“አበባዮሽ… ለምለም…አበባዮሽ… ለምለም ባለእንጀሮቼ ለምለም ግቡ በተራ ለምለም” በጠዋት ብንን ስል አልጋዬ ላይ እደተጋደምኩ የሰማሁት ድምፅ ነው። ዛሬ አዲስ አመት ነው፤ እኔም አሮጌው ላይ ተኝቼ በአዲሱ ነቅቻለሁ ማለት ነው። ተኝቼ ብውል ደስ ይለኝ ነበር። ህፃናቱ በሬ ላይ ቆመው የሚያሰሙት የአዲስ አመት ብስራት ዜማ አስነቃኝ። ብድግ ብዬ ወደ በሩ ሳመራ፤ አንድ ነገር ትውስ ብሎኝ ቆም አልኩ “ምን ሰጥቼ ልሸኛቸው. ነው?” ኪሴ ውስጥ ቤሳቤሲቲ የለም። በቃ ሂዱ ይበቃል አይባል ነገር። ትላንት እኮ ለዛሬ ያሰብኩት ብር ነበረኝ። ዛሬ ባዶ ኪሴን ነኝ። ለህፃናቱ የምሰጠው እንኳን ልጣ ወይኔ።
ተመልሼ አልጋ ላይ ተቀምጬ ሲደክማቸው እራሳቸው ይሂዱ ብዬ ድምፄን አጠፋሁ። ህፃናቱ ከቤት አለመውጣቴ በሬን አለመቆለፌን አይተው አውቀዋል መሰል ቶሎ መሄድ አልቻሉም። ተነስቼ ከፍቼ ውስን ሳንቲሞች እንድሰጣቸው በተስፋ ሲዘምሩ ለረጅም ሰዓት ቆዩ። እኔም በዝምታ ተውጬ ተስፋ ቆርጠው እንዲሄዱ በውስጤ ፀሎት ማድረስ ጀመርኩ።
ስለራሴ አሰብኩ። እንዴት ይሄ ሁሉ ዓመት ሰርቼ ተሯሩጬ በዓውዳመት እንኳን ምውልበት በሬ ላይ ብስራት ለመንገር እንኳን ዘመን ተለወጠ ብለው የመጡ ህፃናት ጥቂት ሳንቲሞችን ሰጥቼ ምርቃት ለመቀበል ያቅተኛል። እንደ ሰው እሰራለው እነደ ሰው ገቢ አገኛለሁ። ያቃተኝ እንደ ሰው መለወጥና ማደግ ነው። በእርግጥ ስግብግብና ራስ ወዳድ ብሆን ከማንም የተሻለ የመለወጥ እድል ነበረኝ።
የሰዎችን ደስታ ነው ከራሴ ደስታ ማስቀድመው። ለዓመት በዓል ብዬ ከደሞዜ የቆጠብኩት በዋዜማው አስረክቤ ነው። 2500 ብር በወር ከማገኛት 3000 ብር ለ4 ወር ቆጥቤ ነው ያጠራቀምኩት። ግን ሰተሁ። እሺ ቆይ ይሁን መስጠት ጥሩ ነው ግን ደግሞ እንዴት ሁሉንም እሰጣለሁ። ያለኝን ሁሉ ምን ልሁን ብዬ ነው አውጥቼ ያከፋፈልኩት? አይ አይ ልክ ነበርኩ።
ትላንት በዋዜማው ጎረቤቴ ሰለሞን ሚስቱ ምጥ ይዟት ሲራሯጥ ድንገት በሬ ላይ ተገኘሁ። ሰው አይደለሁ ምን ልርዳህ አልኩት። “እባክህ ወንድወሰን ፍጠንልኝ ፍጠን ታክሲ ይዘህልኝ ና፤ ማርቲ ማርቲ ምጥ ይዟት ነው!” ብሎ ተመልሶ ወደቤቱ ገባ። ሰለሞን ከኔ ቤት ቀጥሎ ያለ እንደኔው ተከራይ ነው። ሁለት ክፍል ቤት ተከራይቶ ከሚስቱ ጋር ሁለት ይኖር ነበር። ከትላንትና ጀምሮ ሶስት ሆነዋል። ሚስቱ ወልዳ። ታዲያ እኔም እጄ ላይ የነበረው ቅሪት እንዳሟጥጥ ምክንያት የሆነኝ የሰለሞን ሚስት መውለድ ነበር።
ተሯሩጬ ታክሲ ይዤ ስመለስ ሰለሞን ውጪ ሚስቱን በተቀመጠችበት ደግፎ ይዞዋት ጠበቁኝ። ደግፈን ላዳ ታክሲ ውስጥ አስገባናት። ወደስራ ለመሄድ ባስብም የተወሰነ ቀንም ቢሆን ጉርብትና አገናኝቶን አወዳጅቶን ነበርና ዝም ከማለት ”ሰሎሞን ብቻህ እዳትሆን ልምጣልህ”አልኩት። እሱም “አስቸግርሀለሁ እንጂ ብቻዬን ከምሆንማ ደስ ይለኛል..” ሲለኝ ሳላስብ በሌላኛው የላዳው የፊት በር ከፍቼ ከሹፌሩ ጋር ተቀመጠርኩ። ታክሲው እየተቻኮለ ወደ ዋናው አስፓልት እየወጣ “ወዴት እንሂድ?” ብሎ ጠየቀ።
የሰለሞን ሚስት ጩኸትዋን ታቀልጠዋለች። “ወይኔ እማዬ እእእ እ” ታቋርጥ የምታወጣው የጭንቀት ሲቃ ነው። ሴት ልጅ ምጥ ይዟት አይቼ አላውቅም ነበርና በሁኔታዋ ተረበሽኩ። የላዳው ሹፌር ጥያቄውን ደገመ። “ወዴት ልንዳው ወዳጄ?” በትህትና ጠየቀ። ሰለሞን ግን የሰማው አይመስልም፤ ልክ እንደ ህፃን ልጅ የሚስቱን አንገት እቅፍ አድርጎ በማባበል ላይ ነው። ድንገት ቀና ብሎና ተኮሳትሮ መናገር ጀመረ።
ሰለሞን ቆጣ ብሎ “ወደ ዳንስ ቤት አንሄድ ሀኪም ቤት ነዋ ምጥ ይዟት እያየህ…”አለው በቁጣ የሰለሞን ሁኔታና ቁጣ ገረመኝ። ብዙም ቅርበት ባይኖረንም እንዲህ ሲቆጣ አይቼው አላውቅም። በእርግዝና ሰዓት ሴቶች አይደል እንዴ ፀባያቸው ይቀየራል የሚባለው ነው ባሎቻቸውም ያግዙዋቸውዋል። ሆሆ…። እኔ የሰለሞንን ሁኔታ ሳይ ምን አልባት በጭንቀት ይሆናል ብዬ “አይዞኝ ተረጋጋ ሰላም ትሆናለች ይህ እኮ የሚፈጠር ነው” አልኩት።
የላዳው ሹፌር ሌላ ጥያቄ አላቀረበም። ዝም ብሎ ሲነዳው እኔ ግራ ተጋባሁ። የሁለቱ ምልልስ በማሰብ ላይ ሳለሁ ድንገት ቀና ስል፤ ሹፌሩ ዋናው መንገድ ተጠማዞ መኪናው ወደአንድ ቀጠን ያለ ኮብል ስቶን መንገድ ይዟት ገባ። እኔ ጠየኩት “እዚህ ሰፈር ሀኪም ቤት…” ብዬ ጠየኩት። መንገዱን በደንብ አውቀዋለሁ። እንኳን ውስጥ ለገባ በበር ለሚተላለፍም ክፍያ ይጠይቃሉ ተብሎ ይታማሉ። ይሄ ልጅ እዚያ ገብቶ ጉድ እዳይሰራን አልኩኝ። ሰለሞን የምንሄድበት ሀኪም ቤት መሆኑ እንጂ ወዴት እንደሆነ እየተከታተለ አይደለም። ሚስቱ ላይ ነው ትኩረቱ ሁሉ።
ያልኩት ትልቅ የግል ሆስፒታል ውስጥ ይዞን ገብቶ በሩን ከፍቶ ወረደና “ነርስ ነርስ ፍጠኑ ፍጠኑ” ብሎ ተጣራ። አቤት የነርሶቹ ፍጥነት ከመኪና አፋፍሰው አስወርደው ወደውስጥ ሲያስገብዋት ደቂቃ አልፈጀባቸውም። ሰለሞን ግራ ተጋብቷል። ሀኪም ቤት ያለው እዚያ እንዳልነበር እንኳን እሱ እኔም አውቃለሁ። በጉልበት ስራ የሚተዳደር ለፍቶ አደር ነው። ሹፌሩ ላይ ማንቧረቅ ጀመረ። በጩኸት “አንተ እዚህ ይዘኸኝ ና ብዬሀለው?”ሲለው “ጠይቄህ ሀኪም ቤት አልከኝ እኮ ጌታው ምን አጠፋሁ እኔ?” አለው።
ልጁ ግን ቂመኛ ነገር ነው፤ የሰለሞንን ንግግር ሰምቶ ብድሩን ሊከፍል ፈልጎ ነው። ሰለሞን ትቶት ወደውስጥ ሮጦ ገባ። ልጁ እኔን ሲያየኝ “ስንት ነው?” አልኩት“ 500 ብር” አለኝ። 300 ይበቃሀል ብዬ ከኪሴ ብር ላወጣ ስል “ሰውዬው መኪናዬን አየኻት ወንበሩ ተበላሽቷል እኮ…300 ማሳጠቢያም አይበቃም ምን ያደርግልኛል።” አለኝ። ውነትም ሳየው ወንበሩ ተበላሽቷል። ያለው ከሰጠሁት ኪሴ ውስጥ ምን አይቀርም። ምንም ማድረግ አልቻልኩም፤ ያለኝን ከፍዬው ወደ ውስጥ ገባሁ።
ሰለሞን እንግዳ መቀበያ ጋር ሲንቆራጠጥ አገኘሁት። 20 ሺ ብር አሲዝ መባሉን ነገረኝ። ይዟ እንዳይወጣ ማወለጃ ክፍል አስገብተዋት ማዋለድ ጀምረዋል።
በሁኔታው ግራ ተጋባሁ። እዚያ ሆነን እያሰብን ቆየን። ሰለሞን በድንጋጤ ደንዝዟል፤ እኔም ግራ ገብቶኛል። የሞት ሞቱን “ካኝ ላይ የቆጠብኩት 10 ሺ 500 ብር አለ እሱን አውጥቼ አምጥቼ ልስጣቸው ምን አደርጋለሁ።” ብሎ እምር ብሎ ተነስቶ ወጣ። እኔም ባንክ ያስቀመጥኩት 2000 ብር እንኳ ሳይቀር ለማውጣት ሄድኩ። ከባንክ ያለውን ይዞ መጣ። የኔን ልጨምርልህ ልለው ሳስብ ቀደም ብሎ ወደ የሆነውን ሁሉ ነገራት። ወደአንድ ክፍል ይዛው ገባች። ሲወጣ ተጣድፎ መጣና… “ማናጀሩን አናገርኩት ወደፊት ትከፍላለህ አለኝ አሁን ያለኝን ከፍዬ ሚስቴ ሊያዋልድዋት ነው።” እያለ በደስታ ዘለለ። ወይ መዝለል ከዚያስ ሚስቱ ምን ልትበላ…ልጁስ ምን ሊለብስ ብዙ ጥያቄዎች ተደራረቡብኝ። በዚያው ቅፅበት በሰላም መገላገልዋ ተነገረውና ቆይተን ከሰዓት ይዘናት ወደቤት ሄድን። የላዳ ተከራክሬ 200 ብር ከፈልኩ።
ተመልሰን ቤት ስንገባ የሚላስ የሚቀመስ የለም። ሰለሞንን በጥያቄ ሳየው። ለወጪ ብሎ ያስቀመጠው ሁሉ መስጠቱን ነገረኝ። ቅድም ለህክምናው የበኩሌን ላዋጣ ያወጣሁት ብር ከኪሴ አውጥቼ ሰጥቼው መሽቶ ስለነበር ገብቼ ተኝቼ ነው ልጆቹ የሚቀሰቅሱኝ። ዋዜማውን እንዲህ ውዬ በዓሉ እንዲህ ሊያልፍ ግድ ሆነ።
በዚህ ገጠመኝ ነበር የአመት ባል ተቀማጬን አሳልፌ የሰጠሁት። አሁን ባዶዬን የቀረሁት። “ አይ ደግ አደረኩ…እኔ ብቻዬን አይደለሁ ምን እሆናለሁ… ይህ በዓል ቢያልፈኝ ምን እጎዳለሁ።” አልኩኝ ለራሴ። ል ጆቹ አሁንም አልሄዱም። ዜማቸውን ቀጥለዋል። እኔም ከአልጋዬ ሳልነሳ እዚያው ቁጭ ብዬ ዜማቸውን አደምጣለሁ። … እንኳን ቤትና ለምለም የለኝም አጥር ለምለም.. እደጅ አድራለሁ ለምለም ኮከብ ስቆጥር ለምለም… ይሄን ስሰማ “ለካስ የሚሰጥም የሚቀበልም ምንም የለውም” አልኩ ለራሴ …………. አበቃ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5/2013