* የአዲስ አበባ ማሻሻያ ፕሮጀክት በ62 ሚሊዮን ዶላር እየተሰራ ነው
አዲስአበባ፤ ለኤሌክትሪክ ኃይል ጥራት መጓደል መነሻ የሆኑትን በመለየት ያከናወነው የመስመር አቅም የማሳደግ ሥራ ውጤታማ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ማሻሻያ ፕሮጀክት በ62 ሚሊዮን ዶላር እየተሰራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የ2011 ግማሽ ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ አሁን ካለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎት ጋር የሚጣጣም የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ ሥራ በመከናወን ላይ ነው፡፡
ባለፉት ስድስት ወራትም በአዲስ አበባ፣በአዳማ፣በሀዋሳ፣ድሬዳዋ፣ጅማ፣ባህርዳር፣መቀሌና ደሴ የተከናወነው የመስመሮችን አቅም የማሳደግ ሥራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አፈጻጸሙም 97 በመቶ መድረሱንና በቅርቡም እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል፡፡ የአገልግሎት መሻሻልንና የኃይል ብክነት የሚቀንስበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መስመር(ኔትወርክ) ማሻሻያ ፕሮጀክት ሥራ በ62ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በመከናወን ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽፈራው፣ አፈጻጸሙ 75 በመቶ ላይ መድረሱንና በምስራቅ አዲስ አበባ በኩል ያለው ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በደቡብ፣በሰሜንና በምዕራብ ያሉት የከተማዋ አካባቢዎች ደግሞ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በተወሰነ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡የፕሮጀክቱን ሁለተኛ ምዕራፍ ሥራ ለመጀመርም የአማካሪ ቅጥር እና የቅድመዝግጅት ሥራ ከወዲሁ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የኢንዱስትሪ አካባቢዎች የመስመር አቅም ለማሳደግም በተመሳሳይ የሚከናወን ፕሮጀክት መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ በትላልቅ ከተሞች በአጋዥ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ለመስጠትም የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁም ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ ባለፉት ስድስት ወራት 589ነጥብ8ኪሎሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ማስፋፊያ፣አንድ ሺ554ኪሎ ሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር የመልሶ ግንባታ፣25ሺ537 ኪሎ ሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ጥገና እንዲሁም 61 የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ማዳረስ ወይንም መልሶ ግንባታ፣በተጨማሪም 1ሺ188ነጥብ5ኪሎ ሜትር የገጠር ከተሞችና መንደሮችን መካከለኛ ቮልቴጅ መስመር ግንባታ እንዲሁም 675ነጥብ 92ኪሎ ሜትር የገጠር ከተሞችና መንደሮችን ዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
አጠቃላይ የተቋሙን የሰው ኃይል፣ የግዥ፣ አሰራሩን የማዘመን፣የደንበኞች አገልግሎትን አሰጣጥንም በስፋት የሚያሻሻል፣ተጠያቂነትንም የሚያሰፍን፣የክትትል ሥርዓቱንም ጠንካራ የሚያደርግ የመረጃና የክትትል ስርዓት ለመዘርጋት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ዘጠኙን ክልሎችና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች ማዕከል አድርጎ በመከናወን ላይ ያለው የኦፕሬሽንና ኤሌክትሪክ የማስፋፋት ሥራ ተናቦ ለመስራት ማስቻሉን የገለጹት አቶ ሽፈራው፣በጋራ እቅድ ለማውጣትና አፈጻጸሙንም ለመገምገም እንዲሁም ክልሎች በበጀት በመመደብም የሚያደርጉት ጥረት ጥሩ ጅምር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2011
በለምለም መንግሥቱ