የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራቸውን ካስቀመጡ ተቋማት አንዱ ነው:: ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በርካታ መምህራንን በማፍራት በሀገሪቱ የትምህርት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ሲጫወት ኖሯል:: በሰርተፊኬት መምህራንን ማስመረቅ የጀመረው ተቋም ዛሬ በርካታ ተማሪዎችን እየተቀበለ ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ ሙያዎች እያሰለጠነ ይገኛል:: በ2014 ዓ.ም በሁለት የትምህርት ዘርፎች የሶስተኛ ዲግሪ ለመስጠት ዝግጅቱን ጨርሷል::
ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ከተቋምነት ወደ ኮሌጅ፤ ከኮሌጅ ወደ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ማደጉ ይታወሳል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተብሏል:: ተጠሪነቱም ለትምህርት ሚኒስቴር ሆኗል:: ዩኒቨርሲቲው ከሚታወቅበት የመምህራን ማሰልጠኛነቱ ባሻገር በተለያዩ ሙያዎች ተማሪዎችን እያስመረቀ ለመንግሥት ተቋማት ትልቅ አቅም እየፈጠረ ይገኛል::
ለአብነትም ዩኒቨርሲቲው ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ጋር በመተባበር በጤና ዘርፍ ተማሪዎችን እየተቀበለ በማሰልጠን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ሰጪነቱን እያስመሰከረ ይገኛል:: የሀገር ኩራትና ተስፋ የሆኑ ተማሪዎችንም እያፈራ ነው::
ዩኒቨርሲቲው በ2013 ዓ.ም በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ መርሃግብር ትምህርታቸውን በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የተከታተሉ 2,526 ተማሪዎችን አስመርቋል:: ከነዚህ ተመራቂዎች መካከል ከጤናው ዘርፍ አንዲት ተማሪ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የዋንጫና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች:: በዛሬው የአስኳላ አምዳችን ስለተሸላሚዋ ጥቂት ብለን በእለቱ በክብር እንግድነት የተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ያስተላለፉትን መልዕክት እናስነብባለን::
ከ2013 ዓ.ም የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች መካከል በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሂውማን ኒውትሬሺን /ስነምግብ/ የትምህርት ዘርፍ፤ ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ሰባት በማምጣት የዋንጫና የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ቃልኪዳን ወንዳጥር ነች:: ቃል ኪዳን ከአማራ ክልል፣ ሰሜን ወሎ ዞን፣ መቄት ወረዳ፣ ገረገራ ከሚባል አነስተኛ ከተማ የመጣች ነች:: የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ትኩረት ሰጥታ በመማር ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባቷን ትናገራለች::
ሴትነቷ ከምትፈልገው ነገር አላገዳትም፤ የቤት ውስጥ ሥራን በመሥራት እናቷን እያገዘች፤ ለትምህርቷም ጊዜ እየሰጠች ለዚህ መብቃቷን ትገልጻለች:: ባሳለፈቻቸው የትምህርት ዓመታት በርካታ ተግዳሮትን እንዳሳለፈች ትናገራለች:: በተለይም ያለፉት ስድስት ወራት ለእርሷ ጥሩ አለመሆናቸውን ትገልጻለች::
የትውልድ አካባቢዋ ሰሜን ወሎ ዞን በአሸባሪው የትህነግ ቡድን መወረሩን ተከትሎ የቤተሰቦቿ የደህንነት ሁኔታ እያሳሰባት ነበር ትምህርቷን የተማረችው:: በተረበሸ ስሜት ውስጥ ሆና መማሯ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቿ ለእርሷ የሚያደርጉት ድጋፍም ተቋርጦባት ነበር:: ድምጻቸውን መስማት ባለመቻሏ ነጋ ጠባ ሃሳቧ እነርሱ ጋር እንደነበር ትገልጻለች::
ቃል ኪዳን በተለይም የመጨረሻውን ሴሚስተር ባልተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ሆና መማሯ በውጤቷ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጠራል የሚል ስጋት ነበረባት :: ነገር ግን ያን ሁሉ መሰናክል አልፋ ከአጠቃላይ የ2013 ዓ.ም ተመራቂዎች ከፍተኛውን ውጤት አምጥታ መሸለሟ አስደስቷታል::
ሁሉም ቤተሰቦቿ በዚህች ቀን ተገኝተው የደስታዋ ተካፋይ ቢሆኑ ትመኝ ነበር:: ያ መሆን ባለመቻሉ ቅር ቢላትም አባቷ ባገኙት አጋጣሚ ከወራሪው ኃይል ሾልከው በመውጣት በምርቃት ፕሮግራሟ ላይ መገኘታቸው ልዩ ደስታ ፈጥሮላታል:: ስለሙሉ ቤተሰቦቿ ደህንነት መስማቷም በደስታ ላይ ደስታ ፈጥሮላታል::
ቃልኪዳን ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች ከዩኒቨርሲቲ በማዕረግ የመመረቅ ምኞት እንደነበራት ትናገራለች:: ለዚህ ያነሳሳት ደግሞ በየዓመቱ የሚመረቁ የማእረግ ተሸላሚዎችን በቴሌቪዢን ማየቷ ነበር:: የገጠሟትን ችግሮች ሁሉ ተቋቁማ ጠንክራ በመማር ህልሟን ማሳካት እንደቻለች ትገልጻለች:: ሰው ጠንክሮ ከሠራ አላማውን የማያሳካበት ምንም ምክንያት አይኖርም ትላለች::
ቃልኪዳን ኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ ምእራፍ በጀመረችበት በዚህ ወቅት መመረቋ ደስተኛ አድርጓታል:: መጪው ዘመን ብሩህ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣ እምነቷ ነው:: ከሰሞኑ በትውልድ አካባቢዋ በወራሪው አሸባሪ ቡድን የተፈጠረው ማህበራዊ ቀውስ የሰላም ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ያሳያት አጋጣሚ እንደሆነ ትናገራለች::
ከጦርነት ጋር በተያያዘ የሰዎች ሞትና መፈናቀል፣ የምግብ እጥረት፣ በሽታም ተያይዞ ሊመጣ ይችላል የምትለው ቃልኪዳን፤ ከዚህ አንጻር በተመረቀችበት ሙያ ወገኗን ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ትናገራለች:: ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ አሸናፊ እንድትሆን ምሁራን ሀገራቸውን በተማሩበት ሙያ በማገልገል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፤ በተለይም በዲፕሎማሲው መስክ የፖለቲካ ሳይንስ፣ የህግ፣ የታሪክ ተመራቂዎች የላቀ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ትላለች::
ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያ ሰላሟ ተጠብቆ ህዝቦቿ ያለስጋት እንዲኖሩ ማስቻል የአዲሱ መንግሥት የመጀመሪያ ተግባር ሊሆን ይገባል ትላለች:: እርሷም በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ በሀገሯ የወደፊቱ እድገትና ብልጽግና የራሷን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀቷን ትገልጻለች::
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ለድህረ ምረቃ ትምህርት በሰጣት ነጻ የትምህርት እድል ሌላ ስኬት ለማስመዝገብ መዘጋጀቷን ተናግራለች:: ዩኒቨርሲቲው ለሰጣት ነጻ የትምህርት እድልም ምስጋና አቅርባለች::
በምርቃ መርሀ ግብሩ ላይ ከተገኙ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት አንዱ አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው:: ባደረጉት ንግግርም አዲሱ ትውልድ ሀገሩን ወደፊት ለማራመድ ከምንግዜውም በላይ ኃላፊነት የሚቀበልበት ወቅት አሁን ነው ብለዋል:: ያለንበት ወቅት ተስፋና ተግዳሮት ያለበት እንደሆነ በንግግራቸው የጠቆሙት የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ፤ በአንድ በኩል ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ አዲስ መንግሥት የተመሰረተበትና ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ማየት የጀመርንበት፤ በሌላ በኩል የውስጥና የውጭ ተገዳዳሪ ሃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየሠሩ ያሉበት ነው ብለዋል::
አዲሱ ትውልድ ሀገር እናፈርሳለን የሚሉትን የጥፋት ሃይሎች እየመከተ የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና በማረጋገጥ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትና ለሀገሩ ተስፋ መሆኑን በተግባር ማሳየት እንደሚገባው ተናግረዋል:: የእለቱ ተመራቂዎችም በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ሀገራቸውን የሚጠቅም ሥራ እንዲሰሩ፤ በተለይም የሀገራቸውን ሰላም እንዲያስጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል::
አዲሱ መንግሥት ለመላው ኢትዮጵያዊ ይዞ የመጣው አዲስ ተስፋ እንዳለ የገለጹት አቶ አባዱላ፤ ተስፋው እንዳያብብ የሚጥሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን ነቅቶ ከመጠበቅ አንጻር ከአዲሱ ትውልድ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል::
ሰው መኝታ ከተመቸው ለረዥም ሰዓት ይተኛል፤ ከቆረቆረው ግን ቶሎ ብሎ ይነሳል ያሉት አቶ አባዱላ፤ የገጠሙን ተግዳሮቶችም የብልጽግና ጉዟችንን አፋጥነን ያሰብነው ላይ እንድንደርስ የሚያነቁን እንጂ የሚያስተኙን አይደሉም ብለዋል::
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው፤ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ኢትዮጵያ የገጠማት ውጫዊና ውስጣዊ የሴራ ፖለቲካ ያስከተለውን ቀውስ አልፈው ለዚህ ቀን በመብቃታችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል ብለዋል::
የዘንድሮ ተመራቂዎችን ለየት የሚያደርጋቸው በኮቪድ ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረውን ትምህርት በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ማጠናቀቅ መቻሉ፤ በአሳታፊነቱ፣ በሰላማዊነቱና በዲሞክራሲያዊ ልምምድ ሂደቱ ፍጹም ምሳሌ በሆነ ምርጫ ማግስት መመረቅ መቻላቸው እና ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ኮሌጅ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር በሆነ ጊዜ የተከናወነ ምርቃ ስለሆነ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል::
ዩኒቨርሲቲው ከመማር መስተማር ኃላፊነቱ ውጭ ማህበራዊና ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ዶክተር ብርሃነመስቀል ገልጸዋል:: ለህዳሴ ግድቡ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር፤ ከአማራና ከአፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት አልባሳት ቁሳቁስና የምግብ አይነቶችን ማበርከቱንም ጠቅሰዋል::
በአረንጓዴ ልማትና በደም ልገሳም ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን ተወጥቷል:: የምእራባዊያንን እውነት ያላገናዘበ ፍርደ ገምድል በመቃወም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በራሱ ተነሻስነት ነጩን ፖስታ ወደ ነጩ ቤተመንግስት በመላክ የኢትዮጵያን ድምጽ አሰምቷል::
ዩኒቨርሲቲው በዲሞክራሲ፣ በዲፕሎማሲና በገጽታ ግንባታ ረገድ ለውጡን መሰረት የሚያስይዙ ውይይቶችን በማድረግ፤ አቅጣጫዎችን በመቀየስና በመተግበር ምሁራዊ እገዛ እያደረገ ነው::
መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የዲሞክራሲ ስርዓትን ይበልጥ ለመገንባት ህዝቡን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም የሀገሪቱን ሰላም እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ የከፍትኛ ትምህርት ተቋም ሚናውን እንደሚወጣ ቃል ገብተዋል::
የትምህርት ስርዓቱ ብዙ ሸር ሲሠራበት የነበረና ብዙ ውድቀትን ያስከተለ ነበር ያሉት ዶክተር ብርሃነ መስቀል፤ ዩኒቨርሲቲው ይህን ችግር ለመቅረፍ ለመንግሥት ምክረሃሳቦችን ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል::
የቀድሞው የኮተቤ ኮሌጅም ሆነ በሽግግር ላይ ያለው ሜትሮፖሊታን የኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ የነበረውን ደማቅ አሻራ መሰረት በማድረግ ቀጣይም ይህንኑ በጠበቀ ሁኔታ ወደ ላቀ ደረጃ ይሸጋገራል ብለዋል::
እንድንሸነፍ፣ እንድንበረከክ፣ ጫና እንዲበረታብን ለሚያደርጉ አካላት እጅ መስጠት እንደማያስፈልግና ሸፍጠኞች ሀገራችንን እንዳያፈርሱ ተማሪዎች ሀገር የማዳን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዶክተር ብርሃነመስቀል ጥሪ አስተላልፈዋል::
ተማሪዎች በምርቃ መርሃ ግብሩ ላይ የለበሱት ካባ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደሆነ ተረድተው ሳይከፋፈሉ በፍቅርና በአንድነት ቆመው ሀገራቸውን እንዲጠብቁ መልእክት አስተላልፈዋል:: ተማሪዎች በሥራ ዘመናቸው ሀገር ወዳድ ፣ ታታሪ፣ ታማኝ ሆነው እንዲሰሩም መክረዋል::
በእለቱ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ መርሃግብር ትምህርታቸውን በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የተከታተሉ 2,526 ተማሪዎችን ማስመረቁን የተናገሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ወንድ 1285፤ ሴት 1241 መሆናቸውን አሳውቀዋል:: ይህም በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የትምህርት ተሳትፎ ልዩነት ማጥበብ እንደተቻለ ያሳያል:: ዩኒቨርሲቲው አዳዲስ የማስተር ዲግሪና የፒ.ኤች.ዲ ትምህርቶችን በመጪው ዓመት ለማስጀመር መዘጋጀቱም ተገልጿል::
በመማር ማስተማር ሂደት ወደ አስር የሚደርሱ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በአዲስ መልክ ተቀርጸዋል:: በተለይም በቴፍልና አብላይድ ስታትስቲክስ የፒ. ኤች. ዲ መርሃ ግብሮችን ለመስጠት አስፈላጊው ሂደት ታልፎ በ2014 ዓ.ም ተማሪዎችን መቀበል እንደሚጀመር ተናግረዋል::
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ ሰላም ተሰምቶን እንዲህ አይነት ፕሮግራም እንድናከናውን ላበቃን ጀግናው መከላከያ ሰራዊት ምስጋና ይገባል በሚል ንግግራቸውን ጀምረዋል:: ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየተሯሯጡ ያሉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ባሉበት በዚህ ወቅት ሰላሟን ለማስጠበቅ እየተዋደቀ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ምስጋና ማቅረብ ከሁሉ የሚቀድም መሆኑን አስምረውበታል::
አምባሳደር ዲና በንግግራቸው ‹‹ዛሬ የተመረቃችሁ በሙሉ የሀገራችን ዲፕሎማት ናችሁ፤ የሀገራችሁ ሞጋቾችና ጠበቆች መሆን ይገባችኋል›› ብለዋል። ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ለሀገሩ ተቆርቋሪ መሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል::
ከዚህ ዩኒቨርሲቲ ይዛችሁ የምትሄዱት ኢትዮጵያን ነው:: ልዩነቶቻችን ውበቶቻችን ናቸው፤ አንድነታችሁንና ፍቅራችሁን አጠንክራችሁ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን መቃወምና መመከት ይኖርባችኋል:: የሀገራችሁንና ያስተማራችሁን ህዝብ እዳ መክፈል የምትችሉት የኢትዮጵያን ሰላምና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አንጻር ምሩቃን የሚጠበቅባችሁን ስታደርጉ ነው:: የህዝባችንን ኢኮኖሚያዊ ባህላዊና ማህበራዊ ተግዳሮቶች እየተረዳችሁ መፍትሄ ለማምጣት የምትሰሩ መሆን ይኖርባችኋል ብለዋል::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2014