ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትታየው አባቶቻችን ከዛሬ አንድ መቶ ሃያ ሶስት ዓመት በፊት የጭቆና ቀንበር ሊጭንብን የመጣውን የኢጣሊያ ሠራዊት በአድዋ ተራሮች ላይ ድል አድርገው ለመላው አፍሪካዊና ለዛሬው ትውልድ ኩራት በመሆናቸው ነው፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር አለማየሁ አበበ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ 123ኛው የአድዋ ድል በዓል ‹‹የአድዋ ድል የአንድነታችን ማህተም›› በሚል መልዕክት እንደሚከበር በመግለፅ ወጣቶች የአባቶቻችንን የአደራ ቃል ተረካቢ መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ በአድዋ ጦርነት ወቅት ወጣቶች ከጎበዝ አለቆች ጎን በመሰለፍ በጦርነቱ ያደረጉትን ተጋድሎ በመግለጽ ከዚያም ወዲህ ጠላት በአዲስ መልክ ሀይሉን አደራጅቶ ዳግም ወረራ ሲያደርግ እያደፈጡ ጥቃት ከሚሰነዝሩ አርበኞች ውስጥ አብዛኛዎቹ ወጣቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
አምባሳደር አለማየሁ ኢትዮጵያዊያን የአድዋ ጦርነትን በአንድ ቀን ውጊያ ድል ያደረጉበትን ምስጢር ሲገልጹ ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር የንጉስን የክተት ጥሪ ተቀብሎ አስተሳሰቡንም ሀይሉንም አንድ አድርጎ በቁጭት በመዋጋቱ ነው ይላሉ ፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ጠላትን የመመከት ታሪክ ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን በመግለጽ ዛሬ በአገሪቱ ዜጎች መካከል የሚስተዋለው ግጭት አሳፋሪና ከአባቶቻችን ታሪክ ጋር የሚቃረን መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ወጣቱ ከአባቶች የተረከበውን ሀገራዊ አደራ ማክበር እንደሚገባው አስታውሰው ወጣቱ ኢትዮጵያዊነትን አክብሮ ከወገን ጋር ተሳስቦ በፍቅር መኖር ይኖርበታልም ብለዋል፡፡
አቶ ዳኛቸው ተመስገን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ልጅ አባቱን ይከተላል፤ አባቶቻችን ወደ ጦር ሜዳ ሲሄዱ ወጣቶችም አብረዋቸው ይዘምታሉ፤ አንዳንዶቹም ቤተሰባዊ ኃላፊነት ወስደው የግብርና ሥራውን ይመሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን በአንዳንድ ቦታዎች ወጣቶች የሚፈጽሙት ድርጊት ፍጹም ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጽ እንደሆነ በመግለጽ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባቸውና ቅድሚያ ለትምህርታቸው መስጠት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡ ወጣቶች ስለሀገር ፍቅር ስለግብረገብነት ማወቅ እንደሚገባቸውና እንደውም በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ መማር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹ ሰላም ፍቅር አንድነት ለኢትዮጵያ ›› የሚል መልዕክት በማንገብ 25 ተጓዦችን በማቀፍ ወደ አድዋ የእግር ጉዞ ካደረጉት ወጣቶች መካከል አዲስ ዘመን የጉዞውን ተልዕኮ በተመለከተ ከቡድኑ አስተባባሪዎች ውስጥ ወጣት ምኒልክ ፋንታሁንን አነጋግሯል፡፡ ወጣቱ አባቶቻችን ዛሬ የምንኖርባትን ሀገር ጠብቀው ለእኛ ለማውረስ የከፈሉትን መስዋዕትነት ባለመዘንጋት የምናስተውልበት ትልቅ ዕድል ነው ብሏል፡፡
የአድዋ ድል አሁን ያለችው ኢትዮጵያ የተሠራችበት የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ነው የሚለው ወጣት ምኒልክ አባቶቻችንና እናቶቻችን አድዋ ላይ ደማቸውን አፍሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው ለእኛ ብርሀን ሆነዋል፡፡ ይህንንም ለማሳየት ‹‹በጉዟችን መነሻ ለኢትዮጵያ ዓይን ባንክ የዓይን ብሌናችንን ለመለገስ ቃል በመግባት የእኛም ዓይን ለሌሎች ብርሀን እንዲሆን የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ አምባሳደሮች ሆነን ወደ አድዋ ተጉዘናል›› ይላል፡፡
የአድዋ ድል ብዙ ትሩፋት አስገኝቶልናል የሚለው ምኒልክ አድዋ ላለፈውም፣ ለአሁኑም ይሁን ለመጪው ትውልድ የሰጠው ትልቁ ስጦታ አንድነትን ነው፡፡ የአድዋ ድል የአንድ ብሄር ወይም የአንድ ንጉስ ታሪክ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ ተሰውቶና ቆስሎ ያበረከተልን ትልቅ ሀብት እንደሆነ አስረድቷል፡፡
የአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የቆሙበት የመጀመሪያው መድረክ ነው የሚለው ወጣቱ ዛሬ ይህ ትውልድ ይህን አኩሪ ታሪክ ሊዘክረው ይገባል። አድዋ እየቀነሰ የመጣውን አንድነታችንን ለመመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ እናም ‹‹እኛ ኑሯችንን ትተን የሁለት ወር የእግር ጉዞ ለማድረግ የፈለግነው ኢትዮጵያን ፍለጋ ነው›› ብሏል፡፡
በመካከላችን የቱንም ያህል ልዩነቶች ቢኖሩም ስለሀገራችን ጉዳይ አንድ መሆን አለብን የሚለው ወጣት ምኒልክ በጣሊያን ወረራ ወቅትም በሀገራችን በነበሩ ገዢዎች መካከል ትልቅ የስልጣን ሽኩቻ እንደነበር፤ ነገር ግን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ሀገሪቱን ከጠላት ለማዳን በአንድ ላይ እንደቆሙና ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነ ታላቅ ጀግንነት በመፈጸም ምሳሌ እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡ እናም የዛሬው ትውልድ ከአባቶቹ መማር ያለበት ይህንን በጎ አስተሳሰብ ነው ይላል ወጣቱ፡፡
ባለንበት ዘመን በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች እዚህና እዛ የሚፈጠሩ ግጭቶች መኖራቸውን የጠቀሰው ወጣቱ ግጭቶቹ በወጣቶች የሚመሩ ናቸው ባይባልም ወጣቶች መጠቀሚያ መሆናቸውን ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል ይላል፡፡ አሁን አሁን ከኢትዮጵያዊነት ስሜት መሳሳት የሚመጡ ችግሮች ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ ተጽዕኗቸው እየበረታ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ወጣቱ ኢትዮጵያዊነት በህዝብ ልብ በተለይም በወጣቱ ውስጥ ፀንቶ መቀመጥ አለበት ብሏል፡፡ በየትምህርት ሥርዓቱ በታሪክም ይሁን በሌሎች መጻህፍት የተካተተ የአባቶቻቻንን ተጋድሎን፣ አንድነትና ሀገር ወዳድነትን አስጠብቀው ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ታሪኮች ቦታ ስላልተሰጣቸው ትውልዱ በራሱ የማይተማመን ፣ እንዳሉት የሚያደርግ ፣ የማይጠይቅ፣ የማይመራመር፣ በአባቶቹ ገድል የማይኮራና የተረከበውን አደራ የማያስቀጥል ትውልድ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል፡፡
አባቶቻችን ሲያድጉ ከመስጊድም ሆነ ከቤተክርስቲያን ወይም ከወላጆቻቸው የወረሱት ኢትዮጵያዊ የሆነ ባህልና ፣ ግብረገብነት አብሯቸው በማደጉ በፍቅርና በሰላም ከሌሎች ጋር መኖር የሚያስችሏቸውን ቁም ነገሮች አግኝተዋል፡፡
‹‹እኛ የዛሬ ትውልዶች በፌስ ቡክ ሀሰተኛ መረጃ ተነስተን የጎረቤት ቤት የምናቃጥል፤ አብሮ አደጎቻችንን የምንተናኮልና የምናጠፋ ሆነናል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ማስተዋልና መረጋጋት ወደ ኋላውም መመልከት አለበት›› ብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፤ የመገናኛ ብዙሀንም ትኩረት ሰጥተው ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ የአድዋ ድል በዓል ሲመጣ ሚዲያዎች ቀረርቶና ፉከራ ከማሰማት በላይ ድሉ የተከፈለበትን የአባቶቻችንን አብሮነትና ትብብር፤ ሀገር ወዳድነትንም ለአዲሱ ትውልድ ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ከሆነ በራሱ የሚተማመን በታሪኩ የሚኮራ ብቻ ሳይሆን ታሪኩንም የሚያውቅ ትውልድ ይፈጠራል፡፡
አንድ ሰው ጥሩም ይሁን መጥፎ ከሰው ያየውን ነው ይዞ የሚያድገው፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ባህላቸውን ታሪካቸውን ማንነታቸውን አውቀው ቢያድጉ ኖሮ ማንም ሰው እንደፈለገ እጃቸውን የሚጠመዝዛቸው አይሆኑም ነበር፡፡ ባለንበት ዘመን ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት ማዕከል መሆናቸው ቀርቶ ግጭት ሲቀሰቀስባቸው ማየት የተለመደ ሆኗል ሲል ይወቅሳል፡፡ ተማሪ በሚማርበት ትምህርት ቤት ላይ ድንጋይ መወርወር ፤ ከዚህም አልፎ ማሕበራዊ ሚዲያ እየተጠቀመ ሌሎች ደቀመዝሙሮችን ለማብዛት አፍራሽ መልዕክት ሲያስተላልፍ ያየነው በኛ ዘመን ነው ይላል፡፡
‹‹ከአዲስ አበባ ተነስተን ወደ አድዋ ጉዞ ስናደርግ በማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ነገር ተብሏል፤ ማህበራዊ ሚዲያ እንደ ሬዲዮ ለሁሉም ህብረተሰብ ቶሎ ሚደርስ ቢሆን ኖሮ ብዙ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል በመጥቀስ ወጣቱ ማሕበራዊ ሚዲያውን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ይገባል›› ሲል አሳስቧል፡፡
በአጠቃላይ የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን አደራ ሊቀበል ይገባል፤ አድዋ ለዛሬው ትውልድ የቀረበ አደራ ነው፡፡ ይህ አደራ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር በምን መጠን ምን ተከፍሎባት እንደቆመች የሚያሳየን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለብዙ ህዝብ፣ ባለብዙ ጥበብ፣ ባለብዙ ሀብት ፣ባለብዙ ቅርስ ባለብዙ ማዕረግ ሆና ተከብራ የኖረች የአባቶቻችን የአደራ ሀገር ነች፡፡ ይህችን ሀገር ጠብቁ ተብሎ አደራ ተሰጥቶናል፤ ኢትዮጵያ ደም ፣አጥንት ህይወት የተከፈለባት የአደራ ሀገራችን መሆኗን ወጣቱ ልብ ሊል ይገባል፡፡ ሁላችንም እንደ ትውልድ ይህንን አደራ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በኢያሱ መሰለ