በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው የተጓተተውን የሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገድን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
ከሞጆ ተነስቶ ሀዋሳ ከተማን መዳረሻው የሚያደርገው የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት በ2008 ዓ.ም ነበር ግንባታው የተጀመረው።
201 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን መንገድ በፍጥነት ለማጠናቀቅም በአራት ምዕራፍ በመከፋፈል ለመገንባት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
ከሞጆ መቂ፣ ከመቂ ባቱ፣ ከባቱ አርሲ ነጌሌ እና ከአርሲ ነጌሌ ሃዋሳ ለተለያዩ ተቋራጮች የተሰጠው ፕሮጀክት፥ የወሰን ማስከበር ችግር፣ በግብዓት አቅርቦትና መሰል ችግሮች ሳቢያ በፍጥነት መገንባት አለመቻሉን የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል።
የሞጆ መቂው የመንገዱ አንድ ምዕራፍ አሁን ላይ አፈጻጸሙ 70 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ በአንጻሩ 37 ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው ከመቂ ባቱ መንገድ ውስጥ እስካሁን 14 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ብቻ መስራት እንደተቻለ ነው የተናገሩት።
57 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ከባቱ አርሲ ነጌሌ ከሚደርሰው የፍጥነት መንገዱ አካልም ከ1 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ስራውን ማከናወን አልተቻለም።
በሌሎቹ የመንገዱ አካል የተስተዋለው ችግርም በባቱ አርሲ ነጌሌ መንገድ ተደግሟል የሚሉት ዳይሬክተሩ፥ የመንገዱ ግንባታ የተደቀነበት ስጋት እንዳይቀጥል መፍትሄ ተቀምጧል ብለዋል።
ከየአካባቢው መስተዳድር ጋር ውይይት በማድረግም በቅርብ ክትትል ፈጣን መንገዱን ለማጠናቅቅ ባለስልጣኑ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
አሁን ላይም በፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም ያጋጠመውን የወሰን ማስከበርና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛልም ነው ያሉት አቶ ሳምሶን ወንድሙ።
201 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሞጆ – ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ በ14 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እየተገነባ ሲሆን በ2013 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
እንደ ኤፍ ቢ ሲ ዘገባ የመንገዱ ግንባታ የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ከማሳለጥ ባለፈም ቀጠናዊና አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር ግብ ላላት አፍሪካ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።