጎ በአስተዋፆኦ ማድረግ መቻል አለባት›› ነው ያሉት::
ኢትዮጵያ ከዚህ የተቃረነ መንገድ ትራመዳለች ብለው እንደማያምኑ አፅንኦት የሰጡት ዶክተር ሳሙኤል፣ ልዩነቶችን በኃይልና በጦርነት መፍታት የመጨረሻ አማራጭ እንደመሆኑም በሱዳን የተረጋጋ መንግሥት ሲመሰረት ውጥረቶችን በሰላማዊ አማራጭ ብሎም በሰከነ መንገድ መጨረስ የሚያስችል እድል ሊፈጠር እንደሚችልም ሳያመላክቱ አላለፉም::
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሙከረም ሚፍታህም፣ በበኩላቸው፣ በሱዳን ፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የወታደሩ ኃይል የጎላ ተሳትፎና ሚና የቅርብ ጊዜ ሳይሆን ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን ያስታውሳሉ::ባለፉት ሁለት ዓመታት የሽግግር መንግሥቱ ውስጥ የተስተዋለውም የዚሁ ነፀብራቅ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ::
የሱዳን የሽግግር ሂደት እንዲጨናገፍ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ የውጭ ጣልቃ ገብነት ስለመሆኑ የሚያነሱት ዶክተሩ፣ ምዕራባውያን በሱዳን የተከሰተውን አሁናዊ ችግር ሕዝባዊ ጩኸትን ለመቀነስና ለማስመሰል ሲሉ መፈንቅለ መንግሥቱን እንደሚቃወሙ ቢገልጹም ጥቅማቸውን ስለሚያስቀድሙ ወታደራዊ መንግሥቱን ከልባቸው ይጠሉታል የሚል እምነትም የላቸውም:: በግብጽ ያላቸውን አቋም በሱዳን የማይደግሙበት፣ በካይሮ አምሳያ ተቀረፀ መንግሥትን ሱዳን ላይ ለማዋለድ የሚታትሩበት ምንም ምክንያት እንደሌለውም ጥርጥር የላቸውም::
‹‹የሱዳን አሁናዊ ችግር ለሱዳን ሕዝብ አደገኛ ነው::ኢትዮጵያንም እንደ አገር ያሳስባታል›› የሚሉት ዶክተር ሙከረም፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ካላት ረጅም ታሪካዊ ግንኙነት ባሻገር በህዳሴውና በአልፋሽካ ድንበር ካላት ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሱዳን ችግር እንደሚያሳስባትና በትኩረት መከታተል እንደሚኖርባት ያሰምሩበታል::
በእርግጥ ስለ ሱዳንና ኢትዮጵያ ሲነሳ የህዳሴ ግድብና የአልፋሽካ ድንበር አጀንዳ አብሮ ይነሳል::በዚህ ረገድ አስተያየታቸውን የሚያጋሩ ሌሎች ፀሐፍትና ምሁራንም፣ የሱዳን ቀውስና ቀጣይ እጣ ፈንታ ለእነዚህ ሁነኛ አጀንዳዎች መልስ የሚሰጥ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ::
ይሁንና መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት በሱዳን ላይ የእግድ ውሳኔ ማሳለፉ፣በተለይም በህዳሴው ድርድር ላይ እክል ሊፈጥር እንደሚችል የሚጠቁሙም አልታጡም:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቱ በአንፃሩ፣በኢትዮጵያ በሱዳንና በግብፅ መካከል ያለው የሶስትዮሽ ድርድር በየትኛው ጊዜ ቢደረግ ፍላጎታ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ በማንኛውም ጊዜ ለመደራደር ዝግጁ ስለመሆኗ አረጋግጠዋል::
በህዳሴ ግድቡም ሆነ በድንበሩ ጉዳይ የሲቪሉና የወታደሩ አመራሮች ያላቸው አቋም የየቅል መሆኑ ደግሞ ስጋቱን ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርግ ይታመናል::‹‹መፈንቅለ መንግሥቱን የመራው የወታደሩ መሪ አብዱልፈታህ አልቡርሃን የግብፅ ወዳጅና በሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ከስክነት ይልቅ ስሜታዊነት የሚታይበት መሆኑ ደግሞ በተለይ ለኢትዮጵያ ማስጠንቀቂያን የሚሰጥ ነው›› የሚሉም በርካቶች ናቸው::
ዶክተር ሙከረምም፣የሲቪሉና የወታደሩ አመራሮች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አቋም የየቅል ስለመሆኑ ይገልፃሉ:: እንደ እርሳቸው ገለፃም፣በሽግግር ሉአላዊ ምክር ቤት ውስጥ የሲቪሉ መንግሥት በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የድንበር እና የህዳሴ ግድብ አጀንዳ በሰከነ መንገድ እልባት ለመስጠት ፍላጎት አለው::ወታደራዊው ክንፍ በአንፃሩ በዲፕሎማሲና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ስሜታዊነት ኃይል የታከለበት አካሄድን ምርጫው የሚያደርግ ነው::
ከዚህ ባለፈ በተለይ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን በበጎ የማይመለከተው የግብፅ መንግሥት ለሱዳን ወታደራዊ ኃይል ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየና እያደረገ የሚገኝ ስለመሆኑ የሚጠቁሙት ዶክተሩ፣ ይህን አይነት የፖለቲካ አሰላለፍ ኢትዮጵያ በቅጡ ፣መረዳትና በጥንቃቄ መመልከት እንዳለባትም ነው አፅንኦት የሰጡት::
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሱዳን አሁናዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሚከተላቸው አቋሞች የትኛውንም ጎራ የማያስቀይምና ከሕዝብ ጎን መሆን እንዳለበት፣ ይህን እያደረገ መሆኑን መመልከታቸውም ተገቢ ብሎም ትክክለኛ መሆኑንም አስምረውበታል::
በሱዳን የተከሰተውን ችግር የህዝቡ ፍላጎትና ስሜት ባገናዘበ መልኩ ለመፍታት ከውጭ ጣልቃ ገብነት ይልቅ በአፍሪካዊ ተቋማት ችግሩ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያ ግፊት በማድረግ ለሱዳን ሕዝብ አጋርነቷን ማሳየት እንደሚኖርባት ነው ያመላከቱት::
ኢትዮጵያም፣ከሱዳን ሕዝቦች ጎን በሙሉ ልቧ የምትቆም መሆኗን እናረጋግጣለን:: በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ለሉዓላዊና ነጻ ውሳኔዎቻችን ያነሰ ግምት በመስጠት ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚጥሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አስጠንቅቃለች::
ምሁራን እንደሚያስገነዝቡት ከሆነ ግን፣ከሰላም ምኞትና ትብብር ባለፈ የሱዳን ቀውስ ኢትዮጵያ ላይ ያልተጠበቀ ተፅእኖ እንዳያመጣ በንቃት መጠበቅ የግድ ይላል:: ከምንጊዜም በላይ በሁሉ ረገድና አቅጣጫ ነቅቶ መጠበቅ ይገባዋል::
ከሁሉ በላይ ቀውሱን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሱዳናውያንም ሆነ ሌሎች ስደተኞች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል:: አጋጣሚውን በመጠቀም አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሱዳን ውስጥ ያሰለጠናቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ጋሻጃግሬዎችን ለማስረግ እንደሚተጋም ታሳቢ ማድረግ የግድ ይላል:: በመሆኑም በድንበር አካባቢ የሚደረጉ ቁጥጥሮች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2014