በአካባቢው ያሉ ዕድሎችን ፈጥኖ በመጠቀም ያምናል። ዕድሎቹ በጎና ጎጂ መሆናቸውን ቀድሞ በጽሞና መለየት እንደሚገባም ይመክራል። አቅጣጫው በወጣትነት ዘመን ስኬታማ ለመሆን ሁነኛ መንገድ መሆኑንም ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ይናገራል። ሆኖም ሳይመረምሩ በስሜታዊነት ተነሳስቶ መጠቀም ወርቃማውን የወጣትነት ሕይወት አስከፊ አደጋ ላይ ሊጥለው ስለሚችል መጠንቀቅ እንደሚገባም ያሳስባል።
ወጣቱ ይሁነኝ መሐመድ ይባላል። ተወልዶ ያደገው የአዲስ አበባ እንብርት በሆነው አራት ኪሎ ውስጥ ባሻ ወልዴ ችሎት እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ነው። በተለይ እሱ በተወለደበትና ከታዳጊነት በፍጥነት ወደ ወጣትነት የሚያሸጋግረውን ዘመን እያጣጣመ በነበረበት ወቅት አሁን የጋራ መኖሪያ ቤት የተገነባበት ባሻ ወልዴ ችሎትን ጨምሮ በአካባቢው ቁጥራቸው ቀላል የማይባል መሸታና ጭፈራ ቤቶችም ነበሩ።
ወጣቱ እንደሚናገረው እነዚህ ሁሉ በራሳቸው የሚሰጡት ዕድል ቀላል አይደለም። ዕድሉ መጥፎም ሆነ በጎ ሊሆን መቻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ እሱ በነዚህ መካከል ተወልዶ በማደግና ዕድሎቹን በአግባቡ በመጠቀም ነው ወጣትነቱን በስኬታማነት እያጣጣመ የሚገኘው።
እንደዚህ ወጣት አርአያነት ያለው የሕይወት ተሞክሮ ፍልስፍና ታዲያ ፈጣሪ ለሰው ልጅ ከፋፍሎ ከሰጠው ጊዜ የወጣትነት ዕድሜ ክልል አንዱ ነው። በሰው ልጅ የሕይወት ዘመን ውስጥም ወርቃማው የዕድሜ ክልል የሚባለውም ይሄው የወጣትነት ዘመን ነው። ወጣትነት ከታዳጊነት ወደ አዋቂነት የሚያሸጋግር አእምሯዊ፣ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ለውጦች ጎልተው የሚንፀባረቁበትም ነው። ወጣትነት ተስፈኝነትና ለውጥ ናፋቂነት ነው። ቁንጅና ጎልቶ የሚታይበትና በራሱም ውበት የሆነ አጓጊና አንፀባራቂ ዘመን ነው። በአትክልት ውስጥ እንደሚገኙ አበቦችና እንደ ፀሐይ ጮራም ይመሰላል። ወቅቱ በሰው ልጅ ዕድሜ ቀመር ውስጥ የእሳት ዘመን ተብሎ የሚጠቀስ እንደመሆኑ ውጪአዊና ውስጣዊ ፈተና የበዛበት ነው። በዚህ ዘመን የሚገኝ ምኞት ከየትኛውም ዕድሜ ክልል ከሚገኝ ዕድሜ ይልቅ ሰውን በገዛ ምኞቱ ከመጠን በላይ ወደ ጥፋት ይጎትትና ይስባል። ዘመኑ በእጅጉም አታላይ ነው። ሰው ራሱን ለመግዛት ከሚደረግ ግብግብ ጋር ገጥሞ በብርቱ ይቸገርበትና ይፈተንበታል።
ወጣት ይሁነኝ እንደሚለው በዚህ ፈታኝ ዘመን ምንም ያህል አእምሮው የበሰለና በዕውቀት የበለፀገ ሰው ራሱን መግዛት ካልቻለና በአለበት፣ በሄደበትና በደረሰበት አካባቢዎች ሁሉ የሚያገኛቸውን መልካም ዕድሎች በተገቢው መንገድ መጠቀም ካልቻለ ዋጋ አይኖረውም። በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማሕበር ዋና ጸሐፊ ሆኖ በመሥራት ላይ የሚገኘው ወጣት ይሁነኝ ከራሱና ከዕድሜ አቻዎቹ ሰበዝ መዞና፤ ካለፉት ከቀሰመው ተሞክሮ ጨልፎ እንዳወጋን የሚያገኛቸውን መልካም አጋጣሚዎች በአግባቡ ያልተጠቀመ ወጣት ለአዋቂነት ዘመኑ ስንቅ የሚሆነውን አዝላቂና አስፈላጊ ቁምነገር ሳይገነባ በፈተናዎቹ ወድቆ ይቀራል። በፍፁም የፈተናውን ድልድይ ተሻግሮ ለአዋቂነት ዕድሜ ክልል መብቃት አይችልም። አቅጣጫው ይጠፋበታል። በዚህ በፍጥነት እንደ ጤዛ የሚያልፍ ዘመን እያንዳንዱን ጊዜና ደቂቃ በጥንቃቄ ያልተጠቀመ ወጣት ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡና ለሀገሩ ወቅታዊ አሻራውን ማስቀመጥ ሳይችል በከንቱ ያልፋል። ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣትም ሆነ ሀገርን ተረካቢ ትውልድ መሆን አይችልም።
በዚህ ወቅት በደንብ የተኮተኮተና በጥንቃቄና በአስተውሎት የሚራመድ ወጣት በፍፁም በሚገጥሙት ፈተናዎች ወድቆ አይቀርም። ለራሱ፣ ለቤተሰቡ ብሎም ለሀገሩ ይተርፋል። ወደፊት ለሚጠብቀው ጊዜ በተገቢው መንገድ ለመዘጋጀትና ጥሩ ታሪክ ሰርቶ ለማለፍም ይበቃል።
አሁን ላይ እሱ እዚህ ደረጃ ለማቆናጠጥ የሚያስችለኝ እርካብ ላይ ወጥቻለሁ ብሎ ያስባል። እዚህ ደረጃ መድረስ ያስቻለው ደግሞ የሚያገኛቸውን ዕድሎች በአግባቡ መጠቀሙ መሆኑን በእርግጠኝነት ይገልፃል። ዕድሎቹን በአግባቡ የመጠቀሙን ትርክት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በአቅራቢያው በመገኘቱ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሊያጠናቅቅበት ከመቻሉ ይጀምራል። በአካባቢው የሚያገኛቸውን ዕድሎች በሙሉ በአግባቡ መጠቀም መቻሉ ከዚህ ውጪ የሚገኙ ሌሎች ዕድሎች ላይ በቀላሉ ለመንጠላጠል እንደረዱትም ይጠቅሳል።
እንዳወጋን የተወለደበት አካባቢ የሰጠውን እንደ አዲስ ዘመን ያሉ ጋዜጦች የማንበብ ዕድል ተጠቅሞ በውስጡ የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌ ማሳደር ችሏል። ዝንባሌው በወጣትነት ዘመን እጅግ አስደሳችና እንደ ምግብ ሁሉ አስፈላጊም የሆኑ የተለያዩ መፃሕፍቶች፣ መፅሔቶችን ወደ ማንበብና ሬዲዮ ወደ ማድመጥ ጎልብቷል። በዚህ መካከል በለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ ከሚተላለፉት ፕሮግራሞች አንዱ በሆነው ‹‹ትምህርት በሬዲዮ›› የገጠመውን ዕድል መጠቀም ችሏል። ዕድሉ በሬዲዮ ትምህርቱ ‹‹እንደምን አላችሁ ተማሪዎች›› ሲባል ‹‹እንደምን አሉ መምህር›› የሚለውን አንድ ክፍል በዚያው በሬዲዮ ሞገድ ለተማሪዎች በድምፅ ማስተላለፍ ነበር። ቀስ ብሎም ‹‹እንደምን አላችሁ ተማሪዎች እንደምን አሉ መምህር›› የሚሉትን የሁለቱንም ክፍል ድምጾች እሱው ራሱ በማስተላለፍ የሬዲዮ የድምፅ አስተማሪ ለመሆን በቃ። በቴሌቪዥን በሚተላለፉ የተለያዩ ማስታወቂያዎች ላይ ይሳተፍ ጀመረ። ይሄኔ የተፈሪ መኮንን ተማሪ ነበር። ቢሆንም ትምህርቴን እስክጨርስ ልቆይ አላለም። በያንዳንዱ ደቂቃ በሚገጥመው ዕድል ሁሉ በራሱ ሌሎች ዕድሎችን በመፍጠርና በማመቻቸት ተጠቅሞ ነው ያለፈበት። ‹‹የወጣቶች የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሊኖር ይገባል››የሚል ሀሳብ የፀነሰበት ከተጠቀመበት አንዱ ነው። አሁን በዋና ፀሐፊነት እየሰራበት ወደ የሚገኝበት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ሊያመጣው የቻለውም ይሄው ሀሳብ ነው።
ወጣቱ እንዳጫወተን ያኔ የወጣቶች የቴሌቪዥን ፕሮግራም አልነበረውም። ነበረው ቢባልም ቶክ ሾው ዓይነት ነው። በመሆኑም ፕሮፖዛል አዘጋጅቶ እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት ጀመረ። ግን ወዲያው ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም። በወቅቱ አዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ለሚሰራው ጓደኛው ፕሮግራሙን ከቶክ ሾውነት አሻግሮ የወጣቶች የቴሌቪዥን ፕሮግራም የማድረግ ዕቅድ እንዳለው ነገረው።ጓደኛው የቴሌቪዥን ጣቢያውን ኃላፊ አግኝቶ እንዲያነጋግር ረዳውና ፕሮፖዛሉ ተቀባይነት አግኝቶ በማህበሩ አማካኝነት በመግባት በጣቢያው የወጣቶች ቴሌቪዥን ፕሮግራም ተጀመረ። ይሁነኝ እንደሚለው አሁን ላይ በዋና ፀሐፊነት እየሰራበት ወደ አለው አዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የመጣውም ይሄንኑ የወጣቶች የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመሥራት ነበር። ለአንድ ዓመት ሲሰራ ቆየና በዚሁ ሳቢያ የማህበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ ቀጠለ። ፓን አፍሪካ የርቀት ትምህርትአካዳሚ፣ አድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንዲሁም የቴሌቪዥን ማስታወቂዎችን ሥራዎችን ሲሰራም ቆይቷል። በዚህ መካከል በሌላ ሥራ ምክንያት ከማህበሩ ቢለቅም የማህበሩ አባል በመሆኑ በምክር ቤቱ 7ኛ ጉባኤ ለዋና ፀሐፊነት ተመርጦ ወደ ማህበሩ በመመለስ ነው አሁን ወዳለበት ዋና ፀሐፊነት ዕድገት ደረጃ ሊደርስ የቻለው።
‹‹ተሰጥኦ አንድ ጉዳይ ነው›› የሚለው ወጣቱ ሆኖም ዋንኛው ወጣቱ በራሱ ሂደት ውስጥ ሲጓዝ ተሰጥኦ የሚፈጥረው ዕድል መኖሩና ይሄን ዕድል በአግባቡ መጠቀም መቻል እንደሆነም ያሰምርበታል። ወጣቱ እንደሚናገረው፣ ሰዎች የተለያዩ ተሰጥዖዎች ባለቤቶች ናቸው። ተሰጥዖ በዕውቀት መጠናከር እንዳለበት ያምናል። ‹‹መማር በእጅጉ አስፈላጊ ነው። መማር በመደበኛ ትምህርት ቤት ገብቶ ብቻ ሳይሆን ሕይወት ራሱን የቻለ ትምህርት ቤት ነው። የምናደርጋቸው ግንኙነቶች፣ የምንሄድባቸው ቦታዎች፣ የምንሳተፍባቸው ተግባሮች ዕውቀት የምናገኝባቸውና ትምህርት ቤቶቻችን ናቸው። በመሆኑም ከነዚህ በሚገኙ ዕውቀቶች ራስን ማደርጀት፣ መወያየት፣ መስማት፣ ሀሳብ መስጠት አስፈላጊ ነው። በዚህ መሠረትም ወደ ሚፈለገው ደረጃ መድረስ ይቻላል›› ይላል።
ወጣቱ እንደሚመክረው ይሄ የሚደረስበት እያንዳንዱ ጉዳይ ግን ራሱን የቻለ ምቹ ዕድል ብቻ አለመሆኑንም መገንዘብ ይገባል። እንቅፋቶች እንዳሉትም ማሰብ ተገቢ ነው። ወጣቱ ያሰበውን ለማሳካት የገጠሙ ተግዳሮቶችን በምን መልኩ ነው ማለፍ ያለብኝ በማለትም ራሱን መጠየቅና ወደ ውስጡ ማየት ይገባዋል።
ሀገራችን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በየዘመኑ የሚታወቅ ነው። ወጣቱ ለዚህ ይዞ የሚነሳውን ሀሳብ ከውጤት ላይ ማድረስ የሚችለው ግን አንድም እራሴ የራሴን ጥረት ሳደርግ፤ ሁለትም የሰዎችን አቅም፣ ዕውቀት፣ ግብዓት ስቀበል፣ የሰዎችን ምክር ስሰማ፣ የልምድ ልውውጥ ሳደርግና ለመለወጥ ቁርጠኛ ስሆን ነው ብሎ ማሰብ እንዳለበትም ምክሩን ይለግሳል።
‹‹ባለ ራዕይና ሀገር ተረካቢ እንደመሆኔ ይሄ በሕይወቴ ጉዞ ውስጥ የደረስኩበት አንድ ደረጃ እንጂ የመጨረሻው እንዳልሆነም ይገልፃል። በሕይወት እስካለሁ ድረስ ገና ከዚህም በላይ መድረስ አለብኝ ብሎ ማሰብም ተገቢ መሆኑን ይናገራል። አሁን ካለበት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፀሐፊነት በቀጣይ የራሱን ሥራ ሊሰራ ወይም በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ሊሳተፍ እንደሚችል ያስባል። አውሮፓ ሄዶ ፈረንሳይን፣ ቤልጂየምን ቃኝቷል። ከአፍሪካም ኡጋንዳን ጎብኝቷል። በነዚህ ሀገራት ያየውንና በሀገር ውስጥ የሌሉትን እየተማረና ራሱን እያሰለጠነና እያበቃ በመምጣት አሁን የደረሰበት ደረጃ መድረስ መቻሉን ራሱን አብነት በማድረግ ይገልፃል።
ወጣቱ እንደሚናገረው ለመለወጥ ዕውቀትና ዝግጁነት ያስፈልጋል። ‹‹ለመለወጥ የሚያስችል ብዙ ዕድል ያለው ወጣት ይኖራል። ሆኖም ይሄን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ መለወጥ አይቻልም። ምንም ዕድል የሌላቸው ወጣቶች ዕድሎችን ፈልገው አግኝተው የሚቀየሩበት ሁኔታ መኖር አለበት። ማንኛውም ወጣት ሊቀየር የሚችለው በእንደዚህ ዓይነት መልኩ ነው›› ይላል። እንደይሁነኝ ማብራሪያ፣ የተሟላና ያለቀለት ተሰጥኦ ማንም ጋር የለም። ታላላቅ የምንላቸው ታላላቅና ባለታሪክ ሰዎችም ባለታሪክነትና ታላቅነት ደረጃ ላይ የደረሱት በጥረታቸውና አካባቢያቸው ላይ ያለውን ምቹ ዕድል ውስጣቸው ካለው አቅምና ዕውቀት ጋር በማዋሃድ ተጠቅመው ነው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉት ብሎ ያምናል። ወጣቶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ይሄን ማድረግ እንዳለባቸውም ይመክራል። ይሄን ለማድረግ ከታች ጀምሮ በየደረጃው የሚገጥሟቸውን ችግሮች በራስ አቅም መቅረፍ ያስፈልጋል። ችግሮቹን ከሌሎች ትምህርት በመውሰድ፣ ከሌሎች ጋር በመግባባት፣ በመነጋገር፣ በማድመጥ፣ በመማር መቅረፍ ይቻላል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም