በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ላይ እያለን ስለዛፍ ቆራጭ ማውራት ምቾት ላይሰጠን ይችላል:: ያውም ችግኞችን መትከል፣ ዛፎችን መንከባከብ የህይወታችን መርህ አድርገን በተነሳንበት በዚህ ወቅት:: ‹‹ዛፍ ቆራጩ›› ያልናቸው እኚህ ሰው ግን በየመንደሩ አደጋ ያደርሳሉ የተባሉ ዛፎችን እየቆረጡ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ናቸው:: ሠርቶ የመኖርን ሌላ መልክ ያሳዩናል በሚል የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርጋቸው ወደድን::
ምሺቆ አራሶ ይባላሉ:: የሃምሳ ስድስት ዓመት ጎልማሳ ናቸው:: ደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ሀመካ ወረዳ ተወልደው ማደጋቸውን ይናገራሉ:: በልጅነታቸው በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቻቸውን በሥራ እያገዙ አድገዋል:: ከብት ማገድ፣ ማገዶ መስበር፣ አረም ማረም፣ እንሰት መትከልና መንከባከብ የዘውትር ችግባራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ::
በእርሳቸው የልጅነት ዘመን በሀዲያ ገጠራማ አካባቢ የሚያድጉ ልጆች ዛፍ ላይ መውጣትን እየተለማመዱ ያድጉ ነበር:: ዛፍ ላይ መውጣት እንደጉብዝና ስለሚቆጠር እርሳቸውም ከአብሯአደጎቻቸው ጋር ዛፍ ላይ መውጣትን እየተፎካከሩ አድገዋል:: ለማገዶና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቅርንጫፎችን የመመልመል ልምድ ያዳበሩት ያኔ ነው::
የሀድያ ማህበረሰብ በአጎራባቹ ከሚኖረው የጉራጌ ማህበረሰብ ጋር ተወራራሽ ባህል ያለው እንደመሆኑ የሥራ ባህሉ ጠንካራ ነው:: አንድ ልጅ ነፍስ ካወቀ በኋላ የትም ሀገር ሄዶ፤ በየትኛውም ሥራ ላይ ተሰማርቶ ለማኖር ይጥራል እንጂ የቤተሰቦቹን እጅ እየጠበቀ አይኖርም ይላሉ አቶ ምሺቆ:: ከራሱ አልፎ ቤተሰቦቹን እንዲረዳም ይጠበቃል::
አቶ ምሺቆም እራሳቸውን ችለው ለመኖር ሲሉ ከትውልድ አካባቢቸው ርቀው የሄዱት ገና የ15 ዓመት ታዳጊ ሳሉ ነበር:: ያኔ የስደስተኛ ክፍል ተማሪ ነበሩ:: ገና በጠዋቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው ለመሰደድ ያበቃቸው የቤተሰባቸው ችግር ነው:: ቤተሰቦቻቸው ከቁራሽ መሬት እና ከሁለት ጥገት በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ሀብት አልነበራቸውም:: የሚታረሰው መሬት የዓመት ቀለባቸውን እንኳ የሚሸፍን አልነበረም:: በዚህ ላይ ሰፊ ቤተሰብ ነበራቸው::
የያኔው ታዳጊ፤ የአሁኑ ጎልማሳ ታዲያ ሥራ ወዳለበት አካባቢ በመሄድ ራሳቸውን ችለው ለመኖር ይወስናሉ:: ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ:: መርካቶ አካባቢ አርፈው የቀን ሥራ እየሠሩ መኖር ይጀምራሉ:: የአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ውድነት፣ የነዋሪው እና የተሽከርካሪው ብዛት፣ ሁካታውና ግርግሩ ምቾት ሳይሰጣቸው ይቀራል:: ሠርተው የሚያገኙት የቀን ገቢም ከእለት ወጪያቸው አላልፍ ይላል::
በዚህ የተነሳ የተሻለ ሥራ የሚገኝበትን ሌላ ሀገር ማጥናት ይጀምራሉ:: በጥናታቸው መሰረት አፋር ክልል የጥጥ ተክልን የመንከባከብ ሥራ እንዳለ ሰምተው ጉዟቸውን ወደዚያው ያደርጋሉ:: አንደተባለውም ጥጥ ውሃ በማጠጣትና በመልቀም ሥራ ላይ ተሰማርተው ለሁለት ዓመት ያህል አፋር ይቆያሉ:: የበረሃውን ሀሩር ተቋቁመው በሠሩባቸው ጥቂት ዓመታት ገንዘብ እየቋጠሩ ቤተሰቦቻቸውን ይጠይቁ ነበር::
ኋላ ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ጤናቸው እየታወከ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ያቅታቸዋል:: ከሚሠሩበት የማይሠሩበት ጊዜ እየበዛ ለሌላ ችግር መዳረግ ይጀምራሉ:: ለጊዜው ጥጥ መልቀሙን ትተው በሌላ የጉልበት ሥራ ላይ ይሰማራሉ:: ያም ቢሆን ከእለት ወጪያቸው የሚተርፍ ገቢ አልነበረውም:: እንደገና ከአካባቢው ተወላጆች ጋር ሆነው ከሰል እያከሰሉ በመሸጥ ለመኖር ይሞክራሉ:: የደን መመናመንን ተከትሎ ከሰል ማምረት ሲከለከሉ ያለሥራ ለ መቀመጥ ይገደዳሉ::
በዚህ አጋጣሚ ህይወትን በሌላ መንገድ ለመቃኘት የሚያስችላቸው አዲስ አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል:: ጊዜው 1969 ዓ.ም ነው:: ወራሪው የሲያድባሬ መንግሥት እስከ ድሬዳዋ ድረስ ዘልቆ በመግባት የኢትዮጵያን ግዛት ይዟል:: ይህንን ተከትሎ የደርግ መንግሥት የእናት ሀገር ጥሪ ያስተላልፋል:: የ18 ዓመት ወጣት የነበሩት ምሺቆ ሀገራቸውን ከጠላት ለመታደግ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ይመዘገባሉ:: ጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል መሰረታዊ የውትድርና ሰልጠና ከጨረሱ በኋላ በ8ኛ ክፍለጦር፣ 146ኛ ብርጌድ፣ 4ኛ ሻለቃ መትረየስ ተኳሽ ሆነው ይመደባሉ::
ከዚያም በኦጋዴን ግንባር ይዘምታሉ:: ወራሪው የሲያድባሬ ጦር ተጠራርጎ ከወጣና የምሥራቁ ጦርነት በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ምሺቆ ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለሌላ ግዳጅ ይሰማራሉ::
በትግራይ፣ በጎንደር፣ በወሎ ከፍለ ሀገሮች በተለያዩ አውደ ውጊያዎችም ይሳተፋሉ:: በአሻጥሮች ውጊያው ሲበላሽና የደርግ ሠራዊት ሲበታተን ምሺቆ ወሎ አካባቢ እጃቸውን ሰጥተው አዚያው ሀይቅ ከተማ ኢህአዴግ የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ ያቆያቸዋል::
በቀን አንድ እፍኝ ደረቅ በቆሎ ተቆንጥራ እየተሰጠቻቸው ሁለት ወራት ያህል በሀይቅ ከተማ የስቃይ ህይወትን ያሳልፋሉ:: ስልጠናውን ከጨረሱ በኋላ በቀይ መስቀል ዕርዳታ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ይመለሳሉ::
ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል:: አባታቸው በህይወት አልነበሩም:: ምሺቆ ጥቂት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከተቀመጡ በኋላ አሁንም ሠርቶ መኖር ወደሚችሉበት አካባቢ ለመሄድ ይነሳሉ:: ነገር ግን ቤተሰቦቻቸው በሃሳባቸው ሳይስማሙ ይቀራሉ:: ትዳር ይዘው ባለችው መሬት ላይ እንሰት በመትከል እንዲኖሩ ይመክሯቸዋል:: በሃሳባቸው ተስማምተው ትዳር ይይዛሉ::
ከዚያም በኋላ ልጆች ተወልደው የቤተሰቡ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ለችግር ይጋለጣሉ:: የሚላስ የሚቀመስ እስከማጣት ይደርሳሉ:: በዚያችው መሬት ላይ እንሰት ተክለው ባለቤታቸው እንዲጠቀሙ በማድረግ እርሳቸው ሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ::
አዲስ አበባ ሲመጡ የአካባቢያቸውን ሰዎች ተከትለው ነበር:: ሰዎቹ በዋናነት ለዳቦ ቤቶችና ለምግብ ቤቶች እንጨት በመፍለጥ በሚያገኟት ገቢ የሚተዳደሩ ናቸው:: ምሺቆ ምንም አይነት መሳሪያ ስለሌላቸው ከእነርሱ ጋር በመሆ ን ሥራውን መለማመድ ይጀምራሉ::
እንጨት እየፈለጡ ከሚያገኟት ላይ ለልጆቻቸው ይልካሉ:: እንጨት ሲፈልጡ የሚያይዋቸው አንዳንድ ሰዎች ታዲያ ቤታቸው ቆርቆሮ ላይ አደጋ የፈጠሩ የዛፍ ቀርንጫፎችን እንዲመለምሉ፣ አንዳንዶቹም ዛፉን እንዲቆርጡላቸው ያነጋግሯቸዋል:: እንዲህ ዓይነት የሥራ እድሎችንም መጠቀም ይጀምራሉ:: እንደውም አንዱ ሌላውን እያየ ዛፍ ያስቆርጣቸው ጀመር:: መጥረቢያና ገመድ ገዝተው ሥራውን በቋሚነት መሥራት ይጀምራሉ:: ከእንጨት መፍለጥ ወደ ዛፍ ቆራጭነት ይሸጋገራሉ::
ሥራው በየዕለቱ የሚገኝ አይደለም:: በዚህ ላይ ክፍያውም ወጥነት የለውም ፤ እንደዛፉ መጠን ይለያያል:: ተለቅ ያለ የዛፍ ቅርንጫፍ ለመመልመል ከአምስት እስከ ስድስት መቶ ብር ይከፈላቸዋል:: ግንዱን እየቆራረጡ ለመጣል ደግሞ እስከ አንድ ሺ ብር ይቀበላሉ:: ግን አንድ ሥራ ለማግኘት እስከ አንድ ሳምንት ሊፈጅ ይችላል:: በዚህም ላይ ድፍን አዲስ አበባን በእግራቸው ማካለል ይኖርባቸዋል:: የሚቆረጥ ዛፍ ለመፈለግ ቢያንስ በቀን ከሃያ እስከ ሠላሳ ኪሎ ሜትር መንደር ለመንደር በእግራቸው መዞር አለባቸው:: እንደዚያም ሆኖ ሥራው ላይገኝ ይችላል::
ምሺቆ በልጅነታቸው የተለማመዱት ዛፍ መውጣት ዛሬ እንጀራ ሆኗቸው በእርሱ ይኖራሉ:: መነን ትምህርት ቤት አካባቢ ከአራት ጓደኞቻቸው ጋር በአንዲት ትንሽ ቤት ውስጥ በቅናሽ ዋጋ ቤት ተከራይተዋል:: አራቱም ተመሳሳይ ሥራ ያላቸው ናቸው:: ማለዳ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰማርተው ሲመሻሽ ለመኝታ ወደ ቤታቸው ይገባሉ:: ቤቷ ለመኝታ ብቻ የሚጠቀሙባት ነች፤ ጭስ አይጨስባትም:: በለስ የቀናው ሠርቶ ያልቀናውም ባዶ እጁን ይመጣል::
አንዳንዴ የሚሰጣቸው ገንዘብ ከዕለት ምግባቸው አያልፍም:: የሚያሠሯቸው ሰዎች ምግባቸውን በሚችሏቸው ጊዜ ሳንቲሟ ትርጉም ይኖራታል::
ዛፍ ቆረጣ ህይወትን የሚያሳጣ ሥራ እንደሆነ ይናገራሉ:: ከዛፍ ላይ ወድቀው የሞቱ እና ተጎድተው የተቀመጡም ጓደኞቻቸው አሉ:: በተለይም ዝናብ ሲዘንብ ግንዱ የማንሸራተት ባህሪ ይኖረዋል:: ምሺንቆ ግንዱን በገመድ እየጠለፉ መወጣጫ በመሥራት እስከ እሚፈልጉት ከፍታ ድረስ ይወጣሉ:: ከሃያ ዓመት በላይ ዛፍ እየቆረጡ እና እንጨት እየፈለጡ ቤተሰቦቻቸውን አስተዳድረዋል:: አንዳንዴ የሚቆርጡት ዛፍ በድንገት ወዳልተፈለገ ቦታ ወይም በሰው ቤትና አጥር ላይ ሲያርፍና ንብርት ሲጎዳ ተመን እየከፈሉ ኪሳራ እንደሚያጋጥማቸውም ይናገራሉ::
በአንድ ወቅት እርሳቸው የገጠማቸውን አደጋ እንዲህ ይናገራሉ:: ‹‹የምቆርጣት ዛፍ አነስተኛ ስለነበረች ገመድ አላሰርኩባትም ነበር:: የግንዱን ቅርንጫን በቁሙ መልምዬ ከጨርስኩ በኋላ አጠር አጠር አድርጌ እየቆረጥሁ ወደ መሬት እጥለው ጀመር:: አንዱ ቁራጭ መሬት ላይ ነጥሮ ሲያበቃ ዘሎ ሰው ቤት ይገባል:: ቤቱ ውስጥ አቅመ ደካማ ሴት ተኝተው ነበር:: የግንዱ ቁራጭ በሩን አልፎ ገብቶ አልጋቸውን መትቶ ይቆማል:: ያ ግንድ እርሳቸው ላይ ቢያርፍ ኖሮ በህይወት አይኖሩም ነበር፤ እኔም እታሰር ነበር:: ይህ በወቅቱ ይሆናል ብዬ ያላሰብኩትና የማልረሳው አስደንጋጭ ገጠመኜ ነው:: ከዚህ ጪግን አንዳንዴ ጣራ ላይ አንዳንዴ አጥር ላይ እያረፈ ለእዳ ዳርጎኝ ያውቃል::
ምሺቆ ዛሬ የአምስት ልጆች አባት ናቸው:: ሁለቱ ልጆቻቸው ትምህርታቸውን ከአስረኛ ክፍል ጨርሰው የራሳቸውን የጉልበት ሥራ እየሠሩ ይኖራሉ:: ሦስቱ ልጆቻቸው ግን አሁንም የእርሳቸውን ርዳታ የሚፈልጉ በመሆናቸው በእስተርጅና ዛፍ እየቆረጡና እንጨት እየፈለጡ ያስተምሯቸዋል::
ምሺቆ የመስቀል በዓል ሲደርስ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ሀገራቸው ይገባሉ:: ከዚያ ውጪ ግን አዚሁ እየሠሩ ያገኟትን ለቤተሰቦቻቸው ይልካሉ:: ባለቤታቸው አረቄ እያወጡ ባይደጉሟቸው በዚህ ሥራ ብቻ የኑሮ ውድነቱን ተቋቁሞ መኖር እንደማይቻል ይገልጻሉ::
አሁን ምሺቆን እየተፈታተናቸው ያለው ሥራ ማጣት አይደለም:: ሠርተው ገንዘብ አለመጨበጣቸው ነው:: አቅማቸውን ጨርሰው የሠሩበትን ገንዘብ በአንድ ቀንና በሁለት ቀን የምግብ ወጪ እየጨረሱ ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ መላክ ተቸግረዋል:: የኑሮ ውድነቱ የፈጠረባቸውን ጫና በምሬት ይናገራሉ:: እንደከዚህ ቀደሙ ሠርተው ቤተሰቦቻቸውን እንዳይረዱ አድርጓቸዋል:: መንግሥት በየጊዜው እየተባባሰ የሚሄደውን የኑሮ ውድነት አንድ ሊለው ይገባል ይላሉ:: ያ ካልሆነ ሠርቶ የመኖር ጥረታቸው ከንቱ እንደሚሆን ይፈራሉ::
የሀገራቸው የሰላም ጉዳይ ከኑሯቸው በላይ ያስጨንቃቸዋል:: ዛሬም ወታደር ሆነው ኢትዮጵያን ከከበቧት ጠላቶቿ የመታደግ ፍላጎት አላቸው:: መንግሥት ያወጀውን የክተት ጥሪ በመቀበል ሀገር ቤት ሄደው ተመዝግበዋል:: ዛፍ እየቆረጡና እንጨት እየፈለጡ መኖር የሚቻለውም ሀገር ሰላም ስትሆን እንደሆነ ያምናሉ:: ሕወሓት ስልጣን የያዘው የቀድሞ ወታደሮችን አሸንፎ ሳይሆን ልክ አንደ አሁኑ የውጭ ኃይሎች ድጋፍ እያደረጉለት መሆኑን የሚናሩት ምሺቆ ይህ ኃይል በሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ግፍ ክፉኛ እንዳስቆጫቸው ይናገራሉ::
ምሺቆ ቀደም ሲልም ለሀገራቸው ዘብ የቆሙ የቀድሞ ወታደር ናቸው:: አሁንም በእንዲህ ዓይነት የሕይወት ትግል ውስጥ ሆነው ለሀገራቸው ቅድሚያ ይሰጣሉ:: ለመኖር ከሚያደርጉት ጥረትና ከጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው አንድ ቁምነገር እንገኛለን ብለን እናምናለን:: ለዛሬ በዚሁ እንሰናበት፤ በቀጣይ ሳምንት ከሌላ ባለታሪክ ጋር እንገናኛለን፤ ቸር እንሰንብት::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014