አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ 75 በመቶ የስንዴ አቅርቦትን ከአገር ውስጥ ስታሟላ ቀሪውን 25 በመቶ በውጭ ምንዛሬ ትገዛለች። በቅርቡ 400 ሺ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በ3.5 ቢሊዮን ብር ግዢ ልትፈፅም እንደሆነ ከኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው የስንዴ ግዢ ‹‹አገሪቱ የሚለማ መሬት፣ በቂ ውሃና ተመራማሪ ምሁራን እያሉዋት ስንዴ አምርተን ፍላጎታችንን አሟልተን ለውጭ ምንዛሬ የሚተርፍ ምርት ለማግኘት መልካም እድሎች ስላሉ ስንዴ ከውጭ ለምን እንገዛለን?›› ሲሉ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ይጠይቃሉ።
አቶ ደስታ ገብሬ በአገሪቱ በመስኖ ስንዴ ላይ ለ13 ዓመታት ምርምር አድርገዋል። አሁን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ እርሳቸው እንደሚሉት የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የስንዴ አቅርቦት ውስንነት ከ25 እስከ 30 በመቶ አድጓል።
አቶ ደስታ ይህ ፍላጎት በአፍሪካ ደረጃም እያሻቀበ በመምጣቱ እ.አ.አ. ከ2009 እስከ 2011፣ 23 ሚሊዮን ቶን እያመረተች ከውጭ የምታስገባው ግን 36 ሚሊዮን ቶን ነው ሲሉ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ያስረዳሉ። ይህም የአህጉሪቱን አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ከፍተኛ ልዩነት ያሳያል።
የዓለም አቀፉ የግብርና ምርምር ውጤቶችን የያዘው የግብርና ምርምርና ግኝት መፅሔት ቅፅ 6 በሁለተኛ ርዕሰ ጉዳዩ እንዳሰፈረው «በማምረትም ሆነ በመጠቀም ረገድ ስንዴ ለኢትዮጵያውያን ወሳኝ ነው። በዚህም ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አባወራዎች 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በማልማት በዓመት ከአራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያልዘለለ ምርት ያመርታሉ» ብሏል።
በኢትዮጵያ ከ12 ዓመታት በፊት የተጀመረው የመስኖ ስንዴ ልማት አዋጭነቱ ተረጋግጦ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ስራ በመጀመር በ2010 ዓ.ም ከአንድ ሺ ሄክታሩ 40ሺ ኩንታል ተገኘ የሚሉት አቶ ደስታ ተሞክሮዎችን በማስፋት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከ3ሺ 500 ሄክታር በላይ እጅግ የሚያጓጓ ሰብል እየተመረተ ነው ብለዋል።
‹‹በአሁኑ ወቅት 25 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ አቅርቦት የማምረቱን ጥያቄ ለመመለስ የግድ መግዛቱ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። በቀጣይ ዓመታት መንግስት በመቶ ሺዎች የሚቆጠረውን ማሳ፣ የባለሙያዎችን ዕውቀትና በግብርና ባለሙያዎች አንቀሳቅሶ በስንዴ ምርት ራሳችንን ችለን ከውጭ ማስገባት ማቆም አለብን፤ እንችላለንም›› ብለዋል አቶ ደስታ ።
ኢትዮጵያ ባሉዋት12 የሚደርሱ ተፋሰሶች አካባቢ የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ ያደረጉት አቶ ደስታ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለእርሻ ምቹ እንደሆነ፤ ከዚህ መሬት ውስጥ 500 ሺ ሄክታር መሬት ስንዴ ቢለማበት አሁን ባለው አማካይ የምርት መጠን 20 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ በዓመት እስከ 14 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ብታስገባም አራት ሚሊዮን ኩንታል የአንድ ጊዜ ፍጆታ ነው። ስለሆነም በየዓመቱ 500ሺ ሄክታር መሬቱን በስንዴ ብናለማ በየአመቱ ከፍጆታችን የሚተርፈውን አምስት ሚሊዮን ኩንታል ወደ ውጭ በመላክ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ ይገኝበታል ይላሉ አቶ ደስታ በማብራሪያቸው።
የንግድ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደሚገልፁት ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በአገር ውስጥ የሚመረቱበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል:: በዚህም ከውጭ ማስገባት ለማቆም ስትራቴጂ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቀድሞ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አዱኛ ዋቅጅራ ስንዴን በቆላማ አካባቢ ማምረት ሁለት ጥቅሞች እንደሚያስገኝ፤ አንደኛው የምግብ ዋስትናን እንደሚያረጋግጥ፤ ሁለተኛው ደግሞ ከብእርና አገዳ ሰብሎች ውስጥ ከበቆሎ፣ ከማሽላ፣ ከሩዝና ከገብስ ጋር ሲነፃፀር ከ12 እስከ 16 በመቶ የሚደርስ የፕሮቲን ንጥረ ነገር እንዳለው ያስረዳሉ።
ስንዴን በአገር ውስጥ ማምረት የውጭ ምዛሬን ከማስገኘቱ በተጨማሪ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ቆላማ አካባቢዎች በድርቅ በተደጋጋሚ በሚመቱበት ወቅት የስንዴው ገለባ የእንስሳቱን ህይወት ይታደጋል ሲሉ የስንዴውን ምርት ፋይዳም አክለው አስረድተዋል።
አቶ ደስታ የሜክሲኮን ተሞክሮ በአፋር ክልል እየለማ ካለው ማሳ ጋር እያነፃፀሩ ሲያስረዱ «አሁን ባለው ደረጃ በአፋር ክልል የታየው የስንዴው ምርት እንደ ሜክሲኮ ባሉ ባደጉ አገራት በሚመረተው ልክ ምርታማነት እያሳየ ይገኛል። ሜክሲኮዎች አሁን እኛ በአፋር ክልል ማምረት እንደቻልነው በመስኖ እያመረቱ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ነው። ስለሆነም ይህ ነገር በአገራችን ትኩረት አግኝቶ መስፋፋት አለበት›› ብለዋል።
የስንዴ ገለባው ለእንስሳቱ መኖ ይሆናል ሲሉ የዶክተር አዱኛን ሃሳብ የሚያጠናክሩት አቶ ደስታ ይህ የእንስሳት ሀብቱንም በዘላቂነት ይታደጋል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ስንዴውን በማምረት ሂደት የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳደግ ይቻላል፤ በዘርፉ ክህሎትን ማዳበር ሌላው ጥቅም ሲሆን፤ ይህም ምርታማነቱን ይጨምራል ይላሉ።
«የስንዴን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ጉዳዮች የሜካናይዜሽን ጉዳይ ግንባር ቀደሙን ደረጃ ይይዛል። ስንዴ ሲለማ የውሃ ስርጭቱ ተመጣጣኝ እንዲሆን መሬቱ የተስተካከለ መሆን አለበት። ለዚህም መሬትን የሚያስተካክሉ ማሽኖች ያስፈልጋሉ። ስንዴን ከውጭ ለመግዛት የምናወጣውን ገንዘብ ማሽኖቹን በአንድ አስረኛ በማስገባት እርሻው ወደ ዘመናዊነት ይቀየራል። የዚያን ያህልም ምርታማነታችን በእጥፍ ይጨምራል» ይላሉ አቶ ደስታ።
የስንዴን ምርት ለመሰብሰብ የሚያገለግሉት ሀርቨስተርና ፕላንተር ዘመናዊ መሳሪያዎች በአነስተኛ የሰው ሃይል ብዙ ማምረት ያስችላሉ። በዚህም የቴክኖሎጂ እውቀቱ አገር ውስጥ ስለሚገባ አዋጭነቱ ከፍተኛ ይሆናል። በመሆኑም እስከ አሁን የተሰራውና በተግባር የተማርነውን ተሞክሮ ቀምረን ምርቱን በስፋት ማምረት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ ተመራማሪዎቹ ገለፃ መንግስት በዚህ ረገድ ረዘም ላለ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ስንዴን በአገር ውስጥ የማምረትና የመጠቀም ፍላጎት አለው ፤ ይህንን ለማከናወንም ምቹ ፖሊሲ አለ፤ በተለይ ለኢንዱስትሪ ልማቱ ትልቅ አቅም ስለሚሆን በትኩረት ሊሰራ ይገባል። ለመስኖ ስራ ትኩረት ይሰጠው ሲባልም አስፈላጊው መሰረተ ልማቶች በቆላማው የአገሪቱ ክፍል ተሟልተው መሆን አለበት ይላሉ። በመስኖ ስንዴን ማልማቱ ላይ ሁሉም ተቋም ተቀናጅቶ ስራውን ማስጀመር ብቻ ይጠበቅባቸዋል፤ ሌላ ምክንያት መደርደር አይገባም ሲሉ መክረዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ስንዴን ከውጭ ማስገባቱ የሚቀጥል ከሆነ ምርቱን ለመግዛት የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊጎዳ ይችላል፤አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀምና በራስ አቅም ለአገር ውስጥ ፍጆታ ስንዴን ማምረት ያለመቻሏ ለዜጎች የስራ እድልን ያለመፍጠርና በቂ አቅርቦት እንዳይኖር ያደርጋል። በውጭ ምንዛሪ የማስገባት አቅም በሚታጣበት ወቅትም የኢኮኖሚና የሞራል ውድቀት ያስከትላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
ሀብታሙ ስጦታው