የኪነ ጥበብ ሥራ ዘመን ተሻጋሪ ነው። አንዳንድ ሥራዎች ሳይቋረጡ ዘመን በተሸጋገረ ቁጥር ከተፈጥሮ እኩል ይታወሳሉ። መስከረም ሲጠባ ተደጋግሞ በብዙዎች አንደበት ይደጋገማል፤ የታላቁ የጥበብ ሰው መንግስቱ ለማ ግጥም።
ማን ያውቃል!
የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ይህ ግጥም የእንቁጣጣሽና የመስቀል በዓላት ሲደርሱ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ፕሮግራም ማስጀመሪያ ነው። በእነዚህ በዓላት የጋዜጦችና መጽሔቶች የጽሑፍ ማስጀመሪያ ነው።
ይህ ግጥም አደይ አበባ እና የመስቀል ወፍ ባየን ቁጥር ትዝ የሚለን፤ የመስከረም ወር በጠባ ቁጥር ከሰዎች አፍ የማይጠፋው። ከመደጋገሙ የተነሳ የህዝብ ሥነ ቃል የሚመስላቸውም ይኖሩ ይሆናል። የዚህ ግጥም ፀሐፊ መንግስቱ ለማ ይባላል። መንግስቱ ለማ የተለያዩ ቅጽል ስሞች ያሉት እና ብዙ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ያሉት ነው። እስኪ ይህን የመስከረም ወር አስታዋሽ ገጣሚ ሌሎች ሥራዎችንም እንይለት።
መንግስቱ ለማ ‹‹አብዬ መንግስቱ ለማ›› በሚለው ነው በብዙ ቦታዎች የሚጠራው። አሁንም በሌላ መጠሪያ ደግሞ ‹‹አሳቢው መንግስቱ ለማ›› ሲባልም እንሰማለን። ለመሆኑ ከሌሎች ሰዎች በተለየ ለምን ‹‹አሳቢው›› ተባለ?
ከሁለት ዓመት በፊት ነው (ቀኑን በትክክል ማስታወስ አልቻልኩም) ደብረ ያሬድ አሳታሚ ድርጅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር በዕውቁ ፀሐፌ ተውኔት፣ ገጣሚና መምህር መንግስቱ ለማ ሥራና ህይወት ላይ የሚያተኩር ልዩ የውይይት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ነበር። የውይይቱ ተሳታፊ ነበርኩ። በውይይቱ ላይ የስነ ጽሑፍና ፎክለር መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ መንግስቱ ለማ ‹‹አሳቢው›› የተባሉበትን ምክንያት እንዲህ ገልጸው ነበር።
‹‹ሰው ከእንስሳት የሚለየው አሳቢ በመሆኑ ነው፤ አቶ መንግስቱ ለማ ደግሞ ሰው ስለሆኑ አሳቢ ናቸው። ታዲያ ምን አዲስ ነገር አለውና ነው አሳቢ የሚባሉት?›› ብለው በጥያቄ ይጀምሩና ምክንያቱን ሲናገሩ፤ የመንግስቱ ለማ ማሰብ ከሌላው ለየት ያለ ስለሆነ ነው። አብዛኛው ሰው የሚያስበው በትምህርት ቤት ስለሚማረው ነገር ወይም ስለሚሰራው ሥራ ሊሆን ይችላል። ግንበኛው ስለግንቡ፣ ሐኪሙ ስለህክምናው፣ ሁሉም ስለአንድ ሙያ ያስብ ይሆናል። መንግስቱ ለማ ግን ስለብዙ ረቂቅ ነገሮች ሁሉ ያስባሉ። ስለጥበብ በጥልቀት ያስባሉ። ‹‹ነገሮችን ከመሠረቱ የመመርመርና መሠረታዊ ጥያቄዎች እያነሱ ስለ ማህበራዊ ልማት የመመራመር አዝማሚያቸው በድርሰቶቻቸውና በአንዳንድ መጣጥፎቻቸው ውስጥ የተንሰራፉ ናቸው›› ይላሉ ዶክተር ፈቃደ በጽሑፋቸው።
በተማሪዎቻቸው እንኳን እንደሚነገርላቸው ሲያስተምሩ ከብዙ ነገር ጋር አያይዘው ነው። በቤታቸው ውስጥ ብዙ ጊዜ ይመሰጣሉ። እንዲያውም ታመው እንኳን ስለህመማቸው ከመጨነቅ ይልቅ የጥበብ ነገር ነው የሚያስቡት። በአንድ ወቅት ታመው ሆስፒታል ተኝተው ነበር። አየር እንዲያገኙ ተብሎ በአልጋ (ስትሬቸር) እየተገፉ ሲሄዱ ወደላይ አንጋጠው ያያሉ፤ ምን እያደረጉ እንደሆነ ሲጠየቁ የሰማዩን ደመና፤ ‹‹ይህን ነገር እስከዛሬ ከዚህ አንግል አይቸው አላውቅም ነበር›› ብለው ተናገሩ።
አብየ መንግስቱ ለማ በውጭ አገር እያሉ የአገራቸውን ኪነ ጥበብ በጣም ነበር የሚኮሩበት፤ ጥልቅ ፍልስፍና እንዳለው ለውጭ አገራት ሰዎች ያስረዱ ነበር። በተለያዩ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ጋዜጦች ላይ ስለአገራቸው የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይጽፉ ነበር። መንግስቱ ለማ በመምህርነት ሙያቸውም በተማሪዎቻቸው ተወዳጅ ነበሩ።
ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት በ60 ዓመታቸው ያረፉት ከያኒ መንግሥቱ ለማ የሊቁ የአለቃ ለማ ኃይሉ ልጅ ሲሆኑ፣ የቤተ ክህነት ትምህርትን ጠንቅቀው ማጥናታቸውን ታሪካቸው ያስረዳል። ዕውቀትና ልምድን ለተተኪው ትውልድ ከማስተላለፍ አንፃር በተለይ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ በ1970ዎቹ መጨረሻ የታተሙት ‹‹የግእዝ ቅኔያት የሥነ ጥበብ ቅርስ›› በሳቸው አጋፋሪነት መዘጋጀታቸው ይወሳል።
ከቀደምት የግጥምና የተውኔት ሥራዎቻቸው መካከል የግጥም ጉባኤ፣ የአባቶች ጨዋታ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ጠልፎ በኪሴ፣ ፀረ ኮሎኒያሊስት፣ ባለካባና ዳባ፣ ሹሚያ፣ እንዲሁም የታዋቂውን ሩሲያው ደራሲ አንቷን ቼኮቭ ተውኔትን ‹‹ዳንዴው ጨቡዴ›› ብለው የተረጐሙት ተጠቃሾች ናቸው።
በባህልና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገለገሉት ከያኒ መንግሥቱ በ1959 ዓ.ም. በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ተሸላሚ ነበሩ።
መንግሥቱ ለማ ከውጭ አገር ቆይታቸው ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ የተሰማራሩት ወደ መንግስት ሥራ ሲሆን በህንድ አገር ዲፕሎማት ሆነው ከሄዱ በኋላ ምናልባትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ ኮሜድ ተውኔት «ጠልፎ በኪሴ”ን ደርሰዋል:: ከዚያ በኋላ የደረሷቸው እነ «ያላቻ ጋብቻ»፣ «ጸረ-ኮሎኒያሊስት»፣ «ባለካባና ባለዳባ» የመንግስቱን ስም በኢትዮጵያ የስነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሽ ካደረጓቸው ስራዎች መካከል ናቸው። በተጨማሪም «The bear» የተሰኘውን እና የታዋቂው የሩሲያ ደራሲ አንቷንቼኾቭ ተውኔት የሆነውን «ዳንዴው ጨቡዴ» በሚል የተረጎመ ሲሆን የጄ.ቢ. ፕሪስትሊን «The Inspector Calls»ን ተርጉመው ለመድረክ አብቅተዋል።
‹‹ታዛ›› የኪነ ጥበብ መጽሔት ስለአብየ መንግስቱ ለማ በሪቻርድ ፓንክረስት የተጻፈ ጽሑፍ አስነብቦ ነበር። አብየ መንግስቱ ለማ ገጣሚ ነው፣ ፀሐፊ ተውኔት ነው፣ ፈላስፋ ነው፣ የታሪክና ባህል አዋቂ ነው፤ በሥራዎቹ ሁሌም ጥንቃቄን ይፈልጋል። ሪቻርድ ፓንክረስትም ከያኒውን እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል።
መንግሥቱ ሁልጊዜም እንከን አልባ ሆኖ መታየት የሚፈልግ ሰው በመሆኑ፤ ሥራዎቹ የህትመት ብርሃን ከማየታቸው አስቀድሞ ደግሞ ደጋግሞ ለማሻሻል ይሞክራል። ወደ በኋላ አንዳንድ የድርሰት ሥራዎቹን ረቂቅ ያሳየኝ ነበር። እናም የድርሰት ሥራውን ለእኔ ካሳየኝ በኋላ ደጋግሞ ያሻሽለዋል። አንዳንድ ጊዜም የተውኔቱን ገቢር ቁጥር ይቀንሰዋል ወይም ይጨምረዋል። መንግሥቱ ሥራዎቹን ደጋግሞ እንደሚያሻሽል እና እንደሚያስተካክል በቀላሉ መረዳት የምችለው በገፁ ላይ በሚታየው የእስክሪቢቶ ቀለማት ነው። መንግሥቱ ሥራውን ዳግም ሲያሻሽል ቀድሞ ከተጠቀመበት ብዕር የተለየ ቀለም ያለው ብዕር ስለሚጠቀም ሥራው በምን ዓይነት የአርትኦት ሂደት እንዳለፈ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል።
የሪቻርድ ፓንክረስት ምስክርነት ይቀጥላል።
‹‹እዚህ ላይ በአጽንዖት ሊነገር የሚገባው፤ መንግሥቱ የቲያትር ሙያን በተመለከተ አንዳችም አማተራዊ የነገር አያያዝ ያልነበረው መሆኑ ነው።
እኔ ከኢትዮጵያ ወደ እንግሊዝ በሄድኩ ቁጥር ለንደን ከሚገኙት የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች ጎራ ብዬ በድራማ አዘገጃጀት ላይ ያተኮሩ አዳዲስ ሥራዎች መውጣታቸውን፤ እንዲሁም ለህትመት የበቁ አዳዲስ የአውሮፓ የተውኔት ድርሰቶች መኖራቸውን እንዳይለት ይጠይቀኝ ነበር። መንግስቱ በቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት (በአጠቃላይ በቢቢሲ) ይቀርቡ የነበሩ የራዲዮ ተውኔቶችን በከፍተኛ ጉጉት ይከታተል ነበር። ሆኖም በቢቢሲ የሚተላለፉት የራዲዮ ተውኔቶች ከፖለቲካ ዝንባሌ የተጠበቁ እንዳልሆኑ አሳምሮ ያውቅ ነበር። እናም የቀዝቃዛውን ጦርነት ዘመን በማስታወስ፤ በዓይኑ ጠቀስ እያደረገኝ ሌላው ቀርቶ በቢቢሲ የአየር ትንበያ ዝግጅት ጭምር ‹ከምሥራቅ አውሮፓ ይነፍስ የነበረው ቀዝቃዛ ንፋስ…› የሚል አገላለጽ ይሰማ እንደነበር ደጋግሞ አጫውቶኛል››
በነገራችን ላይ በአሁኑ ጊዜ ይኑር አይኑር ባላውቅም ‹‹ጠልፎ በኪሴ›› የተሰኘው የመንግስቱ ለማ የተውኔት ሥራ የ12ኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሐፍ ላይ (እስከ 2004 ዓ.ም) ማስተማሪያ ነበር።
የሙያ አጋሮቹ በተለያየ መድረክ ሲናገሩት እንደሰማነው የአንደኛው የመንግስቱ ለማ ግጥም መነሻ ሃሳብ እውነተኛ ገጠመኝ ነው። ግጥሙም የሚከተለው ነው።
በጠራ ጨረቃ በእኩለ ሌሊት
ዓይኖቿ እያበሩ እንደ ከዋክብት
‹‹ሳማት ሳማት›› አሉት ‹‹ዕቀፍ ዕቀፋት››
አላወላወለም፤ ወጣቱ ታዘዘ፤
ወገቧን አንገቷን በእጅና እጁ ያዘ፤
ከንፈሩ በረአድ ወደ አፏ ተጠጋ።
ምንም እንኳ ጡቷ እንደ ሾህ ቢዋጋ፤
ጣቷ በመሆኑ የጉማሬ አለንጋ፤
ጆሮው ግንዱን ሰማው በጥፊ ሲናጋ።
በጠራ ጨረቃ በእኩለ ሌሊት
ዋ! ጀማሪ መሆን፤ ዋ ተማሪነት፤
ዋ ትእዛዝ መፈጸም፤ ዋ ምክር መስማት!
መንግስቱ ለማ ይህን ግጥም የገጠመው በእንግሊዝ አገር እያለ አንዲት ያፈቀራት ሴት በጥፊ መታው እንደሆነ ራሱም ተናግሯል ተብሏል። ሙሉ ታሪኩንም ግጥሙ ራሱ ገላጭ ነው።
በመጨረሻም ‹‹ማን ያውቃል›› ስለተሰኘውና በመስከረም ወር በተደጋጋሚ ስለሚጠራው ግጥሙ ትንሽ ልበልና ልጨርስ።
የአደይ አበባ እና የመስቀል ወፍ ነገር ለብዙዎች ምስጢር ነው። አደይ አበባ የቱንም ያህል የበጋ ዝናብ ቢኖር አይበቅልም፣ የቱንም ያህል መስኖ ያለበት ቦታ ቢሆን አይበቅልም። ሌላው የተክል አይነት ሁሉ ውሃ ካገኘ ይበቅላል፤ ያብባል፤ አደይ አበባ ግን የሚያብበው የመስከረም ወር ላይ ብቻ ነው።
በተመሳሳይ የመስቀል ወፍ የምትባለዋም እንደዚሁ ናት። በበጋም ወቅትም በክረምት ወቅትም አትታይም። የምትታየው በመስከረም ወር ነው። የት ቆይታ እንደምትመጣ አይታወቅም። ይህ ምስጢር ቢገርመው ነው ከያኒው መንግስቱ ለማ እንዲህ ሲል የጠየቀ
ማን ያውቃል?
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ!
‹‹የግጥም ጉባዔ›› መንግሥቱ ለማ 1950 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2014