በአገራችን ብሄርን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ዘረኝነት እንዲስፋፋና አንዱ ሌላውን ከማቀፍ ይልቅ እንዲጠራጠርና እንዲርቅ እያደረገ ነው፡፡
አቶ ሻለሙ ስዩም በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የውጭ ግንኙነት መምህር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ ጎሳን ወይም ቋንቋን መሰረት በማድረግ ፓርቲዎችን አቋቁሞ እንቅስቃሴ ሲጀመር እወክለዋለው ብሎ ከሚነሳው ጎሳ ውጭ ድምፅ ማግኘት አይችልም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ቅስቀሳ በዘረኝነት ፖለቲካ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ የአንዱ ድል ለሌላው ውድቀት እንዲሆን አድርጓል፡፡ ይሄም የርስበርስ ግንኙነቶች መጠራጠርና በፍራቻ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡
እንደ አቶ ሻለሙ አባባል፤ የዘረኝነት ፖለቲካ ቋንቋን፣ ባህልንና አሰፋፈርን መሰረት አድርጎ ልዩ የሆነ ማንነት ላይ በማተኮር የሚመሰረት ነው፡፡ በነዚህ ምክንያቶች የኔ የተለየ ነው የሚለው ፕሮፓጋንዳ የደህንነት ስጋት ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል የዘረኝነት ፖለቲካን መቼም የማይፈታና የማይታረቅ አስተሳሰብ በማድረግ እዛ ላይ ቁጭ ብለው የራሳቸውን ፍላጎት የሚያስፈፅሙ ሰዎች በብዛት መኖር ችግሮች እንዲባባሱ አድርጓል፡፡
አብዛኛዎቹ ጉዳዮች የተማረው ሰው የሚያንቀሳቅሳቸው ናቸው የሚሉት አቶ ሻለሙ፤ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ አንዱ ቡድን በአገሪቱ ብሄርን መሰረት ያደረገ አገዛዝ ያስፈልጋል ሲል ሌላኛው ቡድን ደግሞ ቅድሚያ የህዝብ አሰፋፈር መታየት አለበት የሚል የሀሳብ ፍትጊያ እንዳለ ያመለክታሉ፡፡ በተጨማሪም ለአገሪቱ የዜግነት ፖለቲካ ያስፈልጋል የሚሉ ሀይሎች በብሄሮች መካከል ግጭትም መቃቃርም የለም ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ በብሄሮች መካከል የማይታረቅ ግጭት ስላለ ሁሉም ለየብቻው ጥቅሙን ማስጠበቅ አለበት የሚል ሀሳብ በመያዛቸው የዘረኝነት ፖለቲካ እንዲስፋፋ በር መክፈቱን ይናገራሉ፡፡
እነዚህን ሀሳቦች ለማስታረቅ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የአገሪቱን ጥቅም ሊያስከብር የሚችለው በሚያመጣቸው ሀሳቦች ከሱ ክልል ውጭ ያለውንም ገዥ ማድረግ እንደሚገባው በመጥቀስ፤ የተለያየ ቋንቋና አሰፈፋር መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ጉዳዮች የዘረኝነት ፖለቲካ መገለጫዎች በመሆናቸው ሊስተካከሉ እንደሚገባ ይናገራሉ ፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ እምቢአለ በየነ፤ የዘረኝነት ፖለቲካ በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ሲታይ ከራስ ማንነት ቡድን ጋር ያለን ጠንካራ ግንኙነት እና አንዳንዴም የሌላው ቡድን መብቶችና ማንነቶች ወደ ጎን እስከማለት የሚያደርስ ስሜትና ርዕዮት አለም ሊባል እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ የዘረኝነት ፖለቲካ የመበደልና የመገፋት ስሜት በመፍጠር እኛና እነሱ የሚል አስተሳሰብ ሊያመጣ የሚችል መሆኑን በመጥቀስ፤ ከቡድን ውጭ ያሉትን በመግፋት ከአገራዊ ማንነት ይልቅ የቡድን ጥቅም ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይገልፃሉ:: በአገሪቱ ያለው የዘረኝነት ፖለቲካ ህገ መንግሥቱ የሚደግፈው ስለሆነ የፖለቲካ ስርዓቱና አደረጃጀቱ የቆመው በዋናነት በዘረኝነት ላይ መሆኑን አቶ እምቢአለ ይጠቅሳሉ፡፡ የተዘረጋው የአገሪቱ መዋቅር ፌዴራሊዝሙ በራሱ በብሄር ላይ የተዋቀረ መሆኑ የአሰራር፣ የአደረጃጀትና የክልሎቹ አወሳሰን አንድ ማሳያ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ እምቢአለ ገለፃ፤ እንደመገለጫ የሚቀመጠው በአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲደራጁ አብዛኛዎቹ የቡድን ማንነት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስኬታማ የሚሆኑት በሀሳብና በርዕዮት ዓለም ተመስርተው አማራጫቸውን አቅርበው ቢወዳደሩ ዴሞክራሲን ያጎለብታሉ፤ ህዝቡንም ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ በአገሪቱ አብዛኛዎቹ በቡድን ማንነት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው የዘረኝነት አስተሳሰቡ ስር የሰደደ መሆኑን ያሳያል፡፡
ክልሎች የየራሳቸውን መገናኛ ብዙኃን አቋቁመው የሚያሰራጩት መረጃ ሲታይ የአገሪቱ ፖለቲካ ወደ ቡድን ማጋደሉን ማሳያ መሆኑን አቶ እምቢአለ ይጠቅሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በሚለው፣ በህገመንግሥት፣ በሰንደቅ ዓላማ፣ በወሰን አከላለል እና በበርካታ ነገር መስማማት አለመቻሉ የዘረኝነት ፖለቲካው መገለጫ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁን ወቅት በአንዱ ብሄር እና በሌላው ብሄር መካከል መተማመን አለመኖሩን ያስረዳሉ፡፡ ይሄንን ጉዳይ ደግሞ በተለያየ የቡድን ግጭት እና የሰው መፈናቀል ማየት እንደሚቻል ያብራራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ስር ጎሰኛ አስተሳሰብ መቼ እንደተጀመረ በውሉ ለማወቅ አዳጋች ቢሆንም ጉልበት እያገኘ የመጣው ግን ዘመናዊ ትምህርትን ቀስመው ወደ አገሪቱ በመጡ ወጣቶች በኩል እንደሆነ ይታመናል፡፡ እነዚህ ወጣቶች የአውሮፓ ሀገራት ብሄርተኝነት በተቀጣጠለበት ዘመን በቦታው መኖራቸውን ተከትሎ በዚያ ያዩትን ነገር በአገራቸውም ለመተግበር ጥረዋል ፡፡ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የተዘረጋው የብሄር ፖለቲካ ሀገሪቱን ለተመሣሣይ ቀውስ ዳርጓታል። በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት የቀድሞ ሥርዓትና መሪዎች በሀገሪቱ ታሪክና በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ የነበራቸውን ሚና እና አስተዋፅዖ አሳጥቷቸዋል። በዚህ ምክንያት፣ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ በአገሪቱ ታሪክና የቀድሞ መሪዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት እንዳይኖር አድርጓል። የብሔር ፖለቲካን ያለ ቅጥ በማጦዝ የብሔር ፅንፈኝነትን እያስፋፋ እና ለሉዓላዊነትና ነፃነት የታገሉ ብሔራዊ ጀግኖችን እየገፋ በመሄዱ አገራዊ መግባባትና የአንድነት ስሜት ከሕብረተሰቡ ውስጥ ተሟጥጦ በማለቅ ላይ ይገኛል።
አቶ እንቢአለ እንደሚናገሩት፤ የአገሪቱን እጣ ፈንታ ለማስተካከል መጀመሪያ የተበላሹትን በህግ አግባብ በማስተካከል፣ በዴሞክራሲ መንገድ መልካም አስተዳደር በማስፈን፣ ፍትሃዊ ልማትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ በመግባባት የእርቀ ሰላም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ቡድንተኝነቱ ለፖለቲካ መነገጃ የሚውል ከሆነ አገሪቱ የብጥብጥና የሁከት አውድማ ትሆናለች፡፡
እንደ አቶ ሻለሙ ገለፃ፤ ወደ መፍትሄ ለመምጣት ግዴታ ሁሉንም ያማከለ ወይም አካታች የሆነ ስርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ፖለቲካው ላይ ወይም ስልጣን የያዙ ሰዎች የሚዘርፉት ነገር ሰለታያቸውና ወይም ልዩ ተጠቃሚነት ለማግኘት የሚሮጡ ከሆነ አንዱ ሲመጣ ከፊሉን መጥቀምና ከፊሉን ደግሞ መጉዳት ይከሰታል፡፡ በዚህ ደግሞ ከነበረው አዙሪት ሳይወጣ በየዘመኑ በዳይን እያወረዱ ሌላ በዳይ እያወጡ መሄዱ ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
መርድ ክፍሉ