እንዴት ከረማችሁ? ክረምቱና ብርዱ እንዴት ይዟችኋል? በተለይ ለብርዱ መላ ካላችሁ ለዛሬ እኔ አለሁላችሁ። ቆፈኑን አስረስተው አገራዊ ፍቅር የሚያላብሱ ደምን የሚያሞቁ ዜማዎችን እያነሳሁ አንዳንድ ነገሮች ልላችሁ ወድጃለሁ።
በተለይ ባዳና ባንዳ አብረው በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ሲረባረቡ እነሱን ለማስተንፈስ ለሚወሰደው እርምጃ ዜማዎቹ ጥሩ ማነቃቂያ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ። በተለይ ግንባር ያሉትን አገር ወዳድ ቆራጦችን ማበረታታት ወሳኝ ነውና እነዚህ ዜማዎች በእጅጉ ያስፈልጋሉ።
በቀደሙት ዘመናት ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ከወራሪ ጠላት ለመታደግ ያደረጉት ብርቱ ተጋድሎ ውጤታማ እንዲሆን የተወዳጅ አርቲስቶቻችን ዜማዎችም ባለውለታዎች ናቸው።የቀደመው ትውልድ ጥበብ የተሞለባቸው ቀስቃሽ ግጥሞች፣ ፉከራና ቀረርቶዎች በድል በዓላት ወቅት፣ የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ጊዜ ሰራዊቱን ለማነቃቃት ህዝቡን በአንድ ለማሳለፍ ሲዜሙ የሀገር ፍቅር ስሜቱ የማይቀሰቀስ የለም።የሀገር ሉዓላዊነትን የሚዳፈር ጠላት በተነሳ ቁጥር ህዝቡ ወራሪዎቹን ለመመከት እንዲነሳሳ የሚያስችሉ አዳዲስ የኪነጥበብ ስራዎች ይወጣሉ፤ የቀደሙት ዜማዎች እንደ አዲስ ይደመጣሉ።
ስነቃል፣ ሽለላ፣ ቀረርቶና አዝማሪ በዓድዋ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያን ሰራዊት በማበረታታት የተለየ ድርሻ ነበረው።አርበኞች አገራዊ ፍቅር በመታጠቅ ለአገራቸው ክብር ጦር ሜዳ ሲውሉ የኪነጥበብ ባለሙያው ወኔን የሚያላብስ ፉከራ፣ ቀረርቶና ግጥም በማሰማት ብርታትና ስንቅ ሆኗቸዋል።ባለሙያዎቹ ‹‹በለው በለውና አሳጣው መድረሻ…የሰው ልክ አያውቅም ባለጌና ውሻ ›› እያሉ ሰራዊቱ ጉልበት እንዲያገኝ ከጎኑ ሆነው አበረታተዋል።
ዛሬም ኢትዮጵያዊያን ጠላታቸውን ድል እንዲያደርጉ ሁሉም ዜጋ በየፊናው ያለውን ማበርከቱን ቀጥሏል። በየጦር ሜዳው የሚዋደቁ ጀግኖች ደጀኔ በሚሉት ህዝብ ይበረታታሉ፤ ይደገፋሉ።
ዜማ አዋቂው “አገር ማለት የጠለቀ ፍቅር፤ ኢትዮጵያ ማለት የመሰዋዕት ምድር” መሆኗን እያዜመ የሞራል ስንቅ ይሰጣል።ጀግናውን አሞካሽቶ፣ ተዋጊውን አበርትቶ፣ ጠላትን እያወረደ በጥበብ የድል ባለቤት መሆን ያስችላል።ከታላላቅ የጦር ሜዳ አገራዊ ድሎች ጀርባ በእርግጥም በኪነቱ ሞራል የሰጡ በዜማቸው ሰራዊቱን ያበረታቱ በርካታ ጥበበኞች ከነዜማዎቻቸው አሉን።
በየዘመናቱ ኢትዮጵያን የተዳፈሩ ጠላቶች ሲገጥሙን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ባሉበት ቦታ ብቻ ሆነው አይደለም ሰራዊቱን የሚያበረታቱት።በሚሰለጥነበት ጣቢያ በግንባር ጭምር እየተገኙ ያበረታቱታል፣ ለደጀኑም በየአደባባዩና አዳራሹ ጥዑመ ዜማዎችን እያቀረቡ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲቀጣጠል ያደርጋሉ። ይህን በማድረግም በተናጠል አልያም በቡድን ሆነው ሰራዊቱን እያበረታቱና እያነሳሱ ለድል አብቅተውታል።
በሙዚቃው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችም የአገር ፍቅር ስሜታቸውን በዜማቸው በመግለፅ ለሰራዊቱ አገራዊ ዜማዎችን በማቅረብ ሲያበረታቱ ኖረዋል።ለአብነትም የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ አንድ ዜማ አንመለክት፡፡
ኢ….ት…..ዮ….ጵ…ያ
ኢትዮጵያ የእኛ መመኪያ……… እያለ አርቲስቱ ሲያዜም ለአገሩ፣ ለወገኑ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ልዩ ስሜት በከፍተኛ ሞራል ተነሳስቶ ያላንጸበራቀ ዜጋ አልነበረም። ወታደሩም ለአገሩ ያለውን ልዩ ስሜት በሙዚቃው ታጅቦ እያነባ ሲገልጽ ተመልክተንበታል፤ ለአገር ክብር በየሸንተረሩ ተዋድቋል።ጥላሁን ገሰሰ በዚህ ዜማው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በማይለቅ ቀለም የተፃፈ፣ በጠንካራ አለት ላይ የተገነባ፣ በደማቅ የመስዋእትነት የክብር ደም የተፃፈ ታሪክ መሆኑን ነግሮናል፡፡
ሰራዊታችን ድል ሲያስመዘግብና ሀገራዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ከአንዱ ግዳጅ ወደ ሌላ ሲዘዋወር በአንድነት ተሰባስቦ በማዜም ለእናት ምድሩ ያለውን ስሜቱን ይገልፃል።አብሮ በመዝፈን ኢትዮጵያን ደጋግሞ ይጠራል።ታዲያ ለዚህ ነው የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን አሁንም ድረስ ተቀርፆ በተቀመጠው ትንፋሹ እንዲህ እያለ የሚያዜመው…
“የጥቁር ህዝብ ክብር የማዕዘን ድንጋይ……
የተጋድሎ አፅመ ርዕስት የደም ፍሳሽ ብቃይ
የደም ፍቅር ብስራት የተጋድሎ የመስዋዕት ሜዳ …… “
በጥሩ ቋንቋና ለዛ የተዜመ ሙዚቃ ወኔን አላብሶ ውስጣችን ያለው ልዩ ስሜት ፈንቅሎ እንዲወጣ ያደርጋል።ለዚህ ትልቅ ማሳያ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ዜማ ነው።በተለይ ኢትዮጵያ ልጆቿን በምትፈልግበትና ለመፅናቷ በምንታገልበት ወቅት የሞራል ስንቅ ይሆነናል፡፡
የትዝታውን ንጉስ መህሙድ አህመድም ሌላው የአገር ፍቅር ስሜትን በተለባሱ ዜማዎቹ ወታደሩን ቀስቅሷል፤ ህዝቡም ለሉዓላዊነቱ ከሚያስጠብቀው ሰራዊት ጎን እንዲቆም ገንዘቡን ደሙን ሞራሉን እንዲሰጥ አድርጓል።ይህ አርቲስት በዜማው በተለየ መልኩ ወኔን የሚከስትና ለኢትዮጵያዊነት የሚከፈል ዋጋ እስከ ምን ድረስ መሆኑን፤
“ለበጎ ከሆነ ለቁም ነገር ጉዳይ…..ጎረቤት ወዳድ ነን እንግዳ ተቀባይ
ግን ሀገራችንን ክፉ ሚያስባት ……ቆራጥ ነን ልጆቿ አንወድም ጥቃት
ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም …. በአባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም….!” እያለ አስገንዝቦናል፡፡
ስለዚህ ዜማ ካነሳሁላችሁ አይቀር አንድ አጋጣሚ ላጫውታችሁ። የመሃሙድን “እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም” የሚለው ሙዚቃ ሰሞኑን ቢሮ ውስጥ ሆኜ ሰማሁ። ከዋናው ጎዳና ነው ድምጹ ይለቀቅ የነበረው፤ ወዲያው ወደ መስኮቱ ጠጋ ብዬ ከየት እየተለቀቀ እንደሆነ መፈለግ ጀመርኩ።በመኪና ላይ ከተደረገ ከፍ ካለ ድምፅ ማጉያ ነበር።
ባልደረቦቼም ወደ ኮሪደሩ ወጥተው በዚያ ካለው መስኮት ወደ ውጪ እየተመለከቱ እያዳመጡ አገኘሁዋቸው።ሁላችንም በየራሳችን ዜማውን ለመከታተል ወደየአቅራቢያችን መስኮች እንደተገኘነው ሁሉ ዜማውንም በየራሳች እናንጎራጉር ነበር።
ዜማው ሁላችንንም በአንድ ቋንቋ እንድንነጋገር አድርገን።ውስጣችን የሚንቀለቀለውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት አጋራን። ዜማውም ከምንም በላይ ይህን ምትሃታዊ ሃይል የመግለፅ ትልቅ አቅም እንዳለው እንድገነዘብ አድረገኝ።
ይህ ድንቅ አገራዊ ዜማ በሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚወደድ እርግጠኛ ነኝ።ለአገሩ መልካም የሚመኝ ሙዚቃውን ሲሰማ ባልጠበቀው ስሜቱ ፈንቆሎት አብሮ ማዜሙ አይቀርም።ሙዚቃው ጥልቅ በሆነ ጥበባዊ መንገድ የተቃኘ ነው።ሀገርን መውደድ እስከ መስዋዕትነት የሚዘልቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ክብርና ማንነት እንዲሁም የመሰዋዕትነት ውጤት መሆኑን ይነግራል።
“ቆላ ወይናደጋ ጋራው ሸንተረርሽ …….
ወንዝና ፏፏቴው ተስማሚው አየርሽ
ለጅብ ይሁን እንጂ ለአሞራ ስጋችን ……
አንቺ አትደፈሪም ይፈሳል ደማችን
ባባቶቻችን ደም የተረከብነሺ ………
እናት ሀገራችን የምንወድሺ በሚለው ዜማውም የትዝታው ንጉስ በዚህ ዜማው ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት፣ የህዝብዋን አትንኩኝ ባይነት፣ የልጆችዋን አብሮነትና ለጠላት የማይመቹ ቆራጥ መሆናቸውን ይነግረናል። ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ሴት ወንዱ አገሩ በፈተና ውስጥ ስትሆን ለመጠበቅና ለማፅናት ራሱንም ለመስጠት የማይሰስት መሆኑን ያነሳል።
ሁለቱን ታላላቅ የሙዚቃ አባቶች ስለ “አገር ፍቅርና ሉዓላዊነትን ስለመጠበቅ” ያዜሙትን አነሳን እንጂ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ሆኖ በሙያው ውለታ ያልዋለ አለ ማለት ድፍረት ይሆናል።
ቴዎድሮስ ታደሰ (እምዬ ኢትዮጵያ )፣ የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ እጅጋየሁ ሽባባው፣ ዳዊት ፅጌ “ኢትዮጵያ” የጥላሁን ገሰሰ “ቃል ኪዳን” የጥላሁን እልፍነህ “አሸው” የፀሀዬ ዮሀንስ “ማን እንደ እናት” የሚሉ ዜማዎች ይነሳሉ። ከራሳቸው በላይ ለሚወዷት ሀገራቸው መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆንን አስተምረውናል፤ እነዚህ ዜማዎቻቸው ዛሬም ተደጋግመው ሲሰሙ የሚወደዱ ናቸው።
በዜማዎቹ ባንዳዎችን ስንወጋ እንደኖርን ሁሉ አሁንም እንዋጋባቸዋለን።እናንተ ደግሞ ቀሪዎቹን እየሞላችሁና እኔ ዛሬ የጋበዝኳችሁን እያዳመጣችሁ ለውድ አገራችሁ ደጀን እንድትሆኑ እመኛለሁ። ቸር ይግጠመን!
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013