
ቤት ለሰው ልጆች አስፈላጊ ከሆኑት ሶስት መሰረታዊ ነገሮች አንዱ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ለሰው አስፈላጊ የሆነው ቤት ባለቤት መሆን ለብዙዎች ቀላል አይደለም። እጅግ አዳጋች ነው። ይሁን እጅግ መሰረታዊ ነገር ማሟላት ከማይቻልበት ምክንያት አንዱ ወጪ ነው። ቤትን መስራት ወይም መግዛት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ለበርካቶች እጅግ ከባድ እየሆነ መጥቷል። በተለይም መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የቤት ባለቤት መሆን ህልም የሆነበት ዘመን ላይ እንገኛለን።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በከተሞች ያለው የቤት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደ መሄዱን ተከትሎ ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት አማራጮችን በመከተል በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የቤት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም፤ ያደረገው ጥረት የሚፈለገውን ያህል ውጤት እያስገኘ ነው ለማለት አያስደፍርም።
በአነስተኛ ወጪ እና በሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂዎች የቤቶችን እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ግንባታዎችን ማካሄድ ችግሩን ለመቅረፍ የተሻለ አማራጭ ነው። ተገጣጣሚ ቤቶችን የመስራት ቴክኖሎጂ በስራ ላይ ማዋል በተለይም በከተሞች አካባቢ እየሰፋ ያለውን የቤቶች ፍላጎት እና አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በዘርፉ የተሰማሩት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ተገጣጣሚ ቤት በመስራት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ኢንጂነር ብርሃኑ ካሳ ለኢትዮ ኮን የሬዲዮ ፕሮግራም እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ ተገጣጣሚ ቤት መስራት በአብዛኛው የተለመደ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረውን ለየት የሚያደርገው ቃጫና ኮንክሪትን በመጠቀም ቀደም ተብሎ በተመረተው አምስት ሴንቲ ሜትር ውፍረት ያለው ግድግዳ በመጠቀም ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ቤት ማጠናቀቅ የሚቻልበት ሁኔታ የሚፈጥር ነው።
በምህንድስና ሙያ ከተመረቁ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደው እንደነበር የሚያነሱት ኢንጂነር ብርሃኑ በዚያው የእንግሊዞች ተገጣጣሚ ቤት የመስራት ቴክኖሎጂ ላይ የመሳተፍ እድል አግኝተው እንደነበር ያነሳሉ። ከዚያን ወቅት ጀምሮ ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገራቸው አስገብተው ስራ ላይ ለማዋል ጉጉት እንዳደረባቸው ይናገራሉ።
የእንግሊዞችን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ለመቀየር ባደረጉት ጥረት ችግሮች እንዳጋጠሟቸው ይናገራሉ። እንግሊዞቹ ጋር የሰው ጉልበት ዋጋ ውድ ሲሆን፤ የቤት መስሪያ ቁሳ ቁስ ዋጋ ደግሞ ርካሽ ነው። በኢትዮጵያ ደግሞ በተቃራኒው የሰው ሀይል ጉልበት ርካሽ ነው። መስሪያ እቃዎች ደግሞ ውድ ናቸው።
በመሆኑም የውጪውን ቴክኖሎጂ ቀጥታ ጥቅም ላይ ከዋላ እንደ መደበኛው ቤት፤ ለማስራት የሚወጣው ዋጋ ከፍተኛ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ቴክኖሎጂውን ለኢትዮጵያ በሚበጅ መልኩ ማላመድ አስፈላጊ ነበር። አነስተኛ ቁሳቁስ የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዲሁም የሰው ሀይል ችግር ስለሌለ የሰው ሀይልን ያለ ስስት በመጠቀም ተገጣጣሚ ቤቶችን መስራት እንደሚቻል አሰቡ።
በዚህ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ጥናት ሲያካሄዱ ቆይተው ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሰለጠነው ዓለም በብረትና በኮንክሪት የሚሰራውን ብረቱን በቃጫ በመተካት በቃጫና ኮንክሪት መስራት እንደጀመሩ ይናገራሉ። በሙከራ ደረጃ ታይቶ ከብሎኬት ያላነሰ ውጤት እንዳስገኘ የሚያብራሩት ኢንጂነር ብርሃኑ፤ ከዚያ በተጨማሪ በሰለጠነ ዓለም የሚሰሩ ተገጣጣሚ ቤቶች ብረትን ከ ኮንክሪት በመቀላቀል ግድግዳውን ከመገጣጣሚ ባሻገር የሚሰሩ ቤቶች ኮሎኖችም ይኖሩታል።
ኢንጂነር ብርሃኑ ግን የውጪውን አሰራር በመተው ኢትዮጵያዊያን አባቶች የሚጠቀሙበትን አሰራር ነው መጠቀም የጀመሩት። ኢትዮጵያዊያን አባቶች የጭቃ ቤት ሲሰሩ ሙሉ ግድግዳው መሬት ላይ ያርፍና ግድግዳው ለጣራ መሰረት ሆኖ ነው የሚያገለግለው።
እሳቸው የጀመሩት ቴክኖሎጂ በጭቃና በእንጨት የሚሰራውን ቤት በቃጫ እና በኮንክሪት በመተካት ወደ ስራ እንደገቡ ይናገራሉ። ግድግዳውን ራሱኑ 50 ሴንቲ ሜትር ወደ መሬት ውስጥ በመቅበር ምንም አይነት መሰረት ሳያስፈልገው ከስር በሚኖረው አነስተኛ ኮንክሪት በመጠቀም ቤቱን ማቆም እንደቻሉ ይናገራሉ።
በተጨማሪም በኢትዮጵያዊያን አባቶች ክብ ቤት የሚሰራው ያለ ምክንያት አይደለም የሚሉት ኢንጂነሩ፤ ክብ ቤት ከአንድ በኩል ግፊት በሚያገኝበት ወቅት ከሁሉም አቅጣጫ ግፊቱን የመቋቋም አቅም አለው። ያንን የአያቶችን የሀገር በቀል ቴክኖሎጂ ከዘመናዊ ቤት አሰራር ጋር በማጣመር የሚሰሩ ተገጣጣሚ ቤት ሁሉም አቅጣጫዎች እንዲደጋገፍ በማድረግ፤ ከዚያም በብረት ቀለበት እንዲተሳሰር በማድረግ ምንም አይነት ኮለን ሳይኖረው ተገጣጣሚ ቤቱን መስራት እንደተቻለ ይናገራሉ።
እንደ ኢንጂነር ብርሃኑ ማብራሪያ፤ አንድ ቤት በሚሰራበት ወቅት የብሎኬት፣ የመሰረት፣ የኮለን እንዲሁም የልስን ወጪ የለውም።በቃጫና ኮንክሪት በተመረተው አምስት ሴንቲ ሜትር ግድግዳ ብቻ ቤቱን በሶስት ሳምንት አጠናቆ መጨረስ ይቻላል።
ቤት ለመስራት ስራ ላይ የሚውሉ ተገጣጣሚ የቤት ግድግዳዎቹ ሁለት ሜትር በአንድ ሜትር የሆኑ በግምት አንድ በር የሚያክሉ ሲሆኑ ውፍረታቸው አምስት ሴንቲ ሜትር ነው። እነዚህን ሁለት ሜትር በአንድ ሜትር የሆኑ ግድግዳዎች 5 ሴንቲ ሜትር መሬት ውስጥ ይቀበራል። አንድ ሜትር ከ50 ሴንቲ ሜትር ደግሞ ከመሬት በላይ ይኖራል።
እያንዳንዱ ግድግዳ 90 ዲግሪ ድጋፍ እንዲያገኝ ከኮርነር በመጀመር መሃል ላይ ያሉትን 90 ዲግሪ ድጋፍ ያልተደረገላቸውን ደግሞ 40 ዲግሪ ስፋት ያለው ኮንክሪት በመጨመር 90 ዲግሪ ድጋፍ እንዲኖረው በማድረግ ሁሉም ግድግዳዎች 90 ዲግሪ ይደጋገፋሉ። ከመደጋገፋቸው ባሻገር መሬት ላይ የሚተከሉ በመሆናቸው ጥንካሬ እንደሚያገኙም ኢንጂነሩ ይጠቅሳሉ።
የጣራ አሰራሩ ደግሞ መደበኛው የጣራ አሰራር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የሚያነሱት ኢንጂነር ብርሃኑ እንደማንኛውም ቤት ባለስድስት ብረት እየታሰረ በመደበኛው አሰራር ይሰራል። በር እና መስኮቶቹ ለአምስት ሴንቲ ሜትር የሚሆን ቻናል ላሜራ የተሰራ ማጠፊያ ይደረግና በልዩ ኮኔክሽን እንደሚሰራም ነው ያብራሩት። ኮርኒሱም እንዲሁም ተገጣጣሚ ሲሆን ኤል እና ቲ ሴክሺን ላሜራዎች በመጠቀም በፕላስቲክ ኮርኒስ ይሰራል። ወለሉ ደግሞ በቃጫና በኮንክሪት እንደሚሰራ ነው ያብራሩት። አጠቃላይ የቤቱ ስራ በሶስት ሳምንት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው።
በተገጣጣሚ መሳሪያዎች የሚሰራው ቤት የብረት ወጪ፣ ኮለን ወጪ፣ ቶፕ ታይ ቪል፣ ግሬድቢምን ጨምሮ የተለያዩ ብክነቶችን የሚቀንስ ከመሆኑም ባሻገር ብሎኬት እና መሰረት ስለማይኖረው ከሌላው አነስተኛ በሆነ ወጪ የሚገነባ ነው። በተለይም ቤት መስራት ህልም ለሆነባቸው መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የተሻለ አማራጭ መሆኑን ያነሳሉ።
ኢንጂነር ብርሃኑ እንዳሉት፤ ቤቱ የሚሰራበት ወጪ መደበኛ ቤት ለመስራት ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ነው። ከዚህ ቀደም በ40 ሺህ ብር 15 ካሬ የሆነ ሶስት በአምስት ቤት መጨረስ ነበር። በቅርቡ የግብዓቶች ዋጋ በመጨመሩ መጠነኛ ጭማሪ ታይቷል። አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ግን ቤቱን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ከ50 እስከ 60 ሺህ ይደርሳል። በመሆኑም ከዋጋ አንጻር አዋጭ ነው።
ተገጣጣሚ ቤቱን ለመስራት የሚወጣው ወጪ አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር ቤቱ የተሰራበት ቦታ ለሌላ ልማት በተፈለገበት ወቅት ቤቱን ነቃቅሎ ሌላ ቦታ ላይ ወስዶ መትከል ይቻላል። በሚነሳበት ወቅትም የሀብት ብክነት አይኖርም ማለት ነው። በመሆኑም ፋይዳው ላቅ ያለ ነው።
ከጭቃ ቤት እንኳ ባነሰ ዋጋ ከመሰራቱም ባሻገር፤ በአነስተኛ እውቀት የሚሰራ መሆኑን የሚያብራሩት ኢንጂነሩ፤ በአነስተኛ ስልጠና ወጣቶች ሊሰሩት የሚችሉት ቀላል ቴክኖሎጂ መሆኑን ይናገራሉ ። በሌላ በኩል በአጭር ጊዜ ማለትም አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቤቱን ማጠናቀቅ መቻሉ፣ ለብረት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ የሚያድን መሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ወደ ስራ በማስገባት የስራ እድል መፍጠር የሚችል መሆኑ፣ ለእንጨት እና ብሎኬት ስራዎች የሚወጣውን የእንጨት ወጪ መቶ በመቶ በማስቀረት የደን ጭፍጨፋ የሚያስቀር በመሆኑ ቴክኖሎጂው ከብዙ ነገር አንጻር ከመደበኛ ቤት የተሻለ ነው።
40 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ክፍል የሚያመርተውን የቆጮ ተረፈ ምርት ለሆነው ቃጫ ገበያ መፍጠሩ፤ እንዲሁም ቃጫን በሚመረትበት ሂደት ውስጥ የተትረፈረፈ የቆጮ ምርት እንዲኖር በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሚና የሚጫወት በመሆኑ የተገጣጣሚ ቤት አሰራር ተቆጥሮ የማያልቅ ጠቃሜታ ያለው ነው ይላሉ።
ቴክኖሎጂውን ለሰው ከማስተዋወቃቸው አስቀድመው የዛሬ አራት ዓመት ገደማ የራሳቸውን ገስት ሀውሶች ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ማስገንባታቸውን ይገልጻሉ። እስካሁን ድረስ ቤቶቹን ምንም አይነት ችግር አንዳላጋጠማቸው ይናገራሉ ። ለራሳቸው ከመስራታቸው ባሻገር የተለያዩ ሰዎች ጥያቄ በማቅረባቸው ከ30 ክፍል በላይ ቤቶችን ሰርተው ማስረከባቸውን ጠቁመዋል። ላለፉት ሶስት ዓመታት የሰሩትን ቤቶቹን ተከታትለው ማየታቸውን ገልጸው እስካሁን ምንም አይነት ችግር የለባቸውም ይላሉ።ይህም በመሆኑ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነቱ እየጨመረ መሆኑን ይመሰክራሉ ።
አዲስ ቴክኖሎጂ ወደ ገበያ ሲወጣ ስታንዳርድ መውጣት እንዳለበት የሚያነሱት አቶ ብርሃኑ ይህ ስታንዳርድ እስኪወጣ ለጊዜው ቤቶችን መስራት አቁመው እንደነበር ይናገራሉ። ስታንዳርዱን የማዘጋጀት ስራው በቤቶች እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከተጠናቀቀ እና ተገጣጣሚ ቤቶቹ ውጤታማ መሆኑ እና ቴክኒካሊም አስተማማኝ መሆኑ ተረጋግጦ የኢትዮጵያ ስታንዳርድ ሆኖ ከጸደቀ በኋላ ወደ ስራ መግባታቸውንም አንስተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013