በዛሬው የሳምንቱን በታሪክ አምዳችን ሁለት ክፍለ ዘመናትን መለስ ብለን በምድራችን ላይ እጅግ አስከፊ ተፅእኖ ከፈጠሩ ጥቁር ጠባሳዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን “የባሪያ ንግድ”ና እርሱን ለማስቀረት ስለተደረገ ታላቅ ትግል እንዘክራለን።
ይህን የትውስታ ማህደር ለማገላበጥ የወደድንበት ምክንያትም በዚህ እኩይ ድርጊት ላይ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛ የነበረችው ታላቋ ብሪታኒያ “የባሪያ ንግድ” በሁሉም ግዛቶቿ እንዲከለከል የሚያደርግ ህግ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ነሀሴ 19 ቀን በ1825 አ.ም አውጥታ ይፋ ማድረጓ ነው።
እርግጥ ነው ታላቋ ብሪታኒያ በዚሕ ዘመን ይህን ብታደርግም እ.አ.አ በ1803 የዴንማርክ ኖርዌይ በአውሮፓ የአፍሪካን የባርያ ንግድ በመከልከል የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ታላቋ ብሪታኒያ የአትላንቲክ ባሪያ ንግድን ከከለከለች ከሶስት ሳምንት በኃላ አሜሪካም በየትኛውም ወደብ በኩል ባሪያ ማስገባትን ከልክላለች። ይህም የሆነው እ.አ.አ ከ1801 እስከ 1809 ድረስ አሜሪካን በፕሬዚዳንትነት በመሩት በሶስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈረሰን ዘመን ነው። ይህን ማድረግ የሚያስችለው ህግም የሀገሪቱ ህግ አካል ተደርጓል።
የባሪያ ፈንጋይ ስርአት የማጥፋቱ ተግባር በተለያዩ ሀገሮች በተለያዩ ጊዜያት ነው የተፈጸመው። ቀስ በቀስ በሂደት የተፈጸመ ሲሆን፣ በተለይ በቅኝ ግዛት ዘመን በቅድሚያ በአንድ ሀገር የባሪያ ንግድ ሲከለከል ቀስ በቀስ በተቀሩት የቅኝ ግዛት ሀገሮችም እየተተገበረ መጥቷል።
በአገራችን ኢትዮጵያም የባርያ ንግድ ይሰራበት እንደነበርና በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ዘመን በአዋጅ ክልከላ እንደተደረገበት መረጃዎች ያመለክታሉ። ድርጊቱ “ ከሃይማኖትና ከሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት” አንፃር የሚወገዝ መሆኑን በማመን ነው ክልከላው የተደረገው። ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ሰዎች ያለ ፍቃዳቸው ጉልበታቸው እንዳይበዘበዝና ሰብዓዊ ክብራቸው እንዳይገፈፍ በማለት የተለያዩ ግዛት አስተዳዳሪዎችን በማስጠንቀቅም ነው የባሪያ ንግድን የሚከለከል አዋጅ ያስነገሩት።
ይህንንም በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ምርምር ያደርጉ የአገር ውስጥና የውጪ ምሁራን በመዛግብቶቻቸው ላይ አስፍረውታል። ይህን ጉዳይ በጥልቀት ከማየታችን በፊት የሰው ልጆችን ሞራላዊ፣ ሰብአዊና አካላዊ ፍቃድ የሚጥሰውና እጅግ የጭካኔ ድርጊትን የሚፈቅደው “የባሪያ ንግድ” መሰረት ምን እንደነበር ወደ ኋላ መለስ ብለን እንመልከት።
መነሻ ታሪክ
ባርነት በጠባብ ትርጉሙ «ሰዎች እንደ ሌላ ሰው ንብረት የሚገዙበት፣ የሚሸጡበት፣ የሚለወጡበት ወይም የሚያዙበት ሁናቴ» ማለት ነው። ይህም ደግሞ «የንብረት ባርነት» ሲባል፣ ይህ ሰዎች እንደ ንብረት ይቆጠሩ የነበረበት ሁኔታ በማናቸውም አገር ሕገወጥ ሆኗል። በሰፊው ትርጉም ሰው ያለፈቃዱ ወይም ያለደመወዝ ሥራ ወይም አገልግሎት ለመፈጸም ቢገደድ፣ ይህ በተግባር ባርነት ሊባል እንደሚችል ይገለጻል።
ስለዚህ በየአህጉሩ ከቅድመ-ታሪክ ጀምሮ ባርነት ይስፋፋ ነበር። በጥንታዊው ዘመን በጥንታዊ ግብጽ (ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት 3000 ዓመት በፊት) ባርነት እንደ ነበረ ይገለጻል። ከዚያም በኋላ ኤላምና ኪሽ የተባሉት ጥንታዊ አገራት የእርስ በርስ ጦርነት ሲጀምሩ ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት 2384 ከተማረኩት ሰዎች ቁጥር የተነሳ የባርነት መሠረት በዓለም ላይ ዳግመኛ ቆመ።
ከዚያን ዘመን ወዲህ፣ በብዙ አገራት ባርነት ሕጋዊ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አገራት ግን ተከልክሏል። በድሮ ዘመን በብዙ አገራት ሕገ መንግሥት የባርነት ልማድ በሕጋዊነት ይጠበቅ ነበር። ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በ600 ዓመተ አለም ግን በግሪክ አገር የአቴና አለቃ ሶሎን ባወጣው ሕገ መንግሥት መሠረት፣ የእዳ ባርነት ተከለከለና ባሮች የነበሩበት የአቴና ዜጎች ነጻነታቸውን አገኙ። የባሪያዎች ሁኔታን የሚቀምሩት ሕግጋት ወይም ልማዶች በጊዜ ላይና ከአገር አገር ይለያዩ ነበር።
የአውሮፓም መንግሥታት በአሜሪካ ውስጥ ቅኝ ግዛት ከተከሉ በኋላ፣ ከአፍሪካ የተማረኩትን ጥቁር ባርያዎች ይገዙ ነበር። በ1764 ባርያ መያዝ በእንግሊዝ ሕገወጥ እንዲሆን ተበየነ። ከዚህም በኋላ በብዙ የአውሮፓ አገራት እንዲሁም የአሜሪካ ሰሜን ክፍላተ አገራት ባርነት ሕገ ወጥ ይደረግ ጀመር። በስተደቡብ ያሉት በባርነት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች ግን ነፃነታቸውን ያገኙት ከአሜሪካ ብሔራዊ ጦርነት ቀጥሎ ነው። በ1858 ዓ.ም የአሜሪካ ሕገ መንግሥት 13 ኛው ማሻሻያ ሲደረግበት የባርያ ፈንጋይ ስርአት ከአሜሪካ ለዘለቄታው እንዲወገድ ተደረገ።
በአፍሪካ ግን የባርያ ንግድ ከዚህ በኋላም ቀጥሎ ነበር። በኢትዮጵያ ደቡባዊ ክፍሎች ይስተዋል እንደነበር መረጃዎች ያመልክታሉ። የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ይህን ስርአት ለማስወገድ ብዙ ደክመዋል። ይህን አስመልክተው ‹‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ ››በሚል በጻፉት መጽሀፍ ውስጥ ባርነትን ለመከልከል ስለተደረጉ ጥረቶች በሰፊው አብራርተዋል። በምዕራፍ 14 ላይ ባሮች ነጻ እንዲወጡ ስለመደረጉና የነፃነታቸውም ነገር በየአመቱ እየተሻሻለ ስለመሔዱ ጠቅሰዋል።
እሳቸው እንደገለጹት፣ የጣልያን መንግስት ወኪሎች ኢትዮጵያን ለመክሰስ ብለው በኢትዮጵያ ስለነበረው ባርነት በማጋነን ይገልጹ ነበር። ይሁንና በፍጥረት ጌታና ባርያ ተብሎ የተለየ ነገር አለመኖሩ በሰው ልብ የታወቀ ስለሆነ ፣ ከ1845 ዓ.ም ጀምሮ የነገሡት ነገስታት ዓፄ ቴዎድሮስ፣ ዓፄ ዮሐንስ ፬ኛና ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የባሪያ ንግድን ሕገ ወጥ የሚያደርጉ አዋጆች ቢያወጡም፣ እነዚህ አዋጆች በአብዛኛው በባላባቶች ዘንድ ቸል ተብለው ነበርና ተግባራዊ አልሆኑም ነበር።
አጼ ኃይለ ሥላሴ በበኩላቸው ባርያዎች ነጻ እንዲወጡ የተለያዩ አዋጆችን አውጥተዋል፤ በባሪያ ንግድ ውስጥ በተገኘ ላይም እስከ ሞት የሚያስቀጣ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አዋጅ አውጥተዋል። ፋሺስቶች ግን በኢትዮጵያ ባርነት አለ እያሉ ይከሱ ነበር።
በኢትዮጵያ ባርነት የቀረው፣በሀገሪቱ ባሮችም ነጻ የወጡት በጣልያኖች ትዕዛዝና ሥልጣኔ ነበረ ሲል ዊኪፒዲያ ያመለክታል፣ ዊኪፒዲያ ሰብአዊ ንግድ (ባርነት) ዛሬም በኢትዮጵያ እንዳለ እስከመጠቆም ይደርሳል፤ ይሁንና ባርነትና ሰብአዊ ንግድ በእውነት በኢትዮጵያ ወይም የትም አገር በዘመናችን በሕግ ክልክል ከሆነ ቆይቷል።
የክልከላው አዋጅ በኢትዮጵያ
የታሪክ ተመራማሪው አቻምየለህ ታምሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የባላባቶችና አገረ ገዢዎች የነገስታቱን ህግ ጥሰው የባሪያ ንግድ ላይ ይሳተፉ እንደነበር ታሪክ አጣቅሶ ሰፋ ያለ ትንታኔና ማስረጃዎች አቅርቦ ነበር። ከዚህ ውስጥም በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የትብብር መድረኮች ላይ
ይፈጥር የነበረውን ችግርና የተወሰደውን እርምጃ በዚህ መንገድ ነበር አስፍረውታል።
በ1916 ዓ.ም ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (League of Nations) አባል ለመሆን ባመለከተችበት ወቅት በእንግሊዝ መንግሥት ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦባት ነበር። የኢትዮጵያን መንግሥት የአባልነት ማመልከቻ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (League of Nations) ለማስገባት ወደ ጀኔቫ የተላከው ቡድን መሪ የነበሩት ራስ ናደው /አባ ወሎ በፈረስ ስማቸው «አባ መብረቅ» / እንግሊዝ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል እንዳትሆን የተቃወመችበትን ምክንያት ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት ገልጸዋል።
ቡድን መሪው «እንግሊዝ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሐን የዘገቡትንና በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኤደንና በግብጽ ባሉት የቅኝ ግዛት መንግሥቷ በኩል የሰበሰበችውን ማስረጃ በማያያዝ በደቡብ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ስለነበረው የባርያ ንግድ ሁኔታ፤ በተለይም በከፋ፣ በማጂ፣ በጊሚራና በጉራፈርዳ ሕዝብ ላይ እያተከሄደ ያለውን መጠነ ሰፊ የባሪያ ንግድ ለማኅበሩ የፖለቲካ ኮሚሲዮንና ለጠቅላላ ጉባኤ በማቅረብ አባል እንዳንሆን ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርቦብናል» ሲሉ አስረድተዋል።
ለዚህ ለራስ ናደው አባ ወሎ ቴሌግራም የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሰጥቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው የባርያ ንግድ ባጭር ጊዜ ውስጥ ጨርሶ እንዲታገድና የሰው ልጅ መብት በመላው የአገሪቱ ግዛት እንዲከበር የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መንግሥት ለመንግሥታቱ ማኅበር ቃል በመግባት ኢትዮጵያ ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ከመስከረም 17 ቀን 1916 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ማህበር 57ኛ አባል ሆና መመዝገቧ በይፋ ታወጀላት።
የዘረመል ችግር
የሰው ልጆችን ሰብአዊነት በእጅጉ የሚጋፋው “የባሪያ ንግድ” ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጥሮ አልፏል። ከዚህ ውስጥ በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናትን ተንተርሶ ዓለም አቀፉ የሚዲያ የማሰራጪያ ጣቢያ የሆነው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ባስተላለፈው ዶክመንተሪ ላይ እንዳስታወቀው፤ ይህ እኩይ ተግባር “የዘረመል ችግር እስከ መፍጠር ደርሷል።
በጥናቱ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን ያሳተፈው የዘረመል ምርምር ተካሂዷል። ጥናቱ ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን በባርያ ንግድ ከአፍሪካ ለአሜሪካ የተሸጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተመለከተ አዲስ መረጃ አስገኝቷል። መረጃው የባርያ ንግድ አሁን ባለው የአሜሪካውያን የዘረ መል መዋቅር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ያመለክታል።
ጥናቱ የመደፈር፣ የመሰቃየት፣ የበሽታ እና የዘረኝነትን ጫና ያሳያል። ከ1515 እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን ተሸጠዋል። ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች፣ ወንዶችና ሕፃናት ወደ አሜሪካ እየተወሰዱ ሳለ ሕይወታቸው አልፏል።
የዘረመል ምርምሩ የተካሄደው “23 ኤንድሚ” በተባለ ድርጅት ነው። በ “አሜሪካን ጆርናል ኦፍ ሂውማን ጄነቲክስ” መጽሔት የታተመው ይህ ጥናት፤ ከሁለቱም የአትላንቲክ ክፍሎች አፍሪካዊ የዘር ሀረግ ያላቸውን 30 ሺህ ሰዎች አካቷል። የማሕበረሰብ ዘረ መል ተመራማሪው ስቲቨን ሚሼሌቲ ለኤኤፍፒ እንዳሉት፤ የሚያገኙትን የዘረ መል ውጤት ከባርያ ንግድ መርከቦች ጋር ለማነጻጸር አቅደው ነበር ጥናቱን የጀመሩት።
አብዛኛው ግኝታቸው ከታሪካዊ ሰነዶች ጋር ይጣጣማል። ሰዎች ከየትኛው የአፍሪካ አካባቢ እንደተወሰዱ እና አሜሪካ ውስጥ የት ለባርነት እንደተዳረጉ ከሚያሳዩ ሰነዶች ጋር አብዛኛው ውጤታቸው ተመሳሳይ ነው። አንዳንዶቹ ግኝቶቻቸው ከታሪካዊው ትርክት ጋር ሰፊ ግንኙነት እንዳላቸው ተመራማሪው ይናገራሉ። ብዙሃኑ የአፍሪካ የዘር ግንድ ያላቸው አሜሪካውያን መነሻቸው የዛሬዎቹ አንጎላ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል። ይህም ዋነኛው የባርያ ንግድ መስመር የነበረ ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013