ዛሬ የመስቀል ደመራ በአል በመላ ኢትዮጵያ በደማቅ ስነ ስርአት ይከበራል። በአሉ የሚከበረው ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘቶችን በተላበሰ መልኩ በደማቅ ስነስርአት ነው፤ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ በልዩ ድምቀት በአደባባይ ይከበራል።
የመስቀል ደመራ በአል መንፈሳዊ እና ባህላዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ከዚህ ባሻገርም ለቱሪዝሙ ዘርፍ እድገትና የሀገር ገጽታን ለመገንባት ያለው ፋይዳም ከፍተኛ ነው።
የመስቀል ደመራ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ሳይንስና ባህል ድርጅት በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እንዲሰፍር ተደርጓል። በዛሬው የሳምንቱ በታሪኩ አምዳችንም የዚህን ታላቅ በአል ታሪክ እናስቃኛችሁዋለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ ማስቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው መሆኑን ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ።
መስቀሉ በተቀበረበት አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በዚህ ስፍራ ላይ በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ። በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት የነበረ ቢሆንም፣ ማውጣት ሳይችሉ ኖሩ። በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ። የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖረ።
በ326 ዓ.ም. የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ እየሩሳሌም ተጓዘች። እዚያም ደርሳ ጉብታዎችን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም። በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበርና አንድ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትንና የተጣለበትን አካባቢ ያውቅ ዘንድ ጠየቀችው። ሽማግሌውም “አንቺም በከንቱ አትድከሚ፤ ሰውንም አታድክሚ ይላታል።
እንጨት አሰብስበሽ እጣን አፍሽበት፤ በእሳትም አያይዢው፤ የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው፤ በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ” አላት፤ እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። እንጨት ደምራ በዚያ ላይም ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ። ንግሥት እሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች።
በዚህም መሠረት ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ። የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል።
ግማዴ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ. ም. ነበር። ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት። ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርራይሶ እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ። ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የእየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት። በኋላም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ወይም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ለመስቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ ተመርቆ የገባው (ቅዳሴ ቤቱ) የተከበረው መስከረም 17 ቀን 327 ዓ.ም. ነው።
በቤተ ክርስቲያን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታ በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት 10 ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የከበረው መስከረም 17 በመሆኑ ነው።
መስቀሉ እንዴት ወደ ሀገራችን መጣ? የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል 47ኛን በወቅቱ የነበረው የግብጽ ፈርዖን አሠራቸው፤ ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን “የእኔን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ በግብጽ መኖር አትችሉም” ብሎ ከአቅማቸው በላይ ግብር ጣለባቸው።
መከራው የጸናባቸው የግብጽ ክርስቲያኖች “ከደረሰብን መከራ ትታደገንና ሊቀጳጳሳችንን ታስፈታልን ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተማጽነናል” ሲሉ ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው።
አፄ ዳዊት “ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት” ብለው አዋጅ በማወጅ ጦርነት ለማካሔድ ወስነው ወደ ካርቱም ጦራቸውን አዘመቱ። ካርቱም ደርሰው ሁኔታውን ሲያዩ ጦርነት ከማካሔድ ለምን የዐባይን ወንዝ አልገድብም ብለው ወሰኑ። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። ይህን የሰሙ የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን እልጋዴን መኳንቱን ሰብስበው “ምን ይሻለናል ብለው ምክር ያዙ” የዐባይን ወንዝ ከምናጣ “ሊቀጳጳሱን አቡነ ሚካኤልን እንፈታለን በክርስቲያኖችም ላይ መከራ አናደርስም” ብለው ቃል በመግባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን ሁለት እልፍ ወቂት ወርቅ እጅ መንሻ አስይዘው ለዐፄ ዳዊት አማላጅ ላኩ።
ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም “ብርና ወርቅ አልፈልግም ጌታዬ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ነው የምፈልገው” አሏቸው። የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን አልጋዴንም የሀገራችን ሕዝብ በውኃ ጥም ከሚያልቅ ብንስማማ ይሻለናል ብለው መስከረም 10 ቀን 1395 ዓ.ም. ከመስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ጨምረው ሰጧቸው። በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን የተቀጸል ጽጌ /የዐፄ መስቀል/ እየተባለ የሚከበረው ይህን መነሻ በማድረግ ነው። ግማደ መስቀሉም በአሁኑ ወቅት በግሽን ማርያም ገዳም በአግዚአብሄር አብ ቤተክርስቲያን ይገኛል።
መስቀሉ የገኘው ንግስት እሌኒ መስቀሉን ለማስወጣት ለሰባት ወራት/ ከመስከረም 17 ቀን እስከ መጋቢት 10 ቀን ድረስ/ ተቀብሯል የተባለበትን ስፍራ አስቆፍራ ነው፡፡ ዛሬ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህን ታሪክ ተከትሎ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህ የመስቀል ደመራ በአል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ተቋም ወይም ዩኔስኮ ኅዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም በአዘርባጃኗ መዲና ባኩ ባደረገው ስብሰባ ይህን በማይደሰሱ የአለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።
ስለቅርሱ ምርመራ ያደረገው ኮሚቴ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ እንደተመለከተው፤ የመስቀል ክብረ በዓል የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን የያዘ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ መምጣቱና በአገሪቱ ማኅበራዊ አንድነትንና የእርስ በርስ ትስስርን፣ ብዝኃነትን የሚያንፀባርቅ፣ በበርካታ ብሔረሰቦች ባህሎች መካከል ትስስርን የፈጠረ በመሆኑ ዓለም አቀፍ መስፈርት መሟላቱንም አስታውቋል።
በወቅቱ ቅርሱን ለማስመዝገብ የተዘጋጀ የኢንቬንተሪ ፎርማት እንደሚያሳየው፤ የመስቀል በአል በየቦታው የተለያየ መጠሪያዎች አሉት። ለምሳሌ በሰሜኑ አካባቢ መስቀል ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ በከምባታ መሰላ በየም ሄቦ በጉራጌ መስቀር በኦሮሞ ጉባ ተብሎ ይጠራል ይላል።
የመስቀል በአል ባለቤቶችም ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ናቸው። በአሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል የበለጠ መንፈሳዊ ይዘት ሲኖረው በደቡቡ ደግሞ የበለጠ ማህበራዊ ቅርጽ አለው። በአሉ አመቱን ሙሉ ተራርቀው የሰነበቱ ማህበረሰቦች የሚገናኙበት፤ የተጣሉ ሚታረቁበት፤ የአዲሱ አመት እቅድ የሚታቀድበት፤ ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁበት እና ሀላፊነት የሚቀበሉበት ነው። ከዚህም በላይ ሰዎች ተሰባስበው የሚደሰቱበት ወቅት ነው።
በተቋም ደረጃ የቅርሱ ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስትሆን ቅርሱን የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ደግሞ ኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው።
በአሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም ከፍተኛ ነው። በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ብዙዎች በአሉን ለማክበር ወደ ቤተሰባቸው የሚመለሱ ሲሆን፣ የከብት እርድም ይፈጸማል። በወቅቱ የሚፈጸመው ግብይት ኢኮኖሚው እንዲንቀሳቀስ እድል ይፈጥራል። በአዲስ አበባ የሚኖረው ደማቅ አከባበር በበኩሉ ብዙ ቱሪስቶችን የሚስብ በመሆኑ ለቱሪዝሙ እድገት ፋይዳ አለው። በአሉ ከአለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ከገባ በኋላ የጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩም በተለያዩ ጊዜያት ተገልጧል።
በአሉ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ በደማቅ ስነስርአት ይከበራል። የዘንድሮውን የመስቀል ደመራ በአል ደግሞ የተለየ አንደሚሆን ይጠበቃል። ምክንያቱ ደግሞ በአሉ የሚከበርበት የመስቀል አደባባይ በአዲስ መልክ መገንባቱ ነው።
በየአመቱ መስከረም 16 ቀን ከሰአት አደባባዩ በብዙ መቶ ሺ በሚቆጠሩ አማኞች፣ ቱሪስቶች፣ ወዘተ የሚሞላ ሲሆን፣ በእለቱ የሚታዩት መንፈሳዊ ትእይንቶች የብዙ ቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው። ከአዲስ አበባው ባልተናነሰ በሌሎች የክልል ከተሞች ዋነኛ አደባባዮችም ላይ መሰል ትእይንቶች ይካሄዳሉ። በየአብያተ ክርስቲያናቱ እና መኖሪያ ቤቶችም መሰል ደማቅ አከባበሮች ይታያሉ። የመስቀል አደባባይ መታደስ እና መዋብ ለአደባባዩ ውበት ከመጨመር ባለፈ ይህ አለም አቀፍ ቅርስ የሆነ በአል ድምቀቱ እንዲጨምር እና ጎብኚዎችም እንዲጨምሩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2014