
በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል አሜሪካ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ባደረሰችው ጥቃት በከተማው አውሮፕላን ማረፊያው ሌላ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት እንዳይደርስ መከላከል መቻሉን የአሜሪካ ወታደራዊ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ጥቃቱ ከአፍጋኒስታን የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ክንፍ ጋር ግንኙነት ባለውና ቢያንስ አንድ ሰው በጫነ በመኪና ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታወቋል።
ከአፍጋኒስታን ሰዎችን የማስወጣት ሥራው እየቀነሰ ቢመጣም አሜሪካ ተጨማሪ ጥቃቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቃ ነበር። ሆኖም አፍጋኒስታኖችን ከካቡል አየር ማረፊያ እስከ “መጨረሻው ሰዓት” ድረስ ማስወጣቷን እንደምትቀጥል ገልጻለች።
ዜጎችን እስከ ነሐሴ 25 ቀን ለማስወጣት በአሜሪካ እና አብዛኛውን ሃገሪቱን በሚቆጣጠረው በታሊባን መካከል ስምምነት ተደርሷል። ሌሎች ሀገሮች በሙሉ የማስወጣት ሥራቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን ተልዕኮዋን ለማጠናቀቅ አሜሪካ የመጨረሻዋ ሃገር ትሆናለች።
ከአፍጋኒስታን የሚመለሱ የመጨረሻዎቹ የእንግሊዝ ወታደሮችን በመጨረሻዎቹ በረራዎች እሑድ ወደ እንግሊዝ አቅንተዋል። አሜሪካ ታሊባን ዋና ከተማውን ከመቆጣጠሩ አንድ ቀን በፊት ጀምሮ ከ 110 ሺህ በላይ ሰዎችን ከካቡል አየር ማረፊያ ማስወጣት ችላለች።
እሑድ ዕለት የመካከለኛው ዕዝ ባልደረባው ካፒቴን ቢል አርባን አሜሪካ በካቡል አየር ማረፊያ ላይ “የማይቀር” ጥቃትን ለማስወገድ የታለመ የድሮን ጥቃት ማድረሷን ገልጸዋል።
‹‹ዒላማውን በተሳካ ሁኔታ እንደመታ እርግጠኞች ነን›› ብለዋል። አክለውም “ከተሽከርካሪው የተሰሙት ሁለተኛ ፍንዳታዎች ከፍተኛ መጠን ያለው የሚፈነዱ ቁሳቁሶች መኖራቸውን ያመለክታሉ” ሲሉ ገልጸዋል።
የድሮን ጥቃቱን ተከትሎ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን ማዕከላዊው ዕዝ መገንዘቡን ተናግረዋል። “ምን እንደተፈጠረ ግልፅ አይደለም። ተጨማሪ ምርመራ እያደረግን ነው። የንጹሃን ሕይወት መጥፋት በእጅጉ ያሳዝናል” ብለዋል።
የእሳቸው አስተያየት የመጣው በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ኃይለኛ ፍንዳታዎች ከተሰሙ በኋላ ነው። በማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ የተለጠፉ አንዳንድ ምስሎች ጥቁር ጭስ ከህንፃዎች በላይ ሲወጡ ያሳያሉ።
የአሜሪካ የስለላ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ “ልዩና ተዓማኒነት ያለው” ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ጥቆማ እንደደረሳቸውና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ወታደሩ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ይቀጥላል ብለዋል።
የካቡል ፖሊስ በበኩሉ እሁድ ዕለት በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ በሚገኝ ቤት ላይ በደረሰ የሮኬት ጥቃት አንድ ሕጻን መሞቱን ተናግሯል። ስለጥቃቱ ግልጽ መረጃ የለም።
ባለፈው ሐሙስ በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት 13 የአሜሪካ ወታደሮችን ጨምሮ 170 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
አይኤስ-ኬ የተባለው የእስላሚክ ስቴት ክንፍ ሐሙስ ዕለት ከደረሰው የቦምብ ፍንዳታ በስተጀርባ መኖሩን ገልጿል። አሜሪካ በወሰደችው የበቀል እርምጃ በምዕራብ አፍጋኒስታን በፈጸመችው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ሁለት “ከፍተኛ” የአይኤስ-ኬ አባላትን ገድያለሁ ብላለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሐሙስ በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ጥቃት ከተገደሉት 13 የአሜሪካዊያን ቤተሰቦች ጋር ተገናኝተዋል። ባይደን በደላዌር በሚገኘው የዶቨር አየር ኃይል ተጎጂዎችን ለመዘከር በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ነው የተሳተፉት።
በአይኤስ-ኬ የቦምብ ጥቃት ከተገደሉት የአሜሪካዊያን በተጨማሪ ሃገሪቱን ለመልቀቅ ተስፋ አድርገው በአውሮፕላን ማረፊያው የተሰለፉ በርካታ አፍጋኒስታኖችም ህይወታቸው አልፏል።
አብዛኞቹ የአይኤስ-ኬ በርካታ ሺህ አክራሪዎች ከካቡል በስተምሥራቅ በምትገኘው ናንጋርር ግዛት ተደብቀዋል ተብሎ ይታመናል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013