የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የነበረበትን ችግር እያወቀ እንኳን ብዙ ዕድሎችንና ሃያ ሰባት የመታረሚያ ዓመታትን ሰጥቶታል። አሸባሪ ቡድኑ ግን በሤራ ተጠንስሶ በጥፋት ያደገ ነውና፣ የሚብስበት እንጂ የሚታረም አልሆነም። ይህ የጥፋት ኃይል በሕዝብ ቁጣ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላም ቢሆን፣ የተሰጠውን ተደጋጋሚ የመታረም ዕድል ለመጠቀም አልፈለገም። ይልቁንም መቀሌ ላይ መሽጎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ጋር በማሤር ጊዜውንና የዘረፈውን ገንዘብ ሲረጭ ከርሟል።
በዚህም የተነሣ ግጭት፣ መፈናቀልና አሰቃቂ ግድያን በመላ ሀገራችን መለኮስና ማስፋፋት የዕለት ተግባሮቹ አድርጎ ቆይቷል። የትግራይ ሕዝብ በዚህ ለጥፋት ተጸንሶ ለአፍራሽነት በተወለደ አሸባሪ ቡድን የተነሣ እንዳይጎዳ በማለት፣ መንግሥታችን ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያልሞከረው መንገድ አልነበረም። ይህ ሁኔታ ውጤት ሳያመጣ ቀርቶ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሀይሉ ላይ በተቃጣው ጥቃት መንግስት ህግ ወደ ማስከበሩ መግባቱ ይታወሳል።
መንግስት ከስምንት ወራት የህግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ ተኩስ አቁም በማድረግ ከትግራይ ክልል ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መከላከያ ሀይሉ እንዲወጣ አደረገ። ነገር ግን ሸብርተኛው የህወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት በንብረትና በሰው ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ይህን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመከላከል መንግስት ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ልዩ ሀይልና ወደ መከላከያ የሚቀላቀሉ ዘማቾችን ይዞ ሽብርተኛ ቡድኑን ለማጥፋት እየተዋጋ ይገኛል።
የአገሪቱን ሁኔታ መነሻ በማድረግ ወጣቱ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና የዓለም አቀፉን አቋም መረዳት አለበት። ከዚህ በዘለለ ወጣቱ ሁኔታዎችን በንቃት መጠበቅ አለበት። ሽብርተኛው ቡድን ከሚነዛቸው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ወጣቱ መጠበቅና እራሱን መከላከል አለበት። ሸብርተኛ ቡድኑ የሚከተለው የፕሮፓጋንዳ ሁኔታ ቀደም ብሎ እንደነበረው ያልተፈጠረ እንደተፈጠረ አድርጎ ወጣቱን ለጦርነት መማገድ ነው። ወጣቱ ህወሓት የሚነዛውም የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመረዳት እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል።
በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ወጣቱ ተሳትፎ በማድረግ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን መወጣት አለበት። በሁሉም ክልሎች የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ብዛት ያላቸው ወጣቶች ሀብት በማሰባሰብና በመዝመት ግንባር ቀደም ተሳትፎ አድርገዋል። ይህም ሁኔታ በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል። ከዚህ አንፃር መከላከያውን ማገዝ ያስፈልጋል። ሌላው ከወጣቱ የሚጠበቀው ሁሉም ወጣት አካባቢውን በንቃት መጠበቅ አለበት። ምክንያቱም ሽብርተኛው ቡድን ጦርነቱን አንድ ቦታ ማድረግ ስለማይፈልግ በተለያዩ አካባቢዎች ብጥብጥ ሊፈጥር ይችላል። የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ከቀድሞ በተሻለ መንገድ እንዲቀጥል ሁሉም ወጣት የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ ፕሬዚዳንት ብርሃኑ በቀለ እንደሚናገረው፤ እንደሚታወቀው በአገሪቱ በሰሜናዊ ክፍል አሸባሪው ህወሓት ጦርነት ከፍቶ ወድመት እያደረሰ ይገኛል። በመሆኑም ወጣቱ ይህን ለመመከት በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ቦታዎች ወጣቱ መከላከያ ሀይሉን እየተቀላቀለ ይገኛል። ሊጉ የወጣት ስብስብ እንደመሆኑ ወጣቱ መከላከያውን እንዲቀላቀሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ አገር ከሌለ ማንኛውም ሰው መኖር አይችልም። በዚህ ምክንያት ብዙ ወጣቶች ወደ መከላከያ እየተቀላቀለ ይገኛል። ይህ ተግባር እንዲፈፀም ሊጉ የግንዛቤ ስራ ሰርቷል።
በአሁኑ ወቅት ሽብርተኛው ቡድን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እያሰራጨ የሚገኝ ሲሆን በዚህም ወጣቱን በማዘናጋት ጥቃት ለማድረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ወጣት ብርሃኑ ይናገራል። ሽብርተኛው ቡድን በሚነዛቸው የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች ህብረተሰቡን በማታለል ስልጣን ለመያዝ አላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አመልክቷል። እያንዳንዱ የጁንታው አስተሳሰቦች፣ የሚሰጣቸው መግለጫዎችና የሚያደርጋቸው ድርጊቶች ውሸት መሆናቸውን ወጣቱ መረዳት እንዳለበት ይጠቁማል። በአገሪቱ ታሪክ ህወሓት አንድም ቀን እውነት አውርቶ የማያውቅ መሆኑን በመረዳት የሚነዙ የተሳሳቱ ፕሮፓጋንዳዎችን ወጣቱ በመረዳት ሊቀለብሳቸው እንደሚገባ ያስረዳል።
እንደ ወጣት ብርሃኑ አባባል፤ በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በመጠቀም ህወሓት የሀሰት መረጃዎችን እያሰራጨ እንደሚገኝና ህብረተሰቡን እያሸበረ መሆኑን ማሳወቅ ይገባል። በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ህብረተሰቡ እንዲጠበቅ ወጣቱ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለበት። ማህበረሰቡ በሚያደርጋቸው ማንኛውም እንቅስቃሴ የሚናፈሱ የተሳሳቱ መረጃዎችን ሊከላከል ይገባል። ህወሓት የሚነዛቸው ወሬዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን ህብረተሰቡ ቀደም ብሎ የሚያውቀው ነገር ነው። በአግባቡ በተደራጀ መንገድ መመከት ከተቻለ ህወሓት የሚነዛቸው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ምንም አይነት ለውጥ አያመጣም።
እንደሚታወቀው በየክልሉ በአሁን ወቅት ከመንግስት አካላት ጋር በመሆን ወጣቱ አካባቢውንና እራሱን እንዲጠብቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በአካል፣ በአዕምሮና በሌሎች ነገሮች ወጣቱ እንዲደራጅ እየተደረገ ነው። በሁሉም ክልሎች ሸብርተኛውን ቡድን ለመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው። በየአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አዲስ ሰዎች ወጣቱ ሲመለከት ከየት እንደመጣ መታወቂያ እየተጠየቀ ይገኛል። ሌላው ደግሞ በየኬላው ከፍተኛ የሆነ የፍተሻና የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ይገኛል። ወጣቱ ከፀጥታ አካላት ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ሁኔታዎች መመቻቸቱን ወጣት ብርሃኑ ይናገራል። ወጣቱ በተደራጀ አቋምና ሁኔታ አካባቢያቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ግንዛቤ መሰጠቱን ያመለክታል። የተለያዩ ድንገተኛ ፍተሻዎች ሲኖሩ ወጣቱ ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባ ወጣት ብርሃኑ ያስረዳል። ፍተሻዎች ሲኖሩ ሁሉም ህብረተሰብ ሊተባበራቸው ይገባል።
አገር መኖር ሲችል ሁሉም ነገር ማግኘት እንደሚቻል የሚናገረው ወጣት ብርሃኑ፤ ጥብቅ ፍተሻዎችን ማድረግ ካልተቻለ ሽብርተኛው ቡድን ሰርጎ በመግባት የተለያዩ የውሸት ፕሮፓጋንዳ በማስወራት እንዲሁም በገንዘብ ሽብርተኛ ቡድኑን የሚደግፉ አካላት እንዲበዙ እንደሚያደርግ ያመለክታል። ስለዚህ ወጣቱ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት መናገርና ማመልከት አለበት። ይህን የአገር ነቀርሳ የሆነውን ሸብርተኛ ቡድን ለማስወገድ ሁሉም በአንድነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስቧል።
በሌላ በኩል የኑሮ ውድነት እንዲከሰት የሚያደርጉ አካላት ለመቆጣጠር የወጣቱ ሚና የጎላ ነው። ነጋዴዎች ያለአግባብ እቃዎች ላይ ጭማሪ እያደረጉ ይገኛሉ። በተለያዩ ሁኔታ የፍጆታ እቃዎች ላይ ጭማሪ እየተደረገባቸው ሲሆን ነጋዴዎቹ ከዚህ ስራቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ወጣት ብርሃኑ ይናገራል። ወጣቱም እንደዚህ አይነት ሁኔታዎችን ሲመለከት ለሚመለከተው ክፍል ማሳወቅ አለበት። አሁን ባለው ሁኔታ ኑሮ ውድነት እንዲከሰት በማድረግ መንግስትን ለማዳከም የሚሞክሩ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ። በእንደዚህ አይነት ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ወጣቱ ሊያጋልጣቸው እንደሚገባ ወጣት ብርሃኑ ያብራራል።
ወጣት ብርሃኑ በቀለ እንደሚናገረው፤ በተያዘው ዓመት የሽብርተኛው ህወሓት ሀይል በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት መንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ እንደወሰደበት ይታወቃል። በዚህም የአገር ደህንነት ችግር ውስጥ እንዳይገባና ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር እንዲሁም በትግራይ ክልል የሚገኙ አርሷ አደሮች እንዲያርሱ በተጨማሪም በተፈጠረው ጦርነት ወጣቱ ህይወቱ እንዳይቀጠፍ መንግስት መከላከያ ሰራዊቱን አስወጥቷል። ነገር ግን ሽብርተኛው የህወሓት ሀይል ይህን አጋጣሚ በመጠቀም መንግስትን አሸንፊያለሁ በማለት ወጣቱን ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል። ህፃናትን ወደ ጦርነት በመላክና መንገዶችን በማፈራረስ እንዲሁም አፍራሽ ተግባራትን በማከናወን ወጣቱ በሽብር ተግባር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው።
‹‹ይህ የሚያሳየው አገሪቱን እየመራ የሚገኘው መንግስት ምን ያክል ትግስተኛ መሆኑን ነው። ›› የሚለው ወጣት ብርሃኑ፤ ሽብርተኛው ቡድን በሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የውጭ ዲፕሎማችን በማሳመን እንደተበደለና እንደተጨቆነ በማስመሰል ማቅረቡን ይናገራል። ቀደም ብሎ ህወሓት በስልጣን በነበረበት ወቅት ወጣቶችን በመግደልና በማሰር እንዲሁም በመዝረፍ የሚታወቅ ነው። በተመሳሳይ በአሁን ወቅትም ወጣቱን በመግደልና ሽብር በመፍጠር ላይ ይገኛል። በዚህም ብዙ ንፁሀን ዜጎች የሞቱበት ሁኔታ አለ። ሽብርተኛ ቡድኑ ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ በመሆኑ ሊጠየቅ ይገባል። ነገር ግን የሽብርተኛው ቡድን አመራሮች ወንጀለኛ መሆናቸውን ዘንግተው ለህዝብ ተቆርቋሪ መስለው እየቀረቡ ናቸው። በአሁን ወቅት በተለያዩ ድንበር አካባቢ በመሄድ ንፁሃን ዜጎችን በሽምቅ ውጊያ እየገደሉ መሆናቸውን ይናገራል።
እንደ ወጣት ብርሃኑ አባባል፤ ስለዚህ አገሪቱን ከዚህ ሽብርተኛ ቡድን ለማዳን መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ትክክለኛና ወቅታዊ ነው። ወጣቱ በዚህ ወቅት ግንባር ቀደም ሆኖ አገሩን ማዳን አለበት። አገሩን የሚወድ ማንኛውም ወጣት እራሱን አገሪቱን ለማዳን መዘጋጀት አለበት። ወጣቱ በአገር መከላከያ ውስጥ ተቀላቅሎ ወታደር በመሆንና በመሰልጠን ጦር ሜዳ በመሄድ መዋጋት አለበት። ሽብርተኛው ሀይል እስኪጠፋ ድረስ መዋጋት አለበት። በየቦታው ሸምቆ የሚገኘውን የሽብርተኛ ቡድን ማጥፋት የወጣቱ ስራ መሆን አለበት። በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጣቱ ወደ መከላከያ ከተቀላቀለ ውጤት ማምጣት ይቻላል። እያንዳንዱ ወንጀለኛ ከነበረበት ዋሻ እየወጣ መደምሰስ ያለበት እየተደመሰሰና መታሰር ያለበት እየታሰረ አገሪቱ ወደ ነበረችበት ሰላም ትመለሳለች።
ሊጉ ወጣቱ ወደ መከላከያ እንዲቀላቀል ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን በሊጉ ስር ከሰላሳ አምስት ሺህ በላይ ወጣቶች አሉ። ሊጉ ቅስቀሳዎችን በማድረግ ወጣቱ መከላከያን እንዲቀላቀል እየተደረገ ይገኛል። አብዛኛው ወጣት ወደ መከላከያ እየተቀላቀለ ይገኛል። ወጣቱ ለአገሩ እንዲቆም ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ማንኛውም የአገሪቱ ተወላጅ ወጣት በአሁን ወቅት ወደ መከላከያ እንዲገባ ጥሪ እየተደረገ ነው ስለዚህ ሊጉ እንደ አገር የሚሰራ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ወጣቶች ወደ ውትድርና እየገቡ ናቸው።
ሊጉ የማስተማርና የመቀስቀስ ስራዎችን የሚያከናውን ሲሆን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ወጣቱ መከላከያን ተቀላቅሎ አገሩን ማዳን አለበት የሚል ጥሪ ሊጉ እንደሚያቀርብ ወጣት ብርሃኑ ያብራራል። ወጣቱ አገሩን ሰላም ለማድረግ ሲዘምት መንግስት ለወጣቶቹ አጭር የውትድርና ስልጠና በመስጠትና አስፈላጊ ግብአት በማሟላት ወጣቱ ሽብርተኞች ላይ እንዲዘምት ማድረግ አለበት። አስፈላጊ ድጋፎችንም ማድረግ አለበት። ወጣቱ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ እየተሳተፈ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። አስፈላጊ ግብዓት ለመከላከያው በማቅረብና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም የሞራል ግንባታ በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ያስረዳል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2013