የአሸባሪው ህወሓት ትናንትና ሲተነተን ጫካና ሰው እናገኛለን። ሰፊ ጫካና ጠባብ ጭንቅላት። እንደሚታወቀው ጫካ የአራዊት መኖሪያ ነው። የሰው ልጅ ጫካ ውስጥ እንዲኖር ተፈጥሮው አይፈቅድለትም። እንስሳዊ ባህሪ ያለው የህወሓት ቡድን ግን ትናንት ከማህበረሰቡ ሸሽቶ ጫካ ነበር፤ ሰው ሆነ ሲባል ተመልሶ ዛሬም ጫካ ገብቷል። ጫካ ውስጥ ምን እንዳለ ህወሓቶች ቢነግሩኝ በግሌ ደስ ይለኛል።
የሰው ልጅ ከሁሉ ጋር ተግባብቶ የሚያኖረው አምላካዊ ጸጋ ተሰጥቶት ነው ወደ ምድር የመጣው፤ የህወሓት ተፈጥሮ ግን አምላካዊ ተፈጥሮ አይመስለኝም…እኔም እናንተም የማናውቀው አጋንንታዊ ባህሪ ለብሰው ወደ ምድር የተላኩ ይመስለኛል። ከትናንት እስከዛሬ ምሳቸው የሰው ደም ነው፤ ሰው እንደበሉ ነው፣ ከትናንት እስከዛሬ በሰው ደም እንደታጠቡ ነው። ከትናንት እስከዛሬ ህዝብ እንደ ዋሹ ሀገር እንዳጭበረበሩ ነው። ታዲያ በዚህ ህላዌ ውስጥ ከጭራቅነት ሌላ ምን ሊኖር ይችላል? ለምንድነው ጫካ የሚገቡት? ነገሮችን ሁሉ ለምን በሀይልና በጉልበት ብቻ ለመፍታት ይሞክራሉ? ሀገር እኮ የብዙ አስተሳሰቦች፣ የብዙ እይታዎች ውጤት ናት።
ሀገር እኮ የእኔና የእናንተ የጋራ እውነት ናት። በሀገር ውስጥ እኮ ትውልድ አለ..በሀገር ውስጥ እኮ አዲስ አስተሳሰብ አለ። ለምን እኛ ያልንው ካልሆነ ሲሉ ቡራከረዮ ይላሉ? ለምን በመግደልና በማሰቃየት ስልጣን ለመያዝ ይህን ሁሉ አሳር ይጠብሳሉ። ጊዜው ጫካ የሚገባበት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮች የሚፈቱበት ስልጡን ዘመን ነው። ጊዜው በውሸትና በማጭበርበር ሀገርና ህዝብ የሚወናበድበት ሳይሆን በቂና እውነተኛ መረጃ ተደራሽ የሚሆንበት ነው።
‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ.. የሚል ሀገርኛ አባባል አውቃለሁ። ድመት መነኮሰችም ዘውድ ጫነችም ያው ድመት ናት። ተፈጥሮ ውስጧ ያስቀመጠው ድመታዊ ባህሪ አለ። ምንም ቢሆን ትናንትናዊ አመሏን አትረሳም። አይጥ ባየች ቁጥር፣ ወተት ባየች ቁጥር፣ ቅቤ በሸተታት ቁጥር፣ ስጋ ባየች ቁጥር ድመትነቷ ትዝ ይላታል። ህወሓትም እንዲሁ ናት።
ትናንት የደርግን መንግስት ሊዋጋ ከነውሸቱ፣ ከነማጭበርበሩ ጫካ ነበር። ትናንት የራሱን ነጻ መንግስት እያሰበ በብሄር ስም ቁማር እየቆመረ ጉሮኖ ውስጥ ነበር። ትናንት በብዙ ውሸትና በብዙ ማስመሰል በንጹሀን እንባና ደም ላይ ተረማምዶ መንግስት ሆነ። አምባገነን መንግስትም ሆኖ አረፈው። ሀገርና ህዝብ የሌሉበት እኔነታዊ መንግስት። ታሪክ ትውልድ የሌለበት ፋሽስታዊ ስርዐት።
ፍቅር እውነት የመከኑበት ኦና ነፍስና ስጋ። ሁላችንም በዚህ ነውረኛ ስርአት ውስጥ ያለፍን ነን። የአሸባሪው ህወሓት የግፍ በትር ያላረፈበት ኢትዮጵያዊ የለም። አሁናዊ ችግሮቻችን ሁሉ የአሸባሪው ህወሓት የአገዛዝ ስርዐት የፈጠራቸው እንከኖች ናቸው። በኔና በእናንተ ጥላቻ ነገውን ሊሰራ፣ በኔና በእናንተ መገፋፋት ስልጣኑን ሊያረዝም ውሸት እየፈጠረ፣ ታሪክ እያበላሸ ያልሆነን እንደሆነ ሲነግረን ነበር። በእኔና በእናንተ መለያየት ዙፋኑን ሊያጸና፣ በእኔና በእናንተ ሞትና መከራ ህልሙን እውን ሊያደርግ ሲያባላንና ሲያገፋፋን ኖሯል። ቀኖች ሁሉ እንደ ትናንት አልነበሩምና..ሁሌም ፋሲካ አይደለምና ዛሬ ሰላም በተራቡ፣ ፍትህና እውነት በናፈቃቸው ኢትዮጵያውያን ተገፍቶ እንደለመደው ጫካ ገብቷል።
ቆይ ጫካ ውስጥ ምናለ? ሀገርና ህዝብ እመራለሁ የሚል አንድ ቡድን በሀሳብ የበላይነት ይደራደራል እንጂ ሰውን ሸሽቶ ጦርና ጎራዴ ይዞ እንዴት ጫካ ይገባል? ኧረ ጊዜው አይፈቅድም…ጊዜው የሀሳብ የበላይነት እንጂ የጠመንጃ አይደለም። ጊዜው የውይይት እንጂ የውሸትና የማስመሰል አይደለም። ጊዜው ሀገርና ህዝብ የሚቀድምበት እንጂ ለራስና ለጥቂቶች ብቻ የሚኖርበት አይደለም። እነዚያ ሀያ ሰባት ዓመታት ለኢትዮጵያውያን በከንቱ የባከኑ ዓመታት ነበሩ እላለሁ።
እጅግ የረቀቁ ውሸቶችን የሰማንበት፣ እጅግ ዘግናኝ ግፍና በደሎችን ያየንበት፣ እጅግ አስደንጋጭ ዝርፊያና ማጨበርበሮች የተስተናገዱበት። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቦታ ያጡበት…የጥቂቶች መብት ተከብሮ የብዙሀኑ የተጣሰበት…ዘመነ ፍዳ። ይህ አሸባሪ ቡድን ትናንትና እንደለመደው ዛሬም ጫካ ሆኖ ጥሩ ውሸቶችን በመዋሸት ህዝብ እያደናገረ ይገኛል። ይሄን ያክል ወታደር ማረክን፣ ምሽግ ደመሰስን…በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጠርን፣ አዲስ አበባ ልንገባ ነው እያለ በህልሙ እንኳን የማይሳካለትን ነገር እንደሆነ አድርጎ በማውራት የተለመደ የማደናገሪያ ተግባሩን ተያይዞታል።
ሰሞኑን ደግሞ ለየት ባለ ውሸት መጥቷል…ግን ህወሓት ውሸትና ማስመሰል ከየት ነው የሚመጣለት? ህዝብን በእውነት መምራትና ማስተዳደር እየተቻለ ውሸትና ማጭበርበር ለምን ይፈልጋል? ሰው እንዴት ከትናንት እስከዛሬ ሀገርና ህዝብን እየዋሸና እያታለለ ይኖራል? ሰው እንዴት ከትናንት ጥፋቱ አይማርም? ሰው እንዴት ውሸት ላይ ይህን ያህል ኢንቨስት ያደርጋል?
የሰሞኑ ውሸት ደግሞ በአይነትና በጥራቱ ከእስከዛሬው እንደሚለይ ደርሼበታለው። ምን ያህል ሀገር ለማፍረስ እንደተነሳ ይሄን ውሸቱን ማየቱ ብቻ በቂ ነው እላለሁ። ግን ተቆጭቻለሁ…ለምን አትሉኝም? ይሄን የተንኮልና የማወናበድ ‹‹ተሰጥኦው››ን ሀገር ለማልማትና ህዝብ ለመቀየር ቢጠቀምበት ስል…።
ሃያ ሰባት አመት ሙሉ በህዝብና በትውልዱ ላይ በሰራው ሸርና ተንኮል ፈንታ እውነትን አስተምሮን ቢሆን፣ ፍቅርና ይቅርታን አልምዶን ቢሆን፣ አንድነትና ወንድማማችነትን አውርሶን ቢሆን ይሄኔ እሱም እኛም የት በደረስን ነበር እላለሁ። አሸባሪው ህወሓት የውሸት ደራሲ እንጂ ሀገር ለመምራት የሚያስችል ምንም አቅም የለውም።
የሰሞኑን ውሸቱን ልንገራችሁና ጽሁፌን ላብቃ…በነገራችን ላይ ይህ ውሸቱ ያኔ ድሮ ከደርግ ጋር ሲዋጋም የሚዋሸው ነበር። እንዴ ሰው እንዴት ውሸት እንኳን አይቀይርም? ጦርነቱን እንደማያሸንፍና 4 ኪሎ ቤተመንግስት ብርቅ እንደሆነበት ሲያውቅ ጉዳያችን ከእናንተ ጋር አይደለም ጉዳያችን ከማዕከላዊው መንግስት ከዐብይ አሕመድ አገዛዝ ጋር ነው ሲል የአማራንና የኦሮሚያ ወጣቶችን መዋሸት ጀምሯል።
ግን ህዝብ ህወሓት ማን እንደሆነ ስለሚያውቅ ጆሮ አልሰጠውም። አሁናዊ መልኮቻችን ሁሉ በህወሓት የተንኮል ሴራ የጎደፉ ናቸው። አሁን ላይ እያሰቃዩን ያሉ ነገሮች ሁሉ የህወሓት ዘመን ውሸቶችና ሴራዎች የፈጠሯቸው ናቸው። እስኪ ተጠየቁ…ሀገር በውሸትና በማጭበርበር ትመራለችን? ሀገርና ህዝብ…ታሪክና ትውልድ በራዕዩ ውስጥ የሌሉት ቡድን እንዴት ለብሄር እኩልነት ነው የቆምኩት ብሎ ሊያወራ ይችላል? ይሄ ቡድን የኢትዮጵያ ጠላት ከመባል ውጪ ምን ሊባል ይችላል? የእኔን ሃሳብ ወርውሬ መልሱን ለእናንተ ትቼዋለሁ። ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013