ብዙ አንባቢያን በትወናዋ ያውቋታል። በተለይ ቴአትር ቤት ገብተው ቴአትር የተመለከቱ በችሎታቸው ተመልካችን ከሚያስጨበጭቡ ተዋንያን መሀከል አንዷ መሆኗን ይመሰክራሉ። የፊልም ተመልካቾችም እርስዋን በደንብ ያውቋታል። ቴአትር ቤት እና ሲኒማ መግባት ያልቻሉም በቴሌቪዥን መስኮታቸው አይተዋታል። የዛሬዋ እንግዳችን በኢትዮጵያ የትወና መድረኮች እና የፊልም ስክሪኖች ላይ ለሶስት አስርት አመታት በብቃት የዘለቀችው ተዋናይት አስቴር አለማየሁ ናት።
የተወለደችው በ1959 ዓ.ም እዚሁ አዲስ አበባ በተለምዶው አስኮ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው። አባቷ አቶ አለማየሁ ጨዋቃ እና እናቷ ወ/ሮ በቀለች ደስታ ከወለዷቸው 9 ልጆች የመጨረሻዋ ናት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ መድሀኔአለም ሁለተኛ ደረጃ እና ጄነራል ዊንጌት ነው ቀጠለች።
“ቤተሰቦቼ በነጻነት ነው ያሳደጉኝ” የምትለው አስቴር ገና በልጅነቷ የነፍሷን መሻት እንድትከተል የቤተሰቦቿ ነጻ የሆነ የአስተዳደግ መንገድ እንዳገዛት ትናገራለች። እንዲያም ይሁን እንጂ ለኪነ ጥበቡ ከአስቴር ይልቅ የተሻለ እድል እንዳለው የሚነገረው ታላቅ ወንድሟ ነበር። ሆኖም እሱ ለቴአትሩ ሲጠበቅ የህይወት ጎዳና ወደሌላ ሙያ መራውና ከቴአትር ጋር ተላለፉ።
በተቃራኒው ጥበብ ወደ አስቴር አዘነበለች። ገና በልጅነቷ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በጥቁር እና ነጭ ቴሌቪዥን ህዝብ ተሰብስቦ የሚያየውን “ያልተከፈለ እዳ” የሚል ድራማ መሬት ላይ ተቀምጣ ያየችው ትንሷ አስቴር ወደፊት ተዋናይ ለመሆን ፍላጎት አሳደረባት።
ትምህርቷን 12ኛ ክፍል ደርሳ ስትጨርስ በቀጥታ ወደ ቴአትር ገባች። የተጓዘችውም ተዋንያንን በማምረት ወደሚታወቀው የፋዘር ቤት (የክብር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ የቴአትር እድገት ክበብ) ነበር። እሷ በገባችበት ወቅት የፋዘር ቤት የራሳቸውን የክብር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ ልጅ አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬን ጨምሮ አርቲስት መለሰ ወልዱ እና ሌሎች ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ቴአትር ቤቶችን በብቃታቸው የተቆጣጠሩ ተዋንያን የመጡበት ጊዜ ነበር።
አስቴርም የፋዘር ቤት ተማሪ እያለች ቀደም ብሎ በታላላቆቹ ተዋንያን በነሲራክ ታደሰ እና ተክሌ ደስታ የተተወነው “የወንደላጤው መዘዝ” የተሰኘ ተውኔት የመተወን እድል አጋጠማት። ከሷ ጋር የመተወን እድል የተሰጠው ሌላኛው የፋዘር ቤት ተማሪ ደግሞ ቴዎድሮስ ተስፋዬ ነው።ወቅቱም 1982 ገደማ ነው።
የአስቴር የኪነ ጥበብ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ካላቸው እና እንደ አርአያ ከምትከተላቸው አርቲስቶች መሀከል ዋናዋ የሰፈሯ ልጅ የሆነችው አርቲስት አለምጸሀይ ወዳጆ ዋናዋ ናት። አስቴር ወደ ኪነጥበቡ መድረክ ጎራ ስትልም አንጋፋው አርቲስት መላኩ አሻግሬ “አንድ ጡት” የተሰኘ ተውኔትን በብሄራዊ ቴአትር ያሳዩ ነበር።በዚያ ተውኔት ላይ ዋናዋን ገጸ ባህሪ ይዛ የምትተውነው ተዋናይ አለምጸሐይ ወዳጆ ናት።
አስቴር ከፋዘር ቤት የነበራት ቆይታ ተጠናቅቆ ወደ አርቲስት መላኩ አሻግሬ ስትሄድ “አንድ ጡት” የተሰኘ ቴአትር ላይ አለምጸሐይ ወዳጆ ይዛው ትተውነው የነበረውን ገጸ ባህሪ ይዛ እንድትሰራ ተደረገ። የዘወትር ህልሟም እውን ሆነ። ነገሩን የበለጠ አስደሳች የሚያደርገው ደግሞ ገና ጀማሪ ሆና በየክፍለ ሀገሩ እየዞረች ቴአትሩን ያቀረበቸው ከአንጋፋዎቹ ጌትነት እንየው ፤ አስናቀች ወርቁ ፤ ዘነበች (ጭራ ቀረሽ) እና ተክሌ ደስታ ጋር ነበር።
ከዚያም በኋላ 1985 ዓ.ም ራስ ቴአትር አዳዲስ ተዋንያንን እቀጥራለሁ አለ። አስቴር አለማየሁም የራስ ቴአትር ሰራተኛ ሆና ተቀጠረች። ከዚያም በኋላም በርካታ የሙሉ ሰአት እና አጫጭር ተውኔቶችን የተጫወተች ሲሆን ለምሳሌ ያህል ዘር አዳኝ ፤ ስውር ሰይፍ ፤ አሻራ ፤ የአንድ ቀን እስረኞች ፤ ክፉ ቀን ደራሽ ፤ ማዶ ለማዶ ፤ ነቢይ ዤሮ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።
በፊልሙም ረገድ በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት በተለየው አርቲስት መስፍን ጌታቸው የተዘጋጀው ዙምራ የተሰኘ ፊልም ጨምሮ ብዙ ፊልሞችን ሰርታለች። በቴሌቪዥን ድራማ በኩል የመጀመሪያ ስራዋ ከሆነው የማለዳ ጤዛ ከተሰኘ ድራማ አንስቶ ባለፈው አመት ከዚህ አለም በሞት የተለየው የአርቲስት አዶኒስ የተዘጋጁትን እና ብዙ ተመልካች ያገኙትን ገመና እና መለከት እንዲሁም ሌሎች ብዙ ስራዎችን ሰርታለች።
በግል ህይወቷ አርቲስት አስቴር ባለትዳር እና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናት። ከ20 አመት በፊት ከባለቤቷ አቶ ምንተስኖት ጌታሁን ጋር ትዳር የመሰረተችው አርቲስት አስቴር ከዚያ በፊትም ለ8 አመታት በፍቅረኝነት አብረው እንደኖሩ ትገልጻለች። በ20 አመት የፍቅር እና የትዳር ቆይታቸውም ለአምላክ ምንተስኖት እና ፍቅር ምንተስኖት የተሰኙ ልጆችን ወልደዋል።
”ባለቤቴ በሙያዬ በሁሉም መንገድ ይደግፈኛል። አንድም ቀን ለምን ብሎ ተቃውሞኝ አያውቅም።የኛ ስራ ማምሸት አለው፤ አዳር አለው ፤ ክፍለ ሀገር መሄድ አለው። በነዚህ ጊዜያት ሁሉ ቤቴን እና ልጆቼን ይዞ ይጠብቀኛል። ባለቤቴ እና ልጆቼ በጣም ነው የሚደግፉኝ” ብላለች።
አርቲስት አስቴር አንደ ብዙዎቹ ተዋናዮች ቅዳሜ እና እሁድ በስራ ላይ የምትሆንባቸው ቀናት ናቸው። ቢሆንም ባሏት የእረፍት ቀናት በምን እንደምታሳልፍ ጠየቅናት።” እኔ እረፍት ቀኔን የማሳልፈው ከባለቤቴ እና ከልጆቼ ጋር ነው። ስራ ከሌለኝ ከቤት አልወጣም። ከወጣሁም የምወጣው ከባለቤቴ እና ከልጆቼ ጋር ነው።” ትላለች።
“ምግብ ማብሰል እወዳለሁ። ልጆቼ እስኪመጡ ምን ሰርቼ ልጠብቃቸው ብዬ ነው የማስበው። እድሜ እየጨመረ ሲመጣ እየተሰበሰብክ ትመጣለህ። አሁን እኔ ወደቤቴ መሆን ነው ደስ የሚለኝ።”ትላለች።
ከዚህ ቀደም በራሷ ፕሮሞሽን ድርጅት በኩል “ጽናት” የሚል ስያሜ የሰጠችው ኪነ ጥበባዊ ዘመቻ አድርጋ አሁን ጦርነት በሚካሄድባቸው በሰሜን አካባቢ ባሉ ቦታዎች ለሰራዊቱ
የኪነ ጥበብ ስራዎች ማቅረቧን የምትናገረው አርቲስት አስቴር “ብዙ ሰው በሰላሙ ጊዜ ሰራዊቱን ይረሳዋል።
እናዝናናው የሚል የለም። እና ዝግጅቱን ላቀርብ በሄድኩ ጊዜ በጣም ደስተኛ ነበሩ።” ትላለች። በቅርቡም ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት ሄደው የኪነ ጥብብ ስራዎችን ካቀረቡ አርቲስቶች መሀከልም ናት።
ከዚህም ባለፈ በጉዲፈቻ ዙሪያ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻን የሚበረታታ ትምህርታዊ ተውኔቶችን እየሰራች እንደሆነ የምትናገር ሲሆን በባላገሩ ቴሌቪዥን ላይም ከሌሎች ሴት አርቲስቶች ጋር በመሆን እናቶችን የሚመለከት ፕሮግራም እንደምታቀርብ ትገልጻለች። ሰላም ሲመለስ ደግሞ ብዙ ስራዎች ለመስራት ማቀዷንም ነግራናለች።
አርቲስት አስቴር አሁን ላይ በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ከሚያሳዝናቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን መሀከል አንዷ ናት። በቅርቡ ሰላም እንዲመለስም ትመኛለች።”እኔ የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባልም ደጋፊም አይደለሁም፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነኝ። የኪነ ጥበብ ባለሙያ ደግሞ ዘር ቀለም ምናምን የለውም። ነገር ግን በኢትዮጵያ አልደራደርም” በማለትም አቋሟን አጠንክራ ተናግራለች። በአዲሱ አመት የእርቅ እና የይቅርታ እንዲሆን እና ሰላም ተመልሶ ባለፉት ሶስት አመታት የታዩ መልካም ነገሮች እንዲቀጥሉ የምትመኘው አስቴር ሁሉም ለሰላም አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርባለች።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013