ተወልዳ ያደገችው በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ ነው። የከፍተኛ ትምህርቷን ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ተከታትላለች። ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ በመቀጠል የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ለመከታተል ወደ ሀገረ አሜሪካ አቅንታለች። በአሜሪካን ሀገር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በአካውንቲንግ ተምራ ተመርቃለች። በኮፕሬት አሜሪካ በተማረችው ትምህርትም አካውንቲንግ፣ ፋይናንስና ኦዲት በመሳሰሉ የስራ ዘርፎች ተሰማርታ ስታገለግል ቆይታ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች።
በሀገረ አሜሪካ የነበራትን የ12 ዓመታት ቆይታ ገታ አድርጋ ፊቷን ወደ ሀገሯ ኢትዮጵያ መልሳለች። ሁልጊዜ ቢሆን በትውልድ ሀገሯ ላይ ማህበራዊ አስተዋጽኦ ያለው ሥራ የመስራት ሕልምና ምኞት ነበራት። ይህን ህልሟን ዕውን ለማድረግና ለሌሎች በመትረፍ ሀገሯ ላይ ኢንቨስት ማድረግን ወስና ከዛሬ አምስት አመት በፊት ወደ ሀገር ቤት ተመልሳለች።
ሁሉም ነገር ከተሟላበት ሀገረ አሜሪካ ብዙ መሰናክሎችን ማለፍና በውጣ ውረዶች መፈተንን ወደ ሚጠይቃት ሀገራ ስትመጣ ብዙ ያልጠበቀችው ነገሮች ገጥመዋታል። በተለይም ከሰለጠነው ዓለም እንደመምጣቷ እንዲሁም ለመስራት ካለት ጉጉት የተነሳ ሀገር ውስጥ ባሉ መጓተቶች ብዙ ተፈትናለች። ይሁንና አብዛኛውን መሰናክል አልፋ ያሰበችውን ፋብሪካ በመክፈት የሀገር ውስጥ አልባሳትን ማምረት ጀምራለች።
በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ አልባሳት እየተለመደ ከመምጣቱም በላይ ትኩረት እየተደረገበት ያለ እና እየተበረታታ የመጣ ዘርፍ እንደመሆኑ በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ነኝ የምትለው የዛሬዋ የስኬት እንግዳችን ጀነት ለማ ዛሬ የጋበር አልባሳት መስራችና ባለቤት ናት። ጋበር የሀገር ውስጥ አልባሳትን ለማምረት ለ12 ዓመታት ከኖረችበትና ከተማረችበት ከሀገረ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው በኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በማመን ነው።
በሀገሯ ሙሉ እምነት ኖሯት ሰርቼ መለወጥ እችላለሁ። ለዜጎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ማህበራዊ አስተዋጽኦ ማበርከት እችላለሁ በማለት ወደ ስራው የገባችው ጀነት በስኬት አምዳችን እንግዳ ስናደርጋት ካላት ተሞክሮ በመነሳት ለሌሎች አርአያ ትሆናለች፤ ታስተምራለች ከሚል እምነት ነው።
‹‹አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ነገሮች ቢመቻቹለት በሀገር ውስጥ መፍትሔ እየሆነ መኖር ይፈልጋል የሚል እምነት አለኝ›› የምትለው ጀነት እርሷም በልቧ ውስጥ ያለውን መሬት ላይ ለማውረድ በጋርመንት ሥራ ውስጥ ተሰማርታለች። ቢዝነስ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ በማሰብ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ቀዳሚ ምርጫ ያደረገችው ጨርቃጨርቅና ልብስ ስፌትን(ጋርመንት) ነው። ይህን ሥራ የመረጠችበት ምክንያት ደግሞ ከልጅነቷ ጀምሮ የፋሽን ዲዛይን ፍላጎት የነበራት በመሆኑና ቤተሰቦቿ በዘርፉ ተሰማርተው ይሰሩ ስለነበር ነው። ከዚህም ባለፈ ዘርፉ ሰፊ የሰው ሀይል በተለይም ሴቶችን የሚጋብዝ መሆኑ ያስደስተኛል የምትለው ጀነት፤ እንዳሰበችውም ለበርካታ ሴቶች የስራ ዕድል መፍጠር ችላለች።
የጋርመንት ኢንዱስትሪ ከሌሎች ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በበለጠ ሰፊ የስራ ዕድልና በርካታ ሴቶችን የሚፈልግ በመሆኑና ሴቶች ማደግ የሚችሉበትና ቀጣይነት ያለው ዘርፍ ነው። ምክንያቱም የጋርመንት ሥራ ዛሬ ተሰርቶ በቃ አለቀ የሚባል ሳይሆን ተያያዥና ቀጣይነት ያለው ነው። በዚህም የድርጅቱ ሰራተኞች በሙሉ እራሳቸውን በማሳደግ በየጊዜው በሚያገኙት ስልጠና ወደፊት መራመድ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
በመሰረታዊነት በጋበር አልባሳት ፋብሪካ የሚመረቱ ምርቶች ሰራተኞቹን የሚያሳውቅበትና ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሸጋግሩበት እንዲሆን ይሰራል። የድርጅቱ ጥረትም የሀገር ውስጥ ምርቶች ከውጭው ዓለም የበለጠ ጥራት ኖሯቸው በተለይም ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ በጥራትም ሆነ በመጠን እንዲሁም በዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ ምርት ለማምረት ነው።
በመሆኑም ጋበር አልባሳት በአሁን ወቅት በሚያመርተው ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲሁም ፋሽን በመከተል ዕውቅናን እያተረፈ የሚገኝ መሆኑን ጀነት ተናገራለች። ከሚያመርቱት ምርቶች መካከል ኮሌታ ያላቸው ቲሸርቶች፣ ሹራቦችና ገበያ ውስጥ በስፋት የሚፈለጉ የተለያዩ አልባሳትን ሁልጊዜ በስፋት በማምረት ለነጋዴዎች ያስረክባሉ።
ከዚህ ውጭ የሆኑ ህትመት ያላቸውን የተለያዩ ምርቶች ደግሞ በትእዛዝ የሚያመርቱ ሲሆን በስፋት የሚጠቀሙትም ትላልቅ ድርጅቶች፣ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ናቸው። እነዚህ ድርጅቶችም በተለያየ ጊዜ መጠቀም የሚፈልጉትን የተለያዩ አልባሳትን በትእዛዝ ያሰራሉ።
ጋበር አልባሳት ወደ ሥራ ሲገባ አምስት ሰራተኞችን ይዞ እንደነበር የምታስታውሰው የድርጅቱ ባለቤት ፤በአሁን ወቅት 100 ሰራተኞችን ይዞ የሀገር ውስጥ አልባሳትን እያመረተ ይገኛል። ፋብሪካው የዛሬ አምስት አመት ሥራውን ሲጀምር የነበረው የሰው ኃይል እና መነሻ ካፒታል አሁን ካለው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ትገልጻለች። በቂ የሆነ መነሻ ካፒታል ይዛ የተነሳች በመሆኑም በፍጥነት ወደ ምርት መግባት ችላለች። በመሆኑ በአሁን ወቅት ጋበር አልባሳት ፋብሪካ ሰባት ሚሊዮን ካፒታል ላይ መድረስ ችሏል።
ጋበር አልባሳት ምንም እንኳን ዛሬ የተለያዩ የሀገር ውስጥ አልባሳትን በስፋትና በጥራት እያመረተ ለገበያ ማቅረብ ቢችልም የመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት ግን ፈታኝ እንደነበሩ ጀነት ታስታውሳለች። በተለይም ገበያ ውስጥ ለመግባትም የነበረው ሁኔታ እጅግ ፈታኝ ነው። ምክንያቱም የአብዛኞች ለሀገር ውስጥ ምርት ያለን አመለካከት የተንሸዋረረ በመሆኑ ገበያ ውስጥ ለመግባት ከባድ ጊዜን አሳልፈዋል።
ይሁንና የነበሩ ችግሮችን በሙሉ በጽናትና በሥራ ለማሳመን በተደረገው ጥረት ከአመት አመት የተሻላ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። በዚህም ባለፈው አመት በተለይም የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እያለ የሽያጭ መጠናቸው በእጥፍ ያደገ በመሆኑ ይህም የዕድገታቸው ምልክት እንደሆነ ትናገራለች።
የማምረቻ ቦታ እና መስሪያ ማሽኖችን በተመለከተ ጋበር አልባሳት የዛሬ አምስት አመት ስራውን ሲጀምር የግለሰብ ግቢ በከፍተኛ ዋጋ ተከራይቶ ነበር። ይሁንና ሥራው የግለሰብ ቤት ተከራይቶ የሚገፋ እንዳልሆነ በመረዳት ቦታ እንዲሰጣቸው ለአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አመልክተዋል። ከሁለት ዓመታት በኋላም ጋበር አልባሳት የሚያመርታቸውን ምርቶችና ያለውን የስፌት ማሽኖች እንዲሁም የወደፊት ራእዩን በመገንዘብ የማምረቻ ሼድ ከመንግስት ማግኘት ችሏል።
የማምረቻ ቦታ ከመንግስት ማግኘት መቻሏ በእጅጉ አግዞኛል የምትለው እንግዳችን ፤ በዚህም እድለኛ እንደሆነች ትናገራለች። በፋብሪካው 90 የሚደርሱ ዘመናዊ የስፌት ማሽኖችም አሉ። በጋበር አልባሳት የሚመረተው ምርት ኢትዮጵያዊ የሆነ እና ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ የሚችል በመሆኑ የሀገር ውስጥ ግብአትን ይጠቀማሉ። ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎችና አክሰሰሪ አምራች ከሆኑ ድርጅቶች ጋር ትስስር በመፍጠር እየሰሩ ይገኛሉ።
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባት ሀገር ኢትዮጵያ አልባሳትን ከውጭ ሀገር ታስገባለች። ይህን መቀየር ይቻላል። በሀገር ውስጥ የተለያዩ ጥራታቸውን የጠበቁና ዘመናዊ የሆኑ ፋሽኖችን ተከትሎ ማምረት ይቻላል። ለዚህ ግን እያንዳንዳችን በተለይም በጋርመንት ዘርፍ የተሰማራን ሰዎች ማመን አለብን። ከአምራች እስከ አመራር ያሉ አካላት አስተሳሰባችንን መቀየርና ለራሳችን ያለንን ግምት ከፍ ማድረግ አለብን የሚል እምነት አላት።
[[በተለይም ለምናመርተው ምርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን አጨራረሱ ላይ በጥንቃቄ መስራት ከተቻለ ከውጭ ሀገር ምርት አብልጦ መስራት ይቻላል። ከኢትዮጵያውያን አቅም በላይ የሆነ ነገር የለም። ነገር ግን ስልጠና ወሳኝ እንደሆነና ከቲዎሪ ትምህርት በበለጠ የተግባር ልምምድ ላይ በማተኮር ጥራት ያለውን ምርት ማምረት ይቻላል]] ትላለች።
በጋበር አልባሳት ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችም በተለያየ ጊዜ ቀደም ሲል ያነበራቸውን ክህሎት በስልጠና የተለያዩ አማራጮችን እንዲያገኙ ይደረጋል። በዚህም በርካታ ሰራተኞች ከነበሩበት የስራ ዘርፍ ወደ ሌላኛው ሙያ በመለማመድና ስልጠና በመውሰድ መሸጋገር ችለዋል።
‹‹በውጭው ዓለም ስኖር ያጣሁት ነገር የለም ነገር ግን አንድ ሰው በውስጡ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር ማድረግ ካልቻለ እርካታን አያገኝም›› የምትለው ጀነት፤ ወደ ሀገር ቤት እንድትመለስ ያደረጋትም በውስጧ ያለውን መሻት ለማሟላት ነው። በዚህም በተወሰነ ደረጃ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደቻለች ታምናለች። ይሁን እንጂ ወደፊት ከዚህ በበለጠ መስራት ይጠበቅብኛል የምትለው ጀነት፤ ውጭው ዓለም ስትኖር ብዙ መማር እንደቻለችና ልምድ ያገኘች መሆኑን ትናገራለች።
በተለይም የአንድ ቢዝነስ ሀላፊ በመሆን ሥራውን መምራት የሚያስችል ልምድና ዕውቀት አሜሪካን ሀገር በተማረችው ትምህርት ማግኘቷን ታስታውሳለች ።ከዚህ ባለፈም አሜሪካ የሥራ ስነምግባርን ተምሬያለሁ። የሥራ ስነምግባር ደግሞ ውጤታማ ያደርጋል ትላለች ። ሁሉም ሰው በስራ የሚያምን እና ሰርቶ በመለወጥ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ በመሆኑ ሥራ ሳልንቅ እስከ ታችኛው የመኪና ጥበቃ ወይም ፓርኪንግ ሥራ ሰርቻለሁ ስትል ታውሳለች። በዚህም ተጠቃሚ እንደሆነች ተናጋራለች።
ሌላው በውጪ ሀገር ያለና በሀገር ውስጥ የሌሉ በርካታ ፈታኝ ነገሮች መኖራቸውን ያነሳችው ጀነት፤ በውጭው ዓለም ሁሉም ነገር በኦን ላይን ይገኛል። አንድ ሰው እንዴት ያለ ቢዝነስ ልጀምር ቢል እንኳን መረጃን በቀላሉ ማግኘት ይችላል። በሀገር ውስጥ ደግሞ በቀላሉ የሚገኝ ነገር የለም ከትንሽ እስከ ትልቅ ሥራ ረጅም ሂደትን ይጠይቃል፤ ጊዜ ይወስዳል። እንዲህ ያለው አሰራር ደግሞ ምርታማ አያደርገንም። ስለዚህ ለጊዜ ትኩረት በመስጠት በሁሉም ዘርፍ በተቻለ አቅም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ቢቻል ምርታማ መሆን ይቻላል።
‹‹የዛሬ አምስት አመት ወደ ሥራ ስገባም ይኸው ችግር ገጥሞኛል ። ነገሮች እኔ በምፈልገው ፍጥነት አልሄዱም ነበር›› በማለት የምታስታውሰው ጀነት፤ በአሁን ወቅት ግን ለውጥ መኖሩን እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት የሚቻልበት አማራጮች እየመጡ መሆናቸውን ትመሰክራለቸ። ይሄ ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥሉ እንደሚገባም ትናገራለች።
ኢትዮጵያዊ የሆኑ ምርቶችን በጥራት እያመረተ የሀገር ገጽታን ለመቀየር እየተጋ ያለው ጋበር ጋርመንት እዚህ ለመድረሱ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል። መማርና መማማር አስፈላጊ እንደሆነም በጽኑ ታምናለች። ሁልጊዜም ለመማር እና ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗንም ትጠቅሳለች ።
በቀጣይም ጋበር አልባሳት የማምረቻና የመሸጫ ሱቆችን በማስፋፈት ከሀገር ውስጥ አልፎ ጎረቤት ሀገራትም ተደራሽ ለመድረግ ይሰራል። አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ አፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ምርት ይጠቀማሉ። አፍሪካ ሀገራትም እርስ በርስ የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ እየተደረገ ያለ ጥረት በመኖሩ ይህን ዕድል በመጠቀም የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት ዕቅድ ያላቸው እንደሆነ ትናገራለች።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለሥራ መነሻ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ቀላል አይደለም ›› የምትለው ጀነት፤ ያም ቢሆን ወጣቱ የሥራ ሥነምግባር ኖሮት ያገኘውን ሁሉ መስራት ቢችል በሮች ሁሉ ይከፈታሉ ፤ብዙ የሥራ ዕድሎች አሉ። ወጣቱ ያሉትን ዕድሎች ሁሉ መጠቀም አለበት። በአቋራጭ ገንዘብ ለማግኘት ሳይሆን በስራ አልፎ ለሚያገኘው ውጤት መትጋት እንዳለበትና ስልቹ መሆን እንደሌለበት ትመክራለች። እኛም ወጣቶች መሮጥ መስራት የሚችሉበትን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ እንዲሆኑ በመመኘት አበቃን!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013