ጊፋታ የወላይታ ዘመን መለወጫ ነው።ከአሮጌ ነገር ወደ አዲስ ነገር መራመድን፣ ከአሮጌ መንፈስ ወደ አዲስ መንፈስ መለወጥን፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን የሚገልጽ የአዲስ ዓመት ብስራት ሲሆን፣በጥቅሉ ጊፋታ የሚለው ቃል ትርጉም በኩር ወይም ታላቅ ማለት ነው።
ጊፋታ ለወላይታ ብዙ ነገር ነው፤ በተለይ ግን ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ነው።ጊፋታ ሰላም ነው፤ ጊፋታ ዕድገት ነው።‹‹እንዴት?›› የሚለውን ኢየሱ ገጃቦ የተባሉ የወላይታ አባት ይነግሩናል።
ጊፋታ ሰላም ይዞ ይመጣል።ምክንያቱም የጊፋታን በዓል ማንም ቅሬታ ውስጥ ሆኖ ማክበር አይችልም።የአካባቢው ሽማግሌዎች ይሄን ያስፈጽማሉ።ከባልና ሚስት ጀምሮ ማንም በአካባቢው የተቀያየመ ሰው ካለ ለጊፋታ ይታረቃል።የእርቅ ሂደቱ በአካባቢው አባቶች የራሱ ሥነ ሥርዓት አለው።
ጊፋታ ዕድገት ነው፣ ልማት ነው፣ ብልጽግና ነው፤ ምክንያቱም የቁጠባ ባህልን ያደብራል።ለጊፋታ ማንም ሰው ተበድሮ አያርድም፤ ይሄ በጊፋታ ነውር ነው።የሚያርደው ቆጥቦ ነው።እግረ መንገዱን ለብዙ ጉዳዮች ይቆጥባል።የጊፋታ ቁጠባ የሚጀመረው በዕለቱ ነው፤ ለሚቀጥለው ዓመት ማለት ነው።ለ2015 ዓ.ም ጊፋታ ቁጠባ የሚጀመረው የ2014 ዓ.ም ጊፋታ ከተከበረበት ዕለት ጀምሮ ነው።
ይህን ሥርዓተ ክዋኔ በቦታው ተገኝኜ አስተውያለሁ።የአካባቢው አባቶች በተገኙበት በሬ ይታረዳል።የታረደው በሬ እርጥብ ቆዳ ላይ ብር ይጣላል፤ ለሚቀጥለው ዓመት በሬ መግዣ ማለት ነው።ይህ የጋራ ክዋኔ ማስጀመሪያ ነው።ከዚያ በኋላ ሁሉም በየግሉ ይቆጥባል።የወላይታ ማህበረሰብ ከባንኮች ማስታወቂያ በፊት ቁጠባን ባህሉ አድርጓል።
የጊፋታ ሌላኛው የሰላምና ዕድገት ተምሳሌትነት፤ መንግስትና ህዝብን የሚያገናኝ፣ ቤተሰብ የሚያደርግ ነው።ጊፋታ መንግስት ዓመቱን ሙሉ በየዘርፉ ሲያከናውን የከረመውን ሥራ፣ ለህዝቡ የሚያስገመግምበት ነው።መንግስት አጠቃላይ ሥራውን ለህዝቡ በማስገምገም፣ ግብዓት የሚሰበስብበት፣ በጉድለቱ የሚወቀስበት እና በመልካም ስራው ደግሞ የሚወደስበት ዕለት ነው።
ጊፋታ የአካባቢ ጥበቃ ተምሳሌትም ነው።ለደመራ የሚሆን እንጨት የሚቆረጠው በወጣቶች ሲሆን ዘው ተብሎ ደን ውስጥ አይገባም።የአቆራረጥ መመሪያ የሚሰጡ አባቶች አሉ፤ ‹‹ኦቾሎ›› ይባላሉ።የደን ሀብትን የሚከታተሉ ናቸው።ለእያንዳንዱ ቆራጭ ወጣት ትዕዛዝና መመሪያ ይሰጣሉ፤ መቆረጥ ያለበት ዛፍ ተመርጦ ተነግሯቸው ነው የሚቆረጥ።
ጊፋታ የጤና ሳይንስም ነው።የወላይታው አባት አባ ኢያሱ እንደሚሉት፤ የጊፋታ በዓል ሲደርስ ቅባት የበዛበት ነገር በአንድ ጊዜ በብዛት አይወሰድም።ቀስ በቀስ በሂደት ነው ሆድን እያላመዱ የሚሄዱት።ቅባትነት ያልበዛባቸውን የአካባቢው ባህላዊ ምግቦች እየተመገቡ ወደ ዋናው በዓል ይዳረሳሉ።በበዓሉ ዕለትም እንደዚሁ አመጋገቡ በጥንቃቄ ይሆናል።
ስለጊፋታ የተጻፉ ሰነዶችም ጊፋታ የልጃገረዶችና ወጣቶች ጨዋታ እንዳለበት ያሳያሉ።የጊፋታ በዓል በዕለቱ ልጃገረዶች አንድ ላይ ሆነው በየቡድን ቁጭ ብለው ወንዴና ሴቴን ከበሮ እየመቱ ‹‹ወላወላሎሜ›› እያሉ የሚመርጡትን ወንድ ሎሚ በመስጠት የሚመርጡበት ነው። እንዲሁም ሴቶች ለሚዜነትና ለጓደኝነት ከመረጧት ሴት ጋር በጥርስ አንድ ሎሚን ለሁለት የሚከፋፈሉበትና ስማቸውን ሲጠራሩ ‹‹ሎሜ ሎሜ›› የሚባባሉበት ጨዋታ የሚጫወቱበት ዕለት ጋዜ አሩዋ ይባላል።
በዓሉ ብዙ ጊዜ የሚከበረው እሁድ ቀን ሲሆን የአዲስ ቀን መጀመሪያ ብሥራትም ነው።የአዲሱ ዓመት 2ኛ ቀን ‹‹ታማ›› ወይም ሰኞ ይባላል።የእሳት ሰኞ መባሉ ነው።በዚህ ቀን አንዱ ከአንዱ ቤት እሳት መዋዋስና መቀባበል አይቻልም።በዓመት አንድ ቀን ወላይታዎች በራሳቸው ቤት እሳት እያነደዱ የሚውሉበት ቀን ነው፡፡
የአዲሱ ዓመት ከገባ 3ኛ ቀኑ ማክሰኞ ‹‹ጪሻ ማክሰኞ›› ይባላል።ዘመድ ለዘመድ አደይ አበባ እና ኮርማ ጪሻ የተባሉ አበባዎችን ይዘው እንኳን አደረሳችሁ እያሉ የአዲስ ዓመት ብሥራት የሚገልጽበት ቀን ነው።
የአዲስ ዓመት 4ኛ ቀን ረቡዕ ‹‹ጋዜ ኦሩዋ›› ሲባል በዚህ ቀን የሰፈሩ ወጣቶች በየመንደሩ በታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች ደጅ ተሰባስበው የግፋታ በዓል ባህላዊ ጨዋታ የሆነውን ጋዜ በጋራ ሆነው ‹‹ሀያያ ሌኬ ›› እያሉ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው የሚጫወቱበትና ልጃገረዶችን ሎሚ በመለመን የሚፈልጓትን የሚመርጡበት ጨዋታ የሚጫወቱበት ቀን ነው።እንዲህ እንዲህ እያሉ ሳምንቱን ሙሉ ይጫወታሉ።
ለመሆኑ፤ ይህ ሳይንሳዊ፣ ልማታዊ፣ ሰላማዊ እና ሌሎች አገራዊ ፋይዳ ያላቸው እሴቶች የያዘ ባህል ምን ታስቦለት ይሆን?
የወላይታ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ገቡ እንደሚሉት ጊፋታ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለመመዝገብ የቅድመ ምዝገባ ሂደት ላይ ነው።ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቅድመ ማስመዝገብ ሥራው በ2013 ዓ.ም ተጀምሯል።ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ጥናትና ውይይት እየተደረገበት ነው።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ጊፋታን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ወላይታን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ ሌሎች ሥራዎችም እየተሰሩ ነው።በአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ መስህብ ቦታዎችን ለጎብኚ ምቹ ማድረግ፣ መሰረተ ልማቶችን መሥራት፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ስለቱሪስት መዳረሻ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እየተሰጡ ነው።የአካባቢው ማህበረሰብ የራሴ ነው ብሎ በባለቤትነት እንዲጠብቃቸውና እንዲንከባከባቸው እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በወላይታ ‹‹የእግዜር ድልድይ›› የሚባለውን ጨምሮ፤ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ አጆራ ፏፏቴ፣ ፍል ውሃ፣ የዳሞታ ተራራ፣ የአዕዋፋትና ዕፅዋት ዝርያዎች የሚጎበኙ ናቸው።በተለይም ዳሞታ ተራራ እስከ አሁንም በብዙ ጎብኚዎች ሲጎበኝ እንደቆየ ተናግረዋል።
በወላይታ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ይኑሩ እንጂ የመሰረተ ልማት ችግር ፈተና መሆኑን ግን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።በተለይም ወደ አጁራ ፏፏቴ ለሚሄዱ የውጭ አገር ጉብኚዎች አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
በሌላ በኩል ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የተከሰተው የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ እና እንደ አገር የነበረው የፀጥታ ሥጋት የቱሪዝም ዘርፉ ሌላኛው መሰናክል ሆኖ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።
እንዲህ አይነት የቱሪስት መዳረሻዎች መሰረተ ልማት ይሟላላቸው ዘንድ ከመንግስትም ሆነ ከህብረተሰቡ ትኩረት ሊሰጣቸው፣ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥበቃና ክብካቤ ሊያደርግላቸው ፣መንግስትም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ሊሰራላቸው ይገባል።እነዚህ አካባቢዎች የአገርን ገጽታ ነውና የሚገነቡት የሁሉም ሀብት ናቸው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም