ብዙ እናቶች ልጄ በጣም ያለቅሳል ቅጭት አለበት መሰለኝ ሲሉ ይደመጣል፤ “ቅጭት በህክምና አይድንም”፤ “ወጌሻ ብቻ ነው የሚያድነው፤ “የሚሉ መላምቶችን የሚያስቀምጡ አሉ። ይህንን ሀሳብ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪም እና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ፋሲል መንበረ እንደሚከተለው አብራርተውታል።
በመጀመሪያ ደረጃ ቅጭት የሚባለው ነገር በሽታ ነው? በዘመናዊ ሕክምና ውስጥስ ቅጭት የሚባል ነገር አለ? መንስኤውስ ምንድነው? ቅጭት የሚለውን ቃል የተለያዩ እናቶችን ጠይቄ እነሱ በሚያስቡት እና ከወላጆቻቸው በወረሱት ትርጉም መካከል ልዩነት ያለ ሲሆን፤ የሰውነት መላቀቅ ወይም የደም ስር መዞር፤ የአንጀት መውረድ ወይም “ቡአ”፣ የህፃናት የአእምሮ መናጋት፤ የአንገት በድንገት መታጠፍ ወይም መዘርጋት (በተለይ አንገታቸውን መደገፍ ያልቻሉ ህፃናት)፤ የሆድ ቁርጠትና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።
ከላይ ያሉት የህመም አይነቶች በዘመናዊ ሕክምና የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥቷቸው እንገኛለን። አንዳንዶቹ ተቀራራቢ ትርጉም እንኩዋን የላቸውም። እስኪ በአጭሩ እንመልከታቸው፤
1. “የሰውነት መላቀቅ” ወይም “ስር መዞር” የሚለው እርግጠኛ መሆን ባይቻልም joint dislocation/Muscle sprain ሊሆን ይችላል። ይሄም አንገታቸውን ወይም ሰውነታቸውን መደገፍ የማያችሉ ህፃናት ስናቅፋቸው በደንብ አንገታቸውን እና ጭንቅላታቸውን መደገፍ እንዳለብን የሚያሳስብ ነው።
2. የአእምሮ መናጋት (shaken baby syndrome) – ይህ በህፃናት ላይ የሚደርስ የጥቃት አይነት ሲሆን የሚከሰተውም የጨቅላ ህፃን ልጅ ጭንቅላት በሀይል ሲወዘወዝ ወይም ሲነቀነቅ ነው። ይህ አደጋ ብዙ ጊዜ የሚከሰተው አሳዳጊዎች የህፃኑ ለቅሶ ለማስቆም በሚል ካለማወቅ ወይም በጣም ከመጨነቅ የተነሳ ልጁን በሀይል ሲወዘውዙት ነው። በዚህ ወቅት የልጁ አንጎል በራስ ቅሉ ውስጥ ከኋላ ወደ ፊት ከፊት ወደ ኋላ እየሄደ ከራስ ቅሉ (አጥንቱ) ጋር ይጋጫል። በዚህም ጊዜ በተለያዩ አእምሮ ወይም አንጎል ክፍሎች ውስጥ ደም መድማትና መፍሰስን ያስከትላል። ይህ ጥቃት የደም ስሮችን እና የአንጎል ህዋሶችን በማውደም አእምሮ ውስጥ በቂ የደም ዝውውር እንዳይኖር እና የነርቭ ህዋሶች ኦክስጅን እንዳያገኙም ይከለክላል። ከዚህ አልፎ ተርፎም የሕፃናቱን አንጎል በመጉዳት ሞትን ሊያስከትል ይችላል።
3. ሌላው የአንጀት መውረድ (ቡአ) የሚለው ነው – በሕክምናው አጠራር “Intussusception” (ኢንቱሰሰፕሽን) ይባላል። ይሄ በሽታ የሚከሰተው የተወሰነው የአንጀት ክፍል በሚቀጥለው የአንጀት ክፍል ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሲገባ እና ሲቀረቀር የሚከሰት የአንጀት መዘጋት ነው።
4. የህፃናት ሆድ ቁርጠት (infant colic) – ህፃናት በቀን ውስጥ የሚያለቅሱበት ሰዓት በአጠቃላይ ድምሩ ከ1 – 3 ሰዓት ሊሆን ይቻላል። ይህ በብዙ ህፃናት ላይ የሚከሰት እና ተፈጥሯዊ ሂደት ነው። ሆኖም ልጆዎ በሚያለቅስበት ሰዓት በቀን ውስጥ ከ3 ሰዓት በላይ ከሆነ እና ለቅሶው በሳምንት ውስጥ ቢያንስ ሶስት ቀን እና ከዛ በላይ ከሆነ እና ከሶስት ሳምንት በላይ ከቆየ ልጆዎ የሆድ ቁርጠት(Infantile colic) አለው ተብሎ ይታሰባል። የህፃናት የሆድ ቁርጠት ብዙ ጊዜ ብዙ ህፃናት ላይ የሚከሰት ጊዜያዊ ችግር ሲሆን በተለይም 4 ወር ዕድሜ ድረስ ያሉ ህፃናት ላይ የሚታይ ህመም አይነት ሲሆን፤ ዋና መለያውም የማያቋርጥ ረጅም ለቅሶ እና መነጫነጭ ነው።
በአጭሩ ቅጭት የሚለው ቃል በባህላዊው ሕክምና እና በተለያየ ማህበረሰብ ውስጥ የተለያየ ትርጉም ቢኖረውም በዘመናዊ ሕክምና ውስጥ ግን አንድ የተወሰነ በሽታ (specific disease) ወይም ተቀራራቢ ውርስ ትርጉም የለውም። ስለዚህ በተለያየ መልኩ ለሚከሰት የህጻናት ህመም መፍትሄውን ለማግኘት ወደ ሀኪም ዘንድ በመሄድ ማሳየት (ማስመርመር) ከሁሉም የተሻለ አማራጭ መሆኑ ይናገራሉ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2013