የጊኒ ዎርም በሽታ የተገኘው እአአ በ1978 ዓ.ም ነው፡፡ በትሮፒካል አካባቢዎች በሽታው መድኃኒት የሌለው
ሲሆን፣ ከ20 ወረርሽኝ በሽታዎች መካከል አንዱ ሆኖም በዓለም ጤና ድርጅት ተመዝግቧል፡፡ ከኩፍኝ ቀጥሎ ያለ መድኃኒት የአኗኗር
ዘይቤን በመቀየር ብቻ ሥርጭቱን መከላከል የሚቻል በሽታ ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የጊኒ ዎርም እንቁላሉን ኩሬዎች ውስጥ የሚጥል ሲሆን፣ ሰዎች የኩሬውን ውሃ ሲጠጡ እንቁላሉን አብረው ይጠጣሉ፡፡ በዚህም በቀላሉ በበሽታው ይያዛሉ፡፡ እንቁላሉ ሰውነት ውስጥ ይፈለፈልና ትሉ ምንም አይነት የህመም ስሜት ሳያስከትል በሰውነት ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ይቆያል፡፡ ከዚያም በብዛኛው ከወገብ በታች የሆነን አካል እያሳከከ ይቆያል፤ ያቆስላል፡፡ በመጨረሻም ረዥም ትል ይወጣል፡፡ በዚህ ወቅት ታማሚው በአፋጣኝ ሕክምና ካላገኘም ለሞት ይዳረጋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤በኢትዮጵያ በ1986 ዓ.ም. ስለ በሽታው በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት በወቅቱ 1ሺ 129 ሰዎች በበሽታው ተይዘው ተገኝተዋል፤ በ99 አካባቢዎችም መስፋፋቱ ታውቋል፤የጋምቤላ ክልል ከተጠቀሱት አካባቢዎች አንዱ ነበር ፡፡
በኢትዮጵያ በሽታውን ለማጥፋት/ ለመከላከል ባለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የሥርጭት መጠኑን 99 በመቶ መግታት ተችሏል፡፡ በበሽታው አዲስ የተያዘ ሰው ሪፖርትም ላለፈው አንድ ዓመት አልቀረበም ፡፡
ይህ አፈጻጸም ሀገሪቱን ከጊኒ ዎርም ነፃ ለመሆን ጫፍ ላይ እንድትደርስ ቢያስችላትም፣በቅርቡ ግን ወረርሽኙ እያገረሸ መሆኑን የሚገልጽ ዜና ከወደ ጋምቤላ ተሰምቷል፡፡ ይህም ሀገሪቱን ወደ ኋላ እንድትመለስ እያደረገ ይገኛል።
ዘንድሮ የተከሰተው የጊኒ ዎርም ወረርሽኝ ካለፉት ጊዜያት የተለየ ሆኗል፡፡ የተለየ ያደረገውም ከሰዎች አልፎ በእንስሳት ላይ መታየቱ ነው፡፡ በበሽታው ውሻና ዝንጅሮዎች የተጠቁበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡
ሊጠፋ ተቃርቦ የነበረው የጊኒ ዎርም በሽታ በጋምቤላ ክልል በሁለት ወረዳዎች ጎግና አበቦ በሚገኙ የእርሻ ቦታዎች በእነዚህ እንስሳት ላይ ታይቷል፡፡ በሽታው በእንስሳቱ ላይ ይታይ እንጂ፣ በአካባቢው ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው በግብርና ስራ ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞችም ስጋት ሆኗል፡፡
በአካባቢው ባለሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ሲሆን፣በአንድ ባለሀብት ኢንቨስትመንት ብቻ እስከ 300 የሚደርሱ ሠራተኞች ይቀጠራሉ፡፡ ለሠራተኞቹ የንፁህ መጠጥ ውኃ ማቅረብ የግድ ነው፤ የመጀመሪያ ህክምና ዕርዳታን የመሳሰሉ ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ ክሊኒኮችም እንዲሁ ያስፈልጋሉ፡፡ በየእርሻዎቹ እነዚህን ማሟላት የግድ ቢሆንም፣ ባለሀብቶቹ ይህንን ሳያሟሉ ፈቃድ እንደሚያገኙ ነው ያነጋገርናቸው የሚመለከታቸው አካላት የሚገልጹት፡፡ ይህም በሽታው በሰዎችም ላይ እንዲከሰት ያደርጋል የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የበሽታው ስርጭት ስላለበት ደረጃ ለመገንዘብ የሚያስችል ጉብኝት በጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የኢንቨስትመንት እርሻዎ ላይ ሰሞኑን እንዲካሄድ አድርጓል፡፡ በጉብኝቱም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
የጎይ እና ሙላት እርሻ ልማት ድርጅቶች በተጎበኙበት ወቅት ባለሀብቶቹ ለሰራተኞቻቸው የሚያቀርቡት የመጠጥ ውሃ ንጽህናው የተጠበቀ መሆኑን ቢገልጹም፣ ከጊኒ ዎርም እንዲሁም ከሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎች የጸዳ አለመሆኑን ሰራተኞች ገልጸዋል፡፡
የሙላት እርሻ ባለቤት አቶ ሙላት ገብረ ስላሴ እንደሚሉት፤ እርሻ ልማቱ 23 ቋሚ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በክረምት ወቅት ደግሞ ከ200 እስከ 250 የሚደርሱ ጊዜያዊ ሰራተኞች ይኖሩታል፡፡ የእርሻ ልማቱ ሰራተኞቹን ከጊኒ ዎርም በሽታ ለመከላከል ንጹህ የመጠጥ ውሃ ቀደም ሲል በአካባቢው ከሚገኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በማምጣት ያቀርብ የነበረ ሲሆን፣አሁን በማሳው የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ንጹህ የመጠጥ ውሃውን እያቀረበ ይገኛል።
አቶ ሙላት እርሻ ልማቱ ለሰራተኞቹ የሚያቀርበው የመጠጥ ውሃ ፍጹም ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰራተኞች ውሃ ሲጠጡ የውሃ ማጣሪያ ቀሰም እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ለእዚህም እንዲረዳ የውሃ ማጣሪያ ቀሰም በደረታቸው ላይ አርገው እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡ በቀጣይም 50 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ሰራተኞቹ እንደሚሉት ግን የሚቀርብላቸወ ውሃ ንጽህናውን የተጠበቀ አይደለም፡፡ ወጣት ኡጁሉ ኡሌሮ በእርሻ ልማቱ ይሰራል፡፡ አካባቢው በጣም ሞቃት መሆኑን በመጥቀስም ለአካባቢው ውሃ ከአስፈላጊም በላይ አስፈላጊ ነው ይላል፡፡ አሰሪዎቻቸው የሚያቀርቡት ውሃ ጥራቱን የጠበቀ እንዳልሆነ የሚናገረው፣ ወጣት ኡጁሉ፣ ‹‹ ውሃ መጠጣት የግድ ስለሆነ ብቻ ንጽህና የሌለው ውሃ እየጠጣን ነው፤ በዚህም ለጊኒ ዎርም በሽታ እንዳንጋለጥ እንሰጋለን›› ይላል ።
የጉድጓዱ ውሃ ከጊኒ ዎርም ባሻገር የተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎችን እያስከተለ መሆኑን ጠቅሶ፣ በዚህ የተነሳም ሰራተኞች እየታመሙ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ አሰሪዎቻቸው ጉልበታቸውን ከመፈለግ ባለፈ ለሚጠጡት ውሃ ትኩረት እንደማይሰጡ የሚናገረው ኡጁሉ፣ ጊኒ ዎርምን ለማጥፋት በመንግስት የተያዘው ጥረት በዚህ መልኩ እየተሰናከለ መሆኑን ይናገራል ፡፡
ሌላዋ ሰራተኛ አቡሩ ቾንጌ እንደምትለው ሰራተኞቹ ጫካ ውስጥ በስራ ላይ ሲሆኑ ኬሚካል ተረጭተዋል የሚባሉ ኩሬዎችን ውሃ እንዲሁም ከስራ ወደ ማረፊያ ሲመለሱ ደግሞ የውሃ ማጥለያ (ፊልተር)በመጠቀም ውሃ ይጠጣሉ፡፡ እንደዚህም ሆኖ ግን ውሃው ጽዳቱን የጠበቀ ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳም ‹‹ጊኒ ዎርም ባይዘንም ለሌሎች የጤና ችግሮች ሁሌም ተጋላጭ ነን››ትላለች።
« በአቦቦ ወረዳ ጊኒ ዎርም የለም ፤ በአጎራባች ወረዳዎች ላይ ግን አለ፤ ይህም ሁሌም ስጋት ውስጥ እንድንሆን አድርጎናል››የምትለው አቡሩ፤ የእርሻው ባለቤቶች የተጣራ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያቀርቡላቸው ትጠይቃለች፡፡
የክልሉ የባለሀብቶች አስተባባሪ አቶ ኡኩማ ኡሙድ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ውስጥ ህግን ተከትለው የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ የማይሰሩ አካላት እንዳሉም ይጠቅሳሉ፡፡ በቀጣይ እነዚህን አካላት በመለየትና በሁሉም እርሻዎች የውሃ ጉድጓድ መኖር አለመኖሩን የማጣራት ስራ እንደሚከናወን ዝናብ ከመጣሉ በፊትም ጉድጓዶች እንዲያዘጋጁ እንደሚደረግ ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ኡኩማ ገለጻ፤ ባለሀብቶቹ ንጹህ ውሃ ለማቅረብ የሚያግዙ እቃዎችን ገዝተው በየእርሻ ማሳቸው ላይ ቢያስቀምጡም፣ በክልሉ የውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽን የለም፡፡ በዚህ የተነሳም ስራውን መስራት አልተቻለም፤ በመሆኑም የክልሉ መንግስት ችግሩ የጋራ መሆኑን በመገንዘብ የውሃ መቆፈሪያ ማሽኖችን ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡
የክልሉ የውሃ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ «እስከ አሁን የውሃ ጉድጓድ መቆፈሪያ አጣሁ፤ ምን ላድርግ ብሎ ለቢሮው ያመለከተ ባለሀብት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡» ቢያመለክቱም እንኳ ቢሮው ማድረግ የሚችለው ውሃ ለማውጣት የሚችል አቅም አለ ወይስ የለም የሚለውን ማጣራት ነው እንጂ የውሃ መቆፈሪያ ማሽኖችን አያቀርብም›› ብለዋል።
ኃላፊው ለዚህ ምክንያት ያቀረቡት ደግሞ ማሽኖች ያሉት በመንግስት እጅ አለመሆኑን ነው፡፡ ማሽኖቹ ያሉት በኢንተርፕራይዞች እጅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለሀብቶቹ ማሽኖቹን ተከራይተው ነዳጅ እና ቢሮው ለሚመድባቸው ሰራተኞች የውሎ አበል ችለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን መፍታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡጅሉ ኡሙት እንደሚሉት፤ ቢሮው የማስተባበር ስራ እያከናወነ ነው፡፡ ሰራተኞች ምን ዓይነት የመጠጥ ውሃ እየቀረበላቸው ስለመሆኑ የመገምገም ስራ በየጊዜው ያከናወናል፤ ሆኖም በግምገማውም በገቡት ውል መሰረት እየሰሩ ያሉ ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ግን ሀላፊነታቸውን እየተወጡ አይደለም።
አቶ ኡጁሉ በተለይም በጎግና አቦቦ ወረዳዎች የሚገኙ ባለሀብቶች በቅንጅት ለመስራት የማይመቹ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት ስብሰባ ሲጠሩ እንደማይገኙም ያመለክታሉ፡፡ በእርሻ ቦታዎቻቸውም ላይ የተወካይ ተወካይ እንደሚያስቀምጡ ጠቅሰው፣ሀላፊነት የማይሰማቸው መሆናቸውን በምሬት ይገልጻሉ።
መጀመሪያ በችግሮቹ ዙሪያ ተቀራርቦ መነጋገር ካልተቻለ ጊኒ ዎርምን ለመከላከል አይቻልም ያሉት አቶ ኡጀሉ፤ ከዚህ በኋላ ምክንያት መደርደር በመተው ወደ ስራ መግባት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አባተ ፤የጊኒ ወርም በሽታ በአገሪቱ የታየው በጋምቤላ ክልል አቦቦና ጎግ ወረዳዎች ብቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በዚህ ላይ ስንነጋገር ሶስትና አራት ዓመታት ሆኗል›ያሉት ዶክተር አባተ ፣በእነዚህ አመታት ወስጥ ትልቅ ለወጥ መምጣት እንደነበረበትም ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች በጤናው ዘርፍ የተቀመጡትን ግቦች ከብዙ አገራት ቀድማ ያሳካች መሆኗን በመጥቀስም፣የጊኒ ዎርም በሽታ ለምን ማጥፋት ተሳነን ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ሁላችንም ልናስበውና ራሳችንን ልናይበት የሚገባ ጉዳይ ነው›› ያሉት ዶክተር አባተ፣ የክልሉ መንግስት የጊኒ ዎርምን የማጥፋቱን ስራ ትልቁን ሀላፊነት ወስዶ በሽታው በአስቸኳይ ከአካባቢው የሚጠፋበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባውም አሳስበዋል።
እንደ ዶክተር አባተ ገለጻ፤ የጤና ሚኒስቴርም በሽታውን ለማጥፋቱ ስራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራም፣ ችግሩን መጋፈጥም ሆነ አንድ ቦታ ላይ ማቆም ግን አልቻለም፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሁን እየሰጠው ካለው ትኩረት በላይ ጠንካራ ስራ በመስራትና ተገቢውን ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን እንዳሉት፤ የጊኒ ዎርምን ለማጥፋት እስከ አሁን የተከናወነው ተግባር ጥሩ ቢሆንም፣ ከችግሩ ነጻ ለመሆን ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ይገባል፡፡ በመሆኑም በሽታውን በመከላከልና ማጥፋት ዙሪያ የሚሰሩ ሁሉም አካላት የቤት ስራቸውን መስራት ብቻም ሳይሆን ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በጊኒ ዎርም ዙሪያ እንደ ፌዴራል ፣ክልል እንዲሁም ወረዳ የተጀመሩ ስራዎችን ተቋማዊ (ኢንስቲትዩሽናል) ማድረግ ቀዳሚ ስራ መሆን አለበት፡፡ ሌላው ንጹህ ውሃ በቀበሌ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ማቅረብ በሚል መስራት ያስፈልጋል፡፡
በቀበሌዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃን ለማቅረብ የሚያስችል አቅምን ለመፍጠር ጤና ሚኒስቴር ከውሃና መስኖ ሚኒስቴር ጋር መስራት እንደ ሚኖርበት ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ለዚህም ችግሮች ተለይተው መቅረብ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
ባለሀብቶችም ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን ከመወጣት አንጻር ለሰራተኞቻቸው ብቻም ሳይሆን ለአካባቢው ማህበረሰብም ቅርብ በመሆን መስራት እንዳለባቸው ዶክተር አሚር ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹አሁን ያፈራችኋትን ሀብት ከህብረተሰቡ ጋር ተጋርታችሁ መጠቀም ካልቻላችሁ ነገ ላለመጥፋቱ ዋስትና የሚሰጥ የለም›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ባለሀብቶቹ በተቻለ መጠን የህብረተሰቡን ስሜት በማዳመጥ ንጹህ ውሃ የማቅረቡን ስራ ዛሬ ነገ ሳይሉ እንዲጀምሩም አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በእፀገነት አክሊሉ