አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ “ስለ ኢትዮጵያ” የሚል አልበም አውጥታችኋል፤ ለመሆኑ ይህ አልበም እንዲሰራ ምክንያት የሆናችሁ ምንድነው?
ደራሲ ሀብታሙ፡- ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ባለችበት ሁኔታ ጦርነት ስደት መፈናቀል አለ። በዚህ ውስጥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድርሻውን እየተወጣ ነው።ብር ያለው በገንዘቡ የሌለው በጉልበቱ ጀግኖቹ አጥንታቸውን እየከሰከሱ፤ ደማቸውን እያፈሰሱ፤ ህይወታቸውንም እየገበሩ፤ለሀገራቸው መስዋእት እየሆኑ ይገኛሉ።በሙዚቃው ዘርፍ የተሰማራን ሰዎች ምን መስራት እንችላለን የሚለውን አሰብን።እኛ ያሰብነው በጣም ጥቂት ነገር እንሰራለን ብለን ነበር።ከቻልን አንድ አልበም ካልሆነ የቻልነውን እንሞክር ብለን ነው የተጀመረው።በዚህ ጅማሮ 110 ባለሙያዎች ተሳትፈው 28 ሙዚቃዎች ስለኢትዮጵያ ሀ እና ስለኢትዮጵያ ለ የሚል ሁለት አልበም ልንሰራ ችለናል፡፡
በ20 ቀን ውስጥ ሁሉም ሰው የእኔ ስራ ነው ብሎ በተነሳሽነት ስለያዘው እና በራስ ተነሳሽነት ስለሆነ ሊሳካ ችሏል።እውነቱን ለመናገር በዚህ አልበም ለሀገራችን ሰራን ሳይሆን ሀገራችን ታሪክ እንድንሰራ እድል ሰጠችን።ስለዚህ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሄን ሁሉ ባለሙያ አሳትፎ ሲሰራ የመጀመሪያው ነው ብዬ አስባለሁ።ሀገራችን እንድንሰራ እድል ሰታናለች፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአልበሙ ላይ እነማን ተሳተፉ?
ደራሲ ሀብታሙ፡- በቅርቡ ህይወቱን ያጣው አንጋፋው አርቲስት አለማየሁ እሸቴን ጨምሮ ሶስት ትውልድ ላይ ያሉ በስልሳዎቹ የነበሩ በሰባ እና በሰማንያ የነበሩ በዘጠናዎቹ የመጣን ሰዎች እና አሁን ያሉትንም ልጆች ሶስት ትውልድ ያገናኘ ስራ ነው።አለማየሁ እሸቴ፣ ግርማ ተፈራ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ንዋይ ደበበ፣ ቤቲ ጂ፣ ጸደኒያ ገብረማርቆስ፣ዘለቀ ገሰሰ፣ አቡሽ ዘለቀ፣ ስለሺ ደምሴ፣ አብነት አጎናፍር፣ አስኔ ዴንዴሾ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ዘቢባ ግርማ፣ ጠረፍ ካሳሁን (ኪያ) በርካታ ናቸው በቅንብሩም ከአስራ ሁለት ያላነሱ አቀናባሪዎች ተሳትፎ አርገዋል ካሙዙ፣ ሚኪ ጃኖ፣ አቤል ጳውሎስ በርካታ ባለሙያዎች በህብረት የሰሩት አልበም ነው።አልበሙን ማስተር በማድረግ አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ ወደ 110 የሚጠጉ አሉ የሚባሉ ድምጻዊያን የግጥምና ዜማ ደራሲዎች አቀናባሪዎች ተሳትፈውበታል።በተለይ ስለ ኢትዮጵያ አለማየሁ እሸቴ ለመጨረሻ ጊዜ የሰራው ስራ የተካተተበት መሆኑ ለአልበሙ ተጨማሪ አንድ ታሪክ ያለው ስራ እንዲሆን እድል ፈጥሯል፡፡
ሀገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ባለሙያዎች በሙሉ ስቱዲዮዋቸው ውስጥ የግል ስራቸውን አቁመው ይሄንን ስራ ሲሰሩ ነበር።ለኔ ይሄ አልበም የመጪዋንም ኢትዮጵያ ያሳያል ብዬ ነው የማስበው።በአጭር ጊዜ ውስጥ ተአምር ልንሰራ እንደምንችል ማሳያ ነው እነ ደቡብ ኮሪያን ስንመለከት ደሀ ሀገራት ነበሩ።በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገርም ተአምር አሳይተው ነው አሁን ትልቅ ከሚባሉት ሀገራት ተርታ የተሰለፉት፤ ኢትዮጵያም ሁሉም ዜጋ በአጭር ጊዜ ተባብሮ የሚሰራ ከሆነ ለኔ የሚለውን ትቶ ስለሀገር ልስራ ካለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተአምር እናሳያለን የሚለውን ያሳያል።
አዲስ ዘመን፡- አንተን የምናውቅህ በግጥም ዜማ ድርሰት ነው።ምን ያህል ያንተ ስራዎች በአልበሙ ውስጥ ተካተቱ? ይዘታቸውስ ምን ላይ ያተኩራል?
ደራሲ ሀብታሙ፡- በአልበሙ ውስጥ ሶስት ስራዎች ነው የሰራሁት።እድለኛ ሆኜ በቅርቡ ያጣነው አርቲስት አለማየሁ እሸቴ የመጨረሻ እስትንፋሱን ማስቀረት ችለናል።የመጨረሻ ስራው በዚህ አልበም ውስጥ የተካተተው እሱ ግርማ ተፈራ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ዘቢባ ግርማ እና ጠረፍ ካሳሁን (ኪያ) በህብረት የሚጫወቱት ‹እኛ እያለንላት› የሚለውን ግጥም እና ዜማ ሰርቻለሁ።ቤቲ ጂ የተጫወተችው ‹ኢትዮጵያ ላይ› የሚለው እና ፍጹም አበረ የተጫወተው ‹ይብላኝ ላላወቀሽ› የሚለው ስራዎች የኔ ናቸው፡፡
ይብላኝ ላላወቀሽ፤ ኢትዮጵያን አለማወቅ በጣም መጎዳት ነው።ኢትዮጵያዊነትን አለማወቅ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል።ኢትዮጵያን ብዙዎች አያውቋትም ስላላወቋትም ነው ዛሬ የሚታየው ምስቅልቅል የመጣው።ኢትዮጵያዊነት በጣም ምስቅልቅል ነው፤ ይብላኝ ላላወቀሽ ለሄደ ባመሉ በመሀሉ ጥሎሽ ለሄደ ሰው ይብላኝለት እያልን ነው።ለቤቲ ጂ የሰራሁላትን ‹ኢትዮጵያ ላይ› የሚለውን ስራ በጣም ነው የምወደው።ከተሰራ ቆይቷል፤ አሁን ወደዚህ አልበም ስራ ውስጥ ገባ እንጂ፤ አዲስ ምድር አዲስ ሰማይ አዲስ አመለካከት ይስፋ ኢትዮጵያ ላይ እንይ የሚል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወጪው እንዴት ተሸፈነ?
ደራሲ ሀብታሙ፡- ሁሉም አርቲስት እዚህ ላይ የተሳተፍነው እውነቱን ለመናገር ሀገራችን ታሪክ እንድንሰራ እድል ሰታናለች።ለሚያስፈልገን ነገር በሙሉ ከኪሳችን እያወጣን የሰራነው ለሀገር ፍቅር ነው።ሁሉም ነገር በፈቃደኝነት እና በፍቅር ለሀገራችን የተበረከተ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ወጪ ወጣበት ለታለመለት አላማስ ምን ያህል ገቢ ያስገኛል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?
ደራሲ ሀብታሙ፡- እኛ ወጪም አወጣን ብለን አናስብም።ይሄን ያህልም ትርፍ ያመጣል ብለንም አንጠብቅም።ትልቁ ነገር ለሀገራችን የሰጠነው ገጸ-በረከት ነው።ሲዲው ተሸጦ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እንዲውል እንፈልጋለን።በተለይ በዚህ ጦርነት ላይ ተሰውተው ቤተሰቦቻቸው ብቻቸውን ለቀሩ የወታደር ቤተሰቦች ቢሆንልን የበለጠ ደስተኞች ነን።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያዊነት ስሜት ተቀዛቅዞ ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ።እዚህ ላይ ያንተ አስተያየት ምንድነው?
ደራሲ ሀብታሙ፡- እኔ በግሌ ኢትዮጵያዊነት ተቀዛቅዟል የሚለው ነገር የተጠና አይደለም፤ የጋዜጠኞች ግምት ነው።አሁን የሚታየው ለሀገር መረባረብ፤ ለምኖ ጭምር ለሀገሬ ልሙት የሚል ወጣት ነው ያለው።ተቀዛቅዟል የሚለውን አልስማማበትም።ኢትዮጵያዊነት መቼም አይቀዘቅዝም፤ ምናልባት ትንሽ ደብዘዝ ሊል ይችላል።ወይ ትንሽ አመድ እላዩ ላይ ሊኖር ይችላል፤ እንጂ ስትጠርጊው የኢትዮጵያ ፍቅር ሁሌም እንደ ፍም እሳት ነው።ሲታይ ትንሽ ሊዳፈን የሚችል ይመስላል፤ ግን እሱም አይሆንም።ሁሌም የሚኖር ነገር ነው፤ ዛሬም አይቀዘቅዝም፤ ነገም ከነገ ወዲያም አይቀዘቅዝም።ሰው ማንነቱ ከሀገሩ ተነጥሎ ሊታይ ስለማይችል፤ ሰው ማንነቱን እንዴት ሊያቀዘቅዝ ይችላል? ትክክለኛ የሆነ ሰው።ስለዚህ የሚሆን አይመስለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ወቅቶች አርቲስቶች ስለሃገራቸው አዚመዋል፤ ስለሃገራቸው ከሃገር መከላከያ ሰራዊት የማይተናነስ ጀብድ ፈጽመዋል፤ ለመሆኑ ሀገር በችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ የአርቲስቶች ሚና ምን ያህል ነው?
ደራሲ ሀብታሙ፡- ኪነጥበብ ሁልጊዜም በሀገር ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ፈላስፎቹ እንደሚሉት ከአምስት ጉዳይ ላይ ከየት መጣሁ? ወዴት ነው የምሄደው? የሚሉትን ጥያቄዎች የሚመልስ ነው።ሁለተኛው እውቀት ምንድነው እንዴት ነው የማውቀው ይሄ የማየው ነገር እውነት ነው ወይ ትክክል ነው ወይ የሚለውን የሚመልስ አካል አለው።ሶስተኛው ፖለቲካው ነው።አራተኛው የቱ ነው ጥሩ፤ የቱ ነው መጥፎ የሚለው ነው።የመጨረሻው ውበት ነው።የሰው ልጅ ከውበት ጥበብ ስራዎች ተነጥሎ መኖር አይችልም።አለም ላይ የሚታየው ዲዛይን ትያለሽ ስዕል ትያለሽ ሙዚቃ ሁሉም ነገር የሰው ልጅ ጥበብ ስለሚያስፈልገው ነው።በጥበብ ስታቀርቢው ወደ ሰው ልብ ይደርሳል የሚያዝነው እንዲያዝን የሚደሰተው እንዲደሰት ጀግና መሆን ያለበት እንዲጀግን የሚያደርግ ነው።ጥበብ የሰው ልጅ እስካለ ድረስ ከሰው ልጅ ህልውና ተነጥሎ የሚታይ ነገር ስላልሆነ በማንኛውም ጊዜ የሰው ልጅ ከጥበብ ተነጥሎ ሊኖር አይችልም፡፡
ለሀገር መስራት ደግሞ መታደል ነው።ጸጋዬ ገብረመድህን አጼ ቴዎድሮስ፣ አቡነ ጴጥሮስን የመሳሰሉ ሀገራዊ ስራዎችን በመስራቱ ነው አሁን ድረስ የምናስታውሰው።ጸጋዬን ሎሬት ያሰኘው እና በትውልድ ውስጥ እስከዛሬ ድረስ የማይሻር ስም ያኖረው።ገብረክርስቶስ ደስታ ሀገሬ ናፈቅሽኝ የሚለው ግጥሙ ነው በደንብ የሚታወሰው።በዓሉ ግርማ ህይወቱን ያጣው ስለኢትዮጵያ ስለጻፈ ነው፡፡
ይሄ ስራ ሀገራችን የገባችበትን ጦርነት (ጦርነት ጥሩ ገጽታ ባይኖረውም) በሌላው አንጻር እንደዚህ ተሰባስበን ሀገራችን ምን ያህል ገናና እና ትልቅ እንደሆነች በውስጣችን ያላትን ቦታ ሊያሳይ የሚችል ስራ እንድንሰራ ትልቅ እድል ፈጥሮልናል።ይሄ አጋጣሚ ሀገራችን ታሪክ እንድንሰራ እድል እንደፈጠረችልን ነው የምንቆጥረው።በርካታ ሀገርን ሊያሳዩ የሚችሉ የግጥምና ዜማ ስራዎች ተሰርተዋል።በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራችን ላይ አሻራችንን ለማኖር በአጭር ጊዜ ውስጥ ባልሳሳት በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ይመስለኛል ከ100 በላይ ባለሙያ የተሳተፈበት ስራ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደፊትም ገናናነቷ እውነተኛ ስሟ ገዝፎ እንዲታይ ሊያደርጉ የሚችሉ ስራዎች ለመስራት እቅድ አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልእክት ካለእድሉን ልስጥህ
ደራሲ ሀብታሙ፡- እኛ እንግዲህ በፍቃደኝነት አልበሙን ለታለመው አላማ እንዲውል ሰጥተናል።እኛ እንግዲህ ኢትዮጵያን ነው ያበረከትነው፤ ኢትዮጵያን በተሰረቀ መልኩ ማዳመጥም ህሊናን የሚወቅስ ነው።ለሀገራችን ትንሽ ያበረከትነው አስተዋጽኦ ፍሬ እንዲያፈራ ህብረተሰቡ ኦርጂናል በመግዛት ለታለመለት አላማ እንዲውል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እጠይቃለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ!
ደራሲ ሀብታሙ፡- እኔም አመሰግናለሁ!