አትሌቲክስ ታሪኩና የክብሩ ምክንያት ለሆነለት የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ኦሊምፒክ ባሉ ታላላቅ መድረኮች ከብርቱ አትሌቶቹ ምን ጊዜም አገርን የሚያስጠራ ውጤት ይጠብቃል። የለመደው ቀርቶ እንደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤት ሲያንስ ደግሞ ማዘኑ የአደባባይ ሃቅ ነው።
በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት የተጠበቀውና ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ እንደታሰበው ባይሆንም፤ ከኦሊምፒኩ ማግስት ተስፋ ሰጪ ውጤት በሌላ ውድድር ታይቷል። በኦሊምፒኩ ማግስት በኬንያ የተካሄደው 18ኛው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳታፊ ቡድን ያስመዘገበው ውጤት ተስፋ መቁረጥን አስወግዶ ደስታን ያስከተለ ሆኗል።
ከአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ አካዳሚዎች እና ክለቦች የተውጣጡ ወጣት አትሌቶች በተካፈሉበት በዚህ ቻምፒዮና የተገኘው ውጤት ከፍተኛ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ከዓለም 4ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 3ኛ ደረጃን እንድትይዝ አድርጓታል። ቡድኑ ያስመዘገበው 3 የወርቅ፣ 7 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳልያዎች ቢሆንም፤ በሌሎች አገራት የወርቅ ሜዳሊያ መጠን ተበልጦ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ አድርጎታል። ይሁን እንጂ የተቆጠሩት የሜዳሊያዎች ብዛት ኢትዮጵያን ከአዘጋጇና በውጤት ቀዳሚ ከሆነችው ኬንያ ቀጥሎ ሁለተኛ ላይ የሚያስቀምጥ ነው።
ይህ በቀጣይ አገርን የማስጠራት አቅሙን ያሳየውና ተተኪነቱን ያረጋገጠው ቡድንም ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል። በዚህም መሰረት በቻምፒዮናው የወርቅ ሜዳሊያ ያመጡት ሶስት አትሌቶች እያንዳንዳቸው የ25ሺ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል። የብር ሜዳሊያ ያገኙት 18ሺ ብር ሲሸለሙ፤ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቶች ደግሞ 10ሺ ብር ተበርክቶላቸዋል። በውድድሩ ዲፕሎማ ያስመዘገቡ አትሌቶች 6ሺ ብር ሲያገኙ ተሳትፎ ያደረጉ አትሌቶች ደግሞ 3ሺ ብር አግኝተዋል። አሰልጣኞችና ባለሙያዎችም እንዳስመዘገቡት ውጤት ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ሽልማታቸውን ተረክበዋል። ፌዴሬሽኑ ለዚህ ሽልማት በአጠቃላይ ከ500ሺ ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም አስታውቋል።
በቻምፒዮናው በ3ሺ ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበው አትሌት ታደሰ ወርቁ አስደናቂ አቋም ያሳየ አትሌትና የከፍተኛ ገንዘብ ተሸላሚም ለመሆን ችሏል። የደቡብ ፖሊስ ክለብ አትሌቱ ታደሰ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤት ያዘነውን ህዝብ የሚክስ ውጤት በመመዝገቡ ደስተኛ መሆኑን ይገልጻል።
ሩጫን ከትምህርት ቤት እንደጀመረ ወጣቱ በቀጣይ አገሩን የሚያኮራ ስመጥር አትሌት የመሆን ራእይ አለው። በትምህርት ቤት ከመወዳደር አንስቶ ዞኑን ወክሎ በተሳተፈበት ውድድር ላይ የሩጫ ችሎታውን በማስመስከሩ ለአገረሰላም አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሊመለመል ችሏል። በማዕከሉ ከዚህ ቀደም ሰልጥነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ የሆኑ እንደነ ሙክታር እድሪስ እና ጥላሁን ኃይሌ ያሉ አትሌቶችን ታሪክ በመስማት እና አንጋፋ አትሌቶችን አርዓያዎቹ በማድረግ እንዲሁም የአሰልጣኞቹን ምክር በመስማት ጠንካራ አትሌት ለመሆንም ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ለወደፊት ውጤታማ የመሆን ውጥን በልቡ ሰንቆም ልምምዱን በአግባቡ መስራቱ አሁን ላለበት እንዳበቃውም ጠቅሷል። በኬንያው ውድድር ቡድኑ የአጭር ጊዜ ዝግጅት በማድረግ ወደ ውድድር ቢገባም የተመዘገበው ውጤት አስደሳች መሆኑንም አንጸባርቋል። በተለይ በዝግጅቱ ወቅት ሲካሄድ በነበረው ኦሊምፒክ ይመዘገብ የነበረው ውጤት ቡድኑን ስጋት ላይ ቢጥለውም በውድድሩ ላይ ይታዩ የነበሩትን ክፍተቶች እንዴት ማረም እንደሚቻል ግን ከአሰልጣኞቻቸው ጋር በመሆን ይማከሩ ነበር። በመሆኑም የቡድኑ ጉዞ በአሸናፊነት ወኔ የታጀበ እንደነበርም ይጠቁማል።
ከዚህ ቀደም በዓለም የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ ተሳትፎ ነበር። በዚህ ቻምፒዮናም የመጀመሪያውን ወርቅ ካስመዘገበ በኋላ ሁለተኛውንም ወርቅ በማግኘት ህዝቡን ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ለአገሩ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው የሚገልጸው ወጣቱ አትሌት በቀጣይም የዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አገሩን ለማስጠራት እንደሚሰራም ነው የሚገልጸው።
በቻምፒዮናው ላይ የቡድን መሪ በመሆን ከቡድኑ ጋ የነበረው የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ አበራ በበኩሉ፤ ከተገኘው ውጤት ለዓለም ቻምፒዮና የሚደርሱ ተተኪ አትሌቶችን መመልከት እንደተቻለ ይጠቁማል። ጥሩ ፉክክር በማድረግ ወርቅ እንዳመጡት ሁሉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በሰከንዶች ልዩነት የብርና ነሐስ ሜዳሊያ ያመጡት አትሌቶችም አስደናቂ ውጤት አምጥተዋል ይላል።
በኦሊምፒክ ማግስት አትሌቱ የተለያዩ ጉዳዮችን እየሰማ ተሳትፎ ውጤት ማስመዝገቡ የሚያስመሰገነውም ነው ያለው ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ከኬንያ ጋር ያለው የአየር ሁኔታ ተመሳሳይ መሆኑ ቡድኑን ያገዘው መሆኑንም ይናገራል። ቡድኑ በወርቅ ቁጥር ተበልጦ አራተኛ ደረጃን ቢይዝም በሜዳሊያ ብዛት ግን ከኬንያ ቀጥሎ ሁለተኛ ላይ እንዲገኝ አድርጓል። ይህም የሚያሳየው አትሌቶቹ በመጪው የዓለም ቻምፒዮና አገራቸውን ለመወከል የሚችሉ መሆናቸውን ነው ሲል ተስፋውን አመላክቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013