የተጠናቀቀው ዓመት ለኪነ ጥበብ መልካም ዓመት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም:: ሆን ተብሎ የተዘነጋው የኪነ ጥበብ ዘርፍ አሁን ላይ የመንግስትን ትኩረት ማግኘት ጀምሯል:: የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩም ፤በሌሎች የመንግስት ተቋማትም ዘንድ እውቅና አግኝተዋል:: የቤተ መንግስቱም ሆነ የሌሎች ሹማምንት ቢሮዎች ለነዚህ ከያኒያን ክፍት ሲሆኑ ባለሙያዎችም ዝቅ ሲል የሹማምንትን ጆሮ ከፍ ሲልም የሹመት ወንበር እያገኙ ነው:: ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን 2013 የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መሰባሰብ እና ስለሙያቸው መነጋገር የጀመሩበት ዓመት ነበር:: ለዚህ ደግሞ ጥሩው ምሳሌ የቴአትር ባለሙያዎች የጀመሩት መሰባሰብ እና እሱ ያስከተለው የቴአትር መነቃቃት ነው:: ስለ ቴአትር የተሰኘው ይህ የቴአትር ባለሙያዎች ፤ ምሁራን እና የሚዲያ ሰዎች የህብረት ንቅናቄ የቴአትር መቶኛ ዓመት እንዲከበር እና ሌሎችም ተግባራት እንዲከናወኑ ያደረገ ነው:: ከሁሉም በላይ ግን ስለ ቴአትር ሰፊ ውይይት እንዲጀመር ማስቻሉ ትልቁ ስኬቱ ነው፡፡
ነገር ግን ይህ መነቃቃት የታየው በቴአትር ዘርፍ ብቻ አይደለም:: የውዝዋዜ ባለሙያዎችም የራሳቸውን የሙያ አብዮት ለመቀስቀስ ወዲያ ወዲህ ማለት ጀምረዋል:: ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በባለሙያዎች የተዘጋጀው እና ከነሀሴ 28 እስከ 30 በኦሮሞ ባህል ማእከል የተካሄደው መልህቅ የተሰኘ የቴአትር ወርክሾፕ ነው:: አዘጋጁ ደግሞ ተወዛዋዥ ነኝና ይመለከተኛል የተሰኘ የተወዛዋዦች ማህበር ነው:: በወርክሾፑ ላይ ከ80 በላይ በተለያዩ ቴአትር ቤቶች ፤ የውዝዋዜ ቡድኖች ፤ እና በግላቸው የሚሰሩ ወጣት እና አንጋፋ ተወዛዋዦች ተሰባስበዋል:: ዓላማው በውዝዋዜ ባለሙያዎች መሀከል ቅርርብ መፍጠር ፤ ሙያዊ ውይይቶች እና ልምድ ልውውጦች እንዲዳብሩ ማድረግ ፤ ውዝዋዜ ጥበብን ማሳደግ በመጨረሻም ለሀገር የሚጠቅም ሙያዊ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው:: በወርክሾፐ ላይ አንጋፋው ሎሬት ይፍሩ ጎበናን ጨምሮ ዝነኞቹ ኬሮግራፈሮች ከድር አሉ፤ ልጅ ተመስገን (ተመስገን መለሰ) ፤ ዘሪሁን ማሩ ፤ ኑሪያ መሀመድ ፤ ይድነቃቸው ይልማ ፤ በድሉ ኢሳይያስ ፤ ሀዋርያት አሰፋ ፤ እና ሽፈራው ደስታ ተሞክሮአቸውን አካፍለዋል፡፡
እኔነትን መስበር
በወርክሾፕ ላይ ያገኘናቸው አዘጋጆቹም ይሁን ተሳታፊዎች በጋራ የሚያነሱት አንድ ችግር አለ:: እሱም በሙያተኞች ዘንድ ያለው ከፍተኛ እኔነት (ኢጎ) ነው:: ”ሁላችንም እኔ ምርጥ ነኝ ነው የምንለው” ትላለች ከአዘጋጆቹ መሀከል አንዷ የሆነችው የራስ ቴአትሯ የዘመናዊ ዳንስ ተወዛዋዥ ጌጤ ክፍሌ:: ይህ የእኔነት ስሜትም ሙያው እንዳያድግ እንደጎተተው ትናገራለች:: የጌጤን ሃሳብ ሌላኛው አዘጋጅ ታምራት እሸቱም ይጋራዋል:: በአሁኑ ወቅት በውዝዋዜው ጥበብ ከምርጦቹ መሀከል ከሚጠቀሱት ቡድኖች አንዱ ሆነው ኢትዮጵያዊነት የውዝዋዜ ቡድን አባል የሆነው ታምራት ሙያው እንዲያድግ ግላዊነትን ማስታገስ ያስፈልጋል ባይ ነው:: ”የተወሰኑ ሰዎች እና ቡድኖች ለብቻቸው ማደግ ጥበቡን አይቀይረውም:: ስለዚህ እኔነትን ቀነስ አድርገን መሰባሰብ ፤ ልምድ መለዋወጥ ፤ መነጋገር እና ተባብሮ መስራት የግድ ይለናል” ይላል:: ስለዚህም ይህን የእኔነት ስሜት ለመግራት እና ለማስታገስ ነው አንጋፋዎቹ ተሞክሮአቸውን እንዲያካፍሉ የተደረገው:: እነሱም ከሰፊው ልምዳቸው ያላቸውን ተሞክሮ በማካፈል አንድነት አስፈላጊ እንደሆነ መክረዋል፡፡
ለተወዛዋዦቹ ልምዳቸውን ካካፈሉት አንጋፋ ተወዛዋዦች መሀከል አንዱ የሆነው ዘሪሁን ማሩ ነው:: ዘሪሁን ለ17 ዓመት ያህል ውዝዋዜን ሰርቷል:: ብዙዎችም ከተወዛዋዥነቱም ባለፈ በባላገሩ አይድል ላይ በነበረው ዳኝነትም ያስታውሱታል:: ”በ17 ዓመት ቆይታዬ ዋነኛ የተማርኩት ነገር ራስን ማብቃት እና ዲሲፕሊንን ነው” የሚለው ዘሪሁን በተወዛዋዦች መሀከል ያን ተሞክሮ ማስረጽ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ ” ድሮ አንደኛ ሁለተኛ የሚባል ነገር አልነበረም:: አሁን ግን ጎራ የመያዝ እና ጥሩ የሚሰሩ ሰዎችን የመግፋት ነገር ይታያል፡፡” ይላል:: ይህ ካልተስተካከለ ደግሞ ሙያውን ማሳድግ ከባድ እንደሚሆን ይናገራል፡፡” ሰው የሚያከብረን ራሳችን ስንከባበር ነው” ይላል:: ይህን የአንጋፋውን አርቲስት አስተያየት ከወርክሾፑ ተሳታፊ ወጣቶች መሀከል አንዱ የሆነው እስካጥናፍ ካብቲመርም ይስማማበታል፡፡” ከዚህ በፊት አንድ ላይ የመስራት ልምድ የለንም ነበር:: ይላል:: ይህ ወርክሾፕም የማንተዋወቅ ሰዎች እንድንተዋወቅ ፤ ልምድ እንድንለዋወጥ ይረዳናል” ብሎናል፡፡
አሁን ቁጭቱ እየታከመ ነው
ጌጤ እንደምትለው ይህን እንቅስቃሴ በጀመሩት ተወዛዋዦች ዘንድ ሙያችን ተበድሏል የሚል ቁጭት እንዳለ ትናገራለች:: ነገር ግን አሁን ላይ ያ ቁጭት በነሱ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ተወዛዋዦች ዘንድ መኖሩን እንዳስተዋለች ትናገራለች:: ነገር ግን ቁጭቱ ብቻ ሳይሆን ህክምናውም አብሮ ተገኝቷልም ትላለች:: እርግጥም በወርክሾፑ ላይ በነበርንበት ወቅት እንዳየነው ሁሉም የወርክሾፑ ተሳታፊ በስልጠናው ላይ በመገኘቱ እንደተደሰተ ያስታውቅ ነበር:: የብዙዎቹ ውይይትም በቀጣይ አብረው መስራት ስለሚችሉት ስራ ነው:: እስካጥናፍ እንደነገረን ተወዛዋዦቹ አሁን በሙያቸው ከታሪካዊው የህዝብ ለህዝብ ዘመቻ ጋር የሚመጣጠን ስራ ለመስራት ዝግጁ ናቸው:: ”ባለን ሙያ ሀገራችንን ማስተዋወቅ እንፈልጋለን ፤ ሰላም እና ፍቅርን የሚሰብኩ ስራዎችን መስራት እንፈልጋለን” ብሎናል:: ጌጤ በበኩሏ “በተወዛዋዦች ዘንድ የሙያ አብዮት ብናስነሳ የሚል ተነሳሽነት አለ” ስትል ሌላኛው አስተባባሪ ታምራት በአንጻሩ “እኛ በሙያችን ለኢትዮጵያ አርበኛ መሆን ነው የምንፈልገው፡ ፡መሰባሰባችንም ለዚያ ነው” ብሎናል፡፡
ይህ ተነሳሽነት አስደሳች ነው:: ባለፈው ሚያዝያ ወር አንጋፋ ተወዛዋዦችን ለፋሲካ በአል ቤታቸው ድረስ ሄዶ በመጎብኘት የተጀመረው የባለሙያዎቹ እንቅስቃሴ አሁን ብዙዎችን ማሰባሰብ ችሏል:: ነገር ግን የውዝዋዜው ጥበብ አሁን ከቴአትር ቤት እና ክበባት ወጥቶ በቲክቶክ እና መሰል ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ተስፋፍቶ ይታያል:: በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚታየው የዘመናዊ ውዝዋዜ ጥበብ እጅን በአፍ የሚያስጭን ነው:: እነሱንስ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ለማስገባት እቅድ አላችሁ ወይ ብለን ላቀረብነው ጥያቄ አዘጋጆቹ በሰጡን መልስ አሁን ለጊዜው ቋሚ ስራቸው ውዝዋዜ የሆኑ ተወዛዋዦችን በማሳተፍ ቢጀምሩም በቀጣይ ግን ሁሉንም ለማሳተፍ እቅድ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡
በጥቅሉ ካየነው ነገር ያስተዋልነው ተወዛዋዦቹ አሁን ሙያቸውን ወደሚገባው ከፍታ ለማውጣት ተዘጋጅተዋል:: ይህ የተወዛዋዦቹ ንቅናቄ ከቴአትር ባለሙዎቹ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከመንግስት በጎ ዝንባሌ ጋር ከተዳመረ በቅርቡ በኪነ ጥበብ ዘርፍ አንድ አቢይ አብዮት ልናይ እንደምንችል መገመት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም