በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት፤ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ዜጎች ቁጥር 71 ከመቶ ነው። ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። በኦፊሴላዊ ግምት ብቻ በ16 ነጥብ አምስት በመቶ የሚያድግ የሥራ አጥነት እንዳለ ይነገራል። ምንም እንኳን ኢኮኖሚው በዕድገት ላይ ነው ቢባልም፣ በየዓመቱ በእጅጉ እየጨመረ ለሚመጣው ለዚህ አምራች ኃይል አቻ የሚሆን በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ግን አልቻለም። በ2011 የወጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ 77 ነጥብ ስምንት በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት ኑሮውን የሚገፋው በቀን ከሁለት ዶላር ባነሰ የገንዘብ መጠን ነው።
ወጣትነት ለሥራ፣ ለትግል፣ ለለውጥ፣ ለአዲስ ነገር ተነሳሽነት ጎልቶ የሚታይበት ዕድሜ እንደመሆኑ፣ የአንዲት አገር ዕድገትም ሆነ ውድቀት በየዘመኑ ባለው ወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ሥራ ፍለጋ ከገጠር ወደ ትናንሽ ከተሞች የሚፈልሱ እንዲሁም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ማስተናገድ የሚችል የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩ፣ ከተሞች የሥራ አጥ ወጣቶች መናኸሪያዎች ሆነዋል። የአገሪቱን ከተሞች ያጨናነቁ፣ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮባቸዋል። በአገራቸው ሥራ አግኝተው የተሻለ ህይወት የመኖር ተስፋ የራቃቸው ወጣቶች፣ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት እየተጋለጡም ነው።
ለዛሬ መነሻውን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አድርጎ በተወሰኑ ከተሞች በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ወጣቶችና ትምህርት ድጋፍ አገልግሎት እንቃኛለን፡፡ ማህበሩ ከተመሰረተ ቅርብ ጊዜው ቢሆንም ተመራቂ ተማሪዎችን በማሰልጠን ስራ እንዲፈጥሩና ስራ እንዲቀጠሩ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝና ሌሎች ጉዳዮች ማነቆ ሆነውበታል፡፡ ከማህበሩ ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ረታ ካደረግነው ቆይታና ማህበሩ ከሰራው ዘጋቢ ፊልም ላይ ያጠናቀርነውን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ።
የማህበሩ አመሰራረት
በ1997 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙትና በተለያዩ አገራት በመሄድ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተማሩት አቶ ፍቃዱ ረታ የድርጅቱ መስራች ናቸው፡፡ ድርጅቱን ለመመስረት ከወንድሞቻቸውና ከልብ ወዳጆቻቸው ጋር የወዳጅነትና የአብሮነት ስምምነት በማድረግ ወደ ስራ ተገባ፡፡ ሁሉም በበጎ ፈቃደኝነት በሚችለው አቅም ማህበሩን ለማሳደግ መስራት ጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ትምህርት ድጋፍ አገልግሎት በዋናነት የሚሰራው ወጣቶች ላይ ሲሆን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ስራ የሌላቸውን ወጣቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የማህበሩ መስራች ከአገር ውጪ በነበሩበት ወቅት የቀሰሙትን የበጎነት ተግባር ወደ ተግባር ለመለወጥ በነበሩበት አገር ከሌሎች ኢትየጵያውያን ጋር በመሆን ከአንድ ሺህ በላይ መፅሀፍ ሰብስበው ለሀዋሳ፣ ለወላይታ ሶዶ፣ ለዋቻሞና ለሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ ከነበሩበት አገር ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የበጎ ስራውን በማጠናከር የተለያዩ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡ ለስልጠና ወደ አሜሪካ በሄዱበት ወቅትም እዛ ከሚገኙ በጎ አድራጊ ሰዎች ጋር በመነጋገር ‹‹ሁሉም ይቻላል›› በሚል መሪ ሀሳብ በ2012 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ ህጋዊ ፈቃድ ያለው ማህበር መሰረቱ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰባት የቦርድ አመራር የሚንቀሳቀሰው ማህበር ስራው ሲጀመር ከወንድሞቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ነበር፡፡
በአገሪቱ የሚገኘውን የስራ አጥነት ለመቀነስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ወጣቶችና ትምህርት ድጋፍ አገልግሎት በዋናነት ወጣቱ ወደ ስራ እንዲሰማራ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሚነገረው በላይ የስራ አጥነት ችግር አለ፡፡ በተለይ አቶ ፈቃዱ በሚያስተምሩበት በስነ ምግብ የትምህርት መስክ ብዙ ተማሪ ስራ እያገኘ አይደለም፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በማሰብ ነበር የኢትዮጵያ ወጣቶችና ትምህርት ድጋፍ አገልግሎት ስራ የተጀመረው፡፡ ስራው ከተጀመረ ሁለት አመት ያስቆጠረ ሲሆን የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ መጀመሪያ ስራው ስራ አጥነት ላይ አልነበረም፡፡ ስራዎች የተጀመሩት በትምህርት ጥራት ላይ አተኩሮ ስራ አጥነትን መቀነስ ላይ ነበር፡፡ ማህበሩ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ በሲቪክ ማህበራት የተመዘገበ ሲሆን የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በተወሰነ መልኩ እንቅስቃሴ ተደርጎ ነበር፡፡ የማህበሩ ስራ በሀሳብ ደረጃ አስር ዓመት ሞልቶት ነበር፡፡ ነገር ግን ተመራቂዎችን የማስቀጠር ስራ ሲከናወን ግን ሁለት አመት ሞልቶታል፡፡
የተከናወኑ ተግባራት
እስካሁን አንድ ሺህ ወጣቶች ላይ ተደራሽ መሆን የተቻለ ሲሆን ወጣቶቹን ማሰልጠን ላይ ያተኮረ ስራ ይከናወናል፡፡ በሌላ በኩል አጫጭር ትምህርቶችን በኦን ላይን ለወጣቶች የሚሰጥ ሲሆን ትምህርቱን በራሳቸው እንዲከታተሉ ይደረጋል፡፡ በቀጥታ ወደ ስራ በማስባት ደግሞ እስከ መቶ ለሚደርሱ ወጣቶች ስራ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዋናነት ስልጠናዎች በስፋት የሚሰጡ ቢሆንም ስራ ማግኘቱ ላይ ግን ከባድ ፈተናዎች አሉት፡፡ በአገሪቱ የስራ ሁኔታው በጣም ጠባብ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ በዋናነት ተማሪዎቹ በክህሎት ዙሪያ ክፍተቶች ስላለባቸው ስራ ለማግኘት እንዳይቸገሩ ማህበሩ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ ስራ እንዲያገኙ ከተደረጉት ውስጥ ስምንቱ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ነበሩ። ተማሪዎቹ ማደሪያ አጥተው ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው ነበር፡፡ አሁን ግን የተሻለ ነገር ያላቸው ናቸው፡፡
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ሀዋሳ ከተማ ላይ መቀመጫውን አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ በሻሸመኔና በአዲስ አበባ ከተማዎች እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ በቅርቡ አዳማ ከተማ ለመንቀሳቀስ ሀሳብ አለ፡፡ በጎንደርና በባህርዳር ከተማዎች ስራዎችን ለመስራት በተወሰነ መልኩ ተጀምሯል፡፡ በሁሉም ቦታዎች ፍላጎት ያለ ቢሆንም የኢንተርኔት አለመኖር ችግር ፈጥሯል፡፡ የፊት ለፊት ስልጠናዎችን ለመስጠት አገሪቱ ያለችበት ሁኔታና የኮሮና ወረርሽኝ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ስራውን ከሚያከናውኑ መስሪያ ቤቶች ጋር እየተሰራ ነው፡፡
ማህበሩ በኢንተርኔት ከ240 በላይ ከታለንት ፈርም ጋር በመተባበር የገፅ ለገፅ 150 በላይ ሰልጣኞችን ይዞ ሰርቷል፡፡ የኮሮና ወረሽኝ ከተከሰተ በኋላ ማህበሩ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አቅም ለሌላቸው ማህበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊ እርዳታ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ለትምህርት ቤቶች አስፈላጊ ግብዓቶች ማህበሩ በድጋፍ መልክ ሰጥቷል፡፡ ስልጠና የሚወስዱ ተመራቂ ተማሪዎች ለስራ ቃለመጠይቅ እንዴት እንደሚያደርጉና ምን ጥያቄ እንደሚነሳላቸው ይነገራቸዋል፡፡ ማህበሩ የሚሰጣቸው ስልጠናዎች በሁለት የተከፈለ ሲሆን ስራ በራሳቸው መፍጠር ለሚፈልጉና በመንግስትም ሆነ በግል ተቋማት መቀጠር ለሚፈልጉ ወደ ስራ ሲገቡ ሊገጥማቸው የሚችለውን ነገር እንዴት ማለፍ እንደሚችሉ የሚሰጥ ስልጠና ነው።
ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ እንደጀመረ የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት እክል ፈጥሮ ነበር፡፡ በብዛት አቅም ያላቸው ሰዎች ያለመረዳት ችግር አለ፡፡ በተለይ በተማሪዎች ላይ ያለውን ችግር እንደራስ ቢያስቡ ክፍተቶችን መሙላት ይቻል ነበር፡፡ ስራው ከተጀመረ በኋላ ያልተጠበቁ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡ በተለይ ወጣቶቹን ለመሰብሰብ ሲሞከር በቤተክርስቲያን ጥግ የሚተኛ ወጣት ማየት ከባድ ነገር ነበረው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ተመርቀው ማደሪያ አጥተው በየጥጋጥጉ ሲያድሩ ነበር፡፡ ዋናው ክፍተት የስራ እጥነት ቢኖርም በስራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙትና ባለሙያዎች ላይ ያለው ችግር ነው፡፡ ሁሉም ኃላፊነት መውሰድ አይፈልጉም፡፡ በቀጥታ ስራ አጥነት ላይ የሚሰሩ ቢሆንም ቀርበው ችግሩን ለመፍታት ያለመፈለግ ነገር አለ፡፡
ሌላው ደግሞ የራስን ችሎታ አለማወቅ ነገር አለ። አብዛኛው መምህር አስተምህሮ ወደ ቤት መሄድን ኃላፊነት እንደተወጣ አድርጎ መቁጠር ነገር አለ። በተለይ ተማሪን ካስመረቁ በኋላ ምንም ኃላፊነት ስሜት የማይሰማቸው በብዛት ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ስራ አጥነቱን አስፋፍቶታል፡፡ ከከተማ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያለው አሰራር የስራ አጥነትን ችግር የሚፈታ አይደለም፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ የስራ አጥነት አጀንዳ በየትኛውም ቦታ ሲነሳ አይሰማም። በስልጠና ደረጃ እንኳን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ምንም አይነት ምቹ ሁኔታ የለም፡፡ ማህበሩ በሁሉም ቦታ ተደራሽ ለመሆን ቢፈልግም የተመቻቸ ሁኔታ የለም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የማህበሩን ስራ የማይቀበሉ አሉ፡፡ በተለይ ተማሪዎቹን ፖለቲካዊ ሁኔታን ነው የምታሰለጥኑት በማለት ክልከላዎች አሉ።
ልጆቹ እንዲሰለጥኑ የሚደረጉት ከክህሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ነበር፡፡ በዚህም የነበራቸውን የህይወት ተሞክሮ በመፅሀፍ መልክ መፃፍ የጀመሩ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ የነበረው ውጣ ውረድ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ አካባቢውን በንቃት የሚያይና የሚከታተል ሰው ለተማሪዎች ስራ መፈለግ ኃላፊነቴ አይደለም ብሎ ማሰቡ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ይህ የግንዛቤ ክፍተት እንደ ችግር የሚወሰድ ነው፡፡
ቀጣይ እቅድ
በየአመቱ ብዙ ተማሪ የሚመረቅ ሲሆን ይህ ሁኔታ የስራ አጥነትን ቁጥር እየጨመረው ይገኛል፡፡ ማህበሩ በሙሉ አቅም እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡ ወጣቱን አሰልጥኖ ወደ ስራ የሚሰማራበት ሁኔታን ማህበሩ ቢፈጥርም ድጋፍ እየተደረገ አይደለም፡፡ ማህበሩ ከከተማ ወጣ ብሎ ለመስራት ሃሳቦች የተቀመጡ ቢሆንም የተፈለገውን ያክል እንቅስቃሴ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ስራውን ለማስፋፋት እቅድ ተቀምጧል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በጋራ መሰራት አለበት፡፡ በትንሽ ካፒታል መስራት የሚቻሉ ነገሮችን ከባንክ ጀምሮ የተወሳሰበ ነገር ስለሚገጥም ወጣቱ ተስፋ ይቆርጣል። ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ማህበሩ ለመስራት እቅድ አስቀምጧል፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013