አዲስ አበባ በአፍሪቃ አዳራሽ መግቢያ በሚታየው በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ ባረፈው ትልቅ የመስታወት ስዕላቸው፣ በአዲስ አበባ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ ስዕሎቻቸው፣ ‘ሞዜይኮች’ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሚገኘው የመጀመሪያው የ’ዳግመኛ ምጽዓት ፍርድ ስዕላቸው ይታወቃሉ፡፡ በሐረር የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት፣ በአዲግራት የ’ዳግመኛ ምጽዓት ፍርድ ስዕላቸውና በሌሎችም ታላላቅ የስዕልና ቅርጻ ቅርጽ ስራዎቻቸው በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡
ለሥራቸው የሚጠቅማቸውን ጉብኝት በሀገር ውስጥና በመላ ዓለም ያደረጉት እኚህ ታላቅ የሀገር እንቁ ፣ ሥራዎቻቸውን ለማሳየትም በርካታ ጉብኝቶችን በመላ ዓለም አርገዋል፡፡ በዚህም ሀገራቸውን በመላ ዓለም አስተዋውቀዋል፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፡፡
እኚህ ታላቅ ሰአሊ ይህችን ዓለም የተቀላቀሉት ጥቅምት ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፭ ነው፡፡ ዛሬ በእዚህ የሳምንቱ በታሪኩ ዓምዳችን ያነሳናቸው ይህን የልደት ቀናቸውን መሠረት አርገን ነው፡፡
የልጅነት ጊዜ
በቀድሞ ሸዋ ክፍለ ሀገር በአሁኑ አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ከተማ ከእናታቸው ወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ፣ ከአባታቸው ተክሌ ማሞ የተወለዱት የተከበሩ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረራ በያዘችባቸው ዓመታት ገና ልጅ ነበሩ፡፡ የልጅነት ትዝታቸውም ይሄው የፋሺስት ኢጣልያ የግፍ ወረራ እና ጦርነት የሚያስከትለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ሆነ፡፡ ከነጻነትም በኋላም በወረራ የተጎዳችውን ሀገራቸውን እንደገና ስለመገንባት ማሰብ ዐቢዩ ሥራቸው ሆነ፡፡
የትምህርት ሕይወት
ኢትዮጵያን ከፋሽስት ጣልያን ወረራ ለመታደግ ከተደረገው ጦርነት በኋላ እአአ በ1947 አፈወርቅ ኢትዮጵያን መልሶ ለመገንባት በማሰብ ወደ እንግሊዝ በመሄድ በምህንድስና ሙያ ትምህርታቸውን ለመከታተል ይወስናሉ፡፡ የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርታቸውን የት እና መቼ እንዳጠናቀቁ የተጻፈ መረጃ ባይገኝም፤ ገና በአሥራ አምስት ዓመታቸው በ ፲፱፻፵ ዓ/ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ እንግሊዝ የተላኩት።
በወቅቱም ለአፈወርቅና ለተመሳሳይ ከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጪ ለሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አሸኛኘት ባደረጉበት ወቅት ‹‹ ጠንክራችሁ መሥራት ይጠበቅባችኋል፤ ትምህርታችሁን ጨርሳችሁ ስትመለሱ አደራችሁን በአውሮፓ ስለተመለከታችሁት ረጃጅም ፎቆች እንዳትነግሩን፤ ስለሰፋፊ ጎዳናዎችም እንድትተርኩልን አንሻም፤ በምትኩ ኢትዮጵያን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ክህሎት ስለመጨበጣችሁ፣ አእምሯችሁንም ለእዚህ ስለማዘጋጀታችሁ እርግጠኛ ሁኑ ›› ሲሉ ጥብቅ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል፡፡
አፈወርቅ ገና ጨቅላ እያሉ የአርቲስትነት እውቀቱ ነበራቸው፡፡ ለሀገር ግንባታ አስፈላጊውን እውቀት መሸመት ይፈልጉ የነበሩትና በማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ተምረው ለመመለስ ሀሳቡ የነበራቸው ቢሆንም፣ ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማዶቻቸው ግን የኪነ ጥበብ ስጦታቸውን በመኖሪያ ቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች ተገንዝበውት ነበር።
በእንግሊዝ አገር የአዳሪ ተማሪ ቤትን ኑሮ ሲያስታውሱ በባዕድ ባህሎች፣ በአየር ለውጥ እና በተለመደው የተማሪ ቤት ህይወት ተቸግረዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ትምህርታቸውን በትጋት መከታተል ችለዋል። በተለይም በሒሣብ፣ በፖካርሲን (chemistry) እና በታሪክ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት ማምጣት ቢችሉም፣ አስተማሪዎቻቸው የተፈጥሮ ስጦታቸው ኪነ ጥበብ እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜም አልወሰደባቸውም።
ይህ እምቅ አቅማቸው በመምህሮቻቸው ዘንድ አድናቆት እያስገኘላቸው መጣ፡፡ ይህ ብቻም አይደል፤ የሚያበረታቷቸውን አስገኘላቸው፡፡ ይሄኔ ነው እንግዲህ አፈወርቅ ምህንድስናውን ተወት በማድረግ ወደ ሥነጥበብ ዘርፍ መማተር የጀመሩት፡፡ የስዕል ትምህርት ለመከታተል በለንደኑ ማዕከላዊ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ተመዘገቡ፡፡ ከዚያም በስላዴ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት በስዕል፣ ቅርጻ ቅርጽና ስነ ህንጻ/ አርክቴክቸር/ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ በውጪ ሀገር ሲከታተሉ የቆዩትን የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም የሚኒስትርነት ደረጃ ሥልጣን ቢጠብቃቸውም፣ የእሳቸው ምርጫ ግን ኢትዮጵያን እየተዘዋወሩ መጎብኘት ሆነ፡፡
“ምኞቴ በዓለም የታወቀ ኢትዮጵያዊ የኪነ ጥበብ ምሑር መሆን ስለነበር፣ የአገሬን ወግና ባሕል ጠንቅቄ ማወቅና ማጥናት እንዳለብኝ አውቄያለሁ። ሥራዬ የዓለም ንብረት ይሆናል፤ ነገር ግን በአፍሪቃዊነት ቅመም የጣፈጠ ሥራ ነው የሚሆነው።” ሲሉ መግለጻቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለዚህም ኋላ ላይ በስዕሎቻቸው ያንጸባረቋቸውን የሀገራቸውን ባህሎች ተዘዋውረው ጎበኝተዋል፡፡
በ1947 ዓ.ም የመጀመሪያውን የኪነጥበብ ሥራ ትርኢታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ አቀረቡ፡፡ ይህ የሆነው በሀያ ሁለት ዓመታቸው ነው፡፡ በዚህ ባገኙት ገቢ ለሁለት ዓመታት በጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ፖርቹጋል፣ ብሪታኒያ እና ግሪክ የጠለቀ የኪነጥበብ ጥናት አካሄዱ፡፡ በእነዚህ ሀገሮች በስደት የተቀመጡ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ የብራና መጻህፍትን በጥልቀት አጠኑ፤ በመስታወት ላይ ስዕል መስራት የሚረዳ ዲዛይን ማውጣት ያስቻላቸውን እውቀትም ቀሰሙ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በእንግሊዝ ቤተመጻህፍት፣ በፓሪስ፣ በቫቲካን የሚገኙ የኢትዮጵያ የተለያዩ ሰነዶችን በመጎብኘት ልዩ ጥናት አድርገዋል፡፡
የስዕል ሥራዎች
ወደ ሀገራቸው ተመልሰውም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመጻህፍት ውስጥ የስዕል ስቱዲዮ ከፈቱ፡፡ እያደገ የመጣው እውቅናቸው የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን በሃይማኖታዊ የግድግዳና ጣሪያ ስዕሎች፣ የ’ሞዜይክ’ ሥራዎች፣ መስኮቶቹንም በመስታወት ስዕሎች እንዲያሳምሩ ምቹ ሁኔታ ፈጠረላቸው ፤ ሥራውንም በንጉሡ ታዘው ሠርተዋል፡፡ በርካታ ስዕሎቻቸውም ለሀገሪቱ የፖስታ ቴምብሮች ውለዋል፡፡
አፈወርቅ ሐውልት በመቅረጽም ይታወቃሉ፡፡ የታላላቅ ሰዎችን ሐውልት እንዲቀርጹ ታዘው የነበረ ቢሆንም፣ የተጠናቀቀው ሐውልት ግን በሐረር ከተማ የሚገኘው የራስ መኮንን ሀውልት ብቻ ነው፡፡
እአአ በ1958 አፍሪካ በአጠቃላይ ነጻነቷን መቀዳጀቷን የሚያሳይ ዲዛይን በአዲስ አበባው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መስሪያ ቤት የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ መስታወት ላይ ሰርተዋል፡፡ ምስሉ ሦስት መስኮቶች ያሉት ሲሆን 150 ካሬ ሜትር ስፋትም አለው፡፡ ምስሎቹም የአፍሪካን ያለፈ የመከራ ዘመን፣ ለነጻነት ይደረግ የነበረውን የትግል ወቅት፣ የአፍሪካን የወደፊት ተስፋ ያመለክታል፡፡
አፈወርቅ ራሳቸውን በራሳቸው በመሳል የሚታወቁ ታላቅ ሰዓሊ ነበሩ፡፡ ይህ ስዕል በጣልያን አንድ ጋላሪ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ራሱን በራሱ የሳለው ሰዕል በሚል በቋሚነት ተቀምጧል፡፡
እአአ 1961 ደግሞ አፈወርቅ አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ ቅኝት አድርገው ‹‹መስቀል አበባ›› የተሰኘውን ስዕላቸውን ሠሩ፡፡ ስዕሉም በሩሲያ፣ በአሜሪካ፣ እና በሴኔጋል ዓለም አቀፍ ኢግዚቢሽኖች ለመታየት በቅቷል፡፡
ስዕሎቻቸውን ተክትሎ ያገኙ የነበረው የገንዘብ ድጋፍም አፈወርቅ አፍሪካን እየተዘዋወሩ እንዲጎበኙ አስቻላቸው፡፡ ወቅቱ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ገና ከቅኝ ግዛት እየተላቀቁ የነበረበት እንደመሆኑ አፈወርቅን በጥቁሮች ለነጻነት የሚደረግ ትግል ላይ እንዲያተኩሩ አረጋቸው፡፡ ይህም ባክቦንስ ኦፍ አፍሪካን ሲቪላይዜሽን እና አፍሪካን ዩኒቲ ላይ በሚገባ አንጸባርቀውታል፡፡
ጉብኝትና ኤግዚቢሽኖች
ዝናቸው በውጭው ዓለም እየናኘ ሲመጣም በሩሲያ በሚካሄድ የስዕል ኢግዚቢሽን እንዲሳተፉ በዚያውም ሶቬዬት ህብረትን ተዘዋውረው አንዲጎበኙ ተጋብዘዋል፡ ፡ የአሜሪካ መንግሥትም በዋሽንግተን ዲሲ እና ኒውዮርክ ኢግዚቢሽን ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ያረጋቸው ሲሆን፣ በእዚህም ቆይታቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በመገኘት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በሴኔጋል. ቱርክ፣ ዛየር፣ የተባበሩት ኤምሬት ሪፐብሊክ፣ ቡልጋሪያ፣ ሙኒክ፣ ኬንያና አልጀሪያም ሌሎች ዓለም አቀፍ ኢግዚቢሽኖች ሥራዎቻቸውን አሳይተዋል፡ ፡ በተለያዩ ሀገሮች በተዘጋጁ ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ኢግዚቪሽኖች ላይም ሥራዎቻቸውን አሳይተዋል፡፡
ሽልማቶች
እአአ በ1964 ደግሞ አፈወርቅ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት የስዕል ጥበብ የመጀመሪያው የሎሬት ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡ የዓለም ሎሬት የተከበሩ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ በሥራዎቻቸው የተለያዩ ሽልማቶችን ከውጭ መንግሥታት አግኝተዋል፡፡
እኚህ ታላቅ ሰዓሊ በጨጓራ አልሰር ህመም ምክንያት ማክሰኞ ሚያዚያ 2 ቀን 2004 በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፤ የቀብር ሥነስርዓታቸውም መንግሥታዊ ሥነሰርዓት ተደርጎሎት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ፤ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ፣ አዲስ አበባ ራሳቸው በነደፉትና ባሠሩት ባለ ሃያ ሁለት መኝታ ቤቱ ‘ቪላ አልፋ’ ይኖሩና ይሠሩ ነበር። ድንቅ ሥራዎቻቸው የሚገኝበትን ይህን ቪላ አልፋ ለመንግሥት ሰጥተዋል፡፡
መውጫችንን በእሳቸው ጥቅስ እናረጋለን፡፡ “የእኔን ሥራ የሚያዩ ሁሉ ተስፋ እንዲያገኙ፣ ስለኢትዮጵያ እና ስለ አፍሪካ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው፣ በፀሐይ ጮራ እንዲሞቁ፣ ከሁሉም በላይ ግን “ይቻላል” የሚል እምነት እንዲኖራቸው ፍላጎቴ ነው።” እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፡፡
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም